Tuesday, 28 August 2018 00:00

የዶ/ር ዐቢይ አስተዳደር አበይት ፈተናዎች

Written by  ደረጀ ይመር
Rate this item
(3 votes)

 የዶ/ር ዐቢይ አስተዳደር፤ የለውጡን ማእበል ተከትሎ፣ መንበረ ሥልጣኑን በተቆናጠጠባቸው ሶስት ወራት ውስጥ በማይታመን ፍጥነት ትልልቅ ለውጦችን አሳይቶናል፡፡ ምንም እንኳን ለውጡ ተቋማዊ ቅርጽን ባይላበስም የፖለቲካውን አውድ ላለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት ተዋርሶት የኖረው ጽልመት በተስፋ ውጋገን መፈገግ ጀምሯል፡፡ ሀገራችን እንደከዚህ ቀደሙ ታሪካዊ አጋጣሚዎች ወሳኝ የለውጥ ቅያስ (critical juncture) ላይ ደርሳለች፡፡ ይህን እጅግ ወሳኝ የታሪክ ምዕራፍ በጥበብና በተገቢው መልክ ማስተናገድ ካልቻልን ፍጻሜው ተገማች በማይሆን ተጨማሪ የመከራ ዘመናት ውስጥ መዳከራችን የማይቀር ነው፡፡ ከኢህአዴጋዊ ቀኖና ያፈነገጠው አዲሱ የለውጥ አስተዳደር፣ ከቀዶ ጥገናዊ ለውጥ ወደ ሥር ነቀል ለውጥ እንዳይሸጋገር የሚያግዱትን ሳንካዎች ለማስወገድ የሚሄድበት ርቀት ከምንም በላይ ወሳኙ ሥራ ይሆናል፡፡
የውስጥ ሉአላዊ ሥልጣንን ማንበር
”ከሚወደድ ልፍስፍስ አስተዳደር ይልቅ ጠንካራና የሚፈራ መንግሥት ይመረጣል፡፡”ይላል የማይካቬሊ መርህ፡፡ እርግጥ ነው አንድ መንግሥት ሉዓላዊ ሥልጣን (soverign power) አለው የሚባለው በዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ዘንድ እውቅና ባገኘባቸው የግዛት ማዕቀፍ ውስጥ  ሕግን የማስፈጸም፣ ሕግን የማውጣትና የዜጎችን ደህንነት የማስጠበቅ አቅሙ ጥያቄ ውስጥ በማይገባ ጊዜ ነው፡፡ ሀገራችንን በዚህ መመዘኛ ስንለካት ገና ወገቧ ያልጠና (ፍራጃይል ስቴት) እንደሆነች ምስክር የሚሆኑን ዘውጌ ተኮር ግጭቶችን በሁሉም ክልሎች እያስተዋልን እንገኛለን፡፡ ላለፉት ሀያ ሰባት ዓመታት እርስ በርስ በምንተሳሰርበት ኢትዮጵያዊ ማንነት ኪሳራ፣ አንዳችን አንዳችንን በዓይነ ቁራኛ የምንጠብቅበት አውዳሚ የፖለቲካ ከባቢ ነው ሲፋፋም የኖረው፡፡ እንደውም እንደ ሕዝብ ለብዙ ዘመናት ከአባቶቻችን ተረክበን ያቆየናቸው ባህላዊ እሴቶቻችን ጨርሰው አለመክሰማቸው እንጂ፣ ከዚህም በላይ የከፋ እልቂት ባስተናገድን ነበር፡፡ በአብዛኛው የአፍሪካ ሀገራት የተለመደው የመንጋ ፍርድ (Mob Justice) አሁን አሁን በሚያስደነግጥ ደረጃ ቀዬአችን እየለመደው መጥቷል፡፡ የፍትህና የጸጥታ አካላት ይህንን ፀጉረ ልውጥ የመንጋ እንቅስቃሴን አደብ የሚያስገዙበት አቅም እንደከዳቸው ዋቢ ምስክር የሚሆኑን የአደባባይ ሰቆቃዎችን በገሀድ እየተመለከትን ነው፡፡ የዓይንህ ቀለም አላማረኝም ተብሎ የመስዋዕት በግ የሚሆነው ዜጋ ቁጥር ዕለት በዕለት እያሻቀበ ነው፡፡
