Monday, 10 September 2018 00:00

የቲ-ሸርት አታሚው ፀሎት

Written by  ቤተማርያም ተሾመ betishk@gmail.com
Rate this item
(1 Vote)

 ጋሽ በዛብህ 27 ዓመት ካገለገሉበት መስሪያቤታቸው በፈቃዳቸው ሥራቸውን ለቀው ወጡ፡፡ ምክንያታቸው ደግሞ ለመደመር  ለሚወጣው ህልቆ መሳፍርት ታዳሚ፣ በግላቸው ቲ-ሸርት አትመው ለመክበር በማሰብ ነበር። ያሰቡትን ያክል ባይሆንም የተወሰኑ የዶክተሩ ምስል ያለባቸውን ቲ-ሸርቶች  ሸጠዋል፡፡ በርካታ ቲ-ሸርቶች መትረፋቸው  ግን ክፉኛ እያሳሰባቸው መጥቷል፡፡ በዚህ ላይ የባለቤታቸው የ”ብዬህ ነበር”  ንዝንዝ እለት ተለት እየናረ መጥቷል፡፡ ከዕለታት አንድ ቀን፡-
“ቆይ .. እኔ የምሎት ለምን በተረፉት የዶክተር ዐቢይ ቲ-ሸርቶች ላይ የኤክስ ምልክት አድርገው፣ ለተቃዋሚ ሰልፈኞች አይሸጡም?“
ባለቤታቸው ንዝንዛቸውን ጀመሩ፡፡
“አንቺ ደግሞ እንኳን ለሰልፍ ሊደርስ ቀርቶ ስሙን በክፉ የሚያነሳ ሰው ሰምተሻል?“
ጋሽ በዛብህ አጉረመረሙ፤ ሳይሸጡ ወደተረፉት ካናቴራዎች እያዩ፡፡
“እ….እ…..እ…እ!!!!!“ ባለቤታቸው ድንገት ከማጀት አንባረቁ ፡፡
“እኔ ምሎት …. ለምን በጎን በኩል በተረፈው ቦታ ላይ የኢሳያስ አፈወርቂን ገፅታ አትመው፣ በደም ተሳስረናል!!! የሚል ፅሁፍ በጉልህ አያሰፍሩበትም?“
ጋሽ በዛብህ ትንሽ አሰብ አድርገው፤
 “ አ…..ይ……ይ!!! ለጥቂት ትንሽ ቢቀድም ነበራ!! አሁንማ አለፈ“ አሉ፤ በቁጭት ቲ-ሸርቱን ፊት ለፊት ወጥረው እያዩ፡፡
“እ….እ…..እ…እ!!!!!“ አሉ ባለቤታቸው በድጋሚ፣ ሚስጥር በተገለጠለት ሰው ድምፅ፡፡
“ምን ሆንሽ!!!?“
“እ….እ…..እ…እ!!!!! ለምን የኢንጂነሩን ፎቶ ከጎኑ አትመው፣ ፍትህ ለኢንጂነሩ!! አይሉበትም?”
“አይ አንቺ ደግሞ ካለፈ በሁዋላ ትቃዣለሽ ልበል?“
ለአፍታ ያህል ዝምታ ሰፈነ፡፡
“እ….እ…..እ…እ!!!!!“
“ምን ሆንሽ!!!!!?“
“ይበሉ ይፍጠኑ!!“
“ምኑን?“
“በተረፈው ቦታ ላይ  በዶክተሩ ምስል ግራና ቀኝ፤ የሁለቱን ጳጳሶች ምስል አትመው፤ ተዋህዶዎች ተዋህደናል!! ብለው ይፃፉበት“
ጋሽ በዛብህ ደንገጥ አሉ፤ ከመቀመጫቸው እመር ብለው ተነስተው ሰዓታቸውን ተመለከቱ፡፡
“አ…..ይ……ይ!!! ሃሳብሽ ሸጋ ነበር፤ ለከሰአት ግን አይደርስም“ ጎርናና ድምፃቸው ይበልጥ ጎረነነ፡፡
“መፍጠን ነበረብን!!!“ ብለው ጠረጴዛውን እየተመተሙ በሃሳብ ተዋጡ፡፡
“ኦ…..ኦ…….ኦ….!!!!!” ጋሽ በዛብህ ድንገት አንባረቁ፡፡
“ምን አገኘህ?“
ባለቤታቸው ከማጀት ደንግጠው ወጡ፡፡
ጋሽ  በዛብህ ወደ መስኮቱ አንጋጠው፣ ወደ ውጪ መጣራት ጀመሩ፡፡
“ጆኒ…….ጆኒ…..”
“አቤት“ ከፌስ ቡክ ላይ የማይነቀለው የጎረቤታቸው ልጅ መለሰ፡፡
“ምን አዲስ ወሬ አለ?“
“ስለ ምን?“
“ያው ስለ ፖለቲካው ነዋ“
“እ……!! ያው ጳጳሶቹ እየመጡ ነው“
“ኤጭ እሱን ማን አለህ…ያ…. የእከሌ ደህንነት ያሳስበኛል፤ የእከሊት ደህንነት ያሳስበኛል እያለ የሚፅፈው ሰውዬ ምን አለ?“
“እ……!! እሱማ….. የእከሌ እና የእከሊት ደህንነት ያሳስበኛል ብሏል“
“አረ….. እባክህ…..!!“
“አዎ”
“ስንት ላይክ አለው?“
“ነፍ!! ነው-- 2.4 ኬ“
“ኬ….? ኬ ደግሞ ምንድን ነው?“
“ሺ…ሺ ማለት ነው“
ጋሽ በዛብህ ወደ ቲ-ሸርቶቹ ዞረው፣ ለባለቤታቸው ቀጭን ትእዛዝ አስተላለፉ፡-
 “እየውልሽ በነዚህ ላይ ፍትህ ለእከሊት! በነዛ ላይ ደግሞ ፍትህ ለእከሌ! ተብሎ ከእነ ምስላቸው ይታተም፡፡”
“በስመኣብ ወወልድ ሳይሞቱ!!! ?” ባለቤታቸው አማተቡ፡፡
“ተናገርኩ!!“ ጋሽ በዛብህ ዞረው ወደ በሩ ተራመዱ፡፡
“እና የት ሊሄዱ ነው?“
“መጣሁ ያልጨረስኩት ስራ አለ“  ጋሽ በዛብህ ንጭንጭ አሉ፡፡
የግቢውን በር ከፍተው ወደ ተራራው እያዩ አማተቡ፤ ፊት ለፊት ተራራው ላይ ወደምትታየው ደብር ፊታቸውን አዙረው ማልጎምጎም ጀመሩ፡፡
“ይቅር በይኝ ….. ይቅር በይኝ …..ይቅር በይኝ …..እናቴ………”
ፀሎታቸውን እንደጨረሱ ወደ ህትመታቸው ተመለሱ፡፡

Read 778 times