Print this page
Tuesday, 04 September 2018 09:35

“ሌላ ዓለም” - ከተማዋን ኤክስሬይ ያነሳ ድርሰት

Written by  ሌሊሳ ግርማ
Rate this item
(1 Vote)

 የመፅሐፉ ርዕስ “ሌላ ዓለም” ይሰኛል፡፡ … “እና ሌሎች ታሪኮች” ምናምን የሚል ቅጣይ የለውም። … “ልቅላቂ”፣ “ጭማቂ”፣ “ቅንጥብጣቢ”፣ “እጣቢ” … የሚሉ አጫጭር የፈጠራ ፅሁፎችን የሚዳበሉ አኮሳሽ ገለፃዎች፤ ከመፅሐፉ አርዕስት ጋር እንደ አልቅት አለመጣበቃቸው ምናልባት ደራሲው የራሱን ስራ አኮስሶ፣ የሰውን አቀባበል ወደ ንቀት መምራት አለመፈለጉን ጠቋሚ ሊሆን ይችላል፡፡ ሊሆን ይችላል ማለት፣ “ነው” ማለት አይደለም፡፡
“ሌላ ዓለም” በሚል ርዕስ ስር “18” ታሪኮች ተጠርዘዋል፡፡ “የፈጠራ ታሪኮች” ናቸው፡፡ ከዚህ ባሻገር “ዘውጋችን ይኼ ነው” ብለው ታሪኮቹ እስካልተናገሩ ድረስ እኔ የአይነት ብያኔ አልሰጥም። ፈጠራ ተከናውኗል፡፡ የስነ ፅሑፍ ፈጠራ፡፡ ፈጠራ ተወልዷል። የፈጠራውን ዓይነት ዘ-ብሔረ ምናምን ብዬ መፈረጅ የእኔ ስራ አይደለም። በፈጠራው ውስጥ ባለው ቁም ነገር ላይ ነው ማተኮር የፈለግሁት፡፡ ቅርፁ ላይ ሳይሆን ይዘቱ ላይ፡፡
መድበሉ ውስጥ ያሉት አስራ ስምንቱም ድርሰቶች በከተማ መቼት ላይ ያጠነጠኑ ናቸው። መቼው? … በዚህ ሰላሳ ምናምን ዓመታት፤ የቱ? እዚሁ አዲስ አበባ። ደስ የሚለው ግን በእውኗ አዲስ አበባና በድርሰቱ (“ሌላ ዓለም”) መሃል ያለው ልዩነት ነው። ድርሰቱ በመፅሐፍ መልክ ሲቀርብ ተሰርቶ አልቋል፡፡ መፅሐፉን ለመስራት ደራሲውን ያገለገለችው ከተማ ግን ዝንተ ዓለም በለውጥ ውስጥ ናት፡፡ “ዝንተ ዓለም” የሚለው ይሰመርበት፡፡ አካልን በኤክስሬይ ማንሳት ይቻላል፡፡ በኤክስሬይ ፎቶግራፍ ተነስቶ ግን አካልን መስራት አይቻልም፡፡ ኤክስሬው የአካሉን መሰረታዊ ዳራ … ፎቶግራፍ በተነሳበት ቅፅበት በጥቁርና ነጭ ስሎ ነው የሚያቀርበው። የማን አካል እንደሆነ ከኤክስሬው ማወቅ አይቻልም። መልክ ላይ ግን የማይገኙ ውስጣዊ ችግሮች በኤክስሬው አማካኝነት ነው ፈክተው የሚወጡት።
ደራሲው ዮናስ ብርሃኑ፤ በአዲሳባ ውስጥ በx-ray እይታ ገብቶ ያየውን፣ እኔ ደግሞ በድርሰቱ ውስጥ እንደዛው አይነት ኤክስሬይ ለማንሳት ነው አሁን እየጣርኩ ያለሁት፡፡
