Monday, 10 September 2018 00:00

የሽግግር ጊዜ ፍትህ ማስፈፀሚያ ስልት እንዲቀየስ ተጠቆመ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

ባለፉት 27 ዓመታት የተሰሩ የፖለቲካ ወንጀሎችን ለመጨረሻ ጊዜ እልባት ለመስጠት የእርቅና የሽግግሩ ጊዜ ፍትህ ማስፈፀሚያ ስልት እንዲቀየስ የኢትዮጵያውያን ሃገር አቀፍ ንቅናቄ (ኢሃን) ጠቆመ፡፡
ንቅናቄው በወቅታዊ የፖለቲካ ጉዳዮች ላይ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫው፤ በተጀመረው የለውጥ እንቅስቃሴ ውስጥ ቅድሚያ ተሰጥቷቸው ሊተገበሩ ይገባል ያላቸውን ፖለቲካዊ ማሻሻያዎች በዝርዝር አስቀምጧል፡፡
ባለፉት 27 ዓመታት የኢትዮጵያ ህዝብ ባካሄደው መራር መስዋዕትነትን ያስከፈለ መራር ትግል ከእንግዲህ ግፍና ጭቆናን እንደማይቀበል አረጋግጧል ያለው የንቅናቄው መግለጫ፤ በዚህም አንፃራዊ የለውጥ ጅማሮ ታይቷል፣ ሃሳብን የመግለፅ ነፃነት ድባብ ሰፍኗል ብሏል፡፡
በዚህ ሂደት ውስጥ በስልጣን ላይ ያለው ኢህአዴግ፣ በህዝቡ ሲነሱ ለነበሩ ጥያቄዎች ግልፅ የመፍትሄ አቅጣጫ ማስቀመጥ ተስኖት፣ የህዝብን ጥያቄ መመለስ በሚፈልጉና በተለመደው መንገድ መቀጠል ባሰቡ ኃይሎች ተከፋፍሎ እንደሚገኝ የጠቀሰው ንቅናቄው፤ ይህም ለውጡን ወደ ኋላ እንዳይመልሰው ሲል ስጋቱን ገልጿል፡፡
ለውጡ አስተማማኘ መሠረት እንዲኖረው፣ በህዝብ ፈቃድ የሚፀድቅ ሕገ መንግስት፣ ነፃ የደህንነት አካል፣ ከመንግስት ተፅዕኖ የተላቀቀ መገናኛ ብዙሃን፣ ነፃ የሙያና የሲቪክ ማኅበሪት፣ ገለልተኛ የምርጫ አስፈፃሚ አካላትን ማቋቋም ቅድሚያ ተሰጥቷቸው እንዲሠሩ ጠይቋል፡፡
የህዝቡ ጥያቄ የመጨረሻውን እልባት ሊያገኝ የሚችለው በህዝብ የተመረጠ መንግስት ወደ ስልጣን ሲመጣ ነው ያለው ኢሃን፤ ለዚህም ትግሉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቋል፡፡ ኢህአዴግ በተከፋፈለበት ሁኔታ የለውጡ ጅማሮ አስተማማኝ አይደለም ያለው ንቅናቄው፤ ይህን ለውጥ እንዳይቀለበስ ጠባቂ የሽግግር ምክር ቤት ያስፈልጋል ብሏል፡፡
በሽግግር ጊዜ ውስጥ ከላይ የተጠቀሱት ፖለቲካዊ ማሻሻያዎች በውይይት እንዲፈፀሙም ንቅናቄው ጠቁሟል፡፡ እስካሁን የቆየነው በአገዛዝ ውስጥ ነው ያሉት የንቅናቄው ሊቀመንበር ኢ/ር ይልቃል ጌትነት፤ በአገዛዙ ዘመን በርካታ በሰብአዊነት ላይ የተፈፀሙ ጥፋቶች አሉ፤ ለእነዚህ ጥፋቶችም ፍትህ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
የተፈፀሙ ጥፋቶች በአደባባይ ተገልጠው፣ ተጠያቂዎች ታውቀው ፍትህ ሊሰጥ ይገባል የሚሉት ኢ/ር ይልቃል፤ ያለፉት ጥፋቶች በዚህ መንገድ ተዘግተው፣ በይቅርታም ሆነ በምህረት ወደ ፊት መራመድ ይገባል ብለዋል፡፡ ይህ አይነቱ ሂደትም በደቡብ አፍሪካና በሌሎች ሃገሮች መተግበሩንም በምሳሌነት ጠቅሰዋል - ሊቀ መንበሩ፡፡

Read 7361 times