Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 12 May 2012 10:18

ህይወትህ በመንግስት እጅ ነው ያልፍልሃል ወይም ያለፋሃል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ይህች አገር የማን ነች? በየወሩ ትገብራለህ፤ ወይም በየወሩ ትደጎማለህ

ህይወት ሎተሪ ነች? በመንግስት እጣ፤ አከራይ ወይም ተከራይ ትሆናለህ

በ”ፍትህ” እና በ”ማህበራዊ ፍትህ” መካከል ያለው ልዩነት ምን እንደሆነ ታውቃላችሁ? “ወንበር” እና “የኤሌክትሪክ ወንበር” እንደማለት ነው - አንደኛው ለህይወት የሚመች ነው፤ ሁለተኛው ደግሞ ህይወትን የሚያጠፋ። እስቲ ከገጠር እስከ ከተማ፤ ከታክስ እስከ ኮንዶምኒየም ... ጥቂት ዞር ዞር ብለን እንመርምረው።እንደምታውቁት፤ የብዙ ዜጎች ኑሮ፤ ከቅዠት በባሰ ምስቅልቅል ተውጧል - በከተማም በገጠርም። አዲስ አበባ ወይም ድሬዳዋ፤ መቀሌ ወይም ናዝሬት፤ ባህርዳር ወይም ሃዋሳ ሊሆን ይችላል። በ400 ብር ደሞዝ፤ ራሱን ጨምሮ ስድስት ቤተሰብ የሚያስተዳድር የጥበቃና የፅዳት ሰራተኛ በየትኛውም ከተማ እናገኛለን -  የአመት ገቢው 4800 ብር መሆኑ ነው።

በሰሜንና በደቡብ፤ በምስራቅና በምእራብ ገጠሮችም፤ ራሱን ጨምሮ ስድስት ቤተሰቦችን የሚያስተዳድር ገበሬ ወይም አርብቶ አደር ይኖራል። እንደከተሜው የጥበቃ ወይም የፅዳት ሰራተኛ፤ የገበሬው የአመት ገቢም ዝቅተኛ ነው - አራት ወይም አምስት ኩንታል አምርቶ 4800 ብር ያገኝ ይሆናል - በወር 400 እንደማለት ነው።

ከገቢው ማነስ ጋር፤ የኑሮ ውድነት ሲጨመርበት አስቡት። ኧረ ለማሰብም ይከብዳል። ከ1999 አ.ም ወዲህ እየተደራረበ የመጣው የኑሮ ውድነትኮ፤ በኢትዮጵያ ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ፤ በመላው አለምም በአስከፊነቱ የሚጠቀስ ነው። ታዲያ፤ ከተሜውም ሆነ ገጠሬው በዚያች ገቢ ብቻ፤  ወሩንና አመቱን እንዴት መዝለቅ ይቻለዋል? አሁን ይሄ፣ ኑሮ ነው? የድህነትና የረሃብ ኑሮ! ግን፤ ለካ የረሃብ ኑሮም ብዙ መልክ አለው። የከተሜው ድሃ ብር ይወሰድበታል፤ የገጠሩ ድሃ ድጎማ ይሰጠዋል።

የአራት መቶ ብር ደሞዝተኛው ከተሜ፤ እጁ ውስጥ የሚገባለት ገንዘብ ከጊዜ ወደ ጊዜ ይቀንሳል እንጂ አይጨምርም። 15 ብር ግብር፤ 20 ብር የጡረታ ታክስ ይቀነስበታል። የህዳሴ ግድብ መዋጮ የመሳሰሉ የተለያዩ ተቀናሽ ገንዘቦችን አልቆጠርናቸውም። ከሚቀጥለው ሐምሌ ወር ጀምሮ እንዲሁም ከአመት በኋላ እንደገና፤ ተጨማሪ ገንዘብ ይቆረጥበታል። ለጡረታ ተጨማሪ 2% ተቀናሽ፤ እንዲሁም ለጤና ኢንሹራንስ ይቆረጣል የተባለው 3% ታክስ ሲመጣበት፤ በየወሩ 20 ብር ያጣል። በአጠቃላይ፤ ከደሞዝ የሚቀነስ የግብር እና የታክስ ተቆራጭ 55 ብር ይሆንበታል ማለት ነው - 400 ብር ደሞዝ ለሚያገኘው የከተማ ድሃ ሰራተኛ።