አዲሱ የለውጥ አስተዳደር የሚፈተንበት ዋንኛ ተግባር ዜጎች ያለ ስጋት ወጥተው የሚገቡበትን ሠላማዊ አየርን ማንበር ይሆናል፡፡ እንደ አዲስ የሚነፈስው የፖለቲካ ንፋስ ጥቅማቸውን ያጎደለባቸው፣ በገዢው ፓርቲ ውስጥ የተሰገሰጉ ኃይሎች፣ የተገኘውን ዕድል ቀልበሰው ወደ ድሮው አዝጋሚና ዝግ የፖለቲካ ሥርዓት ውስጥ መልሰው ለመዶል ማንኛውንም አማራጭ መጠቀማቸው አይቀርም፡፡ ስለዚህ የተገኘውን መልካም አጋጣሚ ወደፊት የማስቀጠሉ ሥራ አልጋ በአልጋ አይሆንም፡፡ መንግሥት ጨከን ያሉ እርምጃዎችን መወሰድ ካልጀመረ የጓጓንለት ዲሞክራሲያዊ የፖለቲካ ሥርዓት ገና በእግሩ ሳይቆም፣ ከመንገድ ተሰነካክሎ እንደሚቀር እሙን ነው፡፡
በየአካባቢው የሚነሳውን ሁከት ለመቆጣጠር በግጭት ውስጥ ሚና ሊኖራቸው የሚችሉ በታችኛው የሥልጠን እርከን ላይ የሚገኙ ሹማምንቶችን በአዲስ መልክ የማዋቀር ሥራ አንዱ መፍትሄ አማራጭ ሊሆን ይችላል። ይህ የመፍትሔ አማራጭ ሰላምንና ፀጥታን በተገቢው መልኩ ማስፈን ካልቻለ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን እስከማወጅ ድረስ የሚዘልቅ ፖለቲካዊ ቁርጠኝነትን መላበስ ተገቢ ይሆናል።  እንደ ኢትዮጵያ ያለች ታዳጊ ሀገር ይቅርና ፈርጣማ የኢኮኖሚና የወታደራዊ አቅም ያላት ምዕራባዊቷ ሀገር ፈረንሳይ እንኳን ከህብዶ የሽብር ጥቃት ማግሥት ለሁለት ዓመታት የሚጸና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማወጅ ነበር ውስጣዊ ሰላሟን ማረጋገጥ የቻለችው፡፡ ለዜጎችና ለሀገር ደህንነት ሲባል ይህ አይነቱ እርምጃ ቢወሰድ የሚገርም አይሆንም። ስለዚህ በምንም መመዘኛ የጎሳ ፌደራሊዝሙ የሚወልዳቸው አካባቢያዊ ግጭቶች እንዳይከሰቱ፣ መንግሥት ተገቢውን ህጋዊ እርምጃ ለመወሰድ ዝግጁ መሆን ይገባዋል፡፡  
ተቋማዊ ቅርጽ ያለው መደመር
የዶ/ር ዐቢይ መሪ መፈክር መደመር፣ በሀገር ጉዳይ ላይ ለሁሉም ዜጋ ክፍት የሆነን ፖለቲካዊ ከባቢን ነው የሚሰብከው፡፡የትኛውም የሀገሪቱ ዜጋ፣ የሀይማኖት፣ የዘርና የፖለቲካ አመለካከት ልዩነት ሳያቅበው ወደፊት በሚገነባው የፖለቲካ ሥርዓት ውስጥ እኩል አስተዋጽኦ ይኖረዋል። ግርምቢጡ እውነታ ግን ይህ ኢትዮጵያዊነትን ያነገሰ አሳታፊ መሪ መፈክር የቆመበት ርዕዮተ-ዓለም የሌለው መሆኑ ነው፡፡እንደሚታወቀው የትኛውም መንግሥት የሚያቀነቅነው መሪ መፈክር ለሚከተለው ርዕዮተ-ዓለም ተጨማሪ ኃይል መፍጠሪያ ሆኖ ያገለግለዋል፡፡ የመንግሥት ርዕዮተ-ዓለም በዜጎች ዘንድ ቅቡል እንዲሆን፣ አንድ ገዢ ማጠንጠኛ መሪ ቃል ላይ ይንጠላጠላል። ታዋቂው የፖለቲካ ፈላስፋ ስላቮጅ ጂጄክ ይህንን ወሳኝ ስሜት ቀስቃሽ መሪ ቃል “ማስተር ሲግኒፋይር” ይለዋል፣
All ideologies turn around certain ‘sublime objects’ of subjects’ belief. These are objects named by what zizek call the ‘master signifiers’ of a particular regime, master signifiers like ‘the American people’, ‘the Soviet Cause’, ‘freedom’, the Serbian/Croatian/Albanian nation’.
