Saturday, 25 August 2018 13:49

“አልበሜ ከአዲሱ ዓመት ተስፋና መነቃቃት ጋር ይጣጣማል”

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)


   ዝነኛው የሬጌ ስልት አቀንቃኝ ጃሉድ አወል፣ ሁለተኛ የዘፈን አልበሙን “ንጉሥ” በሚል መጠርያ ባለፈው ረቡዕ ለአድማጭ ጆሮ አድርሷል፡፡ 18 ዘፈኖችን ባካተተበት አዲስ አልበሙ፤ ያልዳሰሳቸው ርዕሰ ጉዳዮች የሉም፡፡ ስለ ፍቅር፣ ስለ ትብብር፣ስለ አንድነት፣ ስለ አባይ ወንዝ፣ ስለ ታላቁ ሩጫ፣ ወዘተ አቀንቅኗል፡፡ “ንጉሥ ያልኩት ፍቅርን ነው” ይላል - ድምፃዊው፡፡
ከ18ቱ ዘፈኖች 17ቱን ያቀናበረው ዕውቁ የሙዚቃ ባለሙያ ካሙዙ ካሳ፤ ለሙዚቃ ቅንብር ወሳኝ የሆኑትን ድምፅና ዜማ ጃሉድ በተሻለ ሁኔታ ይዞ በመቅረቡ በስራው ደስተኛ መሆኑን ተናግሯል፡፡
ላለፉት ሦስት ዓመታት አልበሙን ለውጤት ለማብቃት ሌት ተቀን ሲሰራ እንደነበር የሚገልጸው ፕሮዲዩሰሩ የአርዲ ሙዚቃ ዋና አዘጋጅ አይንአዲስ ተስፋዬ (ዲጄ ፒቹ)፤ አልበሙ እንዲሰራ ሀሳብ ከማመንጨት ጀምሮ እስኪጠናቀቅ 1.6 ሚ. ብር ማውጣቱን ጠቁሞ፤ አልበሙ የአድማጭን ጆሮ ሊገዙ የሚችሉ በርካታ አገራዊና ማህበራዊ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ የሚያጠነጥን በመሆኑ ተቀባይነትን እንደሚያገኝ ጥርጣሬ የለኝም ብሏል፡፡
የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ፤ በአዲሱ አልበሙ፣ በአዘፋፈን ስልቱ፣ በኮንሰርትና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ድምፃዊ ጃሉድ አወልን እንዲህ  አነጋግራዋለች፡፡

    የመጀመሪያው “ያቺ ነገር” ወይም “የገጠር ልጅ ነኝ” አልበምህ ከወጣ ከአምስት ዓመት በላይ ሆኖታል፡፡ ሁለተኛውን አልበም ለማውጣት ትንሽ አልዘገየህም?
እውነት ነው ትንሽ ዘግይቷል፡፡ የእኔ ፍላጎት ሁለተኛውም አልበም ቶሎ እንዲወጣ ነበር፡፡ ነገር ግን የወቅቱ የአገሪቱ ሁኔታ ትንሽ አስቸጋሪ ነበር። በዚህ ችግር መሃል እንዴት አልበም ይለቀቃል በሚል ይዘነው እንጂ አልበሙ አልቆ እጃችን ላይ ከደረሰ ቆይቷል፡፡
አሁንስ አልበሙን ለመልቀቅ ትክክለኛው ጊዜ ነው ብለህ ታስባለህ?
አዎ! ለእኔ ትክክለኛ ጊዜ ነው፡፡ አልበሙ በአገራዊ ጉዳዮች፣ በፍቅርና በትብብር ዙሪያ የሚያጠነጥኑ ዘፈኖች አሉት፡፡ አሁን ካለው አገራዊ መነቃቃት፣ ከመጪው አዲስ ዓመትና ተስፋ ጋር ይጣጣማል የሚል እምነት አለኝ፡፡
አልበምህ ባልተለመደ መልኩ ምናልባትም ሁለት አልበም ሊወጣው የሚችል 18 ዘፈኖችን ይዟል፡፡ ይህን ያደረግኸው ሆን ብለህ ነው?
