Saturday, 25 August 2018 13:43

“ቾ” መንፈሳዊው - (ምናባዊ ወግ)

Written by  ሌሊሣ ግርማ
Rate this item
(1 Vote)

ስካር ከሰው ሰው ይለያያል፡፡ ቢለያይም “ሆድ ያባውን ብቅል ያወጣዋል” የሚለው ምሳሌ በጥቅሉ ይገልፀዋል፡፡ ሳይሰክር ትዕግሥተኛ የነበረውን ትዕግስቱን አሳጥቶ ግልፍተኛ ሊያደርገው ይችላል። መጠጥ “tone” ነው የሚጨምረው። ወሬ ወዳጁን ያስጮኸዋል፡፡ ፈገግ ባዩን በሳቅ ያንፈራፍረዋል። ብሶተኛውን ያስለቅሰዋል፡፡ ውዝዋዜ ወዳጁን ያስጨፍረዋል፡፡
ስካር ከሰው ሰው ይለያያል፡፡ የቾምቤ ግን ከሰውም ይለያል፡፡ ከቁሳቁስ ዓለም ጋር የነበረውን የአዘቦቱን ቀን ትውውቅ ያስረሳዋል፡፡ ወይንም በአዲስ መልክ ያስተዋውቀዋል፡፡ በእርግጥ ድሮውንም የቁስ ዓለምን በጥርጣሬ የሚያይ ነበር። መጠጥ ማዘውተር ሲጀምር ግን ጥርጣሬው ወደ ተቃውሞ ተቀየረ፡፡ መጠጥ ሰውን ያሳድባል … ወይንም ያደባድባል፡፡ ቾ’ን አመናፈሰው፡፡ መንፈሳዊ አደረገው፡፡
መንፈሳዊ ያደረገው የሚመስለን የተወሰንን ጓደኞቹ ነን፡፡ የተቀሩት “መጠጥ አሳብዶታል” የሚሉ ናቸው። መቶ ብር ለሁለት ቀዶ፣ አንዱን ለጀብሎ፣ ሌላውን ለለማኝ መስጠት … ለነገሩ ምን ይባላል? መንፈሳዊ እብደት ነው፡፡ ኢ - ቁሳዊ እብደት ነው፡፡ ቁስ እንዴት መካፈል እንዳለበት አለማወቅ ንቀትም እብደትም ነው። ዘርዝሮ ማካፈል ሲችል ቁሱን በመንፈሳዊ መንገድ ቆርጦ እነሆ አላቸው፡፡ ጠቢቡ ሰለሞን … በአንድ ህፃን እናትነት ተካሰው የመጡትን ሴቶች፣ ህፃኑን በጎራዴ ቆርጦ እንደ ብርቱካን ለማካፈል እንደፈለገው፡፡
ግን ሁላችንም መጠጣት በምንፈልግበት ቀን ቾምቤን አፈላልገን ከጎናችን እናደርጋለን። እንጋብዘዋለን፡፡ በተመላሽም ብዙ ጨዋታ፣ አንዳንዴም ተግባር እናያለን፡፡ ነገም በጤነኛው ቀናችን መልሰን ብናወራው የሚያስደስተን ተግባር በቾምቤ ይበረከትልናል፡፡
በቀደም በረንዳ ላይ ተሰብስበን ስንጠጣ ሳንጠራው፣ ራሱ መጣ፡፡ መንገዱን እንደ ወንዝ በጥንቃቄ ተሻገረ፡፡ ከዚህ ቀደም መንገዱን እንደ ሀሳብ ለመሻገር ሞክሮ፣ አንድ መኪና ትንሽ ገፍቶት ፊቱ አብጦ ነበር፡፡ ሁለት የፊት ጥርሱን ያጣው ከዚያ በኋላ ነው፡፡ ከዚያ በኋላ ሳይሆን አይቀርም መንገድን እንደ ወንዝ መሻገር የጀመረው፡፡ ወንዙ መሀል ላይ ሲደርስ እንደ ዐይነ ስውር ሆነ … አንዳችን ተነስተን እጁን ይዘን አሻገርነው፡፡
