Print this page
Saturday, 25 August 2018 13:45

በረከት በትንሳዔ መጣ

Written by  ተፈሪ መኮንን
Rate this item
(6 votes)

 ርዕስ፤ ‹‹ትንሳዔ - ዘኢትዮጵያ -ከመንታ መንገድ››
(ከተመጽዋችነት ወደ አፍሪካዊ ኩራት የተደረገ ሽግግር መጻዒ ፈተናዎች እና መልካም ዕድሎች)
ደራሲ፤ በረከት ስምዖን
የሕትመት ዘመን፤ ሚያዚያ 2010
ገጽ፤ 423
ዋጋ፤ 300 ብር
የበረከት ስምዖንን ሁለተኛ መጽሐፍ አነበብኩት። በዚህ ጽሑፌ አንተ እያልኩ በመጥቀሴ አንባቢን ይቅርታ እጠይቃለሁ፡፡  እንደ ተለመደው ደራሲን ‹‹አንቱ›› ማለት ወግ አይደለም ብዬ ነው፡፡ ‹‹ትንሳዔ - ዘኢትዮጵያ -ከመንታ መንገድ››  ሊነበብ የሚገባው መጽሐፍ ነው፡፡ ግን ጊዜ ተቸግሮ ለማንበብ ላልቻለ ሰው፤ አንድ ነገር ልመክረው እችላለሁ፡፡ የፍራንክ ሲናትራን ‹‹I did it my way››ን ቢያዳምጥ የመጽሐፉን መንፈስ ሊያገኘው ይችላል፡፡ እጁ ላይ ያለውን ስልክ ነካክቶ፤ ከአንዱ ድር-አምባ የፍራንክ ሲናትራን ዘፈን ቢሰማ፤ ‹‹ትንሳዔ››ን በእንግሊዝ አፍ፤ በፍራንክ ሲናትራ ውብ ድምጽ ሊቀነቀን መስማት ይችላል፡፡
ዘፈኑ ያለፈውን ነገር ለመዳኘት የሚሞክር ሰውን ስሜት ያንጸባርቃል፡፡ ፍራንክ ሲናትራ ልክ እንደ ሙሐሙድ አህመድ ‹‹ስንቱን አሳለፍኩት፤ ስንቱን አየሁት›› ይላል፡፡ ግን እንደሱ አይቆዝምም፡፡ ራሮታዊም አይደለም፡፡ ይልቅስ፤ መለስ ብሎ ያደረገውን ሲያየው፤ አንዳንዴ በሰራው ነገር ይደነቃል፡፡ የሰራውን ነገር በራሱ መንገድ በመስራቱ ይደሰታል፡፡ የሰራውን ነገር እርግጡን ይናገራል፡፡ ‹‹ትግል ጉዞው የመጨረሻ ምዕራፍ ተቃርቧል፡፡ የአብዮቱ መጋረጃ ይታየኛል፡፡ ወንድሜ ሆይ፤ በግልጽ እነግርሃለሁ፡፡ እርግጠኛ የሆነ ሐሳቤን አመለክትሃለሁ›› የሚል ይመስላል -እንደ ፍራንክ ሲናትራ፡፡ ልዩነታቸው፤ ሲናትራ በትናንቱ ብቻ ያተኩራል፡፡ በረከት ትናንቱን እያነሳ፤ ነገን ለመቀረጽ ይጣጣራል፡፡
ፍራንክ ሲናትራም እንደ በረከት ‹‹እንዳያልፉት የለም›› በሚያሰኙ፣ ሐዘንን በሚያጭሩ እና በሚስቆጩ ክስተቶች ውስጥ አልፏል፡፡ የዘፈኑን ግጥም በዝርው ወደ አማርኛ ስመልሰው፤ ‹‹በሁነት የታጨቀ ህይወት ነው የኖርኩት፤ ብዙ ውጣውረድ አሳልፊያለሁ፤ ግን ከሁሉ በላይ የሰራሁትን ነገር በራሴ መንገድ ሰርቸዋለሁ፡፡ ፀፀት፤ አዎ ትንሽ የሚፀጽተኝ ነገር አለ። ግን እርሱን ለወሬ የሚበቃ አድርጌ አልወስደውም። መስራት ያለብኝ ነገር ሰርቻለሁ፡፡ የሰራሁትንም ነገር አንድ ሳልተው መዝኘዋለሁ፡፡ አዎ፤ አንዳንድ ጊዜያት ነበሩ፤ ሁላችሁም በገዛ ራሳችሁ ህይወት የምታውቋቸው፤ አንዳንዴ ማኘክ ከምችለው በላይ የሆነ ጉርሻ አነሳና፤ ድንገት