የመደመር አስተምህሮት ግን የገዢው ፓርቲ ዋንኛ ርዕዮተ-ዓለም አብዮታዊ ዲሞክራሲ ስሜት ቀስቃሽ መሪ ቃል ወይም  “ማስተር ሲግኒፋይር” ሊሆን አይችልም። ምክንያቱም አብዮታዊ ዲሞክራሲ በጥቂት የፖለቲካ ልሂቃን የውሳኔ ሰጪነት፣ በማእከላዊነት የተያዘበትና ከላይ ወደ ታች በሚወርድ ሥርዓት የተቀየደ አግላይ ርዕዮተ-ዓለም ነው፡፡ አብዮታዊ ዲሞክራሲ ጠላትና ወዳጅ ብሎ የሚፈርጃቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች ይኖሩታል፡፡ በፖለቲካ አቋማቸው ገዢውን የፖለቲካ ቡድን የሚቀናቀኑትን የማኅበረሰብ ክፍሎች ጠባብ፣ ትምህክተኞችና የድሮ ስርዓት ናፋቂዎች በሚል የተዛባ ፍረጃ ከፖለቲካ ምህዳሩ ገሸሽ እንዲሉ ይፈረድባቸዋል። እንግዲህ በዚህ አግላይ የፖለቲካ ርዕዮተ-ዓለም ላይ ነው አዲሱ አካታች የመደመር መርህ የተጣፈው፡፡ መደመር የቆመበት የፖለቲካ ርዕዮተ-ዓለም ገና አልተወለደም፡፡  
የዶ/ር ዐቢይ የለውጥ መርህ እንደ ቀድሞው የኢህአዴግ አስተዳደር በኢትዮጵያዊ ማንነት ኪሳራ አለቅጥ ተጋኖ ሲቀነቀን እንደነበረው የ“ብሔር ብሔረሰብ” መሪ መፈክር ተቋማዊ ቅርጽን መላበስ አልጀመረም፡፡ የመደመር መርህ ከጎሳ አደረጃጀት ይልቅ ሁሉን አሳታፊ የሆነ፣ በምክንያትና በሐሳብ የተሰባሰቡ የዜጋ ፖለቲካን ለሚያቀነቅኑ ቡድኖች የተመቸ ምህዳር በመፍጠሩ ረገድ አሌ የማይባል ሚናን ይጫወታል፡፡
 መደመር ከቅስቀሳ (ፖለቲካል ሪቶሪክ) ባሻገር እጅ እግር እንዲኖረው ከተፈለገ እስከ ታችኛው የሥልጣን እርከን ድረስ የወረደ ተቋማዊ ቅርጽን መላበስ ይኖርበታል፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ ግን የመጀመሪያ  እንቅፋት የሚሆነው ሕገ መንግሥቱ ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱ ሀገሪቱን በየአቅጣጫው ሰንጎ የያዛትን ፖለቲካዊ ምስቅልቅል የወለደ ሰነድ እንደሆነ የፖለቲካ ልሂቃን ይስማማሉ፡፡ ይህ ዘርን ማዕከል ያደረገ ፌደራላዊ አወቃቀር /Ethnic federalism/ የታነጸበት ሕገ መንግሥት፣ ከምዕራባውያን ባለ ብዝሃ ባህል ዲሞክራሲያዊ ፌደራሊዝም ይልቅ ለቀድሞው ሶቭየት ኅብረት የሶሻሊስት ሕገ መንግሥት በእጅጉ የቀረበ ነው። በዚህ ፈታኝ ወቅት ሕገ መንግሥቱን የመከለስ ጥያቄ ይነሳ ቢባል እንኳን ለሌላ ዙር ትርምስ በር መክፈት ይሆናል፡፡ ስለዚህ የሕገ መንግሥቱን ጉዳይ ለጊዜው አዘግይቶ ሌሎች መሰረታዊ መዋቅራዊ ማሻሻያዎችን ማድረግ እንደ ተጨባጭ ሥራ ይቆጠራል፡፡ ከአነዚህም ውስጥ ከመንግሥት ጫና ነፃ የሆነ ሚዲያ እንዲፋፋ ምቹ አሰራርን መዘርጋት፣ ነፃ የምርጫ ቦርድን ማቋቋምና በዲሞክራሲ ሂደት ውስጥ ወሳኝ ሚና የሚጫወቱ ጠንካራ የሲቪክ ተቋማት እንደ ልባቸው የሚንቀሳቀሱበትን የፖለቲካ ምህዳር መፍጠር ይገኙባቸዋል፡፡  
