Saturday, 01 September 2018 15:44

ወ/ሮ ብሔር፣ እትዬ ብሔረሰብ የት ናቸው? አቶ ሕዝብ፣ ጋሼ ህብረተሰብስ?

Written by  ዮሃስ ሰ
Rate this item
(2 votes)

• “የፊታውራሪ አሽከር፣ የቀኛዝማች አገልጋይ” ብሎ ከመፎከር፣... “የወ/ሮ ብሔረሰብ አሽከር፣ የእትዬ ብሔር አገልጋይ”     ወደሚል መፈክር!
 • “የወ/ሮ ብሔረሰብ ቃልአቀባይ” እና “የእትዬ ብሔር አፈቀላጤ”... እያሉ በሁለት ጎራ የሚናቆሩ ዘረኞች፣ ተቀናቃኝ ቢሆኑም፣    ተመጋጋቢ ናቸው።
 • ከአቶ ሕዝብ ጋር ሲያወሩ ወለው ቃሉን ሲቀበሉ ያደሩ፣ ጋሼ ህብረተሰብም ሃሳቡን ሲያወጋቸውና መከራውን ሲያማክራቸው የከረመ
   ያስመስላሉ።
      ዮሃስ ሰ


     እዚያ ማዶ ሰፈር ውስጥ የሚኖር አንድ ነገረኛ ሰውዬ፣...  ወዲያ ማዶ መንደር ውስጥ ቤት የተከራየ ሌላ ነገረኛ ሰውዬ፣... እንደ ቀልድና ተረብ የጀመሩት የቃላት ውርወራ፣... ወደ ብሽሽቅና ስድብ፣... ወደ ውንጀላና ዛቻ፣... ከዚያም ለይቶለት በዱላና በድንጋይ ወደ መፈናከት ተሸጋግሮ  ...በሁለት ነገረኞች አምባጓሮ ሆኖ ያርፈዋል? ይሄማ ተራ አምባጓሮ ነው። “የግል ፀብ”፣ “የግል ጥፋት” ብቻ ሆኖ እንዲያበቃ ሳይሆን፣... በአንዳች ተዓምር፣ ወደ “ጋርዮሽ ፀብ” እንዲቀየርላቸው ነው የሚመኙት።
የግል ጋጠወጥነትን፣ ጥፋትንና ክፋትን፣... ለሰፈር ለመንደሩ ነዋሪዎች ሁሉ ለማጋራት ነው የሚፈልጉት - “ሕዝባዊ” እንዲሆንላቸው። የብሔር ብሔረሰብ ፖለቲካ ደግሞ፣ ለዚህ ይመቻቸዋል። ብሽሽቁና ስድቡን፣... በሰፈርና በመንደር፣ በቋንቋና በጎሳ፣ በተወላጅነትና በሃይማኖት ተከታይነት በጅምላ የሚተላለፍ የመንጋ በሽታ፣ በዘር የሚወረስ ጥፋት የጋርዮሽ ፀብ ማስመሰል ይችላሉ። በጣም ቀላል ሆኖላቸዋል።
የመጀመሪያው ነገረኛ ሰውዬ፣ “እኔን ሰደብክ ማለት፣... ያደግኩበትንም ሰፈሬ ሰደብክብኝ ማለት ነው። የምናገረውን ቋንቋ አዋረድክብኝ፣ የብሔረሰብ ማንነቴንም ሰደብክብኝ ማለት ነው” ይላል። (ሁለት ሶስት ጎረቤቶቹ፣ አጨብጫቢ እንዲሆኑለት፣ በቲፎዞነት እንዲቧደኑለት)።
ሁለተኛው ነገረኛ ሰውዬም በተራው፣ “እኔን ስደበኝ እንጂ፣... የምኖርበትን መንደርማ አትሰድብም። ቋንቋና ብሔርን አዋረድክ ማለት ነው” ብሎ ይንጣጣል (ሁለት ሶስት ጎረቤቶችን በአጫፋሪነት ለማቧደን)።