አንደኛው ምክንያቴ፤ ለሙዚቃ ያለኝ ፍቅር ነው፡፡ ሁለተኛው ምክንያቴ፤ የተለመደውን 12 እና 13 ዘፈን ብቻ አካትቼ ሌላውን ብይዘው ምን አደርገዋለሁ? እኔ ጋ ተቀምጦ ምን ይሰራል፤ ሰው ቢያደምጠውና ቢያጣጥመው ይሻላል ብዬ፣ እንደውም ከ16 ወደ 18 ከፍ ያደረግኩትም እኔ ነኝ። ምክንያቴ ይሄው ነው፡፡
የአልበም ሥራ ተጀምሮ እስኪጠናቀቅ ድረስ ያለው ፈተና ምን ይመስላል?
ጓደኞቼም እንደሚያውቁት፣ እኔ፣ የሃሳብ የግጥምም ሆነ የዜማ ችግር የለብኝም፡፡ ለነዚህ ነገሮች ብዙ የተቸገርኩትና የደከምኩት በፊት ነው - እንደዚህ ልምዴ ባልዳበረበት ጊዜ፡፡ አንድን ሃሳብ አፍልቆ ወደ ግጥም ቀይሮና በዜማ ቀምሮ ወደ ህዝብ ለማቅረብ በጣም ይፈትነኝ የነበረው ከ10 ዓመት በፊት ነው። በተለይ የመጀመሪያው አልበሜና “የእርግብ አሞራ” የተሰኘው ነጠላ ዜማዬ ከተለቀቀ በኋላ በሀሳብም፣ በግጥምም ሆነ በዜማ በኩል ችግር የለብኝም፡፡
የ18ቱም ዘፈኖች ግጥምና ዜማ ደራሲ አንተው ነህ። ነገር ግን ሀሳብ በማዋጣት ደረጃ የተሳተፉ እንዳሉ ሰምቻለሁ፡፡ እውነት ነው?
እውነት ነው፡፡ ግጥምና ዜማዎቹን እኔው ነኝ የሰራሁት፡፡ ሀሳብ በማዋጣት በኩል ለምሳሌ “ሶምሶማ” የተሰኘው ዘፈን የፕሮዲዩሰሩ የአይንአዲስ ተስፋዬ (ዲጄ ፒቹ) ሀሳብ ነው፡፡ ለምን ለኃይሌ ገ/ሥላሴ አንድ ዘፈን አትጫወትም በሚል ሀሳቡን ሰጠኝ፡፡ ያንን ሀሳብ ወደ ግጥም ቀይሬ፣ ዜማ ሰርቼለት ጥሩ ተጫውቸዋለሁ። ዘፈኑ ራሱ ሬጌ ሶምሶማ ነው፡፡ ለረጅም ዓመታት በየዓመቱ ሳይቋረጥ የሚካሄደውን ታላቁ ሩጫን ልክ እንደ አንድ የህዝብ በዓል የማየት ነገርን ያመላክታል፡፡ ሀሳቡን ወደ ግጥምና ዜማ ለመለወጥ ትንሽ ፈትኖኛል፡፡ አንድ ሁለት ጊዜ አስቸግሮኝ፣ በሦስተኛው በሚፈለገው መጠን አመጣሁት፡፡
ብዙ ጊዜ ስለተለያዩ በዓላት ይዘፈናል፤ ነገር ግን ለበዓሉ ድምቀት ብዙ ስለሚለፋባት ዋዜማ ብዙ ትኩረት አይሰጥም፡፡ አንተ “ውቢቷ ዋዜማ” በሚል አቀንቅነሃል፡፡ ሃሳቡ እንዴት መጣልህ?
