Print this page
Saturday, 08 September 2018 14:20

ለግንቦት 7 አመራሮች አቀባበል ከተማዋ ደምቃለች

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(31 votes)

 ነገ ፕ/ር ብርሃኑ ነጋን ጨምሮ 250 አመራሮች ይገባሉ

    ነገ ማለዳ አዲስ አበባ ለሚገቡት የ”አርበኞች ግንቦት 7” ንቅናቄ አመራሮች፤ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የመዲናዋ ነዋሪዎች ደማቅ አቀባበል ያደርጉላቸዋል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን መዲናዋ ለዚሁ የአቀባበል ሥነ ሥርዓት፣በባንዲራና በፖስተሮች ደምቃለች፡፡ ለአመራሮቹ የሚደረገው አቀባበል ከጠዋቱ 12፡30 እስከ ቀኑ 9 ሰዓት በተለያዩ መርሃ ግብሮች እንደሚፈፀምም ታውቋል፡፡
የንቅናቄው አመራሮች ከሚኖሩባቸው የተለያዩ የአሜሪካና አውሮፓ ሃገራት በተለያዩ በረራዎች ከጠዋቱ 12፡30 ጀምሮ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ እንደሚደርሱ ለአዲስ አድማስ የጠቆሙት የአቀባበል ኮሚቴው አስተባባሪ አቶ ብርሃኑ ተ/ያሬድ፤ ሁሉም አመራሮች ከገቡ በኋላ ዋናው የአቀባበልና የዕርቅ ማብሰሪያ ሥነ ሥርዓት ወደ ሚካሄድበት አዲስ አበባ ስታዲየም እንደሚያመሩ አስታውቀዋል፡፡
በነገው ዕለት በመላው ዓለም የሚገኙ የንቅናቄው አመራሮች ተጠናቀው ወደ ሃገር ቤት እንደሚገቡ ያመለከቱት አስተባባሪው፤ ንቅናቄውም ቀደም ሲል ሲያራምድ የነበረውን በትጥቅ የታገዘ ሁለገብ ትግል ፈትሾ፣ በሃገር ውስጥ በሠላማዊ መንገድ ለመታገል የሚያስችለውን ስትራቴጂ ነድፏል ብለዋል፡፡ በቅርቡም ንቅናቄው በአዲስ መልክ ተደራጅቶ ለምርጫ ውድድር እንደሚቀርብ የጠቆሙት አቶ ብርሃኑ፤ ወደ ሃገር ቤት የሚመጡት አመራሮችም ለዚሁ ዓላማ አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ የክልል ከተሞች፣ ህዝባዊ ውይይቶችን እንደሚያካሂዱ ገልፀዋል፡፡
አርበኞች ግንቦት 7 በመንግስት በሽብርተኝነት ተፈርጆ፣ የነፍጥ ትግል ሲያካሂድ  መቆየቱ የሚታወቅ ሲሆን የነበረውን ግጭትና ጥላቻ ለመሻርም በአቀባበል ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የእርቅ ብስራት ይፈፀማል ተብሏል፡፡  
የአቀባበል ሥነ-ሥርዓቱን የደመቀ ለማድረግ ኮሚቴው የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን ሲያደርግ መቆየቱን ያወሱት አስተባባሪው፤ ከኮሚቴው ውጭ በየአካባቢው ያሉ ወጣቶች የመሪዎቹን ፎቶግራፍ የያዙ ባነሮችን፣ ቲ-ሸርቶችንና ባንዲራዎችን በማዘጋጀት ስራ ተጠምደው መሰንበታቸውን ገልጸዋል፡፡ የተለያዩ የመዲናዋ አካባቢዎችም በተለይ ፒያሣ፣ ቦሌ፣ ስታዲየም፣ መርካቶ፣ አራት ኪሎ፣ መገናኛ፣ ካዛንቺስ --- አርማ በሌለው የኢትዮጵያ ሠንደቅ ዓላማና በድርጅቱ የተለያዩ መሪዎች ፎቶግራፎች አሸበርቀው ሰንብተዋል፡፡
ከአርበኞች ግንቦት 7 አመራሮች ጐን ለጐን የጠ/ሚ ዶ/ር ዐቢይ አህመድ፣ የአቶ ለማ መገርሳ፣ የአቶ ገዱ አንዳርጋቸው፣ የአቶ ደመቀ መኮንን፣ የዶ/ር መረራ ጉዲና፣ የአቶ በቀለ ገርባና የሌሎች ፖለቲከኞችና አክቲቪስቶች ፎቶ ግራፎችም በየአደባባዩ ተሰቅለው ታይተዋ.ል፡፡ በየመንገዱም የመሪዎቹ ፎቶግራፍና የተለያዩ ፖስተሮች እንዲሁም ሠንደቅ አላማዎች ከ10 ብር ጀምሮ እስከ 500 ብር ሲሸጡ መሰንበታቸው ይታወቃል፡፡  

Read 8611 times