የአብዛኛው ሰው ጨዋነትና ዝምታ!
አንዱ ነገረኛ የለኮሰው እሳት ሌላኛው ተቀናቃኝ ነገረኛ እንደሚያጋግልለት፤... አንዱ ዘረኛ የለቀቀው መርዝ ሌላኛው ተቀናቃኝ ዘረኛ አስፍቶ እንደሚነዛለት ያውቃል።
በእርግጥ፣ የሁለቱ አመለኞች የዘወትር ስድብ፣ የሁለቱ ነገረኞች የተለመደ አምባጓሮ፣... ውሎ ሲያድር፣ ለብዙ የሰፈር የመንደሩ ነዋሪዎች፣ በጣም አሰልቺ ረብሻ ሲሆንባቸው እንጂ፣... ለእንዲህ አይነት አስቀያሚ ሁከትና አስፀያፊ አመል፣... አጫፋሪ ለመሆን በሆታ ሲነሱ አይታይም። እንደ መንጋ ግልብጥ ብለው አገር ምድሩን በፀብ ለማናወጥና ለማጋየት ሲዘምቱም አልታዩም - አብዛኞቹ ነዋሪዎች። ይሄ እውነት ነው። ግን ለምን?
በተለያዩ የአገራችን አካባቢዎች፣ በየጊዜው የሚፈጠሩ ሁከቶችንና ጥፋቶችን መታዘብ ትችላላችሁ። ጥቂት ክፉ ወንጀለኛ ሰዎች፣ በየቦታውና በየጊዜው እኩይ ጥፋት ቢፈፅሙም፣... መኖሪያ ቤቶችንና ሱቆችን ለማቃጠል፣ ብዙ ሺ ሰዎች ለጥፋት የዘመቱበት ክስተት እስካሁን አልተፈጠረም። ጎረቤታቸውን ለመግደል፣ ሚሊዮን ነዋሪዎች በጥላቻ የዘመቱበት ክፉ ጥፋትም እስካሁን አልተከሰተም።
ይሄ፣... በተደጋጋሚ በእውን የተረጋገጠ፣ ተጨባጭ ሃቅ ነው። ግን ለምን? አብዛኛው የአገሪቱ ነዋሪ፣... ይብዛም ይነስ፣... ሰው አክባሪ ጨዋነትን፣ ህግ አክባሪ ሰላማዊነትን የተላበሰ ስለሆነ ይመስለኛል - ዋናው ምክንያት።
(ታዲያ ልብ በሉ። ሰው አክባሪነትም ሆነ የጨዋነት ባህርይ፣ የግል ባህርይ እንጂ፣ አንድ ላይ ተጠፍጥፎ የተጋገረ የጋራ ባህርይ (የአቶ ሕዝብ ባህርይ) አይደለም። ህግ አክባሪነትም ሆነ የሰላማዊነት ባህርይም፣... በጅምላ አንድ ላይ ተጨፍልቆ የታጨቀ የጋራ ግብረገብነት አይደለም። የጋራ አንጎልና አእምሮ፣ የጋራ አካልና ሕይወት፣ የጋራ እውቀትና የጋራ ባህርይ የለም። ሁለት ሰዎች፣ የቱንም ያህል ቢመሳሰሉ እንኳ፣ ሁለት ነጠላ ሰዎች እንጂ፣ አንድ ላይ ተጨፍልቀው “የጋራ ሰውነት” እንደማይፈጠር ግልፅ አይደለም? ለዚያም ነው፣ በጅምላ “የህዝቡ ጥያቄ”፣ በደፈናው “የብሔር ብሔረሰብ እምነት”... ምናምን እያሉ በጭፍን መናገር፣ ወይ አላዋቂነት ነው። አልያም፣ “ሃሰትን እንደ እውነት አስመስሎ የመናገር ሙከራ” እንጂ ሌላ ትርጉም ሊኖረው አይችልም። አይተንና አጥንተን፣ አገናዝበንና አመዛዝነን፣... የትኛው አይነት ሃሳብና ባህርይ በብዙ ሰው ዘንድ እንደሚያመዝንና እንደሚዘወተር፣ ያወቅነውን ያህል ነው መናገር የሚገባን)።
እናም፣ በመጠንና በደረጃ ከሰው ሰው ቢለያይም፣ የተወሰነ ያህል የግብረገብነትና የቁጥብነት ባህርይ፣ በብዙ ሰው ዘንድ ዛሬም ድረስ ተሸርሽሮ ስላላለቀ ይመስለኛል - ሚሊዮኖች የሚጨፈጨፉበት ጥፋት እስካሁን ያልተከሰተው። ቢሆንም ግን፣...
ቢሆንም ግን፣ ጥቂት ነዋሪዎች፣ የፀብ አጫፋሪና አጨብጫቢ ለመሆን ወደ ጥፋት ጎዳና እንደሚቀላቀሉ በተደጋጋሚ ያየነው እውነት ነው። …እገሌና እገሊት ተብለው የሚዘረዘሩ፣… አንድ ሁለት ተብለው የሚቆጠሩ የሰፈር የመንደሩ ነዋሪዎች፣ እንደየግል ውሳኔያቸው… በሰፈርና በመንደር፣ ወይም በዘርና በሃይማኖት መቧደንን መርጠው፣ ሁለት ነገረኞች በፈጠሩት አምባጓሮና ሁለት ዘረኞች በቆሰቆሱት እሳት ውስጥ ገብተው ያጋግላሉ። በእነዚሁ ወንጀለኞች፣... በጭፍንና በክፋት በተቧደኑ ሰዎች ነው ጥፋት የሚፈፀመው እንጂ፣... በአቶ ብሔረሰብ ወይም በወ/ሮ መንደር ስለሚጋጩ አይደለም። የማይጋጩት ጨዋ ስለሆኑ አይደለም። በእውን የሌሉ የምናብ ፈጠራ ስለሆኑ ነው።