የገጠሩ ድሃስ? የሱም ኑሮ፤ ያው የድህነት ኑሮ ነው። በወር ከ400 ብር በማይበልጥ ገቢ፤ ራሱን ጨምር ስድስት ቤተሰቦቹን ለማስተዳደር መሞከር፤ ከድህነትም በታች እንደመቀበር ነው። ነገር ግን፤ ሴፍቲ ኔት (የምግብ ዋስትና) በሚባለው ፕሮግራም፤ በየወሩ ድጎማ ይሰጠዋል። ለአንድ ሰው በሰባ ብር ስሌት፤ ከነቤተሰቡ በወር 420 ብር ከመንግስት ወይም ከእርዳታ ድርጅቶች ይከፈለዋል። ራሱ በሚያገኘው የስራ ገቢ ላይ ድጎማው ሲደመርበት፤ በየወሩ 820 ብር ገቢ ይኖረዋል ማለት ነው።

“በሴፍቲ ኔት” ድጎማ አማካኝነት፤ የገጠር ድህነት እንደቀነሰ የሚገልፁ የመንግስት ባለስልጣናት፤ “ማህበራዊ ፍትህ በተግባር እውን እየሆነ ነው” በማለት ስኬታማነታቸውን በተደጋጋሚ አብስረውናል። “የማህበራዊ ፍትህ” ትርጉም ሲያብራሩም፤ “ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል” ማለት እንደሆነ ይናገራሉ። ያው፤ ከሃብታሞች ላይ ከፍተኛ ታክስ በመውሰድ፤ ለድሆች መስጠትና መደጎም እንደማለት ነው - “ማህበራዊ ፍትህ”። መንግስት፤ እንደ ሮቢን ሁድ፤ ከአንዱ ዜጋ ሃብት ወስዶ ለሌላው ዜጋ ይለግሳል - ከአንዱ ተቀብሎ ለሌላው መስጠት፤ አንዷን ዘርፎ ሌላዋን መርዳት፤ ከአበበ ነጥቆ ለከበደ።

በእርግጥም፤ መንግስት የሆኑ ዜጎችን ልደጉም ወይም ልርዳ ካለ፤ ሌላ አማራጭ የለውም፤ የግድ ከሌሎች ዜጎች ገንዘብ መውሰድ ወይም መንጠቅ ይኖርበታል። የድጎማ ስጦታ ሲጀመር፤ የታክስ ክፍያ ይበረታል። ድጎማው ሲበራከት፤ የታክስ ጫናው ከጣራ በላይ ይከመራል። የሆነ ሆኖ፤ እንዲህ ድጎማ የሚያገኙ ከ1ሚሊዮን በላይ ድሃ የገበሬ ቤተሰቦች (በጥቅሉ ከ7 ሚሊዮን በላይ የገጠር ነዋሪዎች) አሉ። “ምናለ ድሆቹ ገበሬዎች ቢያልፍላቸው! ከረሃብ ስቃይ ቢገላገሉ ምንኛ አስደሳች በሆነ!” ያሰኛል። ደግሞም፤ በርካታ ሰዎች ህይወታቸው ሲሻሻልና ከድህነት ሲወጡ፤ ሌሎች ሰዎችንም ይጠቅማል። ሃብታሞች ሲበራከቱ፤ የሌሎች ሰዎች ኑሮም ይሻሻላል። በድህነት የተማረሩ ኢትዮጵያውያን፤ ወደ አሜሪካና አውሮፓ ለመሄድ የሚናፍቁትኮ በሌላ ምክንያት አይደለም። ሃብታሞች በበዙበት አገር ውስጥ፤ ህይወትን የሚያሻሽል ብዙ የስራ እድል ይገኛል። በተመሳሳይ መነገድ፤ የድሃ ገበሬዎች ህይወት ቢሻሻልና ገቢያቸው ቢጨምር፤ ጥቅሙ ለሌሎች ይተርፋል። ለገበያ የሚያቀርቡት ምርት ይጨምራል - እጥረት ተቃለለልን። ከገበያ የሚገዙት ምርትም ይጨምራል - ደንበኛ በረከተልን ማለት ነው። ግን ምን ዋጋ አለው? የድሆቹ ገበሬዎች ገቢ ከፍ ያለው፤ ምርታቸው ስላደገ ሳይሆን፤ ድጎማ ስለተሰጣቸው ነው። ለነገሩ፤ ድሃው ገበሬ ድጎማ ቢያገኝም፤ በችጋር መለብለቡ አልቀረም። ድጎማው፤ ምናልባት የገበሬውን የረሃብ ቀናት በጥቂቱ ይቀንስለት ይሆናል እንጂ ከረሃብ አይገላግለውም።