በህሊናዬ የሆነ ጥርጣሬ ሽው ሲልብኝ፤ የጠቀለልኩትን ዝም ብዬ እጎርሰውና፤ ደግሞ መልሼ አተፋዋለሁ፤ ሁሉንም ነገር እጋፈጠዋለሁ፤ ሸብረክ ሳልል እቆማለሁ፤ ሁሉንም ነገር በራሴ መንገድ ሰርቸዋለሁ፤ አፍቅሬአለሁ፤ ከልቤም ስቄአለሁ፤ ደግሞም አልቅሻለሁ፤ መሸነፍንም በደንብ አውቀዋለሁ፤ ሰውን ሰው የሚያሰኘው ምንድነው፤ ሰው ራሱን ካልሆነ፤ አለሁ ማለት የቻለው በምንድን ነው፤ ሰው ራሱን ካልሆነ ምን ሊሆን ነው፤ በእውነት ስሜቱን ደፍሮ ካልተናገረ፤ በተንበረከከ ሰው ቃል ሳይሆን፤ በድፍረት ካልተናገረ፤ እንዴት ሆኖ ሰው ተባለ፤ እውነቱን ተናግሬ ከመሸበት ማደር እንጂ እኔ ሌላ ታሪክ የለኝም፤ በቃ የሰራሁትን ነገር በራሴ መንገድ ሰርቸዋለሁ›› እያለ ይዘፍናል፡፡ እንግሊዝኛውን ጥቂት ተመልከቱት፡፡
I’ve lived a life that’s full
I’ve traveled each and every highway
But more, much more than this
I did it my way
Regrets, I’ve had a few
But then again, too few to mention
I did what I had to doAnd saw it through
without exemption
Yes, there were times, I’m sure you knew
When I bit off more than I could chew
But through it all, when there
was doubtI ate it up and spit it out
I faced it all and I stood tall
And did it my way
For what is a man, what has he got
If not himself, then he has naught
To say the things he truly feels
And not the words of one who kneels
The record shows I took the blows
And did it my way
Yes, it was my way
በረከትም ‹‹I did it the EPRDF’s way›› እያለ፤ እንደ ፍራንክ ሲናትራ የሚያዜም ይመስላል፡፡
‹‹ትንሳዔ - ዘኢትዮጵያ -ከመንታ መንገድ›› (ከዚህ በኋላ በአጭሩ ‹‹ትንሳዔ›› በሚል እጠቅሰዋለሁ)፤ የበረከት ሁለተኛ መጽሐፍ ነው፡፡ ስለዚህ በረከት በድርሰቱ ዓለም ወንበር መያዙን አረጋገጠ ማለት ነው። አሁን በሁለቱ መጽሐፎች መካከል ንጽጽር በማድረግ ስለደራሲው ማውራት የምንችልበት አንድ ተጨማሪ የሂስ በር ተከፍቶልናል፡፡ ግን በሩ ቢከፈትም፤ አሁን ንጽጽር ለመስራት አልችልም፡፡ ያለው ቦታ እና ጊዜ የሚያዝናና ባለመሆኑ ብቻ አይደለም፡፡ ንጽጽር፤ ‹‹ትንሳዔ››ን ከማንበብ የበዛ ሥራ የሚጠይቅ በመሆኑም ነው፡፡
