Tuesday, 04 September 2018 09:33

ከንቱነት!

Written by  አብይ ተስፋዬ አሳልፍ (አተአ)
Rate this item
(8 votes)

 … ከንቱነት ምስኪንነት
ራሱን እንደመጥላት
እሷንም እንደመጥላት … (ቅዠት … ቅዠት፣ …..
ደበበ ሰይፉ)
አለምንም እንደመጥላት … (እኔ!)
ከእንጦጦ አለቶች ላይ ተቀምጬ እኔንና ጋሙዱን ቀደም አድርጌ አሰብኩ፡፡ የእኔንና የእርሱን የመሰሉ ሰዎች ታሪክ የለንም፡፡ ታሪክ ሳይሆን እንደ ስልቻ ያለፋነውና ረግጠን ያለፍነው ዕድሜ ነው ያለን። ከዚህ ህይወታችንና ከዝቃታ ኑሯችን መሃል ፍቅርና ጥላቻ መሳ ለመሳ መገኘቱ ያስገርማል፡፡ ልቤ ለበቀል ተነስቶበታል፣ ሆኖም እንዴት እንደማሳካው አልተገለጠልኝም። ጋሙዱን ለምን ጠላኸው! ምን አድርጎህ ነው! የሚለኝም አይጠፋም፡፡ ቆይ አንዴ ታገሱኝና ተረጋግጠው ባለፉት ዕድሜያችን መሀል የተከሰተ ነገር ላውራ፡፡
***
እርሱ ጡንቸኛና ግዙፍ፣ እኔ ደግሞ ኮሳሳ ነን፡፡ የጉልበት ስራ ስለሚሰራ ፈርጣማ፣ እኔ ደግሞ የሽያጩን ስራ ስለምሰራ ኮሳሳ የሆንን ይመስለኛል፡፡ (ብዙ ግዜ ስለሚያመኝና ደቂቃዎች የሚቆይ ትክትክ የሚል ሳል ተጣብቶኝ ከሰው ተራ አውጥቶኛል፡፡) ወይም ደግሞ አካላዊ ሁኔታችንን አጢነን ወደ ስራ ተሰማርተናል ልበለው፡፡ (እርሱ ድንጋይ ፈላጭ፣ እኔ ደግሞ ሻጭ!)
ማታ ማታ ከምናመሽባት ከዚያች ‹ገደል ግቡ!› ከሚሏት ጠጅ ቤት ከምታስተናግደው ልጅ ፍቅር ያዘኝ፡፡ ፍቅር እንደያዘኝ በምን አወቅሁ! ሳያት መደንገጤ ምልክት ሆነኝ፡፡ ከዚያ በፊት እንዲያ ሆኜ አላውቅምና፡፡ ድንጋጤዬን ለመደበቅ እርሷ ወደ እኔ ስትመጣ የጠጅ ብርሌ ማንሳትና ማንደቅደቅ ጀመርኩ፣ እጄ ቢንቀጠቀጥም መጠጣት ይሻላል፡፡ በጽሁፍ እንዳልሰጣት መጻፍ አልችልም፣ ፍላጎቴንም አስረድቼ ልነግራት አልቻልኩም፣ ምላሴ አጭር ይሆንብኛል፡፡ ነገር ግን እዛ ጠጅ ቤት በሄድኩ ቁጥር ንዴቴን መቆጣጠርም አቃተኝ፡፡ የሚጎነታትላት ሰው ብዙ ነው፡፡ ከሁሉም የሚያበሳጨኝ ያ ጊዮርጊስ ፊት ለፊት ቀን ቀን ተጋድሞ ታምሜያለሁ እያለ ሲለምን የሚውለው ሰውዬ መሸት ሲል እዚህ ይመጣና ከበር መልስ ይጋብዛል፡፡ እናም ልጅቱን ስትወርድና ስትወጣ፣ ማሳሳቅና ማሽኮርመም ስራው ሆነ፡፡
በዚህ ተበሳጭቼ አንድ ቀን ልፋለመው ተነሳሁ፡፡ ተንደርድሬ ቡጢ ብሰነዝር ለካንስ ከጠጁ ገፋ አድርጌ ኖሮ ከጎኑ የተቀመጠውን (ታክሲ ተራ አስከባሪው!) አለሙን ግንባሩ ላይ አቀመስኩትና ከአግዳሚው ላይ ወደቅሁ፡፡ ወጠምሻው ከወደቅሁበት ሳልነሳ እዚያው ደቁሶ ለደቂቃዎች ያዘኝና መሳቂያ አደረገኝ፡፡ ከዚያ ጋሙዱ በቀስታ እየተንጎማለለ መጥቶ ሁለቱንም ሰዎች በየተራ አንድ አንድ ቡጢ አቀመሳቸውና ከመሬት ቀላቀላቸው፡፡ እሰይ እንኳንም ወንድ ልጅ ተወለደልን ብዬ አመሰገንኩ፡፡
የለማኙ የፊት ጥርሶች ረግፈው ነበርና በሚቀጥሉት ቀናት ሽምግልናው ቀላል አልነበረም። ሽምግልና ላይ ተቀምጠን እያለ ጋሙዱ ምን ቢለው ጥሩ ነው ‹‹እንዲያውም ለልመና እንዲመችህ ስላደረግኩልህ ለእኔ ትከፍላለህ!›› ነገርዬው ቀላል አልነበረም፣ ቢሆንም ጥቂት መቶ ብሮች ካሳ ሰጠንና ስምምነት ወረደ፡፡ ያው መቼም የምከፍለው እኔ ነኝ፡፡ (ጉዳዩ በእኔ የመጣ ስለሆነ!)
