Print this page
Monday, 10 September 2018 00:00

የሚካኤል ደወል ይሰማኛል

Written by  ተፈሪ መኮንን
Rate this item
(2 votes)

ደረጀ በላይነህ ወዳጄ ነው፡፡ የሚጽፋቸውንም ጽሑፎች አነባለሁ፡፡ አንዳንዴ በሐሳብ እንለያይ ይሆናል፡፡ ነገር ግን እንዲህ እንደ ዛሬው፤ ብዕር ለማንሳት የሚገፋፋ የሐሳብ ልዩነት የፈጠረብኝ ጽሑፍ ገጥሞኝ አያውቅም፡፡ ደረጀ በቅርቡ የታተመውን የሚካኤል ሽፈራውን ‹‹የማስጠንቀቂያ ደወል›› አንብቦ፤ በሁለት ክፍሎች የሰጠው አስተያየት፤ ከወዳጄ ጋር በዓይን  እንኳን መተያየት የማያስችል የአንድ ቀን መንገድን የሚያህል ርቀት በመካከላችን በመፍጠሩና አስተያየቱ ወርቅን በአፈር ከመመንዘር ያልተለየ ተግባር ሆኖ ስለታየኝ፤ ከቅሬታ ብቅ - ከቁጣ ዝቅ ያለ ስሜት ተፈጥሮብኝ፤ ለስሜቴና ለእውነቴ መመጠኛ ይሆነኝ ዘንድ የሚከተለውን አልኩ፡፡
በመጀመሪያ፤ ሚካኤል ሽፈራው ‹‹የማስጠንቀቂያ ደወል›› እየመታ ከየቦታው የቀሰቀሳቸው ሐሳቦች በርካታ በመሆናቸው፤ እንኳን የደረጀን አስተያየት ጨምሬበት፤ የእኔ ሐሳብ ብቻውን ከት/ቤት እንደ ተለቀቀ ሁዳድ የሚሞላ ተማሪ፤ በየአቅጣጫው ግር እያሉ፤ ትኩረት ለማግኘት እየተንጫጩ፤ ከመሐል አድርገው እያጋፉኝና በጉንተላ እረፍት እየነሱ አስቸግረውኝ ነበር፡፡ መጽሐፉን አንብቤ ከጨረስኩ በኋላ፤ የህሊናዬ ግቢ ጸጥታ የነገሰበት ቢመስልም፤ ‹‹የማስጠንቀቂያ ደወል›› የፈጠራቸውና ከእንቅልፍ ያነቃቸው አንዳንድ ሐሳቦች፣ ወደ ህሊናዬ ጓሮ ዘወር ብለው ሲከራከሩ፣ የደራሲውን ዜማ ተከትለው ሲዘምሩ፤ ይበል ሲሉ፤ ስለ ሐገሬ ነገር በገና ሲደረድሩ እሰማ ነበር፡፡
በዚህ ከፍታ ለመቆየት አስቤና ቃል ገብቼ ብዙ ከሄድኩ በኋላ፤ የመጀመሪያው ክፍል የደረጀ አስተያየት በዚሁ ጋዜጣ ወጥቶ አነበብኩ፡፡ ንባቡን ጨርሼ፤ በገና ድርደራውን ሳስተካክል፤ ሁለተኛው ክፍል መጣ፡፡ አየሁት፡፡ ንባቡን ስጨርስ፤ ከሚካኤል ከፍታ ወጥቼ ለማየት የማደርገውን መፍጨርጨር ተውኩት፡፡ ሐሳቤም ከተቀደደ ጆንያ እያፈተለከ በየአቅጣጫው ተንከባለለ፡፡ አማዲየስ ሞዛርት፤ ‹‹ከአሪፍ ወደ ከረፈፍ ለመውረድ አንድ እርምጃ ብቻ ይበቃል›› (‹‹It is only a step from the sublime to the mediocre››) የሚለው ነገር ደረሰብኝ፡፡ አዎ በደንብ ካልተጠነቀቅንና ሙሽራው እስኪመጣ ድረስ መቆየት የሚያስችል ዘይት ካላዘጋጀን፤ የያዝነው ዘይት ያልቃል ‹‹የእርፍናው›› በርም ይዘጋብናል፡፡ በአንድ እርምጃ፤ ከአሪፍ ወደ ከረፈፍ ማዕረግ እንወርዳለን፡፡ በእኔ አስተያየት ደረጀ በጎላ በተረዳ አኳኋን ሚካኤል የጻፈውን ነገር አልተመለከተውም፡፡ ሚካኤል ጨረቃውን ሲያሳየው እርሱ የሚመለከተው ጣቱን ነበር፡፡