ሆኖም ሥራ የማይጠይቅ ንጽጽር አድርጌ ማለፍ እችላለሁ፡፡ ደራሲው ከ‹‹የሁለት ምርጫዎች ወግ›› እስከ ‹‹ትንሳዔ -ዘኢትዮጵያ›› እንደኛ እንደ አንባቢዎቹ በዕድሜ ስድስት ዓመት ጨምሯል፡፡ የአጻጻፍ ዘይቤውም ተቀይሯል፡፡ ‹‹ትንሳዔ›› የጥናት ሥራ መስሏል፡፡ ደራሲው ‹‹ትንሳዔ››ን ሲጽፍ ከሥልጣን ራቅ ብሏል፡፡ ሥራው የጥናት ሥራ ቅርጽ ይዟል፡፡ 114 የሚሆኑ ዋቤ መጻህፍት እና ‹‹ማስታወሻዎችን›› (End note) አክሏል፡፡ የመጀመሪያው መፅሐፉ፤ ወደ ውጭ ሲያተኩር፤ ሁለተኛው ወደ ውስጥ ይመለከታል፡፡ ስለዚህ፤ በረከት ወደ ውስጥ የሚሰነዘርን ሂስ በውጭ መድረክ (በመጽሐፍ) ሲጽፍ የምናይበት ሥራ ነው። የትኩረት ዘመኑም ሰፍቷል፡፡ ‹‹የሁለት ምርጫዎች ወግ›› የትኩረት ዘመን 15 ዓመት (በዋናነት 5) ነበር። የ‹‹ትንሳዔ›› የትኩረት ዘመን 50 (በዋናነት 30) ዓመት ሆኗል፡፡ ‹‹በተለይ ከ1980 ዓ.ም ወዲህ ያሉትን የለውጥ እና የትግል ሂደት ይዳስሳል፡፡ ከዚህ በመነሳት የወደፊቱን ዕድላችንን የሚወስኑ መሠረታዊ ጉዳየችን ያመላክታል፡፡›› የአጻጻፍ ዘይቤውም ከ‹‹ወግ›› ወደ ‹‹ሐቲት›› ተሸጋግሯል፡፡ እንዲያ እንጂ ነው፡፡
መቼም የማቀርበው ሂስ አይደለም፡፡ የአንባቢ ችኩል አስተያየት እንጂ፡፡ ስለዚህ ከሽፋን ገጹ እንጀምር። የሽፋን ገጽ ስዕሉ፤ የሕትመት ሥራውን ጥራት ቀድሞ ይናገራል፡፡ የሽፋኑ ስዕል ሊናገር የሚፈልገው ቁም ነገር እንዳለው ያስታውቃል፡፡ ግን መልዕክቱን ለመግለጽ መሞከር ቱልቱላ ያስብለኛል፡፡ እሱን ስዕል አዋቂ ይናገረው፡፡ ግን በመንገደኛ አስተያየት ገና ቅርጽ ያልያዘች ሐገር መሆኗን የሚያመለክት ይመስለኛል፡፡
አቶ በረከት የመጽሐፉን መታሰቢያነት፤ ‹‹የተገለጠ መጽሐፍ›› ለሚላቸው እና ‹‹ሐገሪቱ ካሸለበችበት እንድትነቃ›› ማድረግ ችለዋል በሚል ለሚያመሰግናቸው ለአቶ መለስ ዜናዊ፤ እንዲሁም ‹‹በሒስ ውስጥ መኖርን አስተማርከኝ›› በሚል ለሚዘክረው እና በኢህአፓ አባልነቱ ህዝባዊ ተልዕኮ ለመፈጸም ጎጃም ውስጥ ሲንቀሳቀስ ተይዞ በደርግ ለተገደለው በሪሁን ዳኘው (ጋንች)፤ በመጨረሻም ‹‹የትግል እና የመስዋዕትነት ትውልድ›› ለሚለው የ1960 እና 70ዎቹ ትውልድ አባላት አድርጓል፡፡  
ከዚህ ቀጥሎ የሚመጣው የመጽሐፉ መግቢያ ነው። አቶ በረከት ስንዱ መግቢያ ጽፏል፡፡ መግቢያው መልክዐ ድርሰቱን ያሳየናል፡፡ ደራሲው ስለመጽሐፉ አደረጃጀት ሲናገር፤ ሐቲቱን በምን መንፈስ ለማቅረብ እንደፈለገም አመልክቶናል፡፡ መግቢያው የትረካውን ድምጸት ለመደንገግ ይሞክራል፡፡ በሦስት ክፍል የሚያቀርበውን ሐተታ በአጭሩ ያሳየናል፡፡ ስለደራሲው ሰብእናም ፍንጭ የሚሰጡ ሐሳቦችንም አትሞበታል፡፡