እንግዲህ ጋሙዱ ባለውለታህ ነው ትሉኝ ይሆናል። የሚቀጥለው ታሪክ ግን እንዲህ ነው፡፡
***
በሚቀጥሉት ሳምንታት ከጠጅ ቤቱ እግሬን አሳጠርኩ፡፡ በልጅቱ የተነሳ የሚነሳውን አምባጓሮ መቋቋም ተሳነኝ፡፡ በእኔ የተነሳ ጥርሳቸው የሚረግፈው ዜጎች አሳዘኑኝ፡፡ ለጋሙዱም የጠጅ ሒሳብ መክፈል ሰለቸኝ፡፡ እናም ማታ ማታ ከሳር ፍራሼ ላይ ተጋድሜ በግድግዳዬ ላይ የለጠፍኩትን ‹አዲስ ዘመን› ጋዜጣ አስተውላለሁ፡፡ ስዕል አያለሁ ልበለው እንጂ ማንበብማ አልችልም። ሱፍ ለብሰው ፎቶ የተነሱ፣ መነፅር ያደረጉ፣ የለምለም ሰብል ፎቶ፣ የሚያማምሩ ከብቶች …. ይህቺ አገር ተስፋ አላት የምለው ይህንን ጋዜጣ ሳይ ብቻ ነው። (ግሩም ነው፡፡ የእኛ ኑሮና የእነሱ የጋዜጣ ወሬ ተስማምተው መሳ ለመሳ ይጓዛሉ!)
***
ትዝታዋና ናፍቆቷን ቻል አድርጌ ሰነበትኩ፣ አንዳንዴ ስትናፍቀኝ ከጠጅ ቤቱ በራፍ ላይ ሶስት አራት ግዜ እመላለሳለሁ (ካየኋት እፎይ ብዬ እመለሳለሁ፣ እናም ጥሩ አንቀላፋለሁ!)፣ ደግሞ ካልሆነልኝ ቁርጥ እሷን የምትመስለውንና ከኮብልስቶን መንገዱ አጠገብ በቆሎ እየጠበሰች የምትሸጠው እህቷን ለማየት እሔዳለሁ፤ በብርዱ ከሚንጣጣው ከሰል ላይ የተቀመጠች በቆሎ እየተገላበጠች ስትጠበስ በማስተዋል ቆይቼ አንዷን በቆሎ እገዛና ወደ ቤቴ እገባለሁ፡፡(በቆሎ ሲጠበስ ማየትና የልጅቷን ፊት ማጥናት መሳ ለመሳ ይካሔድልኛል!) ይህንንም ማድረጌን ስደጋግም ጠላት መጣብኝ፡፡ ለካንስ እርሷም ባለ ባል ኖራለች። ዛቻ ሲመጣብኝ ከዚያም ቀረሁ። እናም ከመደቤ ላይ ተጋድሜ፣ እንደ ሽንብራ ከሚጠረጥሩኝ ቁንጮች ጋር እየታገልኩ፣ (ጠረጠሩኝ፡- ቆዳዬን እንደ ሽንብራ እሸት ከገላዬ አላቀቁ፣ ለማላቀቅ ጥረት አደረጉ፣ ነከሱኝ፣ ቆነጠጡኝ ፣ በትንንሽና ድቁቅ ነቁጥ በምታካከል መንቆራቸው ለመዘጉኝ (መዘለጉኝ!)…) የጋዜጣ ስዕል በማስተዋል ከሚመሹት ቀናት የሆነ ቀን ማታ፤ ጋሙዱ ድንገት በሬን ብርግድ አድርጎ ገባ። በመቀጠልም ‹ግቢ እንጂ!› አይላትም!፡፡ ወይ ግሩም! ትንፋሼ ጠፋች። ልጅቱን አመጣት፡፡ በደሳሳ ጎጆዬ በራፍ የክፍሌን ጨለማ የምትቀይር ጨረቃ ወደ ውስጥ ዘለቀች፡፡
