Saturday, 25 August 2018 13:03

በሀሳብ መንገድ ላይ

Written by  ተመስገን
Rate this item
(3 votes)


       “መደመር ማወቅ የሚሆነው፤ መደመር ነፃነት የሚሆነው፤ መደመር ፍትሃዊ የሚሆነው … እያንዳንዳችን ሃላፊነት ስንወስድና ስንተጋገዝ ብቻ ነው፡፡”
      
     የሼሪያ ህግ በሚተገበርባት አንዲት ሃገር ውስጥ ነው። ሰውየው  የመንግሥት ሚስጢር አውጥቷል በሚል ሰበብ ባልሰራው ወንጀል ፍርድ ቤት ቆመ። አንገቱ እንዲቀላ ተፈረደበት፡፡ እጆቹ የኋሊት ተጠፍረው ወደ መቁረጫው ቀረበ። ንጉሡና ባለስልጣናቱ ፍርዱ ሲፈፀም ለማየት በቦታው ነበሩ፡፡ በህገ ልማዱ መሠረት ፍርደኛው መናገር የሚፈልገው ነገር እንዳለ ሲጠየቅ…ራሱን ነቀነቀ።… “አልፈልግም” በሚል ስሜት፡፡ …በዚህን ጊዜ ንጉሡ ለቅጣት አስፈፃሚው ሰው ምልክት አሳየና ፍርደኛው ከፊቱ ቀረበ፡፡ ንጉሡም ለትንሽ ጊዜ ሲያስተውለው ቆይቶ…
“ካሁን ቀደም ያየሁህ ይመስለኛል፣ የምታስታውሰው ነገር አለ?” ሲል ፍርደኛውን ጠየቀ፡፡
“አዎን ንጉሥ ሆይ”  መለሰ ፍርደኛው፡፡
“የት?”
 “እዚሁ ቦታ፡፡ ዛሬ ተራው የኔ ከመሆኑ በፊት የሌሎችን አንገት የምቆርጠው እኔ ነበርኩ”
ንጉሡም እንዳስታወሰው ጭንቅላቱን እያወዛወዘ…
“ራስህ ፍርድ አስፈጻሚ ሆነህ እንዴት ታጠፋለህ?” ሲል ጠየቀው፡፡
ፍርደኛውም፤ “ንጉሥ ሆይ፤ በሰው ልጆች ታሪክ ውስጥ ያልተደገመ ስህተት ያውቃሉ?” በማለት ጥያቄውን በጥያቄ መለሰ፡፡… ንጉሡ ማሰብ ጀመረ።.. ከቃየል ጀምሮ ይኸው እስካሁን ድረስ ወንድም ወንድሙን ይገድላል፣ ውሸት ከመደጋገሙ የተነሳ የእውነትን ቦታ ተክቷል፣ ስርቆት ባህል ሆኗል፣ የክህደት ድግግሞሽ በህግ እንኳ ሊገታ አልቻለም፡፡… ታዲያ ያልተደገመ ስህተት ምንድን ነው?... ለንጉሡ ሊገለፅለት አልቻለም፡፡… ቢቸግረው እንዲህ ሲል ጠየቀው፤
“አንተ የምታውቀው ያልተደገመ ስህተት አለ?”
ፍርደኛውም፤ “አዎ አውቃለሁ” አለው፡፡… ምን ይሆን?
* * *
ድርጊት የሀሳብ መጨረሻ ነው ይባላል፡፡ ጥያቄው፡- ድርጊቱን የፈፀምነው በነፃ ፈቃደኝነት ነው? ...ወይስ በሌሎች ተፅዕኖና ፍራቻ ተገደን? ወይስ በጥቅም ተደልለን? ወይስ…በምክኒያታዊነት? እያለ ይቀጥላል፡፡
ወዳጄ፡- አንድን ነገር ለማድረግ ከመወሰናችን ወይም ከመናገራችን በፊት ያለንበትን የስሜት ዝንባሌ አውቀን መገራት ያለበትን መግራትና እራሳችንን ማቀዝቀዝ ስንችል ነው… ድርጊታችን “በነፃ ፈቃድ ላይ የተፈፀመ” የሚባለው፡፡ ምክንያታዊነት… እራስን ከማወቅና ሌሎችን ከመረዳት የሚመነጭ፣ ማንኛውም ድርጊት ለራሳችንም ሆነ ለሌሎች ሊያስገኝ የሚችለውን ማህበራዊ፣ ግላዊና መንፈሳዊ ጥቅም ወይም ጉዳት አስቀድሞ ማሰብ መቻል ነው፡፡
በኑሮ ልማዳችን “አንዴ ከመናገር ሁለት ጊዜ አስብ፣ ታሞ ከመማቀቅ አስቀድሞ መጠንቀቅ፣ አንዴ ለመቁረጥ አስር ጊዜ ለካ ወዘተ” መባሉ በራሳችን ያለንን እምነት አስተማማኝና ምክንያታዊ ስለሚያደርግልን ነው። ተጠንቅቀን፣ አስበን፣ ለክተን ያደረግነው ነገር ቢሳሳት እንኳ በስሜታዊነትና በውጫዊ ሃይል ተፅዕኖ ያላደረግነው ስለሆነ ይጠቅመናል፡፡ “የስህተቱን ልክ ያወቀ እንደታረመ ይቆጠራል፡፡” እንደሚባለው፡፡
