Print this page
Monday, 03 September 2018 00:00

የለውጥ መርሆች

Written by  ኤርምያስ ጥላሁን (ከካሊፎርኒያ)
Rate this item
(10 votes)

 “በዓለም ላይ ልታየው የምትፈልገውን ለውጥ ሁን” - ማህተማ ጋንዲ
             
     ለውጥ አስፈላጊና ተፈጥሮአዊ ሂደት ቢሆንም ቀላል ደግሞ አይደለም። ሁሉም ነገር በለውጥ ሂደት ላይ ነው። በተፈጥሮ፣ በቴክኖሎጂ፣ በማህበራዊ ሕይወት፣ በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ፣ በዕድሜ፣ በግንኙነት ወ.ዘ.ተ ለውጦች አሉ። ለውጥን ማስቀረት አይቻልም። በተለይ ሃያኛው ይልቁንም ደግሞ ሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን ለውጥን ብቻ ሳይሆን ፍጥነት ያለውን ለውጥ ያየንባቸውና እያየንባቸው ያሉ ክፍለ ዘመኖች ናቸው። በእነዚህ ክፍለ ዘመኖች በቴክኖሎጂና በሳይንስ ረገድ ብቻ ሳይሆን በሰው ልጆች ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ሕይወት ላይ ዘርፈ ብዙ፣ መጠነ ሰፊና እጅግ ፈጣን ለውጥ ከመካሄዱ የተነሳ ለውጥ ራሱ በሰዎች ዘንድ ምንነቱና ይዘቱ በሳይንሳዊ መንገድ እንዲጠና ግድ ብሏል። በዚህ ፅሁፍ ለውጥን ከሳይንሳዊ መርሁ አንጻር በግርድፉ ለመዳሰስ እንሞክራለን፡፡
የለውጥ ምንነት
ለውጥ ሁሉም ነገር ባለበት እንደማይቀጥል ነገር ግን ከአንድ ደረጃ ወደ ሌላ ደረጃ መሸጋገሩን የሚያሳየን ነው። “የማይለወጥ ነገር ቢኖር ለውጥ ራሱ ነው” እንደሚባለው፣ ከለውጥ በቀር ሁሉም ነገር የሚለወጥ ነው። ልንለውጠው የማንችለው የለውጥን መኖር ነው። አንድ ልጅ ሕጻን ሆኖ አይቀርም ይለወጣል። አንድ ማህበረሰብም ባለበት አይቀጥልም ይለወጣል። ለውጥ ባይኖር ሕይወት ትርጉም አይኖረውም። ሕይወትን አጓጊና አስደሳች የሚያደርገው ለውጥ መኖሩ ነው። ለውጥ ባይኖር የመኖር ትርጉም ይጠፋብንና እንሰለች ነበር። ነገር ግን ዛሬ ያለውን ሕይወታችንንና ኑሮአችንን ባንወደው፣ ይለወጣል ብለን ተስፋ በማድረግ እንኖራለን። ስለዚህ ለውጥ የመኖር ተስፋ ነው ልንል እንችላለን።
የለውጥ ዓይነት