ገፋ አድርጎ አስገባትና ‹‹በል እዚሁ ስለምታድር አጫውታት!›› ብሎኝ ሔደ፡፡ በሩን መለስ አድርጎ ከወጣ በኋላ፣ ከእንደገና መለስ ብሎ ‹‹ስትጠፋ ልጠይቀው ብላ ነው የመጣችው!›› አለኝ፡፡ (በሽራፊ ሰከንዶቼ መሃል ትንፋሼን ያዝ አድርጌ ሀሳቤን ሳዳውር እንዲህ ይገለጥልኛል …) ምናልባት በጉልበት አስፈራርቶ ይሆናል ያመጣት፡፡ ምናልባት እዚህ ከመምጣቷ በፊት በሻካራ መዳፉ እዚህ ቀይ ጉንጯ ላይ አንዴ አቅምሷት ይሆናል። ምናልባት ላይሆንም ይችላል፡፡ ወዳኝም፣ እንደተናገረው ልትጠይቀኝ ይሆናል፡፡ ዋናው ነገር እርሷን አመጣት፣ ለቤቴም ብርሃን ሆነላት። እናም ከዚያን ቀን ጀምሮ በዘመኔ አይቸው የማላውቀውን የለሰለሱ ከንፈሮችና ሰማያዊ የመሰለ ደስታ ለማጣጣም ታደልኩ፡፡ (ለቀናት!)
***
ከቀናት በኋላ እኔና እሱ ቁጭ ብለን ስናወራ፤ ‹‹በጣም ደስተኛ ሆነሃል! እንዴት ናት!›› ብሎ ጠየቀኝ። እኔም ደስታዬንና ምስጋናዬን ገለጽኩለት። ህይወቴ መቀየሩንና ላገባት መወሰኔን ነገርኩት፡፡
‹‹አትቀልድ ባክህ!››
‹‹ቀልድ አይደለም ጋሙዱ፡፡ እንዴት አይነት ጣፋጭ ልጅ መሰለችህ፡፡ ከዚህ በኋላ ከድንጋይ ስራ እንወጣለን፡፡ አብረን ህይወታችን ይቀየራል እያለችኝ ነው፡፡ በህይወቴ ለመጀመሪያ ግዜ ከድህነት መጋረጃ ማዶ ተስፋ እየታየኝ ነው፣ ልጅም ለመውለድ አቅደናል…›› እያልኩ አወራሁት፤ ፀጥ ብሎ ሰማኝ፡፡ በድንዙዝ ልቦናዬ ብሩህ ተስፋዬን ለፈለፍኩ፡፡
‹‹በዚህ ኑሮ ነው የምትወልደው!…›› ብሎ ሳቀብኝ
‹‹እንቀይራለንኮ! መቼም ዘላለም እንዲህ አንሆን!…›› ስል የሰሞኑን የምሽት ምኞታችንን በተስፋ መስኮት በሃሳቤ ቃኘሁ፡፡
የሚገርመው የዚያን ቀን ማታ ቤት ሳትመጣ ቀረች። በማግስቱም እንዲሁ፡፡ በሶስተኛው ቀን ወደ ተውኩት ጠጅ ቤት ሄድኩና አገኘኋት፡፡
‹‹ምነው!›› ብዬም ጠየኳት፡፡
‹‹አልተመቸኝም››
‹‹ዛሬ ትመጫለሽ!››
‹‹አዎ!›› … ማታ ላይ ብጠብቃትም አልመጣችም፡፡
በሌላው እርጉም ቀን ግን ጋሙዱ ቤት ጠቅልላ መግባቷን አረጋገጥኩ፡፡ ምን ላድርገው! የማልጋፋው ሰው ነው፣ ማለቴ ሰይጣን ነው። የእኔን አይነት አስር አይችለውም፡፡ ዝም አልኩት። ከዚያን ወዲህ የተውኩትን ጠጅ በስፋት ገፋሁበት፡፡ እናም ባለ ረዣዥም ምላስ ድሆች ግጥም የሚያወጡት በእኔ መልክና ትካዜ ሆኖ አረፈ፡፡ እንዲያውም እንዲህ የሚለው ግጥም በቁስሌ ላይ የተነሰነሰ ጨው ሆኖብኛል፡፡