“ግንኮ...” የሚል ሃሳብ እንደሚመጣላችሁ እገምታለሁ። አዎ፤ ከተማ ውስጥ ድሃው የፅዳት ሰራተኛና የገጠሩ ድሃ ገበሬ፤ አመቱን ሙሉ ይሰራሉ። በራሳቸው ጥረትና ስራ የሚያገኙት የወር ገቢም 400 ብር ነው ብለናል። በዚህ ገቢ ራስን ጨምሮ ስድስት ቤተሰብ ለማኖር መሞከር፤ የቅዠት ያህል አይደል? ግን፤ ከተሜው ድሃ ሰራተኛ፤ ተጨማሪ ቅዠት አለለት። ከላይ እንደተጠቀሰው፤ በየወሩ 35 ብር ለታክስና ለግብር ይቆረጥበታል። ከሚቀጥለው አመት በኋላ ደግሞ፤ ከደሞዝ ተቀንሶ በመንግስት የሚወሰደው ተቆራጭ 55 ብር ይሆንበታል - ከ400 ብር የሚቀነስ። በራሱ ጥረትና ስራ 400 ብር የወር ገቢ የሚያገኘው ገበሬ ግን፤ በየወሩ 420 ብር ድጎማ ከመንግስት ይሰጠዋል። ከአንዱ ዜጋ ገንዘብ መውሰድ፤ ለሌላው ዜጋ ገንዘብ መስጠት፤ በአንዱ ዜጋ ኪሳራ ሌላውን ዜጋ መጥቀም ...እንዴት ሆኖ? አንዱ ዜጋ የኮንዶሚኒየም እጣ ደርሶት ያከራያል፤ ሌላው ዜጋ ለኮንዶምኒየም ግንባታ ታክስ እየከፈለም የኪራይ ጫና ይከመርበታል... እኮ ለምን?

መቼም ኢትዮጵያ ሁላችንም የምንኖርባት አገር ነች። ለድሃው የፅዳት ሰራተኛና ለድሃው ገበሬ፤ እኩል አገራቸው አይደለችም? አንዱ በሌላው ኪሳራ ለመጠቀም ሳይሞክር፤ እንደየዝንባሌው ለስራ የሚሰማራባት የነፃነት አገር መሆን የለባትም? አንዱ የሌላውን ምርትና ገቢ በሃይል ለመውሰድ ሳይሞክር፤ እንደየጥረቱ ውጤት ተጠቃሚ የሚሆንባት የፍትህ አገር ልናደርጋት አይገባም? የአገሪቱ መንግስትስ፤ ሁሉንም ዜጎች በህግ ፊት እኩል የሚያይና የሚያስተናግድ መሆን የለበትም? ሁሉንም የአገሪቱ ሰው፤ የከተማና የገጠር ድሆችንም ጭምር፤ በእኩል የዜግነት አይን የሚመለከት፤ የሰዎችን ነፃነትና መብት የሚያስከብር፤ በህግ የበላይነት ፍትህን የሚጠብቅ መንግስት ሊኖረን አይገባም? ታዲያ ምነው፤ ከአንዱ ድሃ ብር ይወሰድበታል፤ ለሌላው ድሃ ብር ይሰጠዋልሳ? ምነው፤ ፍትህ ተንጋደደችሳ?

