Print this page
Saturday, 01 September 2018 15:22

በዚምባቡዌ 60 ዓመት ያልሞላው ፕሬዚዳንት እንዳይሆን ሊታገድ ነው

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

 ገዢው ፓርቲ ያልበሰሉ ፖለቲከኞች አገር እንዳያጠፉ ያሰጋል ብሏል

    በአወዛጋቢ ምርጫ ስልጣኑን ያስጠበቀው የዚምባቡዌ ገዢ ፓርቲ ዛኑ ፒኤፍ፣ ምራቃቸውን ዋጥ ያላደረጉና በወጉ ያልበሰሉ ግለሰቦች ለፕሬዚዳንትነት እየተወዳደሩ አገሪቱን ለቀውስ እየዳረጓት በመሆኑ፣ ዜጎች ለፕሬዚዳንትነት መወዳደር የሚችሉበትን የዕድሜ ገደብ ከ40 አመት ወደ 60 አመት ከፍ ለማድረግ እንደሚሰራ መግለጹን አፍሪካን ኒውስ ዘግቧል፡፡
በቅርቡ በተካሄደው የዚምባቡዌ አገራዊ ምርጫ ፕሬዚዳንት ኤመርሰን ምናንጋዋ በአብላጫ ድምጽ ቢያሸንፉም፣ ዋነኛ ተቀናቃኛቸው የነበሩት ሙቭመንት ፎር ዲሞክራቲክ ቼንጅ የተባለው የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ኔልሰን ቻሜሳ፤ ምርጫው በመጭበርበሩ ውጤቱ ይሰረዝልን በሚል ለፍርድ ቤት ቢከስሱም በለስ እንዳልቀናቸው ያስታወሰው ዘገባው፣ የ40 አመት ዕድሜ ያላቸው ኔልሰን ቻሜሳ ምርጫውን የልጅ ጨዋታ አድርገውታልና ከአሁን በኋላ ለፕሬዚዳንትነት የሚወዳደሩት ቢያንስ 60 አመት የሞላቸው ዜጎች ሊሆኑ ይገባል ሲል ዛኑ ፒኤፍ ማስታወቁን አመልክቷል፡፡
የተቃዋሚው ፓርቲ መሪ ቻሜሳ በምርጫው ሲሸነፉ እንደበሳል ፖለቲከኛ ሳይሆን እንደህጻን ልጅ በማኩረፍና የማይገባ ድርጊት በመፈጸም ጉዳዩን የልጅ ዕቃ ዕቃ ጨዋታ አድርገውታል፤ ከአሁን በኋላ እንደ እሳቸው ያለ ያልበሰለ ሰው ዘልሎ ለፕሬዚዳንትነት መወዳደር የለበትም ብለዋል፤ የገዢው ፓርቲ የዛኑ ፒኤፍ የብሄራዊ ደህንነት ጸሃፊ ላሞር ማቱኬ፡፡
በአገሪቱ ክምር ቤት አብላጫ ወንበር የያዘው ፓርቲያቸው፤ ዜጎች ለፕሬዚዳንትነት መወዳደር የሚችሉበትን የዕድሜ ገደብ ከ40 አመት ወደ 60 አመት ለማድረግ በህገ መንግስቱ ላይ ማሻሻያ መደረግ የሚችልበትን ዕድል ለመፍጠር ጠንክሮ እንደሚሰራም አስታውቀዋል፡፡

Read 1417 times
Administrator

Latest from Administrator