Print this page
Tuesday, 04 September 2018 09:33

ህንድ ለ154 ጊዜያት ኢንተርኔት በመዝጋት ከአለማችን 1ኛ ሆናለች

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትን ለማፈንና ተቃውሞን ለመግታት በማሰብ የኢንተርኔት አገልግሎት ፍጥነትን የሚገቱ ወይም ጭራሽ የሚያቋርጡ የአለማችን አገራት መንግስታት ቁጥር እያደገ መምጣቱን የዘገበው ፎርብስ፣  በተደጋጋሚ ኢንተርኔት በመዝጋት ህንድ ከአለማችን አገራት ቀዳሚነቱን መያዟን አመልክቷል፡፡
አክሰስ ናው የተባለው አለማቀፍ ተቋም ያወጣውን ሪፖርት ጠቅሶ ዘገባው አንዳለው፣ የህንድ መንግስት ባለፉት ከጥር ወር 2016 እስከ ግንቦት ወር 2018 በነበረው ጊዜ ውስጥ ለ154 ጊዜያት ያህል የኢንተርኔት አገልግሎቱን ዘግቷል ወይም ፍጥነቱን ገትቷል፡፡
በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ ለ19 ጊዜያት ያህል ኢንተርኔት የዘጋቺው ፓኪስታን፤ አዘውትሮ ኢንተርኔት በመዝጋት ከአለማችን አገራት ሁለተኛ ደረጃን ስትይዝ፣ ኢራቅ እና ሶርያ ለተመሳሳይ 8 ጊዜያት ያህል ኢንተርኔት በመዝጋት ሶስተኛ ደረጃ ላይ መቀመጣቸውን ዘገባው አመልክቷል፡፡
ቱርክ ለ7፣ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እና ኢትዮጵያ ለ5፣ ኢራን ለ4 እንዲሁም ቻድና ግብጽ ለ3 ጊዜያት ያህል ኢንተርኔትን በመዝጋት ተከታዮቹስ ስፍራ እንደያዙ ሪፖርቱ መግለጹንም ዘገባው ጠቁሟል።
መንግስታት የፖለቲካ ቀውስ ሲያሰጋቸው፣ ተቃውሞ ሲበዛባቸውና ወታደራዊ ጥቃት በሚፈጽሙበት ወቅት የመረጃ ፍሰትን ለመግታት ኢንተርኔት እንደሚዘጉ የጠቆመው ዘገባው፣ በተለያዩ የአፍሪካና የእስያ አገራት ደግሞ ፈተናዎች እንዳይጭበረበሩ ለማድረግ ኢንተርኔት እንደሚዘጋ አመልክቷል፡፡
አገራት ኢንተርኔትን በመዝጋት ሊከሰቱ የሚችሉ ጥፋቶችን ለመቀነስና አደጋዎችን ለማስቀረት እንደቻሉ ቢናገሩም፣ በሌላ በኩል ደግሞ ኢንተርኔት በመዝጋታቸው ሳቢያ ኢኮኖሚያቸው በከፍተኛ ሁኔታ ሲጎዳ ታይቷል ያለው ዘገባው፣ እኤ.አ ከ2012 እስከ 2017 በነበሩት ጊዚያት በድምሩ ለ16 ሺህ 315 ሰዓታት ኢንተርኔትን በመዝጋቷ ሳቢያ በኢኮኖሚዋ ላይ የ3.04 ቢሊዮን ዶላር ኪሳራ እንዳጋጠማት በአብነት አስታውሷል፡፡


Read 4748 times
Administrator

Latest from Administrator