እንዲህ አይነቱ ፍትህን የሚጥስ ተግባር፤ “ማህበራዊ ፍትህ”፤ “ፍትሃዊ ክፍፍል” ተብሎ መሰየሙ ደግሞ፤ ይበልጥ ህሊናን ይቆረቁራል። “ማህበራዊ”፤ በሚሉ ቅጥያ የፍትህ ትርጉም በአናቱ ተገለበጠ። ከዚያማ፤ ዝርፊያ እንደ ስጦታ ይቆጠራል። የተለመደና ሲደጋገም የኖረ ዘዴ ነው። “ፍትህ”፤ “ነፃነት”፤ “መብት”፤ “እኩልነት” እና ሌሎች ትክክለኛ ፅንሰሃሳቦችና መርሆች፤ በየጊዜው በዚሁ መንገድ ይጣሳሉ - ፅንሰሃሳቦቹንና መርሆቹን የሚያፈርስ ቅጥያ እየተጨመረባቸው።

ጆርጅ ኦርዌል፤ አኒማል ፋርም በተሰኘው መፅሃፉ ይህንን ለመግለፅ ሞክሯል። እንሰሳት ባቋቋሙት ማህበር ውስጥ፤ የተወሰኑ እንሰሳት ተቧድነው፤ የሌሎች ወገኖቻቸውን ድርሻ መውሰድ ፈልገዋል። ነገር ግን፤ “All Animals are Equal” የሚለው የማህበራቸው መፈክር እንቅፋት ሆነባቸው። ሁሉም እንሰሳት እኩል ናቸው እየተባለ እንዴት የሌሎችን ድርሻ መንጠቅ ይቻላል? እናም፤ የ”እኩልነት”ን ትርጉም የሚያጠፋ አዲስ መፈክር ፈጠሩ - “All Animals are Equal. But Some Animals are More Equal than others” ... “ሁሉም እንሰሳት እኩል ናቸው። ነገር ግን አንዳንድ እንሰሳት ከሌሎች የበለጠ እኩል ናቸው” ይላል አዲሱ መፈክር። “የበለጠ እኩል”? ... በቃ፤ “እኩል” የተሰኘው ቃል፤ አዲሱን ቅጥያ ተሸክሞ ሞተ።

ጎረቤታሞች የነበሩ ሁለት የአዲስ አበባ ወጣቶች ላይ የተከተሰተውንም ለውጥ ማየት ይቻላል - “የማህበራዊ ፍትህ”ን ትርጉም ለመገንዘብ። ምግብ ቤት ተቀጥሮ ይሰራ የነበረው ወጣት፤ ሰፈሩ ውስጥ አንዲት አነስተኛ የቆርቆሮ ክፍል ተከራይቶ ቁርስ ቤት ከፍቷል። ዋጋው ዝቅተኛ ስለሆነ ገበያ ደህና ነው፤ በመጠኑም ቢሆን ህይወቱና ገቢው ተሻሽሏል። በዚያ ላይ፤ 1997 አ.ም አዲስ ተስፋ ይዞ መጣለት - መንግስት በዝቅተኛ ዋጋ ኮንዶምኒየም ቤቶችን ሰርቶ ለነዋሪዎች ያዳርሳል ተባለ። እንደሌሎቹ የሰፈሩ ነዋሪዎችና ወጣቶች ሁሉ፤ ለኮንዶምኒየም ቤት ተመዝግቧል።

በየአመቱ ሃምሳ ሺ ኮንዶምንኒየም እየተገነባ ለተመዝጋቢዎች ሁሉ በሰባት አመት ውስጥ እንደሚዳረስ ሲነገር የነበረ ቢሆንም፤ እስካሁን ከሃያ በመቶ በላይ አልተሳካም። ግን የተወሰነ ያህል እየተገነባ ስድስት ዙር እጣ ወጥቷል። በዚህ መሃል፤ ሁለት የሰፈሩ ወጣቶች፤ ስራ ባይኖራቸውም፤ ታክስ ባይከፍሉም፤ ከአራት ኪሎ ወደ መገናኛ በሚወስደው መንገድ አቅራቢያና ላፍቶ አካባቢ የኮንዶምኒየም እጣ ደርሷቸዋል። ሌሎች በርካታ ወጣቶችና በምግብ ቤት ህይወቱን ለማሻሻል የሚጣጣረው ወጣት ግን አልሆነላቸውም። ምኑ ይገርማል? ለኮንዶምኒየም ከተመዘገበው 450ሺ የአዲስ አበባ ነዋሪ መካከል፤ ከ350ሺ በላይ የሚሆነው ነዋሪ እጣ አልወጣለትም።

