Monday, 10 September 2018 00:00

አክራሞትና ምኞት!

Written by  አብይ ተስፋዬ አሳልፍ (አተአ)
Rate this item
(1 Vote)

 “--ተስፋችንን የጣልንበትን አትንሳን ጌታየዋ፡፡ እያቃሰትኩ አቀበቱን ስወጣ በሩቁ የቤተ ክርስትያኒቱን አፀድ አየሁና ፈገግ አልኩ፡፡ እና በመጨረሻ እንዲህ የሚል ፀሎት ጮክ ብዬ አደረስኩ፤ ‹‹ያሳለፍነውን ከባድ ዘመን አትመልስብን፡፡ ያጣናቸውንና የተነጠቅናቸውን አስብልን፡፡ አገር አፍርሰን በፍርስራሽ ላይ ለመቆም አቅደን የነበረ ቢሆንም እንዳሰብነው አታውለን፡፡ ከንቱ ምኞታችን፣ ክንቱ መሆኑ ይገባን ዘንድ ግለፅልን …”
    
    (የዋዜማ ወግ)
የአልቃሻው ሐምሌ ማጉረምረም ብቸኝነቴን ስለሚያባብስብኝ የበቆሎ ጥብስ እየፈጨሁ ሳስብ ከረምኩ፣ እንደተከዝኩ ከነሐሴ ጋር ተጨባበጥኩ። አሁንም የነሐሴ ሰማይ ከማይነጥፍ እኝኝ የሚል መንፈሱ አልፀዳም፡፡  በጣም ሃዘን የጎዳው ወር ሆኖ ይሆን እላለሁ! አልቃሻነቱ በእርሱ ይብሳል። ማልቀሱ ይጠቅመው ይሆናል፡፡ ለእኛ ግን የእንባው መዓት የቆሸሹ መንደሮቻችን እስኪያፀዳ ድረስ ፈይዶልናል፡፡
እናም እነሆ መስከረም ሊጠባ ነው (ልክ ህጻን ከማህፀን እንደሾለከ የእናቱን ጡት እንደሚጨብጠው መሆኑ ነው!)፡፡ በዚህ ወር ነፍሳት እንኳ ከአቅማቸው ሀሴት በማድረግ፣ ጥንድ ጥንድ እየሆኑ መተቃቀፍ ያበዛሉ፡፡ በሰፈራችን ጉራንጉሮች ሳልፍ የሚሸተኝ እንደ ድሮው የበጋ ወቅት የጠነባ ቱቦ ብቻ አልነበረም። የቡሄና የአዲስ አመት ችቦዎች የተሰሩበት ከሴ፣ ጠረኑ ወደ ሳንባዬ ሲዘልቅ መንፈሴ መታደስ ጀምሯል (ይመስለኛል!)፣ የቄጠማ ጉልቶችን ሳይ ያነቃቃኛል (ይመስለኛል!)፣ የአደይ አበባ ሽታና ቀለም ልጅነቴንና ተስፋዬን እኩል ያድሰዋል (ይመስለኛል!)፡፡ አንዳንዴ እንደ ሃምሌ ነጎድጓድ ለብቻዬ ማውራት እጀምራለሁ፣ ቤቴ ገብቼ እንደ ነሐሴ ዶፍ ስቅስቅ ብዬ አለቅሳለሁ፣ እንደ ጳጉሜ ዝናብ ድንገት ደራሽ በሆነ መከፋት ስሜት እኝኝ ማለት አበዛለሁ፡፡ ማፍረስና መናድ እመኛለሁ። ለምን እንደማለቅስ አይገባኝም፣ ራስ ምታቴ ይነሳል፣ ህመሜም አብሮ ይታደሳል፡፡ ብቸኝነቴ ይገዝፋል፣ እናም ብዙ ጊዜ የህይወቴ መስከረም በእውኑ ይመጣ ይሆን እላለሁ…!