የለውጥ መኖር ሊፋቅ የማይችል ተፈጥሮአዊ ሕግ ቢሆንም ለውጥ ሁሉ ደግሞ ጠቃሚ ነው ማለት አይደለም። ስለዚህ ለውጥን ለሁለት ከፍለን አዎንታዊ ለውጥና አሉታዊ ለውጥ ብለን ልንጠራው እንችላለን። አዎንታዊ ለውጥ የምንለው የለውጡ መምጣት በኑሮአችንና በወደፊታችን ላይ አዎንታዊ አስተዋጽኦ ሲኖረው ነው። አሉታዊ ለውጥ ደግሞ በኑሮአችንና በወደፊታችን ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ የሚያመጣውን ነገር ነው። ስለዚህ አንድ ጤናማ ማህበረሰብ የሚፈልገው ለውጥን ብቻ ሳይሆን አዎንታዊ ለውጥን ነው። በነገራችን ላይ ለውጥ በራሱ አዎንታዊም አሉታዊም ላይሆን ይችላል። እኛ ነን ለውጡን አዎንታዊም አሉታዊም የምናደርገው። አንድ ልጅ ወደ አፍላ ወጣትነት ዕድሜ መሸጋገሩ የማይቀር ለውጥ ቢሆንም ይህንን ለውጥ ልጁ አሉታዊም ሆነ አዎንታዊ ሊያደርገው ይችላል። ይህንን የዕድሜ ለውጥ በአካልና በአዕምሮ ለመጎልበት ሊጠቀምበት ይችላል ወይም ደግሞ ወደ አልባሌ ነገሮች ሊያዘነብልበትና ዘመኑን ሊያባክንበት ይችላል። ስለዚህ ከለውጡ ይልቅ ለውጡን የሚያስተናግዱ ሰዎች ወሳኝ ናቸው። አንድ ማህበረሰብም ለውጥን አሉታዊ ወይም አዎንታዊ በሆነ መልኩ ሊጠቀምበት ይችላል። በአገራችን ታሪክ “አብዮት ፈነዳ”፣ ዘመኑ ራሱ “የለውጡ ጊዜ” እየተባለ በተጠራበት ዘመን ላይ የመጣው ለውጥ አሉታዊ ለውጥ ሆኖ፣ ክፉ ጠባሳ በታሪካችን ላይ ጽፎ አልፏል። ስለዚህ ለውጥ የመኖር ተስፋ ሊሆን እንደሚችል ሁሉ በአግባቡ ካልተያዘ፣ ካልተመራና የሁሉም ባለ ድርሻ አካላት በጎ አስተዋጽኦ ካልታከለበት አሉታዊ ሊሆን ይችላል። ከዚህ አንጻር ደግሞ ለውጥ የመኖር ተስፋ ብቻ ሳይሆን የሕልውና ሥጋት ሊሆን ይችላል፡፡
አሁን በአገራችን እየተካሄደ ያለው ለውጥ ታሪካዊና እንደ ሃገር የመኖራችንን ተስፋ ያናረ ነው። ይህ ለውጥ ገና ጅማሬ ላይ ያለ በመሆኑ የለውጥን ሳይንሳዊ መርሆች አውቀን አዎንታዊ ለውጥነቱ እስከ መጨረሻ እንዲዘልቅ ልናደርግ ይገባል።
የለውጥ ሂደት
ሁልጊዜ ለውጥ ውጤት አለው። ለውጥ ውጤት እንዲኖረው መጀመር አለበት። የተጀመረ ለውጥ ደግሞ ሂደት ውስጥ ይገባል። ውጤት ከጅማሬና ከሂደት በኋላ የሚገኝ ነው። ለውጥን የሚያጠኑ ባለሙያዎች እንደሚነግሩን፤ ለውጥ በሚፈጠርበት ጊዜ ሦስት አይነት ቡድኖች ይኖራሉ፡፡ እነዚህም የለውጡ አራማጆች፣ የለውጡ ታዛቢዎችና የለውጡ ተቃዋሚዎች ናቸው። ማንኛውም ለውጥ እንዲህ ዓይነት ሦስት ቡድኖችን መፍጠሩ አይቀርም። የለውጡ አራማጆች፤ ለውጡ ይመጣ ዘንድ እንቅስቃሴ የሚያደርጉና ዋጋ የሚከፍሉ ሲሆን፣ የለውጡ ታዛቢዎች የለውጡ አዎንታዊነትና አሉታዊነት ጥርት ብሎ ያልታያቸው፣ አቋም ለመያዝ ተጨማሪ ጊዜ የሚፈልጉ ናቸው። የለውጡ ተቃዋሚዎች ደግሞ የለውጡ አሉታዊነት ያመዘነባቸው ናቸው።
