Print this page
Monday, 10 September 2018 00:00

በመርሳ ህዝብ ተሰብስቦ “የራሱን” ከንቲባ ሾመ

Written by  አያሌው አስረስ
Rate this item
(0 votes)

 በደቡብ ወሎ አስተዳደር የመርሳ ከተማ ነዋሪ፤ባለፈው ነሐሴ 20 ስብሰባ በማካሄድ፣ የከተማዋን ከንቲባ በመሻር፣ አዲስ የከተማ ከንቲባና ሌሎች ኃላፊዎችን መሾሙ ተገለፀ፡፡ የከተማው ነዋሪ ሕዝብ ወደ እዚህ ተግባር የተሻገረው ከደቡብ ወሎ ዞን አስተዳደር ጋር፣ አስተዳደሩ በስልጣን ላይ የነበሩትን ከንቲባና የሥራ ባልደረቦቻቸውን ገምግሞ ከሙስና የፀዳ አስተዳደር እንዲያቋቁምለት ያቀረበው ጥያቄ ተቀባይነት አለማግኘቱን ተከትሎ ነው ተብሏል፡፡  
“አሁን በስልጣን ላይ ያለው የከተማው ከንቲባ ጽ/ቤት አስተዳደር ችግር ያለበት በመሆኑ ዞኑ በሕዝብ አስገምግሞ አዲስ አመራር ይሰይማል” በማለት የከተማው ሕዝብ ተወካዮችን ወደ ወልድያ መላኩንና ለሁለት ቀን ከዞኑ አመራር ጋር ተነጋግረው መግባባት ላይ ሊደርሱ አለመቻላቸውን ምንጮቻችን ጠቁመው፤ ለተወካዮቹ በመጨረሻ የተሰጠው መልስ “የማይጠበቅ እርምጃ ያስወስድባችኋል” የሚል እንደነበር በዝርዝር አስረድተዋል፡፡ አያይዘውም፤ “ሕዝቡ ይገሉን እንደው እናያለን፡፡ የመጣው ሊመጣ ይችላል” በማለት ወደ ምርጫው መግባቱን ጠቁመዋል፡፡  
“እስከ አሁን ለከተማው በከንቲባ አስተዳደርነት የሚመደቡት ሰዎች በድርጅት የተመለመሉ ናቸው፡፡ ሲመሩን የኖሩት እነሱ ናቸው፡፡ አዲስ ሕዝብ የሚቀበላቸው ሊሆኑ ይገባል” ያሉት የከተማው ነዋሪዎች፤ የራሳቸውን የምርጫ ኮሚቴ አቋቁመው፣እጩዎችን በነዋሪው በማስገምገም  መምረጡን ከከተማው ነዋሪዎች አንዱ አቶ አህመድ ሰይድ ገልፀዋል፡፡ በመቀጠልም “የተመረጡት ከሙስና የፀዱ በትምህርት ደረጃቸው የተሻሉና በሕዝብ የተደገፉ ናቸው” ብለዋል- ነዋሪው፡፡
ለመርሳ አዲስ ከንቲባ ሆነው የተመረጡት አቶ አብዲ እንድሪስ፤ በሕዝብ መመረጣቸውን አረጋግጠው፤ዝርዝር ማብራሪያ ለመስጠት ከከተማው ውጪ ስለሚገኙ የስልኩ ድምጽ ስለሚቆራረጥ እንደማይሰማቸው አስረድተዋል፡፡
የከተማው ሕዝብ በመረጣቸው ምርጫ አስፈጻሚዎች አማካይነት፣ የምርጫውን ውጤት በመግለጽ ለዞኑ አስተደደር፣ ለአስተዳደርና ጸጥታ እንዲሁም ለሚመለከታቸው የዕውቅና ጥያቄ  ደብዳቤ መጻፉ ተገልጿል፡፡
በምዕራብ ወሎ ዞን የአስተዳደርና ፀጥታ ኃላፊ አቶ ደስታው ይማም፤ የመርሳ ከተማ ነዋሪዎች የላኩት የእውቅና ደብዳቤ ለእሳቸው እንዳልደረሳቸው፣ ምን አልባት ለዞኑ አስተዳደር ደርሶ እንደሚሆን ጠቁመው፤ዝርዘር ማብራሪያ ላለመስጠት ስልካቸውን ዘግተዋል፡፡

Read 5166 times