ከኤርትራ ጋር ግንኙነት
ከኤርትራ ጋር የተፈጠረው የሰላም ግንኙነት ለሀገራችንም ሆነ ለቀጠናው ደህንነት የሚያበረክተው አስተዋጽኦ የላቀ እንደሚሆን እሙን ነው፡፡ ለሁለት አሥርተ ዓመታት የውክልና ጦርነትን /Proxy-war/ አንዱ በአንዱ መሬት ላይ ለመትከል በሚደረገው ሩጫ ምትክ አፍላ የትብብር መንፈስ ቀጠናውን እያወደው ይገኛል። ይህ በጎ የመደጋገፍ መንፈስ በአዲስ መልከ እንዲወለድ ዋንኛውን ድርሻ የሚወስደው የዶ/ር ዐቢይ አስተዳደር እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ኢትዮጵያ የአልጀርሱን ስምምነት ሙሉ ለሙሉ ለመቀበል ፍቃደኛ መሆኗ፣ በወዲያኛው የኤርትራ ወገን ያለውን የኢሳያስ አፈወርቂ መንግሥት፣ በሩን ለሰላም ወለል አድርጎ እንዲከፍት አስገድዶታል፡፡    
አሁን የስምምነቱ የመጀመሪያ ምእራፍ ላይ ነው የምንገኘው፡፡ ስለዚህ ፈታኝ ሁናቴዎች መፈጠር ገና አልጀመሩም፡፡ በዶ/ር ያዕቆብ ኃ/ማሪያም አማካኝነት የተሰናዳው “አሰብ የማን ናት”የሚለው መጽሐፍ በገጽ 130 ላይ እንደሚያትተው፤ በአልጀርስ ስምምነት የኢትዮ-ኤርትራ የድንበር ኮሚሽን፣ የሞቱ የቅኝ ግዛት ውሎችን ከመቃብር ቆፍሮ አውጥቶ፣ በሥራ ላይ አውሎ በሰጠው ውሳኔ መሠረት፤ የቀይ ባሕር አፋርን በከፊል፣ ኢሮብን ኩናማንና ጾረናን ለኤርትራ ይሰጣል። ስለዚህ ድንበሩን በተግባር የማካለሉ ወይም የዲማርኬሽን ሥራ ሲጀመር ውዝግብ ሊፈጥሩ የሚችሉ ኹነቶች ሊከሰቱ ይችላሉ፡፡ በመሆኑም የአልጀርሱ ስምምነት ወደ መሬት ከመውረዱ አስቀድሞ የኖርማላይዜሽን (የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት) ሥራ በአግባቡ መከናወን ይኖርበታል። ይህንንም ተፈጻሚ ለማድረግ የሁለቱ ሀገራት ምሁራን በጋራ የሚመክሩበት የውይይት መድረክን በመፍጠር፣ ሲምፖዚየሞችና ባዛሮችን በየጊዜው በማሰናዳት እንዲሁም በኪነጥበብ ባለሙያዎች አማካኝነት ሰፋፊ መድረኮችን በማዘጋጀት ትስስሩን እውን ማድረግ  ይቻላል፡፡ በሁለቱ ሀገራት መካከል ይህን መሰሉን የሕዝብ ለሕዝብ ትስስርን የሚያሳድጉ መድረኮችን ማመቻቸት ኋላ ላይ የሚመጡ ፈተናዎችን በሰጥቶ መቀበል መርህ፣ በውይይትና በሰላም  ለመፍታት የሚቻልበትን የፖለቲካ ከባቢን /Political Climate/ አስቀድሞ ለመፍጠር ያግዛል፡፡