ምን ያህል እንደሰከረ በንግግሩ ወይንም በጠባዩ አይታወቅም፡፡ ከቁሳቁስ ዓለም ጋር በሚያደርገው ግጭት ብቻ ነው ስካሩን ለተመልካች ማስገመት የሚችለው፡፡ እሱ የተሻገረው መንገድ ላይ አንድ ሰውዬ በብዙ ተመልካች ተከቦ የእንጨት መቀመጫና ረከቦት እየገጣጠመ ነው፡፡ እንጨቶቹን አስቆርጦ አዘጋጅቶ ነው የሚመጣው። ከዚህ በፊትም ይሄንኑ ትዕይንት እዚሁ ቦታ ሲያከናውን በተደጋጋሚ አይተነዋል፡፡ ሰው ከቦ እንዲመለከት ያደረገው መስህብ፣ በእግሩ መዶሻ አንስቶ ሲጠቀም ከእጅ ባለሞያ በምንም ረገድ የማያንስ የመሆኑ ጉዳይ ነው፡፡
ቾምቤን ከዚህ በፊት ሰውዬው ላይ ምን አስተያየት አለህ ብለን ጠይቀነው … ምንም የተለየ ነገር ማጣቱን መስክሮልናል፡፡ በእጅና በእግር መሀል ምንም ልዩነት አይታየውም፡፡ የእሱ ስካር ጥሩነት ታዲያ ይሄ አይደል?! … ልዩ ነገሮች ተለይተው አይታዩትም፡፡ “ፎቁ ፊትለፊት” ብለህ ቦታ ከምትጠቁመው፣ “ቁሻሻ መጣያው አጠገብ” ብትለው በቀላሉ ይለየዋል፡፡ ምክኒያቱን ሲያስረዳ፡- “ቁሻሻ መጣያው ይሸታል … የሚሸት ነገርን ባትፈልግም ማየትህ አይቀርም … ፎቅ አይሸትም … በዚያ ላይ ከተማው በአንድ ዓይነት ፎቅ የተሞላ ነው” ብሎናል፡፡
ለሴቶችም፣ ለመኪኖችም፣ ለምሁሮችም … ተመሳሳይ መለኪያ ሊያወጣ ይችላል ሲሰክር። መስከር የጀመረው ከቁስ ጋር ያለው ትስስር የጨቆነው ስለሚመስለው ነው፡፡ በተለይ ለእኔ ይመስለኛል፡፡ የቁሶች ትርጉም በባህልና የስምምነት ህግ የተመሰረቱ መሆናቸው የእሱን ነፃነት ይነፍጉታል፡፡ ነፃነቱን መነገፉን መጠጥ ከጠጣ በኋላ ይወቀው አሊያም መጠጥ የሚጠጣው ስላወቀና ነፃ ለመውጣት የሚያደርገው ሙከራ ነው የሚለው ያከራክራል፡፡
የቁስን የተደመደመ ብያኔ ለመቃረን ሲል ሰካራም ሆነ፡፡ ተቃርኖው ከጊዜና ቦታ ትርጉም ጋር ነው። የታጠረ አጥርን ዞሮ ወደሚፈልግበት ከመሄድ፣ አጥሩን ዘሎ ገብቶ፣ በሰው ግቢ ውስጥ ውሻ እየነከሰው ማቋረጥ ይመርጣል፡፡ ሲሰክር የሰው የታጠረ ግቢ፤ እንደ ሰው ንብረት ሳይሆን በሰው እንደታነፀ ሰው ሰራሽ ኮረብታ ሊታየው ይችላል፡፡ የቁስ አካልን ህግ መተላለፍ ግን ብዙ ጣጣ አለው፡፡ ሌባ ሊያስብለው ይችላል፡፡ ደግነቱ እስካሁን በሰው ግቢ ዘሎ ሲያቋርጥ አልተያዘም። መንገድ ማቋረጥና የሰው ግቢ ማቋረጥ ለእሱ አንድ ናቸው፡፡ መንገዱም የመኪና፣ ግቢውም የሚጮሁት ውሾች አይደለም፡፡ መኪናውም ገጭቶ ጥርሱን አረገፈው … ውሾቹም በተደጋጋሚ ነከሱት፡፡ ለምን እንደሚነክሱት ሲሰክር ይረሳል። የቁስ አለሙ ህግ፤ በንክሻ በድጋሚ እንዳይረሳ ያስታውሰዋል፡፡ ሲነከስ … ያነክሳል፡፡ .. ሲሰክር ማነከሱንም መነከሱንም ይረሳዋል።