‹‹የማስጠንቀቂያ ደወል››ን በትክክል ያነበበ ሰው፤ ‹‹አሪፍ መጽሐፍ ነው›› ብሎ፤ መጽሐፉን ዘግቶ ከጠረጴዛው ጣል በማድረግ ከድርሰቱ ጋር ያለውን ተራክቦ ሊፈጽም አይችልም፡፡ ምነው ቢሉ፤ ከ‹‹የማስጠንቀቂያ ደወል›› ዕረፍት የማይሰጥ የጥሪ ድምጽ ይሰማልና፡፡ ልባም አንባቢ፤ የደራሲውን ሐሳብ እንደ ሬድዮ ይዞ፤ ከ‹‹የማስጠንቀቂያ ደወል›› የሚተላለፈውን ነገር በጥራት ለመስማትና የሐሳብ የአየር ሞገዱን ይበልጥ ለማጥራት ተጨማሪ ጥረት ለማድረግ ይጣጣራል፡፡ በደወሉ ጩኸት በርካታ ሐሳቦች ከየበረቱ ዘለው ይወጣሉ፡፡ ስለዚህ እንደ ፊጋ በሬ የሚራወጠውን ሐሳብ አረጋግቶ ለመያዝ፤ ስሜት ሳይሆን ትዕግስት፣ ማስተዋል፣ ብልሃትና እውነትን ተከትሎ ከመሸበት ለማደር የተዘጋጀ መንፈስ ያስፈልጋል፡፡
‹‹የማስጠንቀቂያ ደወል›› ያነበበ ሰው፤ ስለ ሐገሩ ነገር አብዝቶ ያስባል፤ ከሐሳቡም ጋር መታገል ይጀምራል፡፡ በትግሉም ከሚካኤል ሽፈራው ትከሻ ላይ በመቆም አርቆ ለማየት ይሞክራል፡፡ ሚካኤል አድካሚውን ‹‹የሳይት›› ጠረጋ ሥራ ሰርቶልናል፡፡ ከመሬት ከፍ ብለን ለመቆም የምንችልበትን ወለል አዘጋጅቶልናል፡፡ በዚያ ላይ መገንባት እንችላለን፡፡ ‹‹የማስጠንቀቂያ ደወል›› በዋለልኝ መኮንን አራት ገጽ የማትሞላ ጽሑፍ፤ በቮልሼቪክሶች ‹‹የራን ዕድል በራስ የመወሰን እስከ ከመገንጠል መብት›› ቀመር እና በክብረ ነገስት ተረት የተዋቀረች መጽሐፍ ነች፡፡ ‹‹የማስጠንቀቂያ ደወል›› በነገሮች መካከል የሚገኘውንና በቀላሉ ሊታይ የማይችለውን ግንኙነትን ለመለየትና ለመረዳት ጥረት የሚደረግባት ‹‹መጽሐፈ ሐሳብ፤ ባህረ ሐሳብ፣ መርሃ እውራን ወይም ሐሳበ ብርሐን›› ነች፡፡  ባህረ ሐሳብ የማውጣት ሥራ፣ ለሰው ሁሉ በአንዴ ወገግ ብሎ ሊታይ የማይችል ጎዳናን የሚከተል በመሆኑ ጊዜ ሰጥቶ መመርመርን ይጠይቃል፡፡ ባህረ ሐሳብ ብዙ ሊታወሱ የሚገባቸው ነገሮችን በአንድ አውድ አምጥቶ ማስላትን የሚጠይቅ ነው፡፡ ሚካኤል ብዙ የሐሳብ መሰናክል የበዛበትን አቅጣጫ ተከትሎ፤ አዲስ መንገድ ለመክፈት ሞክሯል፡፡ የታወቀውን ለማዳ ሐሳብ እየፈታ ለቅቆ፤ አድኖ ለመመለስ ዱር የሚገባ ብርቱ የመንፈስ ኃይል ያለው ጸሐፊ መሆኑን እስከ ዛሬ ለንባብ ያበቃቸው ሥራዎች በቂ ማስረጃ ይሰጡናል፡፡  