ጌታዬ ሆይ በኔ እንዴት ቀልደሃል
ፊቴን ስትሰራ አፍንጫን ስተሃል፡፡
(ቤቱ በሳቅ ይሞላና ሁሉም ወደ እኔ ያተኩራል። ድፍጥጥ አፍንጫ ምኑ ያስቃል፡፡ ሰዎች ግን ጅል ፍጥረቶች ናቸው፡፡ ሰርተው ባልቀየሩትና ባላመጡት አካል ይመጻደቃሉ፡፡)
በጋርዮሽ አለም ሃይለኞች ሲነጥቁ፣
መኖር ስለማይቀር ደካሞች ሲወድቁ
መልከኛ ካልሆኑ፣ጉልበትዎ እንዳይዝል፣ በጣም ይጠንቀቁ !
(ሌላ ብዙ ሁካታ! … የመጨረሻውን ብርሌዬን ገልብጬ እጠፋለሁ፡፡ እናም የሰውን ልጅ ሁሉ ከምድር ላይ ከሚጠርጉ የሰይጣን አካላት ጋር ለመተባበር ፈቃደኛ እሆናለሁ፡፡)
***
ሌላ ቀን ጋሙዱ እንዲህ አለኝ ‹‹አውቀሃል አይደል!…››
‹‹አዎ!››
እራሱን እያሻሸ ‹‹እንግዲህ  ፍቅር ስለያዘህ ብዬ ነው መጀመሪያ ያመጣሁልህ፤ ፍቅሩ ያልፍልሃል ብዬ ባይህ አንተ ጭራሽ ቀጠልከው፡፡  ከዚህ በኋላ እራሷ ከምትመርጠው ጋር ትኑር፡፡››
‹‹ይቻላል ብለህ ነው!›› ስል በጥርጣሬ ጠየቅሁ። አይቻልም ይላል ልቤ፡፡ አንዳንዴ የራሳችን ክፍተት የሚታየን በሌሎች ሙላት ንጻሬ መሃል ይሆናል፡፡ ያኔ የራሳችን መራራ ትግል ለብቻው ለውጥ እንደማይሆንና ለውጡ መሰረት የሚያደርገው ሌሎች ሰዎች ላይ ጭምር መሆኑ ይገባናል፡፡ በዚህም ሳቢያ ሌሎች ሰዎች ላይ ተጨማሪ ስቃይ መፍጠር በራሱ ደስታን የሚሰጠን ከሆነ ወደ ኋላ አንልም፡፡ ልቦናዬ ያውቀዋል፡፡ አሁንም ያለነው የጋርዮሽ ዘመን ላይ ነው፡፡ ሃይለኞች ይነጥቃሉ፣ ደካሞች ይወድቃሉ። ስለዚህ በዚህ ዘመን ለመኖርና ከጉልበተኞች ለማምለጥ ደካሞች ብልጠታቸውን ሊጠቀሙ ይገባል፡፡ (አዝማሪዎቹ እንደተረቱብኝ!)
‹‹እንዳትረሳው ወዳጄ! ባለውለታህ ነኝኮ…›› ሲል … አስር ብር በሚመስል አይኑን አፈጠጠብኝ።
‹‹ያደረክልኝንኮ አልረሳም፣ ግና አንዳንድ ጊዜ ውጤቱ ከድርጊቱ በላይ መግለፅ አለበት እንጂ ሒደቱ ብቻ ውለታ አይሆንም፡፡ ውጤቱ ነው የድርጊቱን ትክክለኛነት የሚገልፀው፡፡›› ስል ተፈላሰፍኩ፡፡ (በዚያን ሰሞን ኤፍኤም ላይ የሰማሁት ወሬ ነው!)