‹‹የሐገራችን ሁኔታ ለማንም እረፍት ከሚሰጥበት ደረጃ አልደረሰም›› (መግቢያ፣ I) የሚለው በረከት፤ ‹‹መሻሻል ቢኖርም … ወደ ላይ በተነሳን ቁጥር፤ እንደገና ወደ አዲስ እና ሌላ የተሳሰበ ሁኔታ ውስጥ መግባታችን ስለማይቀር … ከአንድ አስተማማኝ እና የማይቀለበስ የእድገት ምዕራፍ ውስጥ እስከምንገባ ድረስ …እፎይታ በሚነሳ አገር ውስጥ እንኖራለን›› (ዝኒ ከማሁ) ይላል፡፡
በረከት፤ እንስሳትን፣ ጤፍ እና ስንዴን ካለመዱት፤ የኢትዮጵያ ጥንታዊ ስልጣኔዎች መሐንዲሶች ከሆኑት ጀምሮ ባለፉት አርባ ዓመታት በኢህአዴግ መሪነት የተካሄደውን የለውጥ ሂደት የመሩትን ጨምሮ በሺህ ዘመናት የለውጥ ጉዞ ያለፉትን ሁሉንም ትውልዶች ያመሰግናል፡፡ ‹‹ይህ መጽሐፍ በአንድ እና ሁለት ትውልድ፤ የለውጥ ሥራዎች ላይ ያተኮረው፤ ለውጡን ያመጣው እና የጨረሰው ይኸው ትውልድ ስለሆነ ብቻ አይደለም፡፡ [ይልቅስ] በዚህ ትውልድ አባልነቴ የኖርኩትን፣ በቅርብ የማውቀውን እና የተሳተፍኩበትን ሂደት በገባኝ መልክ ለማበርከት ያክል ብቻ ነው›› (መግቢያ፣ II) ይላል፡፡
በኢህአዴግ መሪነት የተካሄደው የለውጥ እንቅስቃሴ ‹‹በጥልቅ ፍልስፍናዊ እሳቤዎች ላይ የተመሠረተ›› መሆኑን የሚገልጸው በረከት፤ ‹‹ለውጥ መስራት እንጂ ታሪከ ማውራት የማይቀናው›› የሚለው ይህ ትውልድ ብዙ ያልተጻፈለት መሆኑን ጠቅሶ፤ ‹‹…ይህ ትውልድ አገሪቱ ለሩብ ምዕተ ዓመት የዘለቀ እና ያልተቋረጠ ዕድገት እንድታስመዘግብ አድርጓል›› (መግቢያ፣ II) ይላል፡፡
በረከት ኢትዮጵያን ‹‹እጅግ የሚያስጎመዥ እና የሚያሳሳ፤ እንዲሁም በጣም የሚያሳስብ እና የሚያስፈራ ሁኔታዎች ተዳብሎ የሚገኝባት ሐገር›› ይላታል፡፡ ከመንታ መንገድ የቆመች የሚላትን ኢትዮጵያ ሁኔታ ሲያብራራ፤ ‹‹ፈረንጆች የመልካም ዕድል መስኮቶች የሚሏቸው አብዛኛውን ጊዜ ጠበብ ብለው የሚከፈቱ …እና በጥንቃቄ፣ በብስለት እና በብቃት ካልተጠቀሙባቸው በስተቀር በላቀ ፍጥነት ሊዘጉ የሚችሉና አንዴ ከተዘጉ ደግሞ እንደገና እስኪከፈቱ ድረስ ሌላ ዘመን ሊጠይቁ የሚችሉ ናቸው›› ካለ በኋላ ‹‹…መለስ ‹ከጫካው ገና አልወጣንም› (We are yet not out of the woods) በማለት ደጋግሞ ይገልጸው እንደ ነበረው፤ በኢትዮጵያ የመልካም ዕድል መስኮቶቹ የተከፈቱት በጅምር ደረጃ ብቻ ነው›› (መግቢያ፣ III) ይላል፡፡
ስለሆነም ባሉት የመልካም ዕድል መስኮቶች እየተጠቀሙ፤ አዳዲስ መስኮቶችን በብዛት መክፈት እንደሚያስፈልግ ጠቅሶ፤ ‹‹የመልካም ዕድል መስኮቶችን የሚያጠቡትን የመልካም አስተዳደር እጦት፣ ሙስና፣ በትንሽ ድል የመኩራራት እና ለችግሮች ደንታ ቢስ የመሆን፣ እንዲሁም በብሔርተኝነት ጭምብል ያለአንዳች ተጠያቂነት ያሻህን የመስራት አዝማሚያዎችን በጥብቅ ማስወገድ ይጠይቃል›› (መግቢያ፣ III) ይላል፡፡
ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው፤ መጽሐፉ በሦስት ክፍል የተደራጀ ሲሆን፤ በዘመን ከታየ፤ ክፍል አንድ ከ1980 እስከ 1993 ዓ.ም፤ ክፍል ሁለት ከ1993 እስከ 2004 ዓ.ም፤ ክፍል ሦስት ከ2004 እስከ 2008 ድረስ ባሉ ዓመታት የተከናወኑ ጉዳዮችን የሚመለከትበት ነው፡፡
አቶ በረከት በመግቢያው ያነሳው አንድ ጠቃሚ ነጥብ አለ፡፡ በመጨረሻው ክፍል የቀረቡት ሐሳቦች፤ ‹‹በመስከረም 2010 ዓ.ም ከኃላፊነት ለመገለል ጥያቄ ካቀረብኩ በኋላ የተለወጠና አዲስ ነገር በመኖሩ የቀረቡ አይደሉም›› ብሎ፤ ‹‹ይልቁንም ከሚሌኒየም  አከባበር ማግስት ጀምሮ በመንግስት እና በድርጅት ኃላፊዎች [ዘንድ] በድል የመኩራራት ዝንባሌ መከሰት እንደጀመረ በመታዘብ ያቀረብኳቸው ናቸው›› (መግቢያ፣ V) ይላል፡፡
‹‹ትንሳዔ›› በረከት በራሱ ድርጅት ላይ የሰነዘረውን ሂስ የምናነብበት ሥራ ነው፡፡ እናም በመግቢያው እንዲህ ይላል፤ ‹‹በየመድረኩ እንደ ተቀናቃኝ  ሳይሆን እንደ ሐሳብ ቋት (Resource Person) እንድታይ ያቀረብኩት ተማጽኖ በተደፈኑ ጆሮዎች ላይ መውደቁን እያረጋገጥኩ መጣሁ፡፡ ውስጣችንን በውል ለማያውቁ የውጭ ታዛቢዎች ስርዓቱን ከኋላ ሆነን የምናሽከረክረው እኛ ተደርገን የምንታይ ቢሆንም፤ ተመካክሮ መስራት በሌለበትና መገለል በበዛበት ሁኔታ ስያሜው ተሰጠን፡፡››
እናም ‹‹የውስጥ መድረከች ሲከሽፉ እና ተደማጭነት በሌለባቸው ጠባብ መድረኮች በሐሳብ የመግጠም ዕድል እያነሰ ሲሄድ፤ ትክክልም ይሁን ስህተት በውስጤ ያሉትን ሐሳቦች በመጽሐፍ መልክ አሳትሞ ሁሉም እንዲያውቃቸው ማድረግን የተሻለ አማራጭ ሆኖ አገኘሁት›› ይላል። ከዚያም በመጽሐፉ በተገለፁት ስኬቶች እንደሚኮራ ሁሉ፤ በድክመቶቹም ኃላፊነት እና ተጠያቂነትን በጋራ እንደሚወስድ ገልፆ፤ ‹‹በግሌ ትልልቅ ስህተቶች ከመፈጸም ተቆጥቤ እንደኖርኩ ህሊናዬ ይነግረኛል›› የሚለው በረከት፤
‹‹አንድም አሟልቶ ባለመታገል፤ አለያም ወደ ኋላ በመሰላቸት…በጠቃሚ ጉዳዮች ላይ ከፊል ወይም ሙሉ ዝምታን በመረጥንበት ጊዜ ሁሉ የፈራነው ደርሷልና በዚህ መጽሐፍ የማነሳቸው ድክመቶች ሆኑ ጥንካሬዎች በአንድ ወይም በሌላ ምክንያት እኔንም ይመለከታሉ›› (መግቢያ፣ VI) ብሏል፡፡