ሌላው ከዚህ ቀደም ግጭት የተገባበትን መንስኤ መለስ ብሎ ማጤን ተገቢ ነው፡፡ በሁለቱ ሀገራት መካከል የሚኖረው የመንግሥት ለመንግሥት ግንኙነት ከማንኛውም ሉዓላዊ ሀገር ጋር እንደሚኖረው ግንኙነት፣ ግልጽ የውጭ ጉዳይ ፖሊስን መሠረት ያደረገ መሆን ይኖርበታል። የፖለቲካ ተንታኞች አጽንኦት ሰጥተው  እንደሚያስረዱት፤ የ1991 የድንበር ግጭት መንስኤ ከግዛት ይገባኛል ይልቅ በአብዛኛው ኢኮኖሚያዊ ባህሪያትን የተላበሰ ነበር፡፡ ይህም የሻከረ ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት ሊፈጠር የቻለው ሀገራቱ እርስ በርስ በገቡበት መርህ አልባ ግንኙነት የተነሳ ነበር፡፡ ስለዚህ በዚህ ረገድ ያለውን ክፍተት ለመሙላት የዶ/ር ዐቢይ አስተዳደር የሚከተለው የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ወሳኝነት ይኖረዋል።    
 ከዚህም በተጨማሪ የዶ/ር ዐቢይ አስተዳደር፤ ሀገራችን ኢትዮጵያ በአሰብ ወደብ ባለቤትነት ላይ ሊኖራት የሚችለውን ሕጋዊ መብት በምን መልኩ እንደሚያስተናግደው እስካሁን ምንም ፍንጭ አላስተዋልንም፡፡ የዶ/ር ያዕቆብ ኃ/ማሪያም ድርሳን በዝርዝር እንዳሰፈረው ከሆነ፤ ኢትዮጵያ የ1947ቱን የተባበሩት መንግሥታት ጉባኤን ውሳኔ እና የ1964ቱን የካይሮ ዲክላሬሽንን ዋቢ በማድረግ፣ በአሰብ ወደብ ላይ የባለቤትነት መብት ጥያቄ ማንሳት ትችላለች፡፡ ይህን መሰሉ ገሀድ እውነታ ከኤርትራ ጋር ያለ ግጭት፣ ሰላማዊ በሆነ ውይይት በምን መልኩ መፍታት እንደሚቻል ገና የጠራ ነገር የለም፡፡
ማሰሪያ ነጥብ
ኢህአዴግ እንደ ፓርቲ ህልውናው ሳያከትም፣ ከእነ ገዢ ርዕዮተ-ዓለሙ፣ በሕዝብ ዘንድ እጅግ ተቀባይነትን ያተረፈ ብሩህ መሪን አግኝቷል። የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ወ/ሮ ሙፍሪያት ካሚል በአንድ ወቅት በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ “ለውጥ ከውጪ ሲመጣ ዕዳ ነው፤ ከውስጥ ሲሆን ግን ዕድል ነው”  ብለው ነበር። በርግጥም ሀገራችንን በታሪክ ፊት ካጋጠሟት የለውጥ ዕድሎች ሁሉ የአሁኑ የላቀ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ የዶ/ር ዐቢይ አስተዳደር፤ ይህንን በታሪክ ፊት ታይቶ የማይታወቅ መልካም አጋጣሚ በአግባቡ ጠብቆ፣ ሀገሪቱን ወደ የተሻለ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ለማሸጋገር የሚላበሰው ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት ከምንም በላይ ወሳኙ ጉዳይ ይሆናል፡፡

Read 4148 times