ይሄውና ጥቁሩ እኔ … በድባቴ ውቅያኖስ ሰምጬ መተንፈሻና መላወሻ አጣሁ፡፡ ለመዋኘት ከማይታሰብበት እንደ በረዶ የቀዘቀዘ ስሜት መውጣት ችግር ሆኖብኛል፣ በውኑ የምድር ህይወት በቃኝ ተብሎ በፍላጎት ተፈርሞ የሚተው ቢሆን፣ በመጀመሪያው ረድፍ እሰለፍ ነበር፡፡ አሁኑኑ እፈርምም ነበር!፣ በቅቶኛል፣ ሰልችቶኛል። ከዚህ በኋላ ለመጣው አዲስ ዓመት ሁሉ ምንም አይነት ጎልና እቅድ መንደፍ አያስፈልገኝም፡፡ ምን አዲስ ዓመት አለና፡፡ ወራቶቹም የዱሮው፣ ቀኖቹም የጥንቱ ራሳቸው ናቸውና በቃኝ እላለሁ። … ግና  አንዳንዴ ህይወት እንደ አፍሪካ ስልጣን በእኔና በመሰሎቼ፣ በተለይ በድሆች ላይ ሙጥኝ የምትለው ነገር አላት፡፡ አጥብቀው ለሚፈልጓትና የኑሮ ምርቃት ለሚጠባበቁት ግን ትነፍጋቸዋለች። ለሰለቿት ደግሞ ሙጥኝ! ኤጭ ህይወት ጥላ ነገር ናት! (ሲርቋት የምትቀርብና የምትከተል ነገር!)
እንዲህ ስለማስብ ይሆናል ቀኖቼ ሁሉ በድባቴ የሚሞሉት፡፡ የምኖረው የማስበውን ይሆን!  ኑሮዬ የሚቀዳው ከማሰላስለው  ይሆን! (ይሆን እላለሁ! … ነውንጂ!)
***
እናም ከዚህ ዙረትና ጡዘት ለመላቀቅ ሄድኩላችሁ … አገራችሁን፣ ከተማችሁን፣ ጭንቅንቃችሁንና እያዩ መተላለፉን ሁሉ ጠቅልላችሁ ተረከቡኝ፡፡
ሰማይና ምድር ተቃቅፈው ከሚውሉበት የአያቶቼ አገር ገባሁ፡፡ የናፈቅሁትን ልምላሜና ከማስመሰል ሰሌዳ ላይ ሳይሆን ከልብ ስር የሚመነጩትን ፈገግታዎች ተቀላቀልኩ፡፡ በየመንገዱ ስሄድ የለበሱትን ጋቢ ወይ ነጠላ ከጭንቅላታቸው ዝቅ እያደረጉ ‹‹…እንደምን አደሩ፣ ጤና ይስጥልን፣ ይክበር ይመስገን!…›› እያሉ ሰላምታ የሚሰጡኝ ህዝቦች መሃል ስገባ የነፍሴ ጰጉሜ ባተ፡፡
እነሆ መስከረም መጣልኝ እላለሁ፡፡ የክርስቲያን ዳዮር፣ የዶልስ ወይ የዶልቼ ሽቶዎች፣ የቪክቶሪያና የኒቪያ ዶዮድራንቶች ተዘነጉኝ፣ የአደይና የከሴ፣ የጥንዡትና የአርቲ፣ የጤናዳምና የበሶቢላ፣ የአደስና የናና ሽታዎች ከበቡኝ … እግዚአብሔር ይመስገን አሁን ደህና ነኝ!
እናም ዛሬ በጧት፣ ገና ሰማይና ምድር እቅፋቸውን ሳያላቅቁ፣  አያቴ ወደተኛሁበት መደብ መጣና እንዲህ አለኝ፤ ‹‹...ጌታ መሳይ! እስቲ ተነሳ ቤተስኪያን ደርሰን እንምጣ!…››
መሄድና ከአልጋዬ መነሳት አልፈልግሁም። ውጪው ይበርዳል፡፡ ጤዛው ገና ከሳሮች ላይ አልረገፈም፣ ቡሬ እንኳ ገና መች ታለበች። የተሸፋፈንኩትን አሮጌ ብርድ ልብስ ከፊቴ ላይ እየገለጥኩ፣ በዚህ ከድባቴ የመሰናበቻ ማለዳዬ ከመሬት ተነሳስቼና የጥርጣሬ በሮቼን ከፍቼ አያቴን ተገዳደርኩት፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ በአደባባይ ስንፍናዬን አጋለጥኩ፡፡ ትንሽ ተምሬ ትንሽ መጠየቅ ስጀምር የነበረውንና የቆየውን እምነቴን እንደመተው አድርጎኝ ነበርና እንዲህ አልኩት፡-
‹‹እስከማውቀው ድረስ ቤተ ክርስትያን ስመላለስ፣ ከ20 ዓመት በላይ ሆነ፣ በሳምንት ለሁለት ቀን ከአጸዶቹ ስር እየተቀመጥኩ ስብከት አዳመጥኩ፣ እናም መመላለሴ ሁሉ ለከንቱ መሆኑ ድንገት ተገለጠልኝ! ተመላለስኩ፤ በሺዎች የሚቆጠሩ ስብከቶችን ሰማሁ፣ ግን አንዱንም አላስታውሰውም፣ አመሰገንኩ፣ አወደስኩ ምን ተጠቀምኩ! ምንም! ስለዚህ በቃኝ፡፡ እንኳን እኔ ልሔድ ሰባኪውንም ወርደህ ወደ ራስህ ስራ ተሰማራ በልልኝ አያያ፤ እዚያ ቆሞ በመለፍለፍ ዕድሜውን አይጨርስ፡፡ እኔም መመላለሱ ይቅርብኝ፡፡››  (ድፍረቴ ለራሴም እየገረመኝ!)