ብዙ ገድሎች አሉት፡፡ አንዳንዶቹን እኛም አብረነው ሆነን እማኝ ነበርን፤ ሌሎቹ በሰው ሲወሩ ወይ እሱ ሲያወራ የሰማናቸው ናቸው፡፡ … መሳሪያ የታጠቀ ፌደራልን “ሲጋራ ለኩስልኝ” ማለቱን ሲወራ እሱ ራሱ ሰምቶ … የሌላ ሰው ተግባር መስሎት ሲደነቅ ነበር። .. የጊዜና የቦታ ልኮች እንዲምታታበት፣ ትዝታዎቹ እንዲምታቱ ሆን ብሎ የሚጥር ይመስለኛል አንዳንዴ። … ጥረቱ ይሳካለታል፡፡ ራሱ ያከናወነውን ገድል መልሰው ሲነግሩት፣ እንደ አዲስ አርዓያ ያገኘ ይመስላል፡፡ ተደምሞ … “እኔም እንደሱ ማድረግ ነው ፍላጎቴ” ሲል ይደመጣል፡፡ … የራሱን ገድል ከሌላ እንደተማረው አድርጎ ይቀበለውና በድጋሚ ያከናውነዋል፡፡
ፌደራል ፖሊሱን ሲጋራ እንዲለኩስለት የጠየቀው በክላሹ ነው፡፡ የፖሊስን ትርጉም በምንነት መለኪያ ወደ ጀብሎ … መሳሪያውን ደግሞ ወደ ላይተር ቀይሮታል፡፡ በመቀየሩ ከፖሊሱ የደረሰበት ዱላ ቀላል አልነበረም። ፖሊሱ ለራሱ የሰጠው የምንነት ትርጉም በሰካራሙ ቾምቤ ግንዛቤን አላገኘለትም፡፡ ግንዛቤ እንዲያገኝ ጥሩ አድርጎ በዱላ መትቶታል፡፡ በዱላ እየመታው ሳለ እየሳቀ ባያስቸግረው … ጣቢያ ይወስደው ነበር። በመሳቁ እብድ መስሎት ለቀቀው፡፡ ለምን ሳቅህ ብሎ ሲጠይቀው፣ “እየኮረኮረኝ” ብሎ መልሷል አሉ። የፖሊስ ዱላ መኮርኮሪያ ላባ ነው፡፡ ሲኮረኮር ደም በደም የሚያደርግ ላባ!
ተመትቶ አያለቅስም፡፡ አውቆ አይደለም። እርግጠኛ ነኝ ማልቀስ ይፈልጋል፡፡ መጠጥ ሲጠጣ መሳቅ ፈልጎ ከሆነ ያለቅሳል፡፡ ወይንም የተገላቢጦሽ። … የሆነ ጊዜ መጠጥ አይቀምስም ነበር፡፡ አሁን ሰካራም ሆኗል፡፡ የሆነ ጊዜ አስተማሪ ነበር፡፡ አሁን አውደልዳይ ሆኗል። የሆነ ጊዜ ሚስትና ልጅ ነበረው፡፡ አሁን የለውም፡፡ የነበሩትን ነገሮች “የት አደረስካቸው?” ተብሎ ከተጠየቀ ግራ ግብት ይለዋል፡፡ … የሆኑ ቁሶችና ቁስ መሸመቻ የሚሆኑ ማዕረጎች … ክብሮች ነበሩት፡፡ … እሱም አይክድም እንደነበሩት፡፡ … እሱ የማያውቀው፤ የነበሩት ነገሮች አሁን የት እንደገቡበት ነው፡፡ … ሀሳብ ወደ ቁስ እንዴት እንደሚቀየር ወይንም ቁስ መልሶ ትዝታ እንደሚሆን አያውቅም፡፡