ልብ በሉልኝ እዚህ ላይ! … ኤክስሬይ ለማንሳትም ሆነ የተነሳውን ለመተርጎም ሰው መሆን ብቻ በቂ አይደለም፡፡ አዲስ አበባን ኤክስሬይ የሚያነሳ ሰው አዲስ አበባን ማወቅ አለበት፡፡ የደራሲው አስራ ስምንት ልብ ወለዶች ተፅፈው ሲነበቡ ጥቅል ቢመስሉም … ዝም ብለው በማንም የሚጠቀለሉ አይደሉም፡፡ ዝርዝሩን ኖሮ የማያውቅ ጥቅሉ ላይ ቢደርስም ሀቀኛ ምስል አያነሳም፡፡ ሀቀኛ ምስል ከሀቀኛ የመኖር ተሞክሮ የሚመጣ ነው፡፡ ዮናስ ብርሃኔ የሚያወራቸውን ነገሮች እንደኖራቸው ያስታውቃል፡፡ (ፅሁፉ ስለሚናገረው ነገር ላውራ ብዬ እንጂ እንደኖረማ እኔም አውቃለሁኝ)
እሱ ያነሳውን ፎቶግራፍ እኔ ደግሞ መተርጎም እችላለሁኝ እያልኩ ነው፡፡ ከዝርዝር ወደ ጥቅል በድርሰቱ ያወጣውን ፅሁፍ፤ እኔ ደግሞ “decypher” ማድረግ (ቀኝ ኋላ አዙሬ መፍታት) እችላለሁ፡፡ ምክኒያቱም እሱ መነሻ ያደረጋት ከተማ (አዲስ አበባ) እኔም መፅሐፉን ሳነብ ተመልሼ የማርፍባት ናት፡፡ ምክኒያቱም፤ ከተለያየ አቅጣጫም ቢሆን (ደራሲው እንደ ፀሐፊ፣ እኔ ደግሞ እንደ አንባቢ) በአንድ ቅፅበት አገናኝቶ እንድንነጋገር ያደረገው “ሌላ ዓለም” የተሰኘው መፅሐፉ ስለምናውቀው አዲስ አበባ ነው፡፡ ከዛሬ ብዙ አመታት በፊት ፅፌ ያልታተመ አንድ የእንግሊዝኛ ልብ ወለድ ውስጥ የተጠቀምኩትን አንቀፅ መልሼ ልጥቀሰው፡፡ በዚያ አንቀፅ ውስጥ ያቀረብኩት ጥያቄ፤ “በሌላ ዓለም” መፅሐፍ ውስጥ ምላሽ አግኝቷል ብዬ አምናለሁኝ፡፡ በታሪኩ ውስጥ አንድ የሰዓሊ ገፀ ባህርይ እንደሚከተለው ይላል፡-
“Addis Ababa is a book, a masterprice, that has no author, a book with scenes vividly described, but with no prominent character. It’s a book of words. Words that run off the page leaving it empty, or that cluster at the middle to form a verse, or that glitter like mud into litanies, paryers, sobs, sighs, slogans. It’s a book you pretend you were reading with a finger in the middle, and if read, it’s that which doesn’t matter where you begin reading from, middle beginning or end. You are lucky if you live the book and not understand a page of it. And like all the masterpieces you are wiser at the beginning than at the end…”
ሰዓሊው አዲስ አበባን እንደ መፅሐፍ ነው የሚገልፃት፡፡ መሪ ገፀ ባህሪ የሌላት፣ በትዕይንት፣ በፀሎት፣ ለቅሶና መፈክር የተሰራች የቃላት መፅሐፍ፡፡ ጣቱን በመፅሐፉ መሀል አስገብቶ ማንም የሚጠነቁላት መፅሐፍ፡፡ ከየትም ጀምረው ወደየትም ቢያነቧት የማትገድ፡፡ በመፅሐፉ ውስጥ ተፅፈው ለሚኖሩትም ፍቺዋ ያልገባቻቸው፡፡ ማስተርፒስ የሆነች መፅሐፍ፡፡
ዮናስ ብርሃኔ “ሌላ ዓለም” ብሎ በፃፈው ድርሰቱ ውስጥ የዚህች ያልተነበበች መፅሐፍ ኤክስሬይ ቁልጭ ብሎ ተቀምጦ ለእኔ ታይቶኛል። “ሌላ ዓለም” የአዲስ አበባ ኤክስሬይ ፎቶ ግራፍ ነው፡፡ መፅሐፉን ለመሳል የተሞከረበት የንድፍ መፅሐፍ፡፡ በ132 ገፆች ደራሲው የኖረበትን የከተማዋን አሻራ ለማስቀመጥ ጥሯል፡፡
“ሌላ ዓለም” የሌላ ከተማ ምስልን ፈፅሞ ሊሰጥ አይችልም፡፡ አዲስ አበባን አዲስ አበባ የሚያደርጉ የብቻዋ መገለጫዎች አሏት፡፡ የአዲስ አበባ መገለጫ ፎቆቿ አይደሉም፡፡ “Landmark” የሚባል ፎቅም ሆነ የሀውልት አሻራ የላትም፡፡ መገለጫዋ ሰፈሮቿም አይደሉም፡፡ ማንሸራተት የፈለገ ሰፈሮቿንም ሆነ ነዋሪዎቿን ማንሸራተት ይችላል፡፡ ከመፅሐፉ መሀል ገፅ ቢጎድል ምንም የሚፈጠር የፍሰት ጉድለት የለም። አዲስ አበባ ቃላት እንጂ ምዕራፍ የላትም፡፡ ደም እንጂ ደም ግባትም ሆነ ደም ስር የላትም፡፡ ቆሻሻ ናት። አደባባይ እንጂ ከአደባባይ ያተረፈችው አዎንታዊ አብዮት የላትም፡፡
ይኼንን የከተማዋን የቆሻሻ ስርቻዎች በድርሰቱ ውስጥ ነቅሶ ያስተምረናል - ደራሲው፡፡ “ሌላ ዓለም” ሌላ አዲስ አበባ ነው፡፡ “በጭንቅላቱ ጥርስ ስቆ … ከእነ ጭንቅላቱ የሚረግፍ”፤ በቆሻሻ ላይ የበቀለ የሌላ ዓለም ሌላ አበባ ነው፡፡
በመፅሐፉ ውስጥ ከተሰነዱ ልቦለዶች በአቀማመጥ ቅደም ተከተልም ሆነ በርዝመት መሪ የሆነው ታሪክ፤ ስለ ባንጌ ሰፈር ነዋሪዎች የሚከተለውን ይላል፡-
“የባንጌ (ሰፈር) ልጆች ህፃንም ሆነው እንዳቅሚቲ ለቤተሰቦቻቸው የገቢ ምንጭ ሆነው ነው የሚያድጉት። ተፍ - ተፍ ማለትና መሸቃቀልን ከልጅነታቸው ጀምሮ የሚያድጉበት ነገር ነው፡፡ እናቱ ሽንኩርትና ድንች የሚሸጡበት መደብ ስር ድክ ድክ እያለ ያድጋል፡፡ ድክ ድክ እያለ ተፍ ተፍንም እዚያው ይጀምራል፡፡ ያ ማለት ሽንኩርትም ሆነ ድንች አይሱዙ ላይ ሲጫን የሚዝረከረከውን ለቃቅሞ ከማምታትና እዚያው ከእናቱ መደብ ላይ የተገዛውን ነገር ከከርፋፋ ገበያተኛ ፌስታል ውስጥ መልሶ ከመቀነስ ይጀምራል። በውስልትና ውስጥ ማደግ ማለት ይሄ ነው፡፡ ከዚያማ ማርሽ ቀይረው ወይ የለየለት ቀስቴና ላቦሩ (ኪስና ቤት አውላቂዎች) ይሆናሉ። አልያ ከዚያ ካመለጡ የሆነ የቢዝነስ እንቅስቃሴ ውስጥ የሆነች ጥግ ይይዛሉ” ይላል፡፡ (ገፅ 27)