በድንጋጤና በቦዘዙ አይኖች እያስተዋለኝና ባለ መንታ ጫፍ ዘንጉን ደገፍ ብሎ ተካከዘና እንዲህ አለ፤ ‹‹ይገርምሃል ልጄ! ይህንን በደጃችን ያለውን መሬት ሳርስ፣ በአንተ አባት ዕድሜ ኖርኩ፡፡ ዘመኑ የተቀየረና ሳይንሱ ያደገ ቢሆንም እኔ በዘመናቱ መካከል በእርሻ ስራዬና በበሬዎቼ ከመስራት የተለየ ለውጥ አላመጣሁም፡፡ ምርቱ በየአመቱ ለቤተሰቤ የምግብ ዋስትናና የገቢ ምንጫችን ነው።
ታዲያ አንድ የሆነ እንዳንተ ወፈፍ ባደረገኝ እለት፤ ቁጭ ብዬ ከማሳው ላይ የሰበስብኩትን የእህል ብዛት፣ አይነትና የበላሁትን የምግብ አይነት ስቆጥረው ምንም የማስታውሰው የተለየ ምግብ አልነበረም፣ (ህልቆ መሳፍርት ከመሆኑ ውጪ!)፡፡ በዝንጋኤ ህሊናና በብዛቱ የተነሳ በተለየ የማስታውሰው የእህል አይነት ስለሌለ አልጠቀመኝም ብዬ አሰብኩ፡፡ ግና ልክ አልነበርኩም፡፡ ያንን ሁሉ አመት ጣፋጭና ለጤና ተስማሚ የተመጣጠነ ምግብ እየመገበ፣ የሚችለውን ሁሉ ምርት እየሰጠ ህይወቴን ማቆየት ብቻ ሳይሆን ጤነኛ ሆኜ እንድኖር አድርጎኛል። ልጆቼን አስተምሬ ድሬበታለሁ፡፡ ራሳቸውን የቻሉት በዚሁ ነው፡፡ ፈጽሞ ውለታውን ባልቆጥርና ባላስታውሰውም፣ ለእኔ ዛሬ ላይ መቆም ግን ዋናው ተጠሪ የለፋሁበት ይህ መሬት ነው፡፡ እርሱም ስለ እኔ ውለታ አይቆጥርም፤ እኔም አመስግኜው አላውቅ፡፡ ግና እስከለፋሁበት ድረስ ሳይቆጥር ሲሰጠኝ ነው የኖርነው፡፡
እንግዲህ እነዚህ ምግቦች ባስታውሳቸውም ባላስታውሳቸውም አኑረውኛል፣ ምግቡ በሃይልና በሙላት እንድቀጥል፣ በተስፋና በፍቅር የልጅ ልጄን እያየሁ እንድቆም አድርጎኛል፡፡ ከዚህም ተሻግሮ ለብዙ ቤተሰብ እለታዊና አመታዊ ምግብ ሆኗል፡፡ እናም ልጄ፤ አንተም እነዚያን ስብከቶችና ምስጋናዎች ለይተህ አስታወስካቸውም አላስታወስካቸው፣ በህይወትህ እየተመገብካቸው፣ በመንፈስህና በነፍስህ ከመሞት ታድገው ያኖሩህ እነሱ ናቸው፡፡ አይደለም እንዴ! ፈሪሃ እግዚአብሔርን በልቦናህ እነርሱ ባይተክሉ፣ በብዙ ነገር የአሁኑን አንተ አትሆንም ነበር አይደል! ›› … ሲል ፈገግ ብሎ በዋዛ ጠየቀኝ፡፡
