Print this page
Saturday, 01 September 2018 15:13

በጣሊያን ኤምባሲ የሚገኙት የደርግ ባለስልጣናት ምህረት እንዲደረግላቸው አምነስቲ ጠየቀ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(5 votes)

 ላለፉት 27 ዓመታት በጣሊያን ኤምባሲ በግዞት ላይ የሚገኙት ሁለቱ የደርግ ባለስልጣናት ምህረት ተደርጎላቸው ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንዲቀላቀሉ ለኢትዮጵያ መንግስት አቤቱታ ቀረበ፡፡
በደርግ የመጨረሻዎቹ ዘመን የኢትዮጵያ ጦር ኢታማዦር ሹም የነበሩትና አሁን የ74 ዓመት ዕድሜ ባለፀጋ የሆኑት ሌተና ጀነራል አዲስ ተድላ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የነበሩት ሌተና ኮሎኔል ብርሃኑ ባየህ በአዲስ የጠ/ሚ ዶ/ር ዐቢይ አህመድ አመራር ምህረት እንዲደረግላቸው አምነስቲ ኢንተርናሽናል ለመንግስት ጥያቄ አቅርቧል፡፡
ሁለቱ የቀድሞ መንግስት ባለስልጣናት ከዚህ ቀደም በሌሉበት ሞት የተፈረደባቸው ሲሆን በድጋሚ ጉዳያቸው ታይቶ በ2003 ዓ.ም ፍርዱ ወደ እድሜ ልክ እንደተለወጠላቸው ያስታወሰው አምነስቲ በኢትዮጵያ አንድ የእድሜ ልክ ፍርደኛ ከአመክሮ ጋር ተደማምሮ ከ23 ዓመት በላይ ሊታሰር እንደማይችል በመጠቆም፣ ባለስልጣናቱ ከሚገባቸው በላይ ለ27 ዓመታት ከቤተሰቦቻቸውና ከአገራቸው ተነጥለው በግዞት አሳልፈዋል ብሏል፡፡
ከ27 ዓመት በላይ ከማህበረሰብ ተገልሎ መኖር ከመደበኛ የፍርድ ቅጣት በላይ ነው ያለው አምነስቲ፤ የእድሜ ልክ ፍርደኛ የነበሩት የባለስልጣናቱ የስራ ባልደረቦች ከ6 ዓመት በፊት በይቅርታ መለቀቃቸውን በማስታወስ፣ ሁለቱ ባለስልጣናት የይቅርታና ምህረት አዋጁ ተጠቃሚ እንዲሆኑ መንግስትን ጠይቋል፡፡
ባለስልጣናቱ በመንግሥት የኃላፊነት ዘመናቸው ሃገራቸውን ከውጭ ወራሪ ኃይል የጠበቁ ብቁ ወታደሮች እንደነበሩ መንግስት ከግምት በማስገባት ጉዳያቸውን በቀና ልቦና እንዲመለከተው ተቋሙ ጠይቋል፡፡
ሁለቱ የደርግ ከፍተኛ ባለስልጣናት በቅርቡ በወጣው የምህረት አዋጅ ተጠቃሚ መሆን እንደሚችሉ ቀደም ሲል ተገልፆላቸው የነበረ ቢሆንም በኋላ ግን አዋጁ እንደማይመለከታቸው ተጠቁሟል፡፡ የምህረት አዋጁ ተጠቃሚ የማይሆኑበት ምክንያት በቀይ ሽብር ወንጀል ተሳትፎ ተጠያቂ በመሆናቸው ነው ተብሏል፡፡

Read 9739 times