Print this page
Saturday, 01 September 2018 15:10

በእነ አቶ በረከት ጉዳይ የመጨረሻው ፖለቲካዊ ውሳኔ ከብአዴን በጠቅላላ ጉባኤ ይጠበቃል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(14 votes)

 ከሰሞኑ በጥረት ኮርፖሬት ላይ የአሰራር ብልሽት ፈጥረዋል፤ ብአዴንን አዳክመዋል በሚል ተገምግመው በብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ በታገዱት በአቶ በረከት ስምኦን እና በአቶ ታደሰ ካሳ ጉዳይ ላይ የመጨረሻውን ፖለቲካዊ ውሳኔ የሚሰጠው መስከረም ወር የሚካሄደው የድርጅቱ ጠቅላላ ጉባኤ ነው ተብሏል፡፡
ሁለቱ ከፍተኛ አመራሮች በማዕከላዊ ኮሚቴው የተላለፈብን ውሳኔ ተገቢ አይደለም ብለው ካመኑ ጉዳያቸውን ለጠቅላላ ጉባኤው አቅርበው መከራከር እንደሚችሉ የገለፁት የብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ አባሉ አቶ ንጉሱ ጥላሁን፤ ጉባኤውም የማዕከላዊ ኮሚቴውንና የእነሱን ክርክር መዝኖ የመጨረሻውን ውሳኔ እንደሚሰጥ ለአዲስ አድማስ አስታውቀዋል፡፡
ማዕከላዊ ኮሚቴው በጠቅላላው ጉባኤው ሙሉ ውክልና ያለው እንደመሆኑ ጥፋት ያጠፉ አባላትን የማገድ ስልጣን አለው ያሉት አቶ ንጉሱ፤ ሰሞኑን እነ አቶ በረከትን ያገደውም በዚህ ስልጣኑ ነው ብለዋል፡፡
ጠቅላላ ጉባኤው በእነ አቶ በረከት ላይ በማዕከላዊ ኮሚቴው የተላለፈው ውሳኔ ስህተት ነው ካለ እግዱን ሊያነሳ ይችላል ያሉት አቶ ንጉሱ፤ እግዱ ትክክለኛ ነው ብሎ ካመነ ደግሞ ከድርጅቱ ሙሉ ለሙሉ የሚሰናበቱበት ሁኔታም ሊኖር እንደሚችል አስረድተዋል፡፡
ከፍተኛ አመራሮቹ የተላለፈባቸውን ውሳኔ አስመልክቶ በጉባኤው ፊት ቀርበው መከራከር እንደሚችሉም አቶ ንጉሡ የድርጅቱን መተዳደሪያ ደንብ ጠቅሰው ገልፀዋል፡፡
“ጠቅላላ ጉባኤው ከመካሄዱ በፊትም ቅሬታቸውን ለድርጅቱ ኦዲት እና ኢንስፔክሽን ማቅረብ ይችላሉ፤ ኦዲት እና ኢንስፔክሽን አመራሮቹ ላይ የተላለፈው ውሳኔ ተገቢ አይደለም ብሎ ካመነም ጉዳዩን ለጠቅላላ ጉባኤው ያቀርባል፤ ጠቅላላ ጉባኤውም በማዕከላዊ ኮሚቴው በተላለፈው እግድና በግለሰቦቹ ቅሬታ እንዲሁም በኦዲትና ኢንስፔክሽን ግኝት ላይ ተወያይቶ የመጨረሻውን ውሳኔ ያሳልፋል” ሲሉ አቶ ንጉሡ አብራርተዋል፡፡ በመስከረም ወር የሚካሄደው ጠቅላላ ጉባኤ፤ ምናልባት የማዕከላዊ ኮሚቴው ውሳኔ በቡድንተኝነት ያለ አግባብ የተወሰነ ነው ብሎ ካመነ፣ በተገላቢጦሽ ማዕከላዊ ኮሚቴውን ተጠያቂ ሊያደርግ የሚችልበት አግባብ እንዳለም አስረድተዋል፡፡
ባለፈው ሚያዚያ ወር አቶ ታደሰ ካሳ ከጥረት ኮርፖሬት ዋና ስራ አስፈፃሚነት በአስተዳደራዊ እርምጃ መነሳታቸው የሚታወስ ሲሆን የማዕከላዊ ኮሚቴው እገዳ ደግሞ ፖለቲካዊ መሆኑ ይታወቃል፡፡ በሌላ በኩል የህግ አካላት በታገዱት አመራሮች ላይ በቂ ማስረጃ ካገኙ ክስ ሊመሰርቱ እንደሚችሉም ተጠቁሟል፡፡
አቶ በረከት ስምኦን በብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ መታገዳቸውን ተከትሎ በተለያዩ ሚዲያዎች ላይ በሚሰጡት ቃለ ምልልስና ማስተባበያ፤ የማህበራዊ ሚዲያው መነጋገርያ ሆነው ሰንብተዋል፡፡ ከዚህ በኋላም አቶ በረከት በፖለቲካው እንደማይቀጥሉ መግለፃቸው ይታወቃል፡፡


Read 11460 times