አንድ ትልቅ መዝገበ ቃላት አለ፡፡ አንድ ቀን ከጓደኛዬ ጋር ስናገላብጥ፤ ዋዜማ ማለት፡- ዜማ አዚም አቀንቅን ማለት ነው ይላል - ትርጓሜው። ይሄ ነገር ምንድን ነው ብዬ ነገሩ ላይ ትኩረት አደረግሁኝ፡፡ እንደገና በግዕዝ “ውዥም” እና “ውዥምዥም” የሚል አየሁኝ፡፡ አሁንም ግዕዙ ወደ አማርኛ ሲተረጎም፣ ውዥም ማለት፣ ያ አዚያሚው (የሚያዜመው) ሰው በዋዜማው ዕለት ተነስቶ ውዥም ሲል፤ “ውዥምዥም” ማለት ደግሞ ሰው ተነስቶ በተግባር ሲያዜምና ሲከውን ማለት ነው። ይህንን ካነበብኩ በኋላ ሀሳቡን ወደ ግጥም ቀይሬ “ውቢቷ ዋዜማ” የሚል ቆንጆ ዘፈን ሰርቻለሁ፡፡ መነሻዬ ግን ትልቁ መዝገበ ቃላት ነው፡፡ እና “ዋዜማ፤ ሀሳብሽ ከአቅሜ በላይ ስለሆነ ብዕር አነሳሁልሽ” ብሎ ነው ዘፈኑ የሚጀምረው፡፡
“ወዲያ ማዶ” የተሰኘው ዘፈንህ በአባይ ዙሪያ ያጠነጥናል፡፡ ለመሆኑ አባይን አይተኸው ታውቃለህ?
ውይይይ …. አባይን ካየሁት ማለትም ከተሻገርኩት በጣም ቆይቷል፡፡ ሁሉም እንደሚያውቀው፤ ዛሬ እዚህ አገር ከሆንኩ ትንሽ ቆይቼ የሆነ አገር እሄዳለሁ። እርግጥ ነው ወለጋን፣ ጎጃምን የዛሬ 20 ዓመት አካባቢ አውቃቸዋለሁ፡፡ አባይ ሸለቆን (ድልድይን) ስሻገር አይቸዋለሁ፣ ነገር ግን አባይን ለማየት ብዬ ቆሜ አይቼው አላውቅም። አሁን አባይ ላይ ህዝቡ የሚያደርገውና የሚሆነው ሁኔታ፣ እኔን የሚያሳትፍ ነው፡፡ አባይ ከኢትዮጵያ ተነስቶ፣ ሄዶ … ሄዶ ግብፅ ብዙ ስራ ይሰራል፡፡ ስለዚህ የግብፅ አርቲስቶች በአባይ ጉዳይ ላይ ብቻ ከመቶ ሺህ በላይ ዘፈኖች አላቸው፡፡ ምክንያቱም ህይወታቸው ነው፡፡ አንድ የግብፅ ዘፋኝ፣ ዘፈን ሲያወጣ፣ የግድ አንድ ዘፈን ስለ አባይ ይኖረዋል። እኛ ጋ ይሄ ብዙ ትኩረት አልተሰጠውም፤ ተዘፍኖም ከሆነ በጣም በጥቂት ዘፋኞች ብቻ ነው። ስለዚህ የእኛ አገር አርቲስቶች በዚህ ላይ ትኩረት ሰጥተው፣ አንድ አልበም ሲያወጡ፤ ስለ አባይ አንድ ዘፈን ጠብ ቢል ትልቅ ነገር ነው፡፡ ትልቅ ሀብታችን ታሪካችንም ነውና። ይህን አስቤ ነው “ወዲያ ማዶ”ን የሰራሁት፡፡ ያለፈው አልፏል፤ ወደፊት አልበም ስሰራ ስለ አባይ በተለያዩ ጭብጦች ላይ አንድ አንድ ዘፈን አካትታለሁ፡፡
“ንጉሥ” የተሰኘው የአልበምህ መጠሪያ ዘፈን፣ ስለ ኢትዮጵያዊነት፣ ስለ ህብረትና ስለ ፍቅር የሚሰብክ ነው፡፡ ነገር ግን አልበሙ ተሰርቶ ያለቀው ከአራት ወራት በፊት ነው፡፡ ከአራት ወራት ወዲህ ደግሞ በአገራችን የተለያዩ ለውጦች ተከስተዋል፡፡ ከአራት ወራት በፊት መታተሙ አሁን ባለው ወቅታዊ ጉዳይ ላይ ያለህን ስሜት ለማንፀባረቅ እድል አልነፈገህም?
ሁሉም የሚለው ይህንኑ ጉዳይ ነው፡፡ ነገር ግን አሁን አገራችን ላይ ለመጣው አዲስ አካሄድ፣ የእኔ አልበም ውበት ይሆነዋል ብዬ ነው የማምነው፡፡
በምን መልኩ ነው ውበት የሚሆነው?