አንድ ለውጥ በሚመጣበት ጊዜ ታዛቢ መሆንና ተጨማሪ ጊዜን መፈለግ የሚጠበቅ ነው። የለውጥ ታዛቢ የሆኑ ሰዎች ተጨማሪ መረጃና ማስረጃ እስኪያገኙ ድረስ ፈጥነው አቋም ስለማይዙ፣ በወታደራዊው ዘመን “መሃል ሰፋሪ” እየተባሉ ሥነ ልቦናዊ መሸማቀቅ ይደርስባቸው ነበር። ነገር ግን እነዚህ የለውጥ ታዛቢዎች አብዛኛውን ጊዜ ስሜታዊ ስላልሆኑና አሳማኝ ነገሮችን ስለሚፈልጉ ለለውጡ አዎንታዊነት ወሳኝ ናቸው። ለውጡን በሩቁ የሚያዩና ከስሜት በጸዳ መልኩም የሚያገናዝቡ ናቸው። ለውጡ አሸናፊ እየሆነ መምጣቱ የሚለየው እነዚህ ታዛቢዎች የለውጡ ደጋፊ እየሆኑ ሲመጡ ነው። አብዛኛውን ጊዜ በቁጥር ስናየው የለውጡ አራማጆችና የለውጡ ተቃዋሚዎች ጥቂት ናቸው። ብዙሃኑ የሚገኘው በታዛቢነት ነው። አሁን በአገራችን እየተካሄደ ያለው ለውጥ፣ ብዙዎችን ከታዛቢነት ወደ ደጋፊነት ያመጣ ለውጥ ነው። እንደ እውነቱ ከሆነ፣ ለውጡ ከጥቂት ዓመታት ቀደም ብሎ የተጀመረ ቢሆንም ብዙዎቻችን የዚህን ለውጥ ለውጥነት ተረድተን የለውጡ ደጋፊ የሆንነው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ነው።
በአገራችን ታሪክ ብዙ ታዛቢዎችን የለውጥ ደጋፊ በማድረግ ረገድ አሁን እየተካሄደ ያለው ለውጥ ምናልባት ብቸኛው አሊያም በንጽጽር ከፍተኛው ነው ማለት ይቻላል። አንድን ለውጥ ስኬታማ የሚያደርገው ግን ታዛቢዎችን ወደ ደጋፊነት በማምጣቱ ሳይሆን ደጋፊዎቹ ባለ ድርሻ አካላት ሆነው የለውጥ አራማጆች ሲሆኑ ነው። ታዛቢ የሆኑት ሰዎች ደጋፊ እንዲሆኑ ብዙ ሥራ የሚጠበቀው ከለውጡ አራማጅ ነው። የለውጡ አራማጅ፣ ብዙዎችን ከታዛቢነት ወደ ደጋፊነት ለማምጣት በቃሉና በድርጊቱ መካከል ልዩነት አለመኖሩን ማስመስከርና ተአማኒነቱን ማሳየት ይኖርበታል። የለውጥ አራማጁ ብዙዎችን ከታዛቢነት ወደ ደጋፊነት ካመጣ በኋላ ግን በአብዛኛው ወደ ለውጥ አራማጅነት መምጣት የደጋፊዎች ድርሻና ኃላፊነት ነው። አሁን በአገራችን እየተካሄደ ባለው ለውጥ ከደጋፊነት ወደ ለውጥ አራማጅነት መምጣት የሚያስፈልገው ደረጃ ላይ የደረሰ ይመስለኛል።
ለውጥ የሚፈጥራቸው ሰዎች