እትዬ ብሔረሰብና አቶ ሕዝብ፣ የትም የሉም። መቼም አይኖሩም።
“ተጣሉ፣ ተቧድነው ተጋጩ” ከተባለ፣... መጣላትና ተቧድነው መጋጨት የሚችሉት ፍጡራን፣ “ይሄ፣ ያኛው፣ ይሄኛው…” ተብለው ሊለዩ የሚችሉ ሰዎች፣ በሰበብ አስባብ ለጥፋት የሚቧደኑ ግለሰቦች ናቸው። መጣላትም ሆነ ተቧድነው መጋጨት የሚችሉ፣... “ወ/ሮ ሰፈር” እና “እትዬ መንደር” የተሰኙ ፍጡራን፣ በየትኛውም አገርና በየትኛውም ፕላኔት የሉም።
አፍ አውጥተው የሚሰዳደቡና የሚበሻሸቁ፣ “አቶ ጊዮርጊስ-ክለብ” እና “ጋሽ ቡና-ክለብ”... የተሰኙ ልዩ ፍጡራንን፣ የትም አታገኙም።  “ወ/ሮ እከሊት ብሔር” እና “እትዬ እገሊት ብሔረሰብ” የተሰኙ፣ በተቀናቃኝነት የሚወነጃጀሉና ለመጠፋፋት የሚጋጩ ልዩ ፍጡራን፣... በየትኛም አገርና ፕላኔት አለመኖራቸው ብቻ ሳይሆን፣... በየትኛውም ዘመን... ዛሬ በዘመናችን እንደሌሉ፣ በካሁን ቀደም እንዳልነበሩ፣ ካሁን በኋላም እንደማይኖሩ ግልፅ አይደለም? ይሄኮ፣ እለት በእለት አይተን ማረጋገጥና መገንዘብ የምንችለው እውነት ነው።
ይህንን እውነት መካድ፣ አልያም ይህንን እውነት በፅናት አለመያዝ ነው - ወደ ባሰ ጥፋት ሲያንሸራትተን የምንመለከተው።
የትም ቢሆን፣ መቼም ቢሆን፣ በየትኛውም ጉዳይ ላይ ቢሆን፣ ግለሰቦች ናቸው የሚጋጩት፣… ሁለት ሰዎችም ሆኑ ሁለት ሺ ሰዎች… ያው ግለሰቦች ናቸው።
ነገር ግን፣ እትዬ ሰፈር እና እትዬ መንደር፣ ወ/ሮ ብሔር እና ብሔረሰብ፣ አቶ ሕዝብና ህብረተሰብ የተሰኙ ፍጡራን አፍ አውጥተው እንደሚበሻሸቁና አካል ለብሰው እንደሚጋጩ “ማስመሰል”፣... በጣም ተለምዷል። እንዲህ አይነቱ የማስመሰል ውሸት፣... በጣም ከመለመዱም በላይ፣ እንደ አዋቂነትም ሲቆጠር ይታያል። ምን ይሄ ብቻ!
“ያኛው ሰፈር ነው ተጠያቂው፤ ይሄኛው ሰፈር ነው ጀማሪው…” በሚል ሌላ የቅዠት ፉክክር አማካኝነት የጭፍንነት ጎራው እየተስፋፋ፣ ወደ ባሰ ጥፋት ይሸጋገራል።
ሁለቱ ነገረኞች፣ የሰፈር እና የብሔር አፈቀላጤ፣ የመንደርና የብሔረሰብ ቃልአቀባይ የሚል ስያሜ ለመታወቅና ዝና ለማግኘት፣... አብዛኛውን ሰው ዝም አሰኝተው፣ ጥቂት አጨብጫቢዎችን በመንደርም ሆነ በብሔር፣ በቋንቋም ሆነ በሃይማኖት አቧድነው፣ በሰፊው አካባቢውን ማተራመስና መቀወጥ፤ ለጥፋትና ለእልቂት ክፉ ጥላቻን እየነዙ የመዝመት እድል የሚያገኙት በዚህ መንገድ ነው።