ጥሩ! እንዴት መሰለሽ … እንዳልሽው አልበሙ ካለቀ ቆይቷል፡፡ ግማሾቹ ዘፈኖች የመጀመሪያውን አልበሜን እየሰራሁና ከመስራቴ በፊትም የተሰሩ ናቸው፡፡ ካሙዙ ነው “የጫካው” እና “ጎጃም ጎጃም” የተሰኙትን ዘፈኖቼን፣ አሁን ካላወጣኋቸው ዋጋ የላቸውም ያለኝ፡፡ ተፅፈው ከተቀመጡ ግን በጣም ቆይተዋል፡፡ ፕሮዲዪሰሩ አይናዲስ (ዲጄ ፒቹ) ደግሞ “በል አለችኝ”  የተሰኘውን ዘፈን እንዳካትት ጠየቀኝ። “በል አለችኝ” የመጀመሪያውን አልበሜን ባወጣሁ በወሩ ነው የሰራሁት፤ አምስት ዓመት አልፎታል። ነገር ግን በዚያ ጊዜ እነዚህን ዘፈኖች የሰራኋቸው፣ አገሬ እንድትሆንልኝ የምፈልገውን ህልሜን ነው፡፡ ስለ አንድነት፣ ስለ ህብረት፣ ስለ ፍቅር የሚሰብኩ ናቸው። አሁን የሚቀነቀነው ፍቅር፣ አንድነት፣ መደመርና ይቅር መባባል ነው። እኔ ይህንን ቀድሜ ተመኝቼ ነበር። አልበሜ ለወቅቱ አካሄድ ጌጥ ይሆነዋል የምለው ለዚህ ነው። ለምሳሌ የአልበሜ መጠሪያ “ንጉሥ” የሚለው ፍቅርን ነው፡፡ ለዚህ ዘፈን ንጉሥ የተባለው ፍቅር ነው፡፡ “በል አለችኝ”፤ ኢትዮጵያ እኔ ውስጥ ገብታ መልዕክቷን እንዳስተላልፍላት የላከችኝ አይነት ውክልና አለው። ኢትዮጵያ እኔ ውስጥ ሆና ልጆቿን ትወቅሳለችም ታመሰግናለችም፡፡ በጣም ደስ የሚል ዘፈን ነው፡፡ መቼም ለእኔ ደስ ሲለኝ ነው ሌላውን ደስ የሚያሰኘው።
የወቅቱን የለውጥ ነፋስ፣ እንደ አርቲስት እንዴት ታየዋለህ?
የወቅቱ ሁኔታ ለእኔ ተመችቶኛል፡፡ ከበፊቱ የተሻሉ ሁኔታዎችንና መነቃቃቶችን እያየሁ ነው። ለውጥ የሚባለውንም ሂደት በደንብ ማጤንና ማየት ያስፈልጋል፡፡ በቀጣይ በአገሪቱ ላይ የሚከሰቱ ሂደቶች ይኖራሉ፡፡ ያን ጊዜ በህዝቡ መሃል መዘዋወር፣ የህዝቡን ስሜት ማድመጥ፣ በተግባር ነገሮች ሲከሰቱ ማየት ብዙ ሀሳቦችን ያመጣል፡፡ ያን ጊዜ እኔም ለመፃፍና አልበም ለማዘጋጀት እንቀሳቀሳለሁ፡፡ በአልበም ደረጃ እንኳን ባይሳካልኝ ወይ በነጠላ ዜማ አሊያም ሀሳቤን ወደ ግጥምና ዜማ ቀይሬ፣ ለሌላ ዘፋኝ በመስጠት እተነፍሳለሁ፡፡
ከአዲሱ አልበምህ ምን ትጠብቃለህ? የመጀመሪያ አልበምህን ያህል ተወዳጅ የሚሆን ይመስልሃል?