አፈርኩ፡፡ የአመታት የጥርጣሬ አጥሬን ዘወር አደረኩና ተስፈንጥሬ ተነሳሁ፡፡ ይህ በቀለም ትምህርት መሃይም መሳይ አያቴ፤ ስንቴ ነው ገበናዬን ለአደባባይ የሚገልጥብኝ፡፡ ከስንፍናዬ ማዶ በጥርጣሬ መሬቴ ላይ ልገነባው ያልኩት ቤት የሚቆም አልመሰለኝምና ወደ ጥንቱ ደልዳላ መሬቴ ልመለስ ስል አስቤ ተነሳሁ፡፡
ልብሴን እየለባበስኩ እያለሁ፣  እንዲህ ሲለኝ ይሰማኛል፤ ‹‹…አየህ ጌታመሳይ፤ የነፍስ ምግብ ማለት ልክ እንደ አይን መጨፈንና መከፈት ነው። በቀን ውስጥ የአይኖችህ ቆቦች መቼና ለምን ያህል ጊዜ እንደተዘጉ አታውቅም፡፡ ግን ብዙ ጊዜ ይከደናሉ፡፡  ባይከደኑ ኖሮ አይንህ እንደ ከብት ጀንዲ ይደርቅ ነበር፡፡ ነፍስህም ሳታስበውና ሳትቆጥረው የሚያልፍ አስፈላጊ ነገር ሊደረግላት ይገባል፡፡ አሁን ያንተ ጥርጣሬ ከቤትህ ጣሪያ ስር እንደተንጠለጠለ የሸረሪት ድር ነው፡፡ በጥቂት ውይይትና መነሳሳት ጠርገህ ብታፀዳውም ከሳምንት በኋላ ተመልሶ ይንጠለጠላል፡፡ ሸረሪቷ ካልሞተች ሁሌም ይኖራል…››
‹‹…ምን ያገናኘዋል!›› አልኩ በለሆሳስ፣ እያዛጋሁና ከከንፈሮቼ ዳር ዳር የደረቀ ልጋጌን በምራቄ እያላቀቅሁ።
‹‹…ነፍስ ያለውና በስጋ የሚመላለስ ሰው ይጠራጠራል፡፡ ስጋህ እስካልሞተ ድረስም ይቀጥላል! መድሃኒቱም ተግቶ ማጸዳዳት ነው። ቶሎ ተከተለኝ!…›› አለና ፈጠን ብሎ ወጣ፡፡ እውነት ነው፣ ካልሞትኩ እጠራጠራለሁ አልኩ በልቤ! ጋቢዬን ደርቤ ወጣሁ፡፡
***
ውጪው እንዴት ደስ ይላል፣ ክረምት ማለፉን እያረጋገጠ ስለነበር፣ ነሐሴ እንባውን ጠርጓል። ጳጉሜ ኮራ ብሎ ተፅናንቷል፤ በፈገግታ ቆሟል። መስከረምን ለመቀበል እየተሰናዳ ነው። ሜዳና ሸለቆው አረንጓዴ ለብሷል፣ ልምላሜ በጋ እንደሚመጣ ሳያውቅ የሚኖርባትን ወራት በአግባቡ እየተጠቀመ በደስታ ይዘልቃል፣ ይስቃል፣ ይፈነድቃል! ዛዲያ እኔስ በመንፈስ ምን ያጎሳቁለኛል ከንቱ!
