Print this page
Saturday, 01 September 2018 15:23

ሌት ክዋክብቱ እንደ ፀደይ አጥለቅልቆን በቀይ አደይ…

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(9 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!    ይኸው ደግሞ አንደኛውን ዓመት ሸኝተን  ሌላውን ልንቀበል ጫፉ ላይ ደርሰናል፡፡ እኔ የምለው…ዳያስፖራ ወገኖቻችን…ቡሄው እንዴት ነበር? የዘንድሮው…አለ አይደል… እንኳን ለእናንተ ለእኛም ገርሞናል፡፡ ድምቅ አለ እኮ!…እናማ ከበርካታ ዓመታት በኋላ ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች እየመጡ ያሉ ወገኖቻችን ስሜታቸው በእጅጉ እየተነካ መሆኑን እየሰማን ነው፡፡ ሊገርመንም አይገባም…ብዙዎች “ከእለታት አንድ ቀን አገሬን እንደገና አያታለሁ” ማለት የማይችሉበት ደረጃ ላይ ደርሰው ነበርና፡፡ ከአገራቸው ጋር የሚኖራቸው የእድሜ ልክ ትስስር  ከዚህ በሚላከው በርበሬና ሹሮ፣ ከዚህ በሚላከው ሸማና ረከቦት፣ ከዚህ በሚላከው ዘፈንና ዝማሬ ብቻ ተወስኖ የሚቀር ሲመስላቸው ኖሯልና፡፡ እናማ…
የእናት አገር ቀሚስ የአባት አገር ሸማ
ነጠላ አይደለም ወይ የሰው አገርማ
እንዲል የአገሬ ባለቅኔ… በዋሺንግተን ጎዳና በርገር ስለገመጡ፣ በኤሚሬትስ ስቴዲየም ለአርሴ ስላጨበጨቡ፣ በኤፈል ማማ ላይ ወጥተው ፎቶ ስለተነሱ ሲደላቸው ኖሯል ማለት አይደለም፡፡ የደላቸው የሚኖሩትን ያህል የብዙዎቹ ኑሮ ግን አንደ አልጋ ከሚጋሩት የትዳር ጓደኛ ጋር እንኳን ባይተዋር የሚያደርግ መሆኑን እናውቃለን… እኛ ‘አጅሬዎቹ’ በየወሩና በየአስራ አምስት ቀኑ “እስቲ መቶ ዶላር ላክልኝ…”  “አሁን ለእኔ ትንሽ ዶላር መላክ አቅቶሽ ነው!” ማለታችን ባይቀርም ማለት ነው፡፡ እናማ…ከዛ መተንፈሻ የሚያሳጣ ኑሮ ለጥቂት ቀናት ተላቀው ወገናቸው መሀል በመገኘታቸው ስሜታቸው ጣራ ቢነካ አይገርምም፡፡ በወጣቶቻችን ቋንቋ… ይመቻችሁማ!
እናማ… የዘንድሮው ‘ቡሄ’… አለ አይደል… ለከርሞውም እንዲሁ ያድምቀው የሚያሰኝ አይነት ነበር፡፡ (ህጻናቱ እንኳን “የእኔ ማራዶና…” ማለትን የቀነሱበት!) እንደውም ከጭፈራውና ከሆታው ባለፈ… ብዙ ቤተሰቦች የፉርኖ ዱቄት ፉርኖ ነገር ትተው፣ የጥንቱን አይነት ህብስት ምናምን ‘ለመጋገር ሞክረዋል’ ነው የሚባለው፡፡ እሰየው ነው፡፡ (ህብስቱን ‘ስድስት ማእዘን ያደረጋችሁትም አይክፋችሁ…ለከርሞው አምስት፣ ደግሞ አራት እያላችሁ ትለምዱታላችሁ!) መጪዎቹንም በዓላት እንዲሁ ሞቅ፣ ደመቅ ያድርግልንማ፡፡