‹‹የማስጠንቀቂያ ደወል››ን አንብቦ የጨረሰ ሰው፤ ‹‹ይህ መጽሐፍ ፀሐፊው ለኢህአዴግ ወይም ለህወሐት ያለውን ፍቅር ለመግለጽ የጻፈው ነው›› (ክፍል አንድ) የሚል ሐሳብ ይዞ መጽሐፉን ከዘጋ አስቸጋሪ ነው፡፡ ደረጀ በክፍል ሁለቱ ጽሑፍ መጨረሻ፤ ሚካኤል ‹‹ለዶክተር ዐቢይ ብሎ የጻፈውንና ያሰፈረውን ሃሳብ እጋራለሁ! አሁንም ቅር የሚለኝ ግን ያ  ሁሉ ግፍ ከሐገሪቱ ሰማይ ስር ሲፈፀም [እያየ]ጥሩ እንቅልፍ አግኝቶ፣ [የቆየው ሚካኤል] አሁን በለውጡ ጅማሬ ‹ለማስጠንቀቂያ› መባዘኑ ነው›› ብሎ መውቀሱ፤ ከደረጀ ንባብ አንጻር፣ የሚካኤል ጥረት ጨርሶ ከንቱ መሆኑን ያመለክታል፡፡ ደረጀ የሚካኤል መጽሐፍን ከማንበቡ አስቀድሞ በእፍኙ ሙሉ ዘግኖ የያዘው የሐሳብ ቆሎ አለ፡፡ ስለዚህ ከሚካኤል ሰፌድ አንዲት ጥሬ እንኳን ለማንሳት የሚችል አልሆነም፡፡
ደረጀ ሰው አክባሪ ነው፡፡ ከጽጌሬዳው አበባ ውብ ቀለሙን እንጂ እሾሁን ቀድሞ የማያይ ነው። ግን እሾሁንም ይወጋኛል ሳይል አገላብጦ ለማየት አይፈራም፡፡ ግን በእሾሁ አያስፈራራም፡፡ የተበላሸ ነገር ሲያይ በድፍረት ይቆጣል፡፡ ቁጣው ግን እንደ ኃይለ ማርያም አያስበረግግም፡፡ መንፈሱ ጽዱ በመሆኑ ከቁጣው የሐሳቡ ሙቀት እንጂ ነበልባሉ አይደርስባችሁም፡፡ ደረጀን እኔ ሳውቀው እንዲህ ነው፡፡ አሁን በዚህ በሚያነጋግረን አስተያየቱ የታየው የተለየ ዐመል፤ በአንድ አስገዳጅ ሁኔታ የተፈጠረ መዛነፍ አድርጌ እወስደዋለሁ፡፡ አስገዳጁ ሁኔታ ለለውጡ ያለው ቅናት መሆኑን እገምታለሁ። አብዝተን አንድን ነገር ከመውደድ የመጣ መዛነፍ አድርጌ እቆጥረዋለሁ፡፡  ነገር ግን፤ ለመከላከል የምንፈልገውን ነገር ባልተገባ መንገድ ለመከላከል መሞከር፤ ዓላማውን በገዛ እጃችን እንደ ማጥቃት ይቆጠራል፡፡  በገጽታው ሲታይ፤ ደረጀ በዶ/ር ዐቢይ የሚመራውን ለውጥ ለመከላከል የቆመ ይመስላል፡፡ በይዘቱ ግን  አጥቂው እርሱ ነው፡፡
ከጋዜጠኞች ጋር ተያይዞ የሚነሳ አንድ ታሪክ በማንሳት ሐሳቤን ለማብራራት እችላለሁ፡፡ ይህ ታሪክ በክሪሚያ የተካሄደውን የሩሲያ እና የእንግሊዝ ጦርነት ለመዘገብ የተመደበ ጋዜጠኛ ታሪክ ነው፡፡ ይህ ጋዜጠኛ በእንግሊዝ ጦር ውስጥ የታየውን ዝርክርክ አሰራር ተመልክቶ፤ ያየውን ነገር በዘገባው አቀረበ፡፡ በዚህ ዘገባ የእንግሊዝ ጦር ኃይል መኮንኖችን የአስተዳደር ችግር በመግለጹ ጀነራሎቹ በጣም ተቆጡ፡፡ መቆጣት ብቻ አይደለም፡፡ በጋዜጠኛው ላይ ‹‹የእንግሊዝ ጦር ያሉበትን ጉድለቶች በመዘርዘር፤ የጦር ኃይሉን ጉድለት ይፋ በማውጣት ለጠላት ጥቃት የሚያጋልጥ ሥራ ሰርቷል፡፡ የሐገርን ብሔራዊ ጥቅም የሚጎዳ ተግባር ፈጽሟል›› የሚል ክስ በፍርድ ቤት አቀረቡበት፡፡ እርሱም ጠበቃ አቁሞ ተከራከረ፡፡ ጠበቃውም፤ ‹‹ጋዜጠኛው ችግሩን ለህዝብ ይፋ በማድረጉና