መቼም ቢሆን፤ የትም አገር ቢኬድ፤ የትኛውም ፓርቲ ቢመጣ፤ “የመንግስት ቸርነትና ድጎማ” ለሁሉም ሊዳረስ አይችልም። መንግስት በማናቸውም ሰበብ ኢኮኖሚ ውስጥ ጣልቃ ሲገባ፤ ሁሉም ዜጋ ተጠቃሚ ሊሆን አይችልም - አንዱ እንዲጠቀም፤ ሌላው መክሰር አለበታ። አንዳንዱ፤ እጣ ደርሶት በመንግስት የተገነባ ቤት ያገኛል፤ ያከራያል። ሌሎች ደግሞ ለቤቶቹ ግንባታ ታክስ መክፈላቸውን ይቀጥላሉ፤ ቤት የመገንባትም ሆነ የመከራየት አቅማቸው ይሸረሸራል፤ “እጣ ፋንታቸው” ነው። ከእነዚህ “እድለ ቢሶች” መካከል አንዱ የሆነው ወጣት፤ ኮንዶምኒየም ሳያገኝ ከትንሿ የምግብ ቤት ስራው ታክስ መክፈሉ ብዙም ላይቆጨው ይችላል። ነገር ግን፤ በ600 ብር ተከራይቶ በሚኖርባት አንዲት ጠባብ ክፍል ተፅናንቶ መቀመጥ አልቻለም። አከራዮቹ፤ ጥቅምት ወር ላይ ኪራይ ጨምር ብለውታል። ለመውጣትና ሌላ ቤት ለመከራየት ቢያስብም፤ የተሻለ አማራጭ አላገኘም። በከተማዋ ዙሪያ ሁሉ፤ የቤት ኪራይ ንሯል። ምን ያድርግ? 900 ብር መክፈል ጀመረ - በየወሩ ከኑሮ ጋር ትግል ነው። አሁን እንደገና መቶ ብር እንዲጨምር ስለነገሩት ተጨንቋል። በምግብ ቤት ስራው፤ በወር ወደ 2ሺ ብር ገደማ ትርፍ ቢያገኝም፤ ግማሹን ለቤት ኪራይ መክፈል፤ ከአቅሙ በላይ ሆኖበታል።

ኮንዶምኒየም የደረሳቸው የሰፈሩ ሁለት ወጣቶች ግን ጭንቀታቸው ሌላ ነው።  በእርግጥ፤ እንደወትሮው እያንዳንዳቸው ለባንክ በየወሩ 300 ብር ይከፍላሉ - ለኮንዶምኒየም ግዢ መሆኑ ነው። ኮንዶምኒየሙን የሚያከራዩበት ዋጋ ግን፤ ካለፈው ወር ጀምሮ እንዲጨምር አድርገዋል። የአንደኛው ኪራይ ወደ 2800 ብር ጨምሯል፤ የሌላኛው ደግሞ ወደ 1500 ብር። አንደኛው በሌላኛው ምን ያህል ሊቀና እንደሚችል አስቡት። የእጣ ጉዳይ ነው። ቤቶቹ ተመሳሳይ መጠን ቢኖራቸውም፤ ቦታቸው ስለሚለያይ፤ ኪራያቸውም ይራራቃል።

እንግዲህ አስቡት። ሰርቶና ተጣጥሮ ህይወቱን ለማሻሻል የሚሞክረው ወጣት፤ ከወር ገቢው ግማሽ ያህሉን ለቤት ኪራይ እንዲከፍል እየተገደደ ነው። በዚያ ላይ በየአመቱ፤ የግብር እና የታክስ ጫና ይሸከማል። ባለፈው አመት ከአራት ሺ ብር በላይ ቁርጥ ግብር ከፍሏል። ምግብ ቤቱ ውስጥ የሚሰሩ ሶስት ወጣቶች፤ እንዲሁም በምግብ ቤቱ የሚጠቀሙ ግንበኞችና የቀን ሰራተኞች ህይወትም፤ በተመሳሳይ ፈተና የታጠረ ነው - በየጊዜው በሚንር የቤት ኪራይ ይሰቃያሉ። ኮንዶምኒየም የደረሳቸው ሁለት ወጣቶች ግን፤ በየጊዜው ከሚንረው የቤት ኪራይ ተጠቃሚ ናቸው። የኮንዶምኒየም ባለቤት ለመሆን በየወሩ ለባንክ የሚከፍሉትን 300 ብር ከማካካስ አልፈው፤ በየፊናቸው 2500 ብር እና 1200 ብር ትርፍ ያገኛሉ። አየርባየር ልትሉት ትችላላችሁ።