ልክ እንደ ፊት ጥርሱ ነው፡፡ የሆነ ጊዜ ጥርስ እንደነበረው የሚያውቁ፣ በክፍት ድዱ ሲስቅ ጥርሱ የት እንደሄደ ይጠይቁታል፡፡ “እኔ’ንጃ ጠዋት ስነቃ የለም” ብሎ በጣቱ የድዱን ክፍተት ይነካካዋል፡፡ … በፊት እሱ የት እንደገቡ የረሳቸው ብዙ ነገሮች ነበሩት፡፡ መፅሐፍ በጣም ያነብ ነበር። በኋላ ማንበብ አቃተው። ያነበበውንም ረሳው፡፡ መፅሐፍ አዟሪ ሲያይ ይጠራና መፅሐፍ ተቀብሎ ልክ እንደ ትንግርት ያገላብጠዋል። ልክ ከዚህ በፊት ይዞት እንደማያውቅ እቃ ነው የሚያገላብጠው፡፡ እንደ ሽጉጥ ወይንም እንደ ድሪል ወይንም …፡፡
እና ብዙ ነገር ነበረው፡፡ ሚስት ነበረው፣ ቤት ነበረው፣ ልጅ ነበረው፣ መኪና ነበረው፣ እውቀት ነበረው፣ የፊት ጥርስ ነበረው፡፡ በተጨባጩ የቁስ ዓለም ላይ ያደላደለው ስፍራ ነበረው፡፡ … አሁን ምንም የለውም፡፡ ለየት ያለ ስካር ብቻ ነው ያለው። ስካሩ ትዝታውንና  የቁስ ዓለም አስተማማኝ መሳይ ህግን እንዲሽር ያደርገዋል፡፡
መንገዱን ተሻግሮ በወንበሩ ፋንታ መሬት ላይ ተቀመጠ፡፡ ከመንገዱ ባሻገር በእግሩ መዶሻ ጨብጦ ሚስማር የሚመታው ሰውዬ የሚያፈልቀው ድምፅ አለ፡፡ መሬቱ ላይ  ቁጢጥ ብሎ በጣም በረጋ መንፈስ በመንገዱ ላይ የሚያልፉና የሚያገድሙትን ይመለከታል፡፡ ሁልጊዜ በመንገድ የሚያልፉ ሰዎች በድንጋጤ ቆም ብለው አይተውት ያልፋሉ፡፡ ለእነሱ እንደሚታዩት አይደለም ራሱንም ሆነ እነሱን የሚያየው፡፡ ከፎቅ የመጡ .. ፎቅ ውስጥ የሚሰሩ … ትንንሽ ፎቅ የመሳሰሉ ሰዎች ናቸው፡፡ … እሱን ሳይሆን እኛን ስለሱ ይጠይቁናል፡፡ ምን ያህል እሱ የደረሰበት ደረጃ መድረስ እንደሚያስፈራቸው ግልፅ ነው፡፡ ለእሱ የሚያዝኑት እንደሱ እንዳይሆኑ ለመለመን ነው፡፡ የሚለምኑት የቁስ አለሙን አምላክ ነው። ልብስ መኪና … የፎቅ ላይ ስራና የቪላ ቤት ሚስት … እና በሞግዚት የሚያዝ ልጅ የሰጣቸውን አምላክ፡፡ ለቾምቤ ብር አስጨብጠውት ይሄዳሉ። እንደጨበጠው ይቀራል። እንደጨበጠው ይተኛል፡፡ ብልጦቹ ሌላ የሚጨበጥ ነገር በተለይ ብርጭቆ ሰጥተው ይቀበሉታል፡፡ በአደራ ያስቀምጡለታል፡፡ እሱ የረሳውን የቁስ ጥቅም ቢሞቱ እንኳን የማይረሱ ነጋዴዎች በዙሪያው አይጠፉም፡፡
ከመኪና ወርደው እሱ የተቀመጠበት ወለል ደረጃ ዝቅ ብለው የሚያወሩት አሉ፡፡ ብዙዎቹን ኮሌጅ አስተምሯቸዋል፡፡ እነሱ እንዲወጣጡ ያስያዛቸውን መሰላል እሱ ለቋል፡፡ መሰላሉ ላይ ሆነው ቁልቁል ያዝኑለታል፡፡