የተጠቀሰው ችግር በፍጥነት ታርሞ፤ በክሪሚያ ጦርነት እንግሊዝ አሸናፊ ሆናለች፡፡ ስለዚህ ደንበኛዬ የሐገሩን ብሔራዊ ጥቅም የሚጎዳ ነገር አልፈጸመም›› የሚል ክርከር አቀረበ፡፡ በመጨረሻም ፍ/ቤቱ፤ የግራ ቀኙን ክርክር ከሰማ በኋላ ‹‹ጋዜጠኛው የሐገሩን ብሔራዊ ጥቅም የሚጎዳ ነገር አልፈጸመም›› ብሎ በነጻ አሰናበተው፡፡ ፍ/ቤቱ ይህን ውሳኔ ያሳለፈው፤ የጋዜጠኛው ዘገባ በመውጣቱ በእንግሊዝ የጦር ኃይል ውስጥ የነበረው ችግር ሊታረም የሚችልበትን ዕድል መፍጠሩንና በዚህም እንግሊዝ በጦርነቱ አሸናፊ ለመሆን የሚያበቃ ቁመና መያዝ መቻሏን በመረዳቱ ነው፡፡
ሚካኤል አደጋ መስሎ የሚታየውን ነገር ገለፀ። መፍትሔ የመሰለውን ነገር አስቀመጠ፡፡ ደረጀ በዚህ ተቆጥቶ፤ ‹‹ሚካኤል ያ  ሁሉ ግፍ ከሐገሪቱ ሰማይ ስር ሲፈፀም [እያየ] ጥሩ እንቅልፍ አግኝቶ ቆይቶ አሁን በለውጡ ጅማሬ ‹ለማስጠንቀቂያ› መባዘኑ›› ተገቢ አይደለም አለ፡፡ ሚካኤል ችግሩን ለማሳወቅ መድፈሩ መታረም የሚችለው ነገር በጊዜ እንዲታረም ነው፡፡ በዚህ ረገድ ሊነሳ የሚገባው፤ ‹‹ለመሆኑ የማስጠንቀቂያ ደወል የሚያስደውል ችግር አለ ወይስ የለም?›› የሚል ጥያቄ ነው። የደረጀ አቋም ግልጽ ይመስለኛል፡፡ ችግር የለም የሚል ነው፡፡ ነገር ግን ችግር የለም ሲል፤ እንደ ሚካኤል የተጨባጭ ሁኔታ ትንታኔ አቅርቦ አይደለም፡፡ የሚካኤል ትንታኔና ድምዳሜ ስህተት መሆኑን የሚያሳይ ሐሳብ አቅርቦ አይደለም፡፡
ሚካኤል አስቀድሞ ሊያሳየን የሚሞክረው፣ አደጋ በተጨባጭ መኖሩ ከተረጋገጠ፤ ቀጥሎ ‹‹አደጋው ግልጽና ድርስ አደጋ ነው?›› ወይስ ‹‹የሩቅና ምናልባታዊ አደጋ ነው?›› የሚለው ነገር ሊፈተሽ ይችላል፡፡ ይህም መውሰድ የሚገባንን እርምጃ ለመወሰን የሚያስችል ዕድል ይፈጥርልናል፡፡ አደጋው ግልጽና ድርስ ከሆነ፤ እርምጃችን አጣዳፊና ሊወሰድ የሚገባውም እርምጃም ግልጽ መሆኑን ያመለክታል፡፡ በሌላ በኩል፤ አደጋው ግልጽ ሆኖ ሳለ፤ ነገር ግን ድርስ ካልሆነ፤  እርምጃችን አጣዳፊነት እንደ ሌለውና ሊወሰድ የሚገባው እርምጃ የሚያደናግር ባህርይ እንደሌለው ያስረዳናል፡፡ በሌላ በኩል አደጋው ‹‹የሩቅና ምናልባታዊ አደጋ ሆኖ ከታየን፤ አጣዳፊነት ያለው እርምጃ መውሰድ የሚያስፈልገው አደጋ አለመሆኑን እና ሊከሰት የመቻል እና አለመቻል እኩል ዕድል ያለው አደጋ መሆኑን እንገነዘባለን፡፡ በዚሁ ልክ ዝግጅት እናደርጋለን፡፡ ስለዚህ ግልጽ እና ድርስ የሆነ አደጋ ብቻ ሳይሆን የሩቅ እና ምናልባታዊ የሆነ አደጋንም አንስተን መወያየት ለውጡን በመደገፍ እንጂ በመቃወም ስሌት ሊመዘን አይገባም፡፡   