በረከት፤ አግባብ ሆኖ በተገኘበት አጋጣሚ የአንዳንድ ግለሰቦችን እና ተቋማትን ድክመት በሥም እየጠቀሰ ያቀረበ መሆኑን ይገልጻል፡፡ አያይዞም፤ ይህን ያደረግኩት ‹‹ከግለሰቦቹ ወይም ተቋሞቹ ጋር ባለኝ ግላዊ ፍቅር ወይም ጥላቻ ሳይሆን …ለወደፊቱ ትምህርት እንዲወሰድባቸው በማመን …ህገ መንግስታዊው የግልጽነት እና ተጠያቂነት አሠራር እየሸሸን ባለበት በዚህ ወቅት ተገቢውን ድፍረት በማሳየት ወደ ግልጽነት እና ተጠያቂነት አሠራር ስርዓት ለመመለስ እንድንችል የተመረጠ አቀራረብ ነው፡፡ …ዛሬን ብቻ እያሰቡ ህይወታቸውን ያለ ትህትና ለሚኖሩ እና ለሚመሩ ሰዎች ሁሉ የፍርድ ቀን እዚሁ ምድር ላይ እንደሚጀምር ለማስገንዘብም ጭምር ነው፡፡ አለዚያማ ግለሰቦች የአገር መነጋገሪያ ርዕሰ ጉዳይ መሆናቸውን ከእኔ በላይ ማን ሊጠላ ይችል ኖሯል›› (መግቢያ፣ VII) ይላል፡፡
በረከት ዓይን ገላጭ መረጃዎችን እና ትንታኔዎችን ከማቅረቡ በላይ መጽሐፉ ተነባቢ እንዲሆን አስመስጋኝ ጥረት አድርጓል፡፡ በመጽሐፉ፤ አቶ መለስ ‹‹ለኤርትራ መሬት ሰጥተን ሰላም እናውርድ ብለሃል›› በሚል በእነ አቶ ስዬ አብርሃ ክስ ቀርቦባቸው፤ እርሳቸው አላልኩም በማለታቸው፤ የኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ቃለ ገባዔውን አስመጥቶ ይህን ክስ ለማጣራት  እስከ ሌሊቱ 8 ሰዓት ሰፊ ውይይት ካደረገ በኋላ ‹‹መለስ ለኤርትራ መሬት ሰጥተን ሰላም እናውርድ አላለም›› የሚል ውሳኔ ማሳለፉን እና ከስብሰባው መጠናቀቅ በኋላ ሁሉም ወደ የቤታቸው ለመሄድ ሲጣደፉ ሳለ፤ አቶ መለስ ከአዳራሹ አንድ ጥግ ቆመው ሲያለቅሱ (187) አቶ በረከት እና ህላዌ እንዳገኟቸው ይተርካል፡፡ እነ አቶ ተፈራ ዋልዋ ‹‹ጦርነቱ በሰላም መጠናቀቅ የለበትም የሚል አቋም ያራምዱ እንደነበር እና ‹‹ምንም ሰበብ ቢጠፋ እንኳን ከኤርትራ በኩል ነፋስ ወደ ኢትዮጵያ ነፋሰ በሚል ሰበብ ጦርነቱ እስከ መጨረሻው እንዲቀጥል ማድረግ አለብን›› (171) የሚል አቋም እንዳራመዱ ይነግረናል፡፡
በረከት ከደርግ እና ከኤርትራ ጋር የተደረገውን ጦርነት በሰፊው ያነሳል፡፡ ከዚህ አያይዤ አንድ አስተያየት ማቅረብ እሻለሁ፡፡ በረከት ይህ ጦርነት የእርስ በእርስ ጦርነት መሆኑን በማሰብ፤ ከሃያ ሰባት ዓመታት በኋላ ባለፉት ዓመታት የተከተልነውን የአሸናፊ - ተሸናፊ ትርክት ሌላ አቀራረብ እንዲይዝ በማድረግ ሥራ ሊሰራ ይገባል እላለሁ፡፡ ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት የ17 ዓመታቱን የእርስ በእርስ ጦርነት ስንዘክር የቆየንበት ዘይቤ የአሸናፊ - ተሸናፊ ትርክት የመፍጠር ቅኝንት ነበረው፡፡ በእርግጥ ጦርነቱ አሸናፊ እና ተሸናፊ ነበረው፡፡ ይህ ግን እንደ ቡድን ሲታይ እንጂ እንደ ሐገር ሁሉም ተሸናፊ ነው፡፡ ጦርነቱ የአፈና ስርዓትን ለመታገል የተደረገ ጦርነት መሆኑን ለመካድ አይደለም፡፡ በዚህ ትግል ለተሰዉ ወገኖቼም ሐዘን ይሰማኛል፡፡ ግን ሐዘኑ፤ ‹‹የሞተው ወንድምሽ የገደለው ባልሽ›› ከሚል ሐዘን የተለየ ሊሆን አይችልም፡፡ የተሰለፉበት ጎራ ምንም ይሁን ምን በሁለቱም ወገን የሞቱት ወንድሞቼ ናቸው፡፡ ለዚህ ነው ጦርነቱ የእርስ በእርስ ጦርነት መባሉ፡፡