ግን…ደግሞ ጥግ ድረስ እንዳንመኝ የሚያደርገን ነገር አለ… የኤሌትሪክ ሀይሉ ነገር፡፡ ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…ለሆነ ጥገና ሥራ “በዚህ፣ በዚህ ቦታ ከጠዋቱ አሥራ ሁለት ሰዓት እስከ ቀኑ ስምንት ሰዓት የኤሌትሪክ ሀይል ይቋረጣል” ሲባል…አለ አይደል…ምን ይመስለኛል መሰላችሁ…ለስታንድ አፕ ኮሜዲ የተዘጋጀ ጽሁፍ በስህተት የተነበበ! ሁለትና ሦስት ቀን በተከታታይ በሚጠፋበት፣ በየቀኑ ለመቁጠር በሚያሰለች ብዛት ብልጭ ድርግም በሚልበት (ይቺ ጽሁፍ ተጀምራ እስከምትጨረስ ስንት ጊዜ እየጠፋ እንደመጣ የምናውቀው አንድዬ፣ እኔና ቡሉኖቹን የሚነካኩት ሰዎች ብቻ ነን!) …እንዲህ አይነቱ ማስታወቂያ ግርም ይለኛል፡፡ ልክ እኮ…በወጣቶቹ ቋንቋ ለመጠቀም በእኛ ላይ ‘ሙድ እየተያዘብን ይመስላል፡፡
የምር ግን…እንግዲህ ጨዋታም አይደል… አንድ ወዳጃችን ምን አለ መሰላችሁ…‘ቡሄ’ ለዓመታት ይዞት የቆየውን ቅሬታውን ትቶ “በይቅርታ መንፈስ ከሌሎች በዓላት ጋር ተደምሯል” ብሏል፡፡ አሪፍ አባባል ነው፡፡ ከፊት ለፊታችን ደግሞ በዓላት አሉ። እነሱንም እንዲሁ ደመቅ ያድርግልንማ! ከረጅም ጊዜ በኋላ…
“የዘንድሮው ዓመት እንዴት ነው?” ስንባል…
“ከሚቀጥለው ይሻላል…” ከማለት መዳኑ ቀላል ነገር አይደለም፡፡ ተስፋ ቀላል ነገር አይደለም፡፡ “ይቻላል” ብሎ ማሰብ ደረጃ መድረስ ቀላል ነገር አይደለም፡፡
የዘመናት ዜማችን… የዘመናት እንጉርጉሯችን…የዘመናት የብሶት ቅኔያችን…
የአምናን ቀን ረገምኩት ለአፌ ለከት የለው
የዘንድሮው መጣ እጅ እግር የሌለው
ለጊዜውም ቢሆን የምንረሳበት እድል እንደገጠመን ማወቁ ትልቅ ነገር ነው፡፡ ልዩነቱ የሚመጣው እድሉን እንዴት እንጠቀመዋለን ነው። እድሉን ከተጠቀምን በራችንን ከመከርቸም አልፈን… “ነገ ምሳ እኔ ቤት ነው፣ ልጆቻችሁን ይዛችሁ ካልመጣችሁ ጥል ነው…” አይነት የምንባባልበት፣ ከአንድ መሶብ የምንቆርስበት፣ ለፌስቡክ ‘ፕሮፋይል ፒክቸር’ ሳይሆን፣ ከልባችን… “አንድ ጊዜ ብቻ፣  በሞቴ!” እየተባባልን የምንጎራረስበት ጊዜ ቅርብ ሊሆን እንደሚችል ማወቁ ትልቅ ጸጋ ነው፡፡
ሰብሰብ ብለን እርስ በእርስ የልባችንን የምንጨወዋትበት፣ “እንዲህ ብል ምን ይሉኝ ይሆን!” ብለን የማንሳቀቅበት… አንዲት ‘ተራ’ ቃል አንድ መቶ አስራ አንድ ቦታ እየተመነዘረች ‘ባልተገፋ አጥር’ “ወዮልህ!” የማንባባልበት…
እንግዲህ ነገሬን ከከንፈሬ አልለቀም
የሰው ዶሮ አለና ከአፍ፣ ከአፍ የሚለቅም
አይነት መጠራጠር ባይቀር እንኳን የሚቀንስበትን ጊዜ የማቅረቡም፣ የማራቁም ነገር በእኛው እጅ መሆኑን ማወቁ ትልቅ ነገር ነው፡፡
ሽምብራውን ዘርተን እሸቱን ስንበላ
አወይ የእኛ ነገር ሁልጊዜ ጥርጠራ
የምትል ቅኔ አለች፡፡ በፖለቲካውም፣ በማህበራዊ ኑሮውም ብቻ ሳይሆን በትንሽ ትልቁ እርስ በእርስ መጠራጠር እንደ ባህሪያችን ከሆነ ከራረመ፡፡ አይደለም ባዳና ጎረቤት በአንድ ቤተሰብ ውስጥ እንኳን መተማመን የጠፋበት፣ እርስ በእርስ በጎሪጥ የምንተያይበት ደረጃ ደርሰናል፡፡
አጥብቀው ሰላም ካሉን እንጠራጠራለን። (“ይሄኔ ተንኮል አስባ እንጂ ከመቼ ወዲህ ነው እሷ እኔን እንዲህ ሰላም የምትለኝ! አጅሪትን አጣኋሁዋትና ነው!)  