መንግስት፤ የአንዳንዶችን የስራ ገቢ በታክስ ይወስዳል። ለአንዳንዶች ደግሞ፤ ያለ ስራ ገቢ እንዲያገኙ ያደርጋል - አየርባየር። ይሄው ነው፤ “ማህበራዊ ፍትህ”። መንግስት፤ “ለአገር ልማት፤ ለህዝብ ፍላጎት፤ ለድሆች ጥቅም፤ ለማህበራዊ ፍትህ” በሚሉ ሰበቦች የኢኮኖሚና የቢዝነስ ስራዎች ውስጥ ሲገባ፤ ሁሌም እንዲህ አይነት “አድልዎ” መፈጠሩ ፈፅሞ ሊቀር አይችልም። ለአንዱ ዜጋ ለመስጠት፤ ከሌላው ዜጋ መንጠቅ የግድ ነው (አንዱን ዜጋ ለመጥቀም፤ ሌላውን መጉዳት)። መንግስት፤ ኮንዶምኒየም ቤቶችን ለመስራት፤ ከተወሰኑ ዜጎች ታክስና ግብር ይወስዳል፤ ቤት የመስራትም ሆነ የመከራየት አቅም ያሳጣቸዋል ማለት ነው። የተገነባውን ኮንዶምኒየም ለጥቂት አልያም ለሌሎች ዜጎች ይሰጣል፤ የኮንዶምኒየም ባለቤት ሆነው እያከራዩ ገቢ ያገኛሉ። ይሄው ነው “ማህበራዊ ፍትህ”።የመንግስት እጅ ያልገባበት የነፃ ገበያ ስርአት ውስጥ፤ የአንድ ዜጋ ጥቅም፤ በሌላው ዜጋ ጉዳት ላይ የተመሰረተ አይደለም። በራሳቸው ጥረትና ቁጠባ ቤት የሚገነቡ ሰዎች፤ ከጥረታቸው ተጠቃሚ ይሆናሉ - ቤቱን ይኖሩበታል፤ ወይም አከራይተው ገቢ ያገኙበታል። ቤቱን ለመገንባት ማንንም ሰው መጉዳት አይችሉም። ሌሎች ዜጎች በከፈሉት ታክስና ግብር አይደለም ቤቱ ተገንብቶ የተሰጣቸው - በራሳቸው ገንዘብና ወጪ እንጂ። በራሳቸው ጥረትና ወጪ አማካኝነት ቤት የሚገነቡ ዜጎች ሲበራከቱ፤ ሌላውንም ይጠቅማሉ - የቤት ኪራይ አማራጭ በማበራከት፤ የኪራይ ዋጋ እንዲቀንስ ይረዳሉ። አዲስ ሃብት እየፈጠሩ እንጂ፤ ከሌሎች ዜጎች እየነጠቁ አይደለማ። ስለዚህ፤ በነፃ ገበያ ውስጥ፤ የበርካታ ዜጎች ቢዝነስ ሲያድግ፤ ግንባታቸው ሲበራከትና ህይወታቸው ሲሻሻል፤ ድርብ ጥቅም እናገኛለን። አንደኛ ነገር፤ የስራ እድልና የምርት አቅርቦት እንዲጨምር እያደረጉ ስለሆነ፤ ህይወታችንን የምናሻሽልበት ተጨማሪ እድል እየፈጠሩልን ነው። ሁለተኛ ነገር፤ በራስ ጥረት መበልፀግና ህይወትን ማሻሻል እንደሚቻል በተግባር እያሳዩን ስለሆነ፤ በአርአያነት መንፈሳችንን ያነቃቁልናል።

መንግስት የአገሪቱ ኢኮኖሚና ቢዝነስ ውስጥ ጣልቃ ሲገባ፤ እናም “በመንግስት ቸርነትና ድጎማ” አማካኝነት የተወሰኑ ሰዎች “ህይወታቸው ሲሻሻል” ግን፤ “በአንዱ ዜጋ ኪሳራ ሌላው ዜጋ መጠቀሙ”፤ ቅሬታንና ሽሚያን ያስከትላል እንጂ፤ የስራ እድልንና የመንፈስ ብርታትን አይፈጠርም።

 

 

 

Read 3964 times Last modified on Saturday, 12 May 2012 10:28