በእርግጥ የከተማ ልጅ ከሽቀላ ጋር የተያያዘ ነው። ሽቀላው ግን ከማጭበርበር ወይንም መጭበርበር አይወጣም፡፡ በሂደት ግን አጭበርባሪወም ተጭበርባሪውም አሻራ ቢሱ የከተማ ገፅ፣ በፖለቲካ አንባቢ እጅ ሲገለጥ፣ ሁለቱም በየስርቻው ይሰወራሉ። የዚህ “የሌላ ዓለም” አዙሪት በመጀመሪያው ታሪክ ላይ አያበቃም፡፡ በእየ ቀጣይ ታሪክና ታሪኩ የሰፈረበት አሻራ ቢስ ገፀ ባህሪ ላይ እየዋለ ይቀጥላል፡፡ ትምህርትና እውቀት የባንጌ ሰፈርም ሆነ የአዲስ አበባ እውነተኛ መገለጫ አይደሉም፡፡ ግን ለምን? … በትምህርት ጥራት ምክኒያት እንደማትሉኝ እርግጠኛ ነኝ፡፡ ትምህርት ራሱ እንደ ሽቀላ የመሰለ ባህሪ ያለው ስለሆነ ፈፅሞ ታንኮም አያቅም፤ ቢታጠብም አይጠራም፡፡ በባንጌ ሰፈር ልጆች ላይ ትምህርት ምን እንደሚመስል ዘኮራ በተባለችው ገፀ ባህሪ አንደበት እንደሚከተለው ይገልፀዋል፡-
“የባንጌ ልጆች ትምህርት ላይ ያላቸው አቋም ዘኮራ እንደምትለው፤ “አበበ በሶ በላ” ሲባሉ፣ ‹ለምን ላጃ አይበላም› የሚሉ ናቸው፡፡ አብዛኞቹ የኤለመንተሪ ሽፍታ ሲሆኑ የተቀሩት እንደምንም ሃይስኩልን ይጨርሳሉ፡፡ ከዚያ አልፈው ኮሌጅና ዩኒቨርሲቲ የሚገቡት በጣም ብርቅ ከመሆናቸው የተነሳ እንትና፣ እንትና እያሉ በስም ሁሉ ሊጠሩልህ ይችላሉ፡፡ … በሪስክ በተሞላ ህይወት ውስጥ በህያው ተዋናይነት ስለሆነ የሚያድጉት፣ ሪስክ ማለት ለነሱ የሚያሰሉት ሳይሆን በደፈናው የሚኖሩት ነው” ይላል፡፡ (ገፅ 27)፡፡
ይሄንን አዙሪት ‹የአራዳ ህይወት› ብሎ መጥራት ይቻላል፡፡ እኔ እላለሁኝ፡፡ አራድነት አንዳንዴ ብልጠት የመሰለ ፋርነት ይሆናል፡፡ የተሻለ ከፍ የሚያደርግ መስሎ ገፅ ሲገለጥ፣ ዘጭ አድርጎ ይጥላል፡፡
“ዳገቶች (ዓመታት ማለት ነው በእነሱ ቋንቋ) ተፈርዶባቸው ሸዋ ሮቢት ወይንም ዝዋይ ከተላኩ እላይ ቤት እንደማለት ነው፡፡ ከዚያ ቀለል ብሎ እስሩ በፍሬዎች ማለትም በወራት ብቻ ከሆነና ከዚሁ ከቃሊቲና ከቂሊንጦ የማያልፍ ከሆነ ታች ቤት ነው። በጣቢያ ብቻ የሚቋጩት የቀናትና የሳምንታት እስሮችማ አይቆጠሩም፡፡ አባ ጋሜ ነው የሚሏት፡፡” (ገፅ 28)
ከእነዚህ እና መሰል አዙሪቶች ከፍ ብሎ ለማሰብ የሞከረው ያው “አውቆ አበድ” ነው የሚባለው። ትርጉም የሌለው የከተማ መፅሐፍን አስተውሎ የሚመለከት ነገሩ ሁሉ እብደት መሆኑ ሊሰማው ይችላል፡፡ አቡ ጠሽ የሚባለው ገፀ ባህርይ የዚያ አይነቱ ነው፡፡