ሚካኤል በ‹‹የማስጠንቀቂያ ደወል›› ያነሳውን ነገር በወጉ ለመረዳትና ትክክለኛ ዳኝነት ለመስጠት፤ በጸሐፊው ሞቲቭ ላይ የተመሰረተ ፍካሬ ከመስጠት መቆጠብ ያስፈልጋል፡፡ ሚካኤልን ለመሄስ  ከክብረ ነገስት፤ ከኮምዩኒስት ርዕዮተ ዓለም፣ ከሥነ ሰብእ፣ ከሚቲዮሎጂ፣ ከታሪክ ወዘተ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን መመርመርን ይጠይቃል፡፡ በሌላ በኩል፤ በኢትዮጵያ በቅድመ አብዮን ዘመን ለረጅም ጊዜ ጸንቶ የቆየውን ስርዓት ‹‹የፊውዳል ሥርዓት ማለት ይቻላል?›› ከሚል ተመልሶ ያደረ  ከሚመስል ጥያቄ ጀምሮ የአማርኛ ቋንቋ ከመንግስታት ጋር ያለውን ትስስር፣ በኢትዮጵያ ተከሰተ የምንለውን የብሔር ጭቆና ሌሎች እንደ ቁም ነገር፣ እኛ እንደ ተረት የምንመለከተውን የንግስተ ሳባ ነገር በማንሳት፤ ሚካኤል በከፈተው በር በርካታ ነገሮችን እያነሳን ውይይቱ ከአንዱ ደረጃ ወደ ሌላው ከፍ እያለ እንዲሄድ ማድረግ ይቻል ነበር፡፡
ታዲያ የረባ ውይይት የሚፈጥር አስተያየት ይዞ ለመምጣት ተጨማሪ ንባብ ማድረግ የሚጠይቅ በመሆኑ፤ በሚካኤል ሥራ ላይ ሒስ ለመሰንዘር ቢያንስ ከእርሱ ትንሽ ከፍ ያለ ቁመት፤ ካልሆነም የተካከለ ቁመና ይዞ መገኘትን ይጠይቃል፡፡ በዚህ ረገድ ያለኝን ብቃት አልተማመንኩትም። እናም ትንሽ ንባብ በማድረግ ቁመቴን ከፍ ለማድረግ ወይም ከእርሱ ለመተካከል የተወሰነ ጥረት ለማድረግ ሞክሬ ነበር፡፡ ግን የደረጀ አስተያየት ሊፈጥረው የሚችለውን የስህተት ጎዳና ለመዝጋትና ሚካኤል ላዳረገው ጥረት አክብሮቴን ለመግለጽ፤ መጽሐፉን ትቼ ወደ ሁለተኛ ማዕረግ ሂስ ገባሁ፡፡ ሚካኤል በ‹‹የማስጠንቀቂያ ደወል›› ያነሳቸው ሐሳቦች እንደ መጠቅለያ ወረቀት ከቤት ስንደርስ ወደ ቆሻሻ ቅርጫት የሚጣሉ ሐሳቦችን አይደሉም፡፡
ሐሳቦችንም ሲፈትሽ የተመሰገነ ዳኛን እንኳን የሚያስንቅ ‹‹ስሜተ -ከል›› ዝንባሌ አለው፡፡ አንድን ነገር ለመፈተሽ የሚነሳ ተመራማሪ ሊኖረው የሚገባውን ገለልተኛ መነጽር አጥልቆ፤ አጀንዳውን በትክክል ለማየት ከሚያስችል ማማ ወጥቶ፤ የፖለቲካ ተምኔቱ ወይም አቋሙ የሚፈጥርበትን የስበት ኃይል ለመቋቋም ከሚያስችል ቦታ ቆሞ፤ የቲፎዞ ጩኸት ሆነ የተቃዋሚ ቡታ በህሊናው መስኮት መጋረጃ እንዳይጥሉበት አድርጎ፤ የህሊናውን ችሎት ፀጥታ አስከብሮ ፍተሻውን ለማድረግ ሞክሯል፡፡ በዚህም ለለውጡ መሳካት የበኩሉን አስተዋጽዖ አበርክቷል፡፡ በመጨረሻም፤ ለጋዜጣው አንባቢዎች፣ ለወዳጄ ደረጀ በላይነህና ለሚካኤል ሽፈራው፤ መልካም አዲስ ዘመን እንዲሆንላቸው እመኛለሁ፡፡


Read 1269 times