ዝም ብለው ካለፉን እንጠራጠራለን፡፡ (“ምን አግኝታ ነው ፊቷን አዙራ የሄደችው! ምቀኛ፣ የምቀኛ ዘር!”)  
መንገዳችን ላይ ድመትም ቢጤ ካቋረጠችን እንጠራጠራለን፡፡ (“በሌላ ቢያቅታቸው ድመት ላይ አስደግመው ላኩብኝ!”)
ወጣቱ  የአስተማሪነት ስልጠናውን እያጠናቀቀ ነው፡፡ ስለሆነም አሰልጣኙን በአንድ ጥያቄ ሊሞግተው ወደደ፡፡ አንዲት ወፍ ያጠምድና በአንድ እጁ መዳፍ ሸፈን አድርጓት አስተማሪው ዘንድ ይሄዳል፡፡
“መምህር፣ ይቺ ወፍ በህይወት አለች ወይስ ሞታለች?” ይለዋል፡፡ አስቦ የነበረው አሰልጣኙ “በህይወት አለች” ቢለው፣ ጨምቆ ሊገድላትና ይኸው ሞታለች ሊል፣ “ሞታለች” ቢለው፣ እጁን ከፍቶ ሊለቃትና “ይኸው በህይወት አለች” ሊል ነው፡፡ እንደገናም…
“መምህር፣ ይቺ ወፍ በህይወት አለች ወይስ ሞታለች?” ይለዋል፡፡ አሰልጣኙም እንዲህ ሲል መለሰለት…
“ውድ ተማሪዬ፣ በህይወት መኖሯም፣ መሞቷም የሚወሰነው በአንተ ነው” አለው ይባላል፡፡
የምር ግን…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…ብዙ ነገሮች ስረ-መሠረታቸው ሲናድ ኖሯል፡፡ በእርግጥ በቀደምት ዘመናት የነበሩ አጉል ነገሮች፣ የማይጠቅሙን ነገሮች፣ ሊታወሱ የማይገባቸው ነገሮችን አለማንሳት ብቻ ሳይሆን መርሳትም ያስፈልጋል…እንደውም በርቀት ተሽቀንጥረው ከእይታችን ውጪ ሁሉ ቢሆኑ አሪፍ ነው፡፡ ጎን ለጎን ግን የትናንት በጎ ነገሮችን ሁሉ አንድ ላይ አፈር ማልበስ ልክ አይሆንም፡፡ ሸጋ የሚሆነው ክፉውን እየጣሉ፣ በጎውን ይዞ መሄዱ ነው፡፡ እናማ…አብዛኞቹ የበዓላት አከባበር ባህሎቻችን የተዋቡ ብቻ ሳይሆኑ የራሳችን ቀለሞች ያሏቸውና ልዩ ናቸው፡፡ አንዳንዴ ስለ ራሳችን የሚወደሰውን ማወደስ መታበይ አይደለም…እውነትን በስፍራዋ ማስቀመጥ እንጂ፡፡
ሌት ክዋክብቱ እንደ ፀደይ
አጥለቅልቆን በቀይ አደይ
ሰማዩ ስጋጃ አጥልቆ
ተሽለምልሞ አንጸባርቆ
ፈክቶ አሸብርቆ ደምቆ…
እያለ ይቀጥላል ሎሬት ፀጋዬ በ‘እሳት ወይ አበባ’ ግጥሙ፡፡ እኛም የሀዘን እንጉርጉሮ እየቀነሰልን…እንደ ፀደይ ስላጥለቀለቁን ክዋክብት፣ ስጋጃ አጥልቆ ስለተሽለመለመውና  ስለሚያንጸባርቀው ሰማይ… በጋራ የምንዘምርበትን ጊዜ ያቅርብልንማ።
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 3049 times