በለውጥ ውስጥ ልናመጣቸው የሚገቡ ሥነ-ልቦናዊ ለውጦች አሉ። ታዛቢ ስንሆን ራሳችንን በውጭ አድርገን ነገሮችን የምንቃኝ (passive) እንጂ ተሳታፊዎች አይደለንም። ደጋፊ ስንሆን ደግሞ በአብዛኛው የምንሳተፈው በስሜት ነው። ይህ በጣም አስፈላጊ ነው። ስሜት በለውጥ ውስጥ ያለው ድርሻ በቀላሉ የሚታይ አይደለም። ስሜት ግን የምክንያታዊነትን ያክል የጸናና የተረጋጋ ስላልሆነ ለመጀመር ይረዳ እንደሆነ ነው እንጂ የመዝለቅ ብቃት የለውም። ስሜታችን ተነሳስቶ የለውጡ ደጋፊ ከመሆን ባሻገር ምክንያታዊ ወደ መሆን መምጣት ያስፈልጋል። ምክንያታዊነት ከለውጥ ደጋፊነት ወደ ለውጥ አራማጅነት ያመጣናል። የለውጥ አራማጅ ስንሆን፣ በለውጡ ውስጥ ያለንን ድርሻ በመለየት፣ እኛ ራሳችን በአዕምሮና በድርጊት የምንሳተፍ እንሆናለን።
አብዛኛውን ጊዜ እንዲለወጥ የምንፈልገው ነገር ይኖራል እንጂ እኛ ራሳችን መለወጥ እንዳለብን ብዙም አናስተውልም። ሳንለወጥ የማይለወጡ ነገሮች እንዳሉ ግን ቅድሚያ ሰጥተን ልናስብበት ይገባል። ስለዚህ የሚለወጥ ነገር መኖሩን የምንናፍቀውን ያክል እኛም ቢያንስ በአስተሳሰብ ልንለውጣቸው የሚገቡ ነገሮች ሊታዩን ይገባል። እነዚህን የአስተሳሰብ ለውጦች በዚህች አጭር ጽሁፍ መዘርዘር አንችልም። ነገር ግን የተወሰኑትን በጨረፍታ እንመልከት፡፡
ከሚናገር ይልቅ የሚሰማ ብጹዕ ነው
ብዙ መናገር የአላዋቂነት ወይም የችኩልነት ምልክት ነው። የእውቀታችን መጠን ለመናገር ያለን ጥድፊያ ይቀንሳል። ከሚናገር ይልቅ የሚሰማ እውቀት ይጨምራል። ስለ ፖለቲካና ስለ ኃይማኖት ሲነሳ ሁሉ ሰው ለመናገር ይፈልጋል። ይህ የሚያመለክተው አብዛኛው ሰው ስለ ፖለቲካና ስለ ኃይማኖት ያለው እውቀት አናሳ መሆኑን ነው። ለመናገር የምንቸኩለው እውቀት ሲያንሰን ነው። ለዚህ ነው እነዚህ ጉዳዮች ላይ ውይይት ሲደረግ፣ ከውይይት ይልቅ ወደ ክርክር የሚገባውና አለመስማማት የሚነግሰው። የማናውቀውን ወይም ስለማናውቀው ነገር ስንናገር በቀላሉ ስሜታዊ እንሆናለን። ስሜታዊ ስንሆን ደግሞ ምክንያታዊ መሆን አንችልም። ምክንያታዊነት ከሌለ ደግሞ ውይይት አይኖርም።
