በህይወት የሙዚቃ ት/ቤት የተዘጋጀውና ህፃናትን ስለ አገራቸው ባህል፣ ታሪክና ወግ ያስተምራል የተባለለት “አደይ አበባ” የመዝሙር ቪዲዮ ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ ረፋድ ላይ ህፃናት፣ ወላጆች፣ መምህራንና የሚመለከታቸው የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት በድምቀት ተመርቋል፡፡
አልበሙ ዘጠኝ የተለያዩ የህፃናት የቪዲዮ መዝሙሮችን የያዘ ሲሆን በህይወት ማሞ ዋና አዘጋጅነት መሰናዳቱንም የምርቃቱ አስተባባሪ እንጀራ ኢቨንትስ አስታውሷል፡፡ መዝሙሮቹ የአገራቸውን ባህል፣ ጨዋታዎች፣ ታሪኮችና አጠቃላይ እውቀትን ለህፃናት ያስጨብጣሉም ተብሏል፡፡ ህይወት የሙዚቃ ት/ቤት ከዚህ ቀደም በርካታ የህፃናት መፅሐፍትና መዝሙሮችን በማሳተምና የሙዚቃ መሳሪያ በተለይም ፒያኖን በማሰልጠን ላለፉት 15 ዓመታት በህፃናት ላይ በጎ ስራን ሲሰራ እንደቆየ በምርቃቱ ላይ ተገልጿል፡፡