“ዋናው የህይወት ግብ ራስን ማክበር ነው” ይል ነበር፡፡ መጠጥ መጠጣት የጀመረ ሰሞን፡፡ ጥርሱን ከማጣቱና የቁስ አካል ህጉን ሙሉ ለሙሉ ከመተላለፉ በፊት፡፡ ምን ማለቱ እንደሆነ ሲጠየቅ፤ መጀመሪያ ላይ በደንብ ዘርዝሮ ያስረዳ ነበር፡፡ በኋላ መፈክሯ ብቻ ቀረች፡፡ “ራስን ማክበር ምን ማለት ነው?” ሲባል፤ “እኔ ምን አውቄ” ብሎ ግራ ወደ መጋባት በሂደት ከፍ አለ፡፡
መሬት ተቀምጦ ቆይቶ … ቀጣይ የመጠጥ ቀጠሮው ወደ ጠራው የአረቄ መፍለቂያ ያዘግማል፡፡ ጊዜ ቀስ ብሎ የሚሄድ የሚመስለው ካለ፣ ቾምቤን ይመልከት። እሱ ላይ በተከሰተው ለውጥ ለሚቆጥር ሰዓት ወር፣ የግማሽ ቀን ፍጥነት ነው ያለው፡፡ ጥቁር ፀጉሩ ሸበተ። … መንጋጋው ተዛነፈ፡፡ ትከሻው ጎበጠ፡፡ መቀመጥ እያቃተው በየጥጉ መጋደም ጀመረ፡፡ ድሮ ገድለ ብዙ በነበረ ጊዜ የምንከበው እኛም እየራቅነው መጣን። … ስሙን ጠርተን በተጋደመበት ስናልፍ፣ መሞት አለመሞቱን እናረጋግጣለን፡፡ … ምግብ ማቆሙን ማንም አላወቀም፡፡ … እኛም አልጠየቅነውም፡፡
በፊት አብሮን በሚጠጣ ሰሞን አስማት የሚችል ሰው ያስደስተው ነበር…፡፡ ምናምን ደብቆ … ምናምን ባልተጠበቀ በኩል ብቅ የሚያደርግ ሰው፡፡ … ከመሀላችን አንዱ ልጅ በተለይ እንደዚያ ዓይነት ተሰጥኦ ነበረው። … ከመሬት ትንሽ ከፍ ብሎ የመንሳፈፍ ትዕይንት ሁሉ ይሞክር ነበር። “አስትራል ትራቭል” ምናምን የሚል ዲስኩር የሚያበዛ ልጅ ነው አስማተኛው፡፡ …. ቾምቤ በአጭር ቆይታ አስማት ሰለቸው፡፡ በአየር ላይ ሳንቲም የሚያንሳፍፍ የነበረው ልጅ፣ ትዕይንቱን እያሳየ ቾ አዛጋ፡፡ አስማተኛው ልጅ እንዴት ቀልቡ እንደተገፈፈ አትጠይቁኝ፡፡ ቀልቡ ለካ በቾምቤ መገረም ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ ቾምቤ አስማቱን መከታተል ሲሰለቸው፣ አስማተኛው ተሰጥኦው እንቢ አለው፡፡
“አንተ ከመሬት ተነስተህ ከምትንሳፈፈው የበለጠ ይሄ ድንጋይ መሬት ላይ መቀመጡ ነው የሚገርመኝ። አንድ ቦታ በትዕግሥት መቀመጥ በጣም የሚገርም አስማት ነው፡፡” ማለት ጀመረ፡፡