በአገራችን ውስጥ እየተካሄደ ባለው ለውጥ የጋራ መግባባት እጅግ አስፈላጊ ነው። ይህ ለውጥ ከዳር እንዲደርስ እርስ በእርስ መስማማት ባይቻል እንኳን እርስ በእርስ መግባባት ግን አስፈላጊ ነው። ከመስማት ይልቅ መናገር እየቀደመን ወደ መግባባት ልንመጣ አንችልም። መስማት የመግባባት መሠረት ነው። ከመስማት ይልቅ መናገር ከቀደመ፣ ማ ማንን ሊሰማ ነው? እንደ ሃገር የመስማት ባህላችን ሊጎለብት ይገባል። ብዙ ጊዜ ከሌሎች ጋር የማንስማማው ሳይገባን ነው። ባንስማማ እንኳን ገብቶን አንስማማ። የመስማት ባህላችን ምን ያክል ደካማ የመሆኑ አንዱ ማስረጃ፣ አንድ ዓይነት የፖለቲካ ፕሮግራም ያላቸው ብዙ ፓርቲዎች መኖራቸው ነው።  የመስማት አቅማችን ከፍ ካላለ፣ የማንግባባው ባልሰማነውና ባልገባን ነገር ላይ ነው።
ይህን ዓይነቱ ችግር ፖለቲካዊ ጉዳዮቻችን ላይ ጎልቶ ይውጣ እንጂ እንደ ማህበረሰብ በብዙ አቅጣጫ ልናስተውለው እንችላለን። ባልና ሚስት ሳይግባቡ ካልተስማሙ አንዳቸው ሌላቸውን ለመስማት ትዕግስቱም ፍላጎቱም ስለሌላቸው ሊሆን ይችላል። ስንሰማ የሌላኛውን ወገን አተያይ ይገባናል። ባንስማማው እንኳን ምን ለማለት እንደፈለገ ገብቶናል። ስለዚህ ተራችንን ጠብቀን ከገባን በኋላ ስንናገር የእኛን አተያይ ለማስረዳት እንሞክራለን እንጂ ሳንሰማ ለመሰማት አንሞክርም። ወላጅ ልጆቹን የሚሰማበት አንጀት ከሌለው ሊቆጣ እንጂ ሊመክር አይችልም። ምክር መስማትን ይጠይቃል። አለቃ ሠራተኛውን ካልሰማ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ እንዳሉት፤ “ሊነዳ እንጂ ሊመራ አይችልም።” አሁን ያለው ለውጥ ፖለቲካዊ ብቻ ሳይሆን ሥነ-ልቦናዊና ማህበራዊ ሲሆንልን የለውጡ መሠረት ሥር ይሰድዳል። እኛ ስንለወጥ የሚለወጡ ብዙ ነገሮች አሉ። ስለዚህ ይህንን የለውጥ ጊዜ ራሳችንንና አስተሳሰባችንን እያየን ለመለወጥ እንጠቀምበት። እኛ እስካልተለወጥን ድረስ እየተለወጠ ያለው ነገር ብዙም ዘላቂነት አይኖረውም።
ከሚሰማ ይልቅ የሚያዳምጥ ብጹዕ ነው
መስማት ከመናገር ይበልጣል፤ ማዳመጥ ደግሞ ከመስማትም ይበልጣል። ቢያንስ በዚህ ጽሑፍ መስማትና ማዳመጥ የተለያዩ ነገሮች ናቸው። መስማት በፈቃዳችን ላይ የተመሠረተ ላይሆን ይችላል። ሳንወዳቸው የምንሰማቸው በጣም ብዙ ነገሮች አሉ። ሳንፈልግ ጆሮአችን ውስጥ ጥልቅ የሚሉ ነገሮች አሉ። በተለይ አሁን ማህበራዊ ሚዲያው ሳንፈልግ ብዙ ነገር ነው የሚያሰማን። ማዳመጥ በፈቃድ ላይ የተመሠረተ በማጤን የታጀበ መስማት ነው። አንድ መረጃ በእኛ ላይ ተጽዕኖ የሚያመጣው ፈልገን ስለሰማነው ብቻ አይደለም፤ ሳንፈልግም ቢሆን እግረ መንገዳችንን የሰማነው ነገር በአስተሳሰባችን ላይ ቀጥሎም በድርጊታችን ላይ ተጽዕኖ ያመጣል። ቢሆንም ግን በአስተሳሰባችን ላይ ትልቅና ፈጣን ለውጥ የሚያመጣው ከምንሰማው ነገር ይልቅ የምናዳምጠው ነገር ነው። አንዳንድ ጊዜ የምንሰማቸው ነገሮች የምንሰማቸው ብቻ ሆነው አያልፉም። የሰማናቸው ነገሮች ቀልባችንን ከገዙት በኋላ እንድናዳምጣቸው ግድ ይሉናል። የምናዳምጠውን ነገር ወደን ፈቅደን ደጋግመን ነው የምናዳምጠው። የምናዳምጠው ነገር ሐሳብ ወደ መሆን ይመጣል። የምናዳምጠው ነገር የምናስበውን ይለውጠዋል።
የምንሰማውና የሚሰማን
ባለፉት ጥቂት ዓመታት በየቦታው ከፍተኛ የሕዝብ ቁጣ ያየንበት ነው። የሕዝብ የቁጣ ስሜት ገንፍሎ አገሪቱን አስጊ ደረጃ ላይ አድርሷት ነበር። ይህንን የሕዝብ ስሜት በመጠቀም ብዙ ኃይሎች በመንግሥት ላይ ጫና ለመፍጠር ሞክረዋል። በተለይ በተለያየ ሚዲያ ይሰሙ የነበሩ ነገሮች ይህንን የሕዝብ ቁጣ የበለጠ እንዲንር ሲያደርጉ ቆይተዋል። የምንሰማው የሚሰማንን ነገር ይጨምረዋል ወይም ይቀንሰዋል። የሚሰማን በምንሰማው ይወሰናል ማለት ነው። ይህ ደግሞ የምሥራችም አለው፤ የምንሰማውን በመለወጥ የሚሰማንን (ስሜታችንን) መለወጥ እንችላለን።
በአንድ በኩል በአገራችን ውስጥ ያለው የለውጥ ጅማሮ ይበል የሚያሰኝ ሆኖ፣ በሌላ በኩል ደግሞ እስከ አሁን ድረስ በተለያዩ ቦታዎች ግጭቶች እየተፈጠሩ የሰው ሕይወት እየጠፋ ነው። በአንድ ወቅት የነበረው የሕዝብ ስሜት የለውጥ ግፊት ለመፍጠር ያስቻለ አቅም (asset) እንደነበር ሁሉ አሁን ደግሞ ይህ ስሜት በሌላ ዓይነት ስሜት ካልተተካ የለውጡ እንቅፋት ወይም ጎታች (liability) መሆኑ አይቀርም። የሕዝቡን የቁጣ ስሜት ከፍ ለማድረግ ይሰሙና ይነገሩ የነበሩ ነገሮች አሁን ደግሞ ሌላ አዎንታዊ ነገር በማሰማትና በመናገር ካልተተኩ፣ ያንን ስሜት በመጠቀም እኩይ ተግባር የሚፈጽሙበት አሉ። ስለዚህ ለለውጡ ግፊት ለመፍጠር ሙከራ ያደርጉ የነበሩ ሚዲያዎች፣ ግለሰቦች፣ ድርጅቶች፣ የሙዚቃ አቀንቃኞች ያንን የተነሳሳና የጦዘ ስሜት መንገድ ላይ ጥለውት ሊሄዱት አይገባም። ይልቁንም ያንን ስሜት በሚያሰክንና ምክንያታዊነትን የተከተለ አስተሳሰብና እንቅስቃሴ እንዲኖር የማድረግ የሕሊና ዕዳ ያለባቸው ይመስለኛል። ተነሳስቶ ሳይሰክን የተተወ ስሜት አለ። እንዲህ ዓይነቱ የሕዝብ ስሜት በሩዋንዳ፣ በሶርያ፣ በሊብያና በየመን ምን ያክል ኪሳራ እንዳስከተለ ታሪክ ራሱ ሕያው ምስክር ሆኖአል። ለውጡን ለማምጣት ጥቅም ላይ የዋለው ስሜት ይሰክን ዘንድ ትኩረት ያለው፣ የተጠና፣ አዎንታዊ ሥራ ይጠይቃል።  