ተቀናቃኝ ዘረኞች በብሔር ብሔረሰብ ሲያቧድኑ ምን ያተርፋሉ?
በዘርና በሰፈር ካቧደኑን፣... የንግግራቸውን እውነተኛነት ሳናመሳክርና ሳናረጋግጥ፣ ዘር እየቆጠርን በቲፎዞነት በአዎንታ እንድንመሰክርላቸው ነው ምኞታቸው።… የሃሳባቸውን ትክክለኛነት ሳናገናዝብና ሳናመዛዝን፣ በብሔረሰብ ተወላጅነት ተቧድነን፣ ጭፍን ንግግራቸውን እንድናፀድቅላቸው… ነው ፍላጎታቸው። ከእውነትና ከፅድቅ መንገድ እንድንሸሽ ነው፤ ወከባቸውና ሁካታቸው - በፕሮፓጋንዳ የማስፈራራት ወከባ፣ በአሉባልታ የማምታታት ሁካታ።
ታዲያ፣ በተቃራኒ ጎራ በዘር ለማቧደን የሚወራጩ ዘረኞች፣... እንደዚያ በየእለቱ እርስ በርስ እየተሰዳደቡ፣ እየተወነጃጀሉ፣ ጥላቻን እየዘሩና ለእልቂት እየዛቱ የሚያምሱን፣ “የወ/ሮ ብሔረሰብ ቃልአቀባይ” እና ተቀናቃኙ “የእትዬ ብሔር አፈቀላጤ”...  ተመጋጋቢ ናቸው። አንዱ ዘረኛ፣ ያለተቀናቃኝ ዘረኛ ለብቻው፣ ተደማጭነት እንደማያገኝ ያውቀዋል። ለምን?
“የወ/ሮ እከሊት ብሔረሰብ ቃልአቀባይ” በሚል ታፔላ ለመታወቅ፣... ከዚያ ማዶ ሌላ ተቀናቃኝ እንዲነግስ፣... ማለትም “የእትዬ እንቶኒት ብሔረሰብ አፈቀላጤ” በሚል ስያሜ የሚናቆር ዝነኛ ባላንጣ እንዲፈጠርለት፣ ዘረኛ ተቀናቃኝ እንዲመጣለት፣ ተሰሚነትና ቲፎዞ እንዲያገኝም ጭምር ይፈልጋል። አለበለዚያ ሰዎችን በጭፍን የማቧደንና፣ የወ/ሮ እከሊት ሰፈር ተጠሪ፣ የእትዬ እከሊት ብሔረሰብ ተቆርቋሪ በሚል ስያሜ የመታወቅ ምኞቱ… ምኞት ብቻ ሆኖ ይቀራል።
በአጭሩ፣ የዘረኝነት በሽታ የተፀናወተው ክፉ ሰው፣ “የአቶ ብሔር ተቆርቋሪ፣ የእንቶኒት ብሔረሰብ አሽከር” እያለ ሰዎችን ለማቧደን ከፈለገ፣... ተቀናቃኝ የሚሆንለት ሌላ ክፉ ሰው፣ ...”የጋሽ ብሔር ተጠሪ፣ የእከሊት ብሔረሰብ አገልጋይ” እያለ ዘረኝነትን የሚቀሰቅስ “ጠላት” እንዲፈጠርለት ይመኛል። አንዱ ተቀናቃኝ ከሌላኛው ተቀናቃኝ ጋር ተመጋጋቢ ነው።
ለነገሩ፣ ያን ያህልም አስቸጋሪ አልሆነባቸው። ያለ ብዙ ጥረት የዘረኞች ምኞት እየተሳካ ነው። ለምን? ዘረኝነትን የሚተካ ሃሳብ ብዙም ጎልቶ አይሰማም።