በደንብ ተቀባይነት ያገኛል፤ አልጠራጠርም፡፡ በመጀመሪያ ሥራው ተጠናቅቆ ለህዝብ መቅረቡ ትልቅ እፎይታን ሰጥቶኛል፡፡ ምክንያቱም ሀሳብ ወደ ተግባርና ወደ ውጤት ሲቀየር ደስ ይላል፡፡ ብዙ እውቀትና ሀሳብ በእጃቸው እያለ መተግበር ላይ አቅም የሚያጡ አሉ፡፡ ይሄ ዋጋ የለውም፡፡ እኔ ይህንን ተገላግያለሁ። በመደመጡ በኩል ከበፊቱ የተሻለ እጠብቃለሁ፡፡ ስራውም ከፍ ባለ ሁኔታ ነው የተሰራው፡፡
ምንም እንኳን በአብዛኛው የሬጌ ስልት አቀንቃኝ ብትሆንም ሌሎች ስልቶችንም ትቀላቅላለህ፡፡ በአዲሱ አልበም ምን አይነት ስልቶችን አካትተሃል? የአማርኛ ዘዬን ቀየር አድርገህ የምትዘፍነውስ?
አሉ! ከዚህ በፊት እንደውም “ባቲ ባቲ” የሚል አክሰንቱን ቀየር አድርጌ የሰራሁት ነበር፡፡ አሁን አዲሱ፤ ከባቲ ባቲ በጣም የተለየና የተሻለ ሆኖ ተሰርቷል፡፡ ከልምድ መዳበር የተነሳ የአዘፋፈን ስልቱ በጣም በጥራት ነው የተሰራው፡፡ “አንቺ ልጅ ነይማ” እንደተሰኘው የበፊት ዘፈኔ፣ በቺክቺካ ስልት የተሰራ ዘፈንም አለኝ፡፡ ሌላው ግን ሬጌ ስልት ነው፡፡
ከአልበም በኋላ የአገር ውስጥና የውጭ አገራት ኮንሰርት ማቅረብ የተለመደ ነው፡፡ በዚህ በኩል ምን አቅደሃል?
አሁን ከአልበሙ መለቀቅ በኋላ ከቡድኔ ጋር ጥናት እጀምራለሁ፡፡ ምክንያቱም ወደፊት ለምናስበው ቱርም ሆነ የአገር ውስጥ ኮንሰርት ከቡድኔ ጋር በጣም መለማመድና መስራት አለብኝ፡፡ ሳውንድ ኢንጂነር ተዘጋጅቷል፡፡ የባንድ መሪ አለን፡፡ ይሄ በውጭው ዓለም የሚታየው፣ ፕሮፌሽናል የሆነው ነገር … እኛም በዚያ ደረጃ ለመስራት አቅደናል፡፡ በጥቂቱ ለሦስት ወራት ልምምድ ካደረግን በኋላ ነው ኮንሰርቱን የምናስበው፡፡
ከየትኛው ባንድ ጋር ነው ልምምድ የምታደርገው?
በቅርቡ ከጓደኞቼ ጋር “ጎቲክ” የሚባል የሙዚቃ ባንድ ልንመሰርት ነው፡፡ አልበማችን ላይ “ጎቲክ” የሚል ዘፈን አለ፡፡ ባንዱ የሚመሰረተው በዚህ ዘፈን ስም ነው፡፡
“ጎቲክ” ማለት ምን ማለት ነው?
ቅድም የነገርኩሽ መዝገበ ቃላት ላይ ነው ያየሁት። ይገርምሻል … የፊደላት ጌጣጌጥ ማለት ነው፡፡ ጎቲክ የውጭ ቃል ነው ሲሉኝ፣ ኧረ ባካችሁ የግዕዝ ቃል ነው፤ ትርጓሜውም የፊደላት ጌጣጌጥ ማለት ነው ብዬ አስረዳኋቸው፡፡
“ጎቲክ” የተባለው ዘፈንህ ምን ሃሳብ ነው የሚያስተላልፈው?