ሊሞት እንደሆነ ሁላችንም አውቀናል፡፡ ግን ምንም ልናደርግለት የምንችለው ነገር አልነበረም። ሊሞት ሲል ተደበቀ፡፡ ሞቱን እያማጠ፡፡ ልክ ሊላቀቅ ሲል ተመልሶ ወደ ጎዳናው ብቅ አለ። ወደ ሞት የሚሄድ ሳይሆን ከሞት የተነሳና ለማረግ የተዘጋጀ መንፈስ ነበር የሚመስለው፡፡ ጥርሱ መውለቁን የሚያስረሳ ውብ ፈገግታ በፊቱ ላይ ይመላለሳል፡፡ ከጥርስ ውበት ሳይሆን ከነፍስ የመነጨ ፈገግታ፡፡ ቁስ አካል ያልገባበት ፈገግታ። የተሻለው ሁሉ መሰለን፡፡ ወደ ኋላ ሊመለስ ሁሉ መሰለን፡፡ አብሮን ተቀምጦ አወጋ፡፡ አንደበቱም ተፍታትቷል፡፡ ሲያነብ የቆየ ነበር የሚመስለው፡፡ የሚናገረው ንግግር አንድም ማስመሰል የለበትም። ፍላጎት የለበትም፡፡ ተቀባይ የማግኘት ሙከራ ፍፁም አይታይበትም፡፡ እውነትን እንደ ታሸገ ሳይነፍስበት ቀስ ብሎ ያከፋፍል ጀመር፡፡ … ለእኛ በጣም የተጨነቀ ይመስላል፡፡ ይመስላል ሳይሆን በእርግጥም ተጨንቋል፡፡ እኛ ደግሞ ለእሱ የተጨነቅን ለመምሰል ብዙ ደሰኮርን፡፡ መምሰል እና መሆን፤ የህይወት እና የሞትን ያህል ልዩነት ነው ያላቸው፡፡
“ዋናው የህይወት ግብ ራስን ማክበር ነው!” አለ። በዚያ አዝማች ግን አልቀረም፡፡ ሙሉ ኮንቸርቶውን ዝግ ብሎ ከአንድ ሙቭመንት ወደ ሌላው እየተሸጋገረ ሙዚቃ በሚመስል የአንደበት ፍሰት ተጠበበው፡፡
ከሚስቱና ልጁ ሞት ተነስቶ … ቀስ በቀስ ሁሉንም ነገር እንዳጣ በመተረክ የሀዘን እንጉርጉሮውን ከዝግታ ጀምሮ … ቀስ በቀስ ጥርሱን ሲያጣ፣ ነፍሱንና አቅጣጫውን እንዴት እንዳገኘ … የህይወት ትርጉም ምን ማለት እንደሆነ እንደገባው … በስካር ውስጥ የሁሉም ነገር እውነተኛ ትርጉም እንደተፈታለት፣ ከራሱ ጋር ሰላም እንደፈጠረ ነው … ከአንደበቱ የሚንፎለፎለው ረቂቅ ሙዚቃ የሚናገረው፡፡
…እየተሰናበተን እንደሆነ አላወቅንም፡፡ እንደ ፊኒክስ ላባውን ቀይሮ ወደ ድሮው ማንነቱ በአዲስ ድል አድራጊነት ሊነሳ ነበር የመሰለን፡፡ ማንም ሰው የሚመስለው የሚፈልገውን ነው፡፡ እኛ የፈለግነው ለውጥ ቾ’ም የሚፈልገው መስሎን ነበር፡፡ ከመምሰልም በላይ እርግጠኛ ሆነን ነበር። ዓመቱ መጀመሪያ ላይ የድሮውን የአስተማሪነቱን ስራ እንደሚጀምር እርግጠኛ ነበርን፡፡ ሁሉም በሚፈልገው እምነት ላይ እርግጠኛ ነው፡፡
ቀጥሎ የሰማነው ሞቶ መገኘቱን ነበር፡፡ ውስጣችን የሚያውቀውን ነገር ለመቀበል ብዙ አለቀስን፡፡ ደነገጥን፡፡ ለወደፊቱ የቾምቤ ህይወት የደለደልነውን ብር ወደ ታች መቃብር ለመቆፈሪያ አዋልነው፡፡ ተስፋም ሆነ ትዝታ በማያስፈልገው የአፈር ጊዜ ነጥብ ላይ እረፍት ያጣውን አካሉን … እረፍት ካገኘው ነፍሱ ጋር አዳበልነው፡፡        

Read 1944 times