አንድ ህብረተሰብ የእርስ በእርስ ጦርነት ውስጥ የሚገባው ችግሮቹን በፖለቲካዊ መንገድ መፍታት ሲሳነው ነው፡፡ ለዚህም ነው፤ ‹‹ጦርነት የከሸፈ የፖለቲካ ነው›› የሚባለው። ስለዚህ እንደ ህብረተሰብ የእርስ በእርስ ጦርነት ውስጥ መግባታችን የሚያመለክተው፤ እንደ ሐገር ፖለቲካ መስራት ወይም ችግራችንን በሰላማዊ - ፖለቲካዊ መንገድ መፍታት አለመቻላችንን ነው፡፡ በመሆኑም፤ የእርስ በእርስ ጦርነቱ የአሸናፊ - ተሸናፊ  የለውም ማለት ይቻላል፡፡ በ17 ዓመታት ጦርነት ደርግን የመሰለ የአፈና ስርዓት ለመገርሰስ መቻሉን እንደ አንድ ስኬት መቁጠር ተገቢ ቢሆንም፤ 27 ዓመት ሙሉ የአሸናፊ - ተሸናፊ ትርክት እንዲጸና ለማድረግ የሚደረገው ሥራ ማስተዋል የጎደለው ይመስለኛል፡፡  
ጦርነቱ የእርስ በእርስ ጦርነት መሆኑ እስኪጠፋብን ድረስ መሄድ የለብንም፡፡ የአንድ ቤተሰብ ልጆች በተለያየ ጎራ ተሰልፈው የሞቱባቸው እናቶች መኖራቸውን እስክንረሳ ድረስ መጓዝ አይገባንም። አሁን የእነዚህን እናቶች መከራ ለመመልከት ጊዜ መስጠት ይኖርብናል።
አንድ ጎራ ይዞ የተሰለፈ ቡድን አሸነፍኩ ሊል ይችላል፡፡ ይህ አሸናፊ በድን አባል የሆነበት እና የእርስ በእርስ ጦርነት ውስጥ የተዘፈቀው ህብረተሰብ ግን አሸናፊ አለመሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ስለዚህ አሸናፊ ነኝ የሚለው በድንም ተሸናፊ ነው፡፡ እንደ ህብረተሰብ በጦርነቱ አሸናፊ አለመሆናችንን የሚመሰክር ሌላም ጉዳይ አለ፡፡ አሁንም እንደ ህብረተሰብ ከእርስ በእርስ ጦርነት ከመግባት የሚጠብቅ ጠንካራ አስተሳሰብ ገንብተናል ብዬ አላምንም፡፡  
ስለዚህ፤ በመደመር ፍልስፍና ግንቦት ሃያን በአሸናፊ - ተሸናፊ ስሌት ማክበሩን ትተን፤ እንደ ህብረተሰብ መውደቃችንን አስታውሰን፤ ጦርነቱ የእርስ በእርስ ጦርነት መሆኑን አስበን፤ የሚያኮራን ብቻ ሳይሆን በሐፍረት ሊያሰማቅቀን የሚገባ ነገር እንዳለው አስታውሰን፤ ከዚያ ጦርነት በድል ወጣን ማለት የምንችለውም፤ እንደ  ህብረተሰብ መልሶ ወደ እርስ በእርስ ጦርነት ሊያስገባን የማይችል የአስተሳሰብ እና የአሰራር ስርዓት በመገንባት ብቻ ነው፡፡
አቶ በረከትን በደብረ ማርቆስ ከተማ ከመዋል ከማደር የምትከለክል ኢትዮጵያ ገና ብዙ እንደሚቀራት ያሳየኛል፡፡ ይህን ሳስብ፤ አቶ በረከት ከ40 ዓመታት በፊት ወደ ሜዳ እንዲወጣ ያደረገችው ኢትዮጵያ፤ በቅርፅ እንጂ በይዘት አልተለወጠችም እላለሁ። አሁንም ኢትዮጵያ በእፎይታ የሚኖሩባት ሐገር አይደለችም፡፡   

Read 10038 times