እኔ ጎቲክን የሰራሁት የመጀመሪያዋን ፊደል “ሀ”ን የፈጠረው ሰውዬ ገርሞኝ ነው፡፡ ፊደል ደርድሮ ሀሁ ብሎ ያስተማረን ሰው ሌላ ነው፡፡ ፊደሎቹን በቅርፅ በቅርፅ አድርጎ ፈጥሮ የቀረፀው የድሮው የጥንቱ ሰው ይገርመኛል፡፡ ስሙንም አላውቀው በታሪክም አልተዘገበም፤ ነገር ግን ራሱን እያስተማረ፣ ሌሎችን ያስተማረ ደሞም አስተማሪ መሆኑን ሳያውቅ ያለፈ ሰው ይመስለኛል። ስለዚህ ጎቲኩን አውጥቼ፣ ማስታወሻነቱን ለእሱ አድርጌ፤ ነገር ግን ጎቲክ የእኛ መሆኑንም የሚያስታውስ፣የፊደል ጣሪያውን ጥንታዊ ሰው ያመሰገንኩበት ዘፈን ነው፡፡ ቃሉን ስለወደድኩትም የምመሰርተውን ባንድ ልሰይምበት ነው፡፡
ባለፉት ዓመታት በአገሪቱ አለመረጋጋት በመፈጠሩና የቅጅ መብት ባለመከበሩ የሙዚቃው ዘርፍ መነቃቃት አላሳየም፡፡ አልበምህ ደግሞ 1.6 ሚ. ብር ወጥቶበታል፡፡ እንዴት ደፈራችሁ?
ምን ችግር አለ ብሩ ቢወጣበት? ለሌላስ ነገር ብር ይወጣ የለ እንዴ! እንኳን ለሙዚቃ! ምን ነካሽ ሰዎች 3 ሚ. ብር እያወጡ፣ ነገ ከሌላ መኪና ጋር የሚያጋጭ መኪና እየገዙ አይደል እንዴ? እግዚአብሔር ከፈቀደ ደግሞ የላባችን ውጤት የትም አይሄድም፤ ለፍተን ደክመን ጥራቱን ጠብቀን ነዋ የሰራነው፡፡ ዋናው አምነሽበት መስራት ነው፤ የማይተማመኑበት ነገር የትም አይደርስም፡፡
የቅጅ መብቱን በተመለከተ እኔ ህዝቡን አምነዋለሁ፤ የእኔን ስራ በህገ ወጥ መንገድ አይነኩብኝም፡፡ ምናልባት ሲዲውን ለማግኘት ጓጉተው ሲዲውን ካላጡት በስተቀር ሲዲው እያላቸው አይነኩብኝም። ከዚህ በፊት ናዝሬት፣ ሀዋሳና ሻሸመኔ አካባቢ ሲዲው አልደረሰንም ብለው፣ በንዴት ኮፒ አድርገው አዳመጡት። ከዚያ በኋላ “ሲዲው ስላልደረሰን ኮፒ አድርገናል፤ ይቅርታ አድርግልን” ብለው ይቅርታ ጠይቀውኛል፡፡
ታዲያ አሁን ከፕሮዲዩሰሮቹ ጋር በዚህ ረገድ ያደረጋችሁት ዝግጅት ምን ይመስላል? ምን ያህል  ሲዲ ነው የታተመው?
በዚህ ረገድ ፕሮዲዩሰሮቹ በደንብ ተዘጋጅተዋል። ይሄን ስራ በዋናነት የሚያውቁት እነሱ ቢሆኑም እኔም የምችለውን አግዛቸዋለሁ። በአሁን ሰዓት 50ሺህ ሲዲ ታትሟል፡፡ ከዚያ በተረፈ የታተመው ቶሎ ካለቀ፣ ሲዲ የሚያትመው ኩባንያ ዘመናዊና ደረጃውን የጠበቀ ስለሆነ በቀን ከ25-50 ሺህ የማተም አቅም አለው። “ቲካብ” ይባላል፡፡ በድሮው ላስታ ሳውንድ አባላትና በሌሎች የተቋቋመ አዲስና ዘመናዊ ሲዲ አታሚ ነው፡፡
በሚፈለግበት ጊዜ በፍጥነት አትሞ የማስረከብ አቅም አለው፡፡ በተረፈ በደንብ ተለማምደንና ተዘጋጅተን ሲዲው ላይ የሚሰማውን ድምፅና የሙዚቃ መሳሪያ አይነት ስራ በኮንሰርቶች ላይ እናቀርባለን፡፡ ከዚያ በፊት ህዝቤ አድናቂዬ፤ ኦሪጂናሉን ሲዲ በመግዛት፣ በተለያየ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ያጠነጠነውን አልበሜን እንዲያዳምጥ ግብዣ አቀርባለሁ፡፡ አመሰግናለሁ!!

Read 1018 times