Print this page
Saturday, 01 September 2018 15:09

የወልቃይት ማንነት ኮሚቴ ለጠ/ሚኒስትሩ አቤቱታ አቀረበ

Written by 
Rate this item
(3 votes)

   በወልቃይት ጠገዴ መከላከያ ሰራዊት ጣልቃ እንዲገባ ጠይቋል

      በወልቃይት ጠገዴ ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች እየተፈፀሙ ነው ያለው የወልቃይት ጠገዴ ህዝብ የአማራ ብሄርተኝነት አስመላሽ ኮሚቴ፤ በአካባቢው የፌደራል መንግስት ጣልቃ ገብቶ የመከላከያ ሰራዊት በማሰማራት መፍትሄ እንዲያበጅ ለጠቅላይ ሚኒስትር በፃፈው የአቤቱታ ደብዳቤ ጠይቋል፡፡
ኮሚቴው ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽ/ቤት ባስገባው የአቤቱታ ደብዳቤ፤ በወልቃይት ህዝብ ላይ በትግራይ ክልላዊ መንግስት የስነ ልቦና እና አካላዊ ጥቃቶች እየተፈፀመ ነው ብሏል፡፡
“አድርሽኝ” በሚባል የአካባቢው ባህላዊ በዓል ላይ “በአማርኛ ቋንቋ ዘፍናችኋል” የተባሉ 20 ያህል ሰዎች ድብደባ እንደተፈፀመባቸው፤ የጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ምስል የታተመበት ቲ-ሸርት የለበሱ ወጣቶችም አካላዊ ጥቃትና እስር እንዳጋጠማቸው የጠቀሰው ኮሚቴው፤ የወልቃይት የአማራ ብሔርተኝነት ጥያቄን የሚያነሱም እየታሰሩ ነው ብሏል ስማቸውን በመዘርዘር፡፡
“በወልቃይት ጠገዴ ህዝብ ላይ እየተፈፀመ ያለው ግፍ ከቀን ወደ ቀን እጅግ እየከበደ መጥቷል” ያለው ኮሚቴው፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለጉዳዩ አስቸኳይ እልባት እንዲያበጁ ጠይቋል፡፡
ከወልቃይት የማንነት ጥያቄ ጋር በተያያዘ በአካባቢው ታስረው የሚገኙ እንዲፈቱ፣ የሰብአዊ መብት ጥሰት የፈፀሙ አካላትም ለፍርድ እንዲቀርቡ በአቤቱታው ላይ ተጠይቋል፡፡
በአካባቢው ያለውን ስጋት ለመቀነስና ማህበረሰቡን ከጥቃት ለመከላከልም በአካባቢው የፌደራል ፖሊስና የመከላከያ ሠራዊት አባላት እንዲሰማሩ ኮሚቴው ጠይቋል፡፡    

Read 5471 times
Administrator

Latest from Administrator