ንሳማ! አልኩት ለራሴ፡፡ ከአያቴ ኋላ ዱብ ዱብ እያልኩ ኮረብታውን እያጋመስኩ፣ ራሴን ገሰፅኩት! ንሳማ! የነፍሴ ነሀሴ ከልቤ እለፍ!  ጥልቁ የድባቴ ወራት ልቀቀኝ፡፡ የነፍሴ መስከረም በአደይ ወደ ልቤ ዝለቂ…! ከልቤ ውስጥ… የእንባና የድባቴ መንፈስ ውጣ! ፀኣዳና የተስፋ ዘመን ግባ! ከአገሬ መቁሰልና መድማት ጋር አብራ ወደ ስቃይ ትንሸራተት የነበረችው ነፍሴ፤ ጥቂት እስትንፋስ ወስዳ በተስፋ መንከላወስ ጀምራለችና ትካዜ ከእንግዲህ ተወኝ፡፡
አቀበቷን መውጣት ስንጀምር ትንፋሼ መቆራረጥ ጀመረ፡፡ አያቴ አየት አደረገኝና፤ ‹‹…ቶሎ ቶሎ ለጥቅ እንጂ ጌታመሳይ! እውነትም ይህ ከተማ አስንፎሃል!….›› ስርቅ በምትል ፈገግታ ፈገገና እንዲህ ቀጠለ፤ ‹‹…አሻፈረኝ አልከኝ እንጂ እዚሁ የአያቶችህን ሁዳድ እያዘመርክ ብትኖር ደስታህ አይጎድልም ነበር፡፡ አሁን ግን የስግብግብነት ጎተራ ከማይሞላበት ከተማ ዘልቀህ ልትሞትብኝ ነው፡፡ ወይ ነዶ!…›› … እናም ሽማግሌው አያቴ፣ ወጣቱ እኔን እየጠበቀ ሽቅብ ነጎደ፡፡
እኔ ቃሉን በልቤ ደጋግሜ እያሰብኩ እንዲህ አልኩ፤… ‹‹እነሆ እኔ የመታደስ ወቅት ላይ ነኝ! ጌታየዋ! ወጣቶች ከአያቶች እየተማሩ መንገድ መምራቱን የሚቀበሉበት ዘመን አምጣ፡፡ እኛ ሁላችን እኩል የምንተያይበትና የምንከባበርበት ዘመን አምጣ፡፡ የምንዋደድበት ዘመን አምጣ፡፡ የምንረዳዳበትና የምንደጋገፍበት ዘመን አምጣ፡፡ የምንፋቀርበት ዘመን አምጣ! (ግን ከየት!)...››
አሜን! መርሃባ ጌታየዋ! … ልባችንን በተስፋ እንሙላና የፈገግታ ህይወት እንኑር! … ምክንያቱም “As a man thinks in his heart, so is he.” …. ይላልና ቅዱሱ መፅሃፍ! ተስፋችንን የጣልንበትን አትንሳን ጌታየዋ፡፡ እያቃሰትኩ አቀበቱን ስወጣ በሩቁ የቤተ ክርስትያኒቱን አፀድ አየሁና ፈገግ አልኩ። እና በመጨረሻ እንዲህ የሚል ፀሎት ጮክ ብዬ አደረስኩ፤ ‹‹ያሳለፍነውን ከባድ ዘመን አትመልስብን። ያጣናቸውንና የተነጠቅናቸውን አስብልን፡፡ አገር አፍርሰን በፍርስራሽ ላይ ለመቆም አቅደን የነበረ ቢሆንም እንዳሰብነው አታውለን። ከንቱ ምኞታችን፣ ክንቱ መሆኑ ይገባን ዘንድ ግለፅልን …!››
‹‹አሜን ልጄ!›› አለ አያቴ … (እኔ ጮክ ብዬ መናገሬን ከቶም አላሰብኩም ነበርና ተገረምኩ!)
‹‹አሜን!›› አልኩ እኔም ለጥቄ፡፡
***
ብዙዎች በብዙ ሀሳቦች ላይ ቢለያዩም በሚከተለው ሐረግ ሀሳብ ላይ ግን የሚስማሙ ይመስላሉ … ‹‹…የምንሆነው የምናስበውን ነው…›› በሚለው! Ralph Waldo Emerson “A man is what he thinks about all day long.” … ‹‹ሰው የሚሆነው ቀኑን ሙሉ የሚያስበውን ነው…››፣ The Roman emperor Marcus Aurelius put it this way: “A man’s life is what his thoughts make of it.” … ‹‹የሰው ልጅ ህይወት የሚቀዳው ከሃሳቡ ነው/እንዳሰበው ይኖራል!››፣ መፅሐፍ ቅዱስም ይላል … ‹‹ሰው የልቡን ሀሳብ ነው! … As a man thinks in his heart, so is he. …. !”
እናም በጎ በጎውን በማሰብ ወደ ተራራው መገስገስ ጀመርኩ፡፡
መልካም በዓል! መልካም አዲስ አመት!

Read 1053 times