‹‹ምን እያልክ ነው፣ ያደረኩህልህን ሁሉ መርሳትህ ባልሆነ…››
‹‹ያደረክህልኝንም፣ ያደረግህብኝንም አልረሳም።›› ስል አረጋገጥኩለት፡፡ አልረሳም፡፡ ታሪክ እንደሚያስረዳው፤ በጊዜ የማይቀየር ነገር ስለሌለ እስከሚቀየር እንጠብቃለን፡፡ ካልሞትን እናየዋለን፣ ለማየት ደግሞ ለመኖር መታገል ግድ ይለናል። ለመኖር ባለ ጥላቻ ውስጥ ለመቆየት መታገል ደግሞ እጅግ ሰቅጣጭ ነው። አይተናል፣ ታላላቅ የሚመስሉት ወድቀዋል፣ ሰጪ የነበሩ ተቀባይ፣ አሳሪ የነበሩ ታሳሪ፣ ባሪያ አሳዳሪ የነበሩ በረንዳ አዳሪ፣ ድምፅ ሰጪና ነሺ የነበሩ የድምፃችን ይሰማ አባል ሆነዋልና፡፡
በሌላው ቀን በጠዋት ከቤቴ እርሷን ስወጣ አገኘኋት፡፡ ለቀናት ከእኔ ጋር የነበረ፣ የእኔ የመሰለኝ ገላዋና ጠረኗ ዱልዱም ከሆነው አፍንጫዬ ስር እንደ ንፋስ ሽው አለብኝ፡፡ እናም የአፍንጫዬ ቀዳዳዎች ወደ ጎን እንደ ላስቲክ ሲሳቡ ይታወቀኛል፡፡ስታየኝ በፈገግታ የሚያበራ ፊቷ ተጨማደደ፤ በቀናት ውስጥ እንደማታውቀኝ ትሆናለች ብዬ አላሰብኩም ነበር። በመቀጠል እንዲህ አለችኝና የመኖርና የመሻሻል ተስፋዬን እንዳይሆን አድርጋ በጠሰችው፡፡
‹‹…እኔ’ምልህ የአፍንጫህ ነገር እንደገረመኝ አለ፤ ቀዳዳው እንዲህ የሰፋው በቅርቡ ነው ወይስ ስትፈጠርም ነው፡፡ ሩፋኤልን አላየሁትም ነበር። ደግሞኮ የውስጥ ፀጉሮችህ እንደ ሰበዝና ግቻ ተገጥግጠውና ጤዛ እዝለው ይታያሉ…›› (ፊቴን አዙሬ ጠፋሁ!)
ከዚህ ቀን በኋላ በራሴና በሰው ልጆች ሁሉ ላይ ጥላቻ አደረብኝ፡፡ በተለይ ለዘመናት አብሮኝ የኖረውና በምርጫ ያላገኘሁት የዚህ አፍንጫዬ ቀዳዳ መስፋት ስላሳፈረኝ ማታ ማታ ስተኛ፣ ጎንና ጎኑ ላይ ቀጫጭን ጣውላዎች አስሬ አሳድር ጀመር፡፡ ቀን ቀን ደግሞ አንገቴ ላይ (ንቅሳቷን ለመደበቅ እንደምትጠመጥመው ጎረቤቴ!) ከክር በተወሰወሰ ስካርፍ ፊቴን መጠምጠም ጀመርኩ። በራሴም፣ በሰው ልጅም ማፈርና ወደ ጥልቅ ጥላቻ ቁልቁል መውደቅ ጀመርኩ፡፡ ለዘመናት ቆንጆ እንዳልሆንኩ ባውቅም፣ ህመሙ እንደ አዲስ ሆነብኝ፡፡ (በምትወዳት ሴት የተነገረ መጥፎ ነገርህ፣ የዘልዓለም ቁስልህ እንደሚሆን የተረዳሁት ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ነበር፡፡) እናም ከጥላቻ በረንዳ ላይ መፃተኛ ሆኜ መኖር ጀመርኩ፡፡ (መጻተኛም ቋሚ ነዋሪም፣ ለመኖር የማይፈልግና የሚፈልግ፣ የሚጠላና የሚወድ፣ የሚያዝንና ጥቂት የሚስቅ … ሁሉንም መሳ ለመሳ ሳይሆን፣ በሆነ መበላለጥ የሚያስተናግድ ኗሪ ሆንኩ፡፡)

Read 2384 times