የለውጥ ሞዴል - ማቅለጥ - መለወጥ - ማቀዝቀዝ (Unfreeze – change – refreeze)
 የፊዚክስና የማህበራዊ ሳይንስ ሊቅ ኩርት ሌዊን የለውጥ ሞዴልን በተመለከተ እ.ኤ.አ በ1940 ማቅለጥ - መለወጥ - ማቀዝቀዝ በሚል ያስቀመጠው ጠቃሚ የለውጥ ሞዴል አለ። ይህንን ሞዴል ለማብራራት አራት ማዕዘን በረዶን ወደ ሦስት ማዕዘን በረዶ ለመለወጥ ያለውን ሂደት መመልከት እንችላለን። በመጀመርያ አራት ማዕዘኑ በረዶ እንዲቀልጥ እናደርገዋለን። ሲቀልጥ መለወጥ የሚችል ይሆናል። ሲቀልጥ አራት ማዕዘኑን በሦስት ማዕዘን ቅርጽ እናደርገዋለን። ሦስት ማዕዘን ሆኖ እንዲቀር ከእንደገና ማቀዝቀዝ ይጠበቅብናል። ይህንን ሞዴል የማኔጅመንት ኤክስፐርቶች በአንድ የቢዝነስ ወይም የድርጅት መዋቅር ላይ ለውጥ ለማምጣት ይጠቀሙበታል። እንደ ሃገርም እንዲቀልጥ የተደረገ ብዙ ነገር አለ። የቀለጠው ነገር ለለውጥ አመቺ የሆነ ከባቢ ፈጥሮአል። የሕዝብ ስሜት መነሳሳት፣ የነበረው ተቃውሞና እንቅስቃሴ የነበረው ነገር እንዲቀልጥ አድርጎታል። ይህ መቅለጥ ደግሞ በአገሪቱ ላይ ባልተለመደ ሁኔታ የአመራር ለውጥ እንዲመጣ አድርጓል። በዚህ የአመራር ለውጥ አብዛኛው ሕዝብ ደስተኛ ነው። ነገር ግን ይህ ለውጥ ውጤታማ፣ የጸናና ከዳር የሚደርስ እንዲሆን ማቀዝቀዝ ያስፈልጋል።
ምናልባት ጥያቄው የቀለጠውን ማን ያቀዝቅዘው? የሚል ይሆናል። ስናቀልጥ የነበርን ሰዎች ሁሉ በማቀዝቀዙ ላይ ድርሻ ሊኖረን ይገባል እንጂ ይህንን የማቀዝቀዝ ሂደት ከመንግሥት ብቻ መጠበቅ ወይም በኃይል በሚወሰዱ እርምጃዎች ማቀዝቀዝ ይቻላል ብሎ ማሰብ ኃላፊነትን አለመውሰድ ወይም አገራዊ ትርፍና ኪሳራውን ጠንቅቆ አለማስላት ነው። በሊቢያ፣ በሶርያ፣ በየመን የማቅለጡ ሥራ ተከናውኗል። ነገር ግን የማቀዝቀዙ ሥራ ቀላል አልሆነላቸውም። የማቀዝቀዙ ሥራ በአንድ ወገን የሚከናወን ሳይሆን የሁሉንም ባለ ድርሻ አካላት የሚጠይቅ ነው። ለዘላቂ ለውጥ የቀለጠውን ማሞቅና ማጋጋል ሳይሆን ማቅዝቀዝ አስፈላጊ ነው። እያንዳንዳችን ኃላፊነት ተሰምቶን የሚያቀዘቅዝ አስተሳሰብ፣ ንግግርና አስተያየት ሊኖረን ይገባል።

Read 8790 times