“ክፍያው ውድ ቢሆንም… ልምድ ጥሩ ት/ቤት ነው። (Experience is a good school although the fee is high)”… ይላሉ ሊቃውንት።
ወዳጄ፡- ለምንፈፅማቸው ማንኛውም ድርጊቶች ሃላፊነት መውሰድ እንዳለብን ማወቅ አለብን፡፡ ደጋግመን እያጠፋን “አላወቅኩም ተሳስቻለሁ” ማለት ማምለጫ ሊሆን አይገባም። ህጋዊ መሠረት ስለሌለውም ከተጠያቂነት አያድንም፡፡ የዲተርምኒዝምና የሌላኛው ገፁ ኤግዚስተንሺያሊዝም ፍልስፍና በዋናነት የሚያስተምረን… ለጥፋታችን ሃላፊነት መውሰድ ተገቢ መሆኑን ነው፡፡ አጉል ባህላችንንና የተተበተቡ ኋላ ቀር ልማዶቻችንን ሽፋን እያደረግን፣ ጥፋትን በሌለና ሃላፊነት መውሰድ በማይችል ነገር (አላወቅኩም፣ ሰይጣን አሳስቶኝ እንደምንለው) ማሳበብ ትልቁ የዕድገት እንቅፋት ነው ይላሉ፡፡
ወዳጄ፡- “እምነት የነፍስ ምስክር ሲሆን አለማመን ደግሞ የሱ ተቃራኒ ነው፡፡ (Belief consists in accepting the affirmations of the soul; unbelief in denying them)” የሚለን ታላቁ ኤመርሰን ነው። ጥፋቱ የራሳችን መሆኑን ሆዳችን እያወቀ በማይሆን ነገር ማሳበብ (Blame shifting) ህሊናን እንደ መካድ ይቆጠራል ማለቱ ነው፡፡ ህሊናን መካድ ደግሞ ራስን መካድ ነው፡፡ ራስን መካድ ጥፋት መፈፀም ሳይሆን ጥፋት ራሱን መሆን ወይም እግዜር ራሱን መግደል ነው፡፡
* * *
ወደ ተረታችን ስንመለስ፡- ንጉሡ፤ … ፍርደኛውን “ያልተደገመ ስህተት ታውቃለህ ወይ?” በማለት ሲጠይቀው፤ “አዎን” ብሎት ነበር።
“ምንድን ነው?” ሲለው..
“ንጉሥ ሆይ፤ የመጀመሪያው ስህተት እውነትን መፈለግ ነበር” መለሰ ፍርደኛው፡፡
“ማለት?”
“የእግዜርን ሚስጢር ማወቅ፣ ከተከለከለው የዕውቀት ዛፍ ፍሬ መብላት… ማለቴ ነው፡፡”
ንጉሡ፤ ባለሟሎቹና ዕድምተኞቹ እርስ በእርስ መተያየት ጀመሩ፡፡ ትንፍሽ የሚል አልተገኘም፡፡ ከጥቂት ደቂቃዎች ፀጥታ በሁዋላ ንጉሡ…
“ማወቅ ስህተት የሆነው ከጥንት ጀምሮ ነው። እስከ ዛሬ ድረስ ግን እንደ ሌሎቹ ስህተቶቻችን ባህል አልሆነም እያልከን ነው?” ብሎ ጠየቀው
“በሚገባ እንጂ” …አለ ፍርደኛው፡፡
“እንዴት እርግጠኛ ሆንክ?” አለ ንጉሡ፤ በድፍረቱ እየተደነቀና እየሳቀ፡፡
“ምክንያቱም በማወቁ ሰው ከገነት ተባረረ፡፡ ፀጋው ተገፈፈ፡፡ ማወቅን ፈራ፣ መጠየቅን ሸሸ፤ “ለምን?” ማለት ጭንቅ ሆነበት፡፡ በተሰሩ ሃሳቦች መደለብ ጀመረ፡፡ ከዚህ ሁሉ በላይ ጥፋቱን መሸክምና ሃላፊነት መውሰድ ሲገባው በሌሎች ያላክካል፡፡” ሲል ተናገረ ፍርደኛው፡፡
ንጉሡ ለአፍታ ሲያሰላስል ከቆየ በሁዋላ፡-
“ልቀቁት!” በማለት አዘዘ፡፡… አዳም የሰራው ስህተት ተደገመ፡፡ ኢ-ፍትሃዊነት ላይ ነቃ!
ወዳጄ፡- ወደኛ ጉዳይ ስንመጣ አንድ ነገር ልብ በልልኝ፡፡ መደመር ማወቅ የሚሆነው፤ መደመር ነፃነት የሚሆነው፤ መደመር ፍትሃዊ የሚሆነው … እያንዳንዳችን ሃላፊነት ስንወስድና ስንተጋገዝ ብቻ ነው፡፡ “ሃምሳ ሎሚ ለአንድ ሰው ሸክሙ…ለሃምሳ ሰው ጌጡ” እንዲሉ!!
“When a person is down in the world, an ounce of help is better than a pound of Preaching” በማለት የሚመክረን… ማን ይመስልሃል? እኔ ታላቁ ቡልዌር ነው ባይ ነኝ፡፡
ሠላም!!

Read 1093 times