“ከዚህ በላይ እብደት ምን አለ? በትክክል ሁሉም ሰው ሳይታወቀው ባለማወቅ አብዷል። ሳይታወቃቸው ቅልጥ ያለ የእብድ ስራ እየሰሩ እንደሆነ አልገባቸውም። ለእኔ ግን ቁልጭ ብሎ እየታየኝ ነው፡፡ ይህን እያየሁ ከእነሱ ጎራ ብቀላቀል ኖሮ እብደታቸው ተጋብቶብኝ፣ እኔም አብሬአቸው አብጄአለሁ ማለት ይሆን ነበር። ግን ማበዳቸውን እያወቅኩ እንዴት አብሬአቸው አብዳለሁ? አውቆ አበድማ ልሆን አልችልም፡፡ የዚህ ኢትዮጵያዊ እብደት ሰለባማ አላደርገውም- እራሴን። ማበድ እንዲህ እንደሚሉት ቀላል አይደለም፡፡ የነፃነት፣ የፍቅርና የአማፂነትን ፅንፍ የሚነካ ቆራጥነት ይጠይቃል፡፡ አውቆ አበድ ማለት እነዚህን ጥያቄዎች ይዞ መራመድ ያቃተው ልፍስፍስ ሰው ነው፡፡ እኔ ግን ልፍስፍስ አይደለሁም፡፡ ከፈለጉ ያው እንደለመዱት እነሱ እብድ ይበሉኝ፡፡ ምድረ እብድ ተሰብስቦ እብድ ቢለኝ ጉዳዬ አይደለም።…” እያለ ገፀ ባህሪው ከራሱ ጋር ይነታረካል - “አውቆ አበድ” በሚለው ልብ ወለድ። (ገፅ 39)
አውቆ አበድና ሳያውቁ ያበዱትን ከገጠማቸው እጣ ፈንታ እንዲጠበቁ ማንቃትና ማስተማር የነበረባቸው ፀሐፊዎቹ፣ አሳቢዎቹ፣ ጋዜጠኞቹ የት ገቡ ብሎ የሚጠይቅ ይኖራል፡፡ ለዚህ ጥያቄ ጥሩ ምላሽ የሚሆን ገፀ ባህርይ “ምልኪተኛው ደራሲ” በተሰኘው ድርሰት ላይ ይገኛል፡፡ አፄ አበበ ታሪኩ ገድሌ … ይባላል፡፡
“አፄ አበበ ታሪኩ ገድሌ ብሎ ራስን ሲጠራ ወይንም ሲያስተዋውቅ፣ ያንን ስም አላውቅም የሚል ካለ፣ ያ ሰው ኢትዮጵያ ውስጥ የኖረ አይደለም፡፡ ከ1980ዎቹ ጀምሮ በዋና አዘጋጅነት ጭምር በተለያዩ ጋዜጦችና መፅሔቶች ላይ ሲፅፍ የኖረን አንጋፋ ጦማሪና የሁለት መፅሐፍት ደራሲ ስም አለማወቅ ማለት እሬሳነት ነው ለእሱ። የራስን ሙትቻነት እንደ ማጋለጥ ነው፡፡ ምንም እንኳን ዘለግ ያሉ አመታቶች ያስቆጠረ ቢሆንም ማንም ሰው ማንበብ የማይችል ገበሬም ቢሆን የሱን ስም ያለማወቅ ወይንም የመዘንጋት መብት የለውም፡፡” (ገፅ 53)
ጋዜጠኛው ሌሎችን ማወቅ ሳይሆን በሌሎች መታወቅ ነው ዋናው ግቡ፡፡ ምንም እንኴን ለመታወቅ የሚያበቃ ምንም ጉዳይ ባይኖረውም … ይመስላል የድርሰቱ አፅንኦት፡፡ ግን ወረድ ይልና የዚሁ ገፀ ባህርይ ባዕድ ባህሪዎችን ይዘረዝርልናል። ያኔ ማህበረሰቡ ውስጥ ያለውን በሽታ ሊፈውስ ይቅርና፣ የማህበረሰብ አንቂው ራሱ በተለየ ደራሲያዊ ንውዘት ውስጥ እንደተደቆሰ እንረዳለን።
“የተቀዳለትን መጠጥ ሳይጨልጥ ለሽንት እንኳን አይንቀሳቀስም፡፡ ሲመለስም በፍፁም በዚያው ትቶት በሄደው ብርጭቆ አይጠጣም”፤ ሌላ መምጣት አለበት፡፡ አንጠልጥሏት የሚዞረው ፌስታል መፀዳጃ ቤትም አብራው ነች፡፡ ሁሉንም የሚያስገርማቸው ነገሩ ደግሞ አካባቢውን የሚቀርፅበት ካሜራ ነው፡፡ የሰዎች አቀማመጥ ለውጥ ለሱ በጣም ተራ ነገር ነው፡፡ ከሽንት ቤት ሲመለስ በ1.5 ዲግሪ ተዛንፋ የጠበቀችውን ሲጋራ አሽትሬ ‹ማን ነው ያንቀሳቀሳት?› ብሎ ይጠይቅሃል፡፡ ‹ልክ እኔ ስገባ ይሄ ሙዚቃ ተቀየረ፡፡ ለምን ይመስልሃል?› እያለ ልብህን ዝቅ ሲያደርገው … በሃገራችን ላይ ከሚያሴሩት የኢሉሚናቲ ስውር ኃይሎች ጋር የገባውን ጦርነትና በላዩ ላይ ያንዣበበበትን ከባድ አደጋ ኮስተር ብሎ እያሳየህ ያወራሃል፡፡” (ገፅ 54)