የታል? ዘረኝነትን የሚተካ ትክክለኛ ሃሳብ!
እየተበራከቱ የመጡ ውይይቶችን መታዘብ ትችላላችሁ። ...በየራሳቸው አእምሮ አስተውለው፣ በእውን ያረጋገጡትን እውነተኛ መረጃ ከመናገር ይልቅ፣... አጥርተው በውል ያገናዘቡትን ትክክለኛ ሃሳብ ከመግለፅ ይልቅ፣... ጠንቅቀው በቅጡ የጨበጡትን አስተማማኝ እውቀት ከማስረዳት ይልቅ፣... “የአቶ ሕዝብ ቃል አቀባይ”፣ “የወ/ሮ ብሔር አፈቀላጤ”፣ “የእከሊት ብሔረሰብ መልእክተኛ” ለመምሰል፣ ከንቱ ፉክክርና የወረደ እሽቅድምድም ላይ የተጠመዱ ምሁራንና ፖለቲከኞች ጥቂት ናቸው? አይደሉም።
ሁሉም ምሁራንና ፖለቲከኞች ባይሆኑም፣ አንዳንዶቹን በተደጋጋሚ እንደምንሰማቸው... “ሕዝቡ... ህብረተሰቡ፣... እከሌ ብሔር፣ እገሌ ብሔረሰብ” እያሉ ከማነብነብ ውጭ ሌላ ነገር ማሰብም ሆነ መናገር የሚችሉ አይመስሉም።
“አመሳክሬ ያረጋገጥኩት እውነተኛ መረጃ... ይሄ፣ ይሄ፣ ይሄ ነው” ብሎ መናገር፣... ቀላል ሃላፊነት አይደለማ። በቅድሚያ ነገሮችን በእውን ማየትና ማስተዋል፣ መረጃዎችንም በእውን ማመሳከርና ማረጋገጥ፣ ማገናዘብና ማመዛዘን፣ በአጭሩ የራስን አእምሮ በትክክል መጠቀም፣... ከባድ ሃላፊነት ነው - እውነተኛ መረጃና ትክክለኛ ሃሳብ ለማቅረብ። እናም ከዚህ ይልቅ፣ ምን ሲዘወተር ይታያል?
“የሕዝቡ ጥያቄና ግንዛቤ”፣... “የህብረተሰቡ እምነትና ሃሳብ”... እያሉ እለት በእለት ለማነብነብ የሚጣደፉ ምሁራንና ፖለቲከኞችን፣ ይህንኑን ተቀብለው የሚያስተቡ በርካታ ጋዜጠኞችና ጸሐፊዎችንም አስተውሉ።
ከአቶ ሕዝብ ጋር ሲያወሩ ወለው ቃሉን ሲቀበሉ ያደሩ፣ ጋሼ ህብረተሰብም ሃሳቡን ሲያወጋቸውና መከራውን ሲያማክራቸው የከረመ ያስመስላሉ።


Read 2935 times