ከተማዋም ሆነ የከተማዋ ኤክስሬይ የሆነው “ሌላ ዓለም” መፅሐፍ፤ ለምን ጠንካራ ገፀ ባህሪ ሊፈራ እንደማይችል የሚገባህ ይሄኔ ነው። ይሄኔ ነው … ታሪኮቹ ለምን ፀለምተኛና ተስፋ የማይታይባቸው እንደሆኑ የሚገባህ። ሰባራ አጥንቶች ያሉት አፅመ አካል ኤክስሬይ ሲነሳ በተአምር የተሰባበሩት አጥንቶች ደህና መስለው ሊወጡ አይችሉም፡፡ በ“ሌላ ዓለም” ውስጥ የሚታዩ ገፀ ባህሪዎች በራሳቸው ታሪክ ላይ እንኳን ጌታ አይደሉም፡፡ የአንዳች ከተማዊ ግጭት መገለጫ ናቸው። በስተመጨረሻ ግጭቱ አመንምኖ፣ አሸማቆ፣ አሳብዶ፣ ወይ አስመሳይ አድርጎ ሲቀጫቸው ነው የሚስተዋሉት፡፡ የአፄ አበበ ታሪኩ ገድሌም መጨረሻ አያምርም፡፡ ድንገት በመኪና ተገጭቶ ይሞታል፡፡ ከታሪኩ አመጣጥ አንፃር ፍፃሜው ድንገትና “የማይመስል ነው” ቢያስብለኝም … በተጨባጩ ከተማ ላይ ከማይመስልም በላይ የማይታመኑ ፍፃሜዎች ስላየሁኝ መለስ አልኩኝ፡፡ በልብ ወለድ ላይ የማይታመን ፍፃሜ፣ በእውኑ አለም ላይ የእለት ተእለት ክስተት ነው፡፡
የ“ሌላ ዓለም” ሌላው ዋና መገለጫ ሱስ ነው፡፡ የጫቱ፣ የሲጋራው፣ የአረቄው … የጋንጃው ሰንሰለት ታሪኩን ከገፀ ባህሪያቱም በላይ የሚያያይዘው ገመድ ነው፡፡ ሱስና በሱስ ዙሪያ የሚሾሩ ተሞክሮዎች፤ የታሪኮቹ ዳራ የሚሰራባቸው አውታሮች ናቸው፡፡ “ዣቪዝም” የሚለው ታሪክ የዚህ ጥሩ ማሳያ ነው፡፡
“ስም ያላቸው ሳቆች” የሚለው ደግሞ ውስብስብ ሳቅን ከውስብስብ ህይወቱ ጋር አዳብሎ በሚኖር ማህበረሰብ ውስጥ ስላለ አያሌው ስለተባለ ገፀ ባህርይ እምነቱን እየተፈላሰፈ የሚገልፅበት ነው፡፡ በገጠር ውስጥ የሚኖር ሰው፣ እንደ ከተማ ሰው ሳቅን እንደዚህ ማራቀቅና ማወሳሰብ አያስፈልገውም እንድል አድርጎኛል፡፡ “ሎዴዎቹ” እና “ውሻውም” የተሰኙት ድርሰቶች ተጨማሪ ምስል ስለ ከተማ ህይወት የሚሰጡ ናቸው፡፡ …የከተማ ህይወትና ችግሩ፤ የውሻን ቅርፅ ወደ በግ ለውጦ የመብላት ፍላጎትን ሁሉ ሊፈጥር ይችላል፡፡
በመጨረሻም በ“ሌላ ዓለም” ላይ እኔ የማውቃትን ከተማና በዚህ ሰላሳ አርባ ዓመት የመከነውን ትውልድ በእውነተኛ ግልፅነት፣ ዝርዝሩን ጠቅልሎ ስላስነበበኝ .. የከተማዋን ኤክስሬይ አንሺ (ደራሲውን) ዮናስ ብርሃኔን በስነ ፅሁፍ ስም አመሰግነዋለሁኝ፡፡     


Read 624 times