Saturday, 25 August 2018 13:33

“ዜሮ ሻማ” ፓርቲዎች

Written by  አያሌው አስረስ
Rate this item
(2 votes)

 ከአዘጋጁ፡- (ከዚህ በታች የቀረበው ባለፈው ሳምንት “የተሰረቁ ፓርቲዎች” በሚል የወጣው ጽሁፍ ተከታይ መሆኑን ለመግለጽ እንወዳለን)
ኢሕአዴግ የኢትዮጵያን ማዕከላዊ መንግሥት ሥልጣን የጨበጠው በመሳሪያ ኃይል ነው፡፡ ነጋ ጠባ ደርግ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ እየተከታተለ መረጃ የሚያቀብል የሥለላ መረብ ከመዘርጋት ጀምሮ የደርግን ደካማ ጎኖች እየበዘበዘ ለሕዝብ የሚያጋልጥ፣ የራሱን የራዲዮ ጣቢያ የያዘ የፕሮፓጋንዳ ጦርም ነበረው፡፡ የቅስቀሳ ክፍሉ ደርግን በማጥላላት ላይ ብቻ የተወሰነ ሳይሆን ለድርጅቱ ተከታይና ደጋፊ አልፎም በጦር ሜዳ የሚሰለፍ ሰራዊት በማስገኘትም የድርሻውን ተወጥቷል፡፡  
ከመቀሌ ጀምሮ በከተሞች የቀበሌ ማህበራትን በራሱ ሰው እያሲያዘ፣ የገበሬ ማኅበራትን በራሱ ሰዎች እየተካ አዲስ አበባ የደረሰ ድርጅት ነው፡፡ ኢሕአዴግ በአዲስ አበባ የከተማ ነዋሪዎች ማህበራትን በራሱ ሰላምና መረጋጋት ኮሚቴ በመተካት አገዛዝ ማደላደሉ ይታወሳል፡፡
በመንግሥት መ/ቤቶች የወሰደው እርምጃም የዚሁ ተመሳሳይ ነበር፡፡ እኔ እሰራበት በነበረው ማስታወቂያ ሚኒስቴር፣ ሚኒስትሩን ከማንሳቱ ሌላ ለቴሌቪዥን መምሪያ አቶ አማረ አረጋዊን፣ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት መቶ አለቃ ተስፋዬ ገብረአብን መመደቡን አስታውሳለሁ፡፡
በ1997 አገር አቀፍ ምርጫ ኢሕአዴግን እንደ ቄጤማ ያርገደገደው ቅንጅት፤ ያንን ሃይል የፈጠረው አራቱን ድርጀቶች በአንድ ግንባር በማሰባሰቡ ብቻ ሳይሆን፣ ድርጅቶቹ በነበራቸው ልዩ ልዩ ባለሙያዎች በመጠቀም  መሆኑም የሚዘነጋ አይደለም፡፡ መኢአድ በዘረጋው የፓርቲ መዋቅር፣ ቅንጅቱ ከከተሞች አልፎ ገበሬ ማህበር ድረስ ሲወርድ፣ ኢዴፓ ያዘጋጀውን የምርጫ ማኒፌስቶ የጋራ ሰነድ አድርጎ ተቀብሎ የትግል መሳሪያ በማድረግ ተገልግሏል፡፡
በየአጋጣሚው በሚከፈቱ የክርክር መድረኮች በተከራካሪነት ይገኙ የነበሩት እነ ዶክተር ብርሃኑ ነጋ፣ እነ አቶ ልደቱ አያሌው ወዘተ ኢሕአዴግ የተሸፋፈነበትን መጋረጃ እያጋለጡ አንዳንድ ጊዜም እየቀደዱ በራሱ እንዲያፍር ከማድረጋቸውም በላይ እንደ ሕፃን አኩራፊ “ንግግሩ የፈለገውን ያህል ልባችሁን ይነካዋል እንጂ ድጋፋችሁን ለመግለጥ አታጨበጭቡም” ብሎ እስከ መከልከል ድረስም እንዲወርድ አድርገውታል፡፡ የቅንጅቱን የራዲዮና የቴሌቪዥ ፕሮግራም ይመሩና ያስተባበሩ የነበሩት አቶ ደበበ እሸቱና አጋሮቻቸው የተጫወቱት ሚናም የሚዘነጋ አይደለም፡፡ የዚህ ሁሉ ኃይል ርብርብ ለቅንጅቱ ታማኝነትና ተመራጭነት እንዳስገኘለትም ሊሰመርበት ይገባል፡፡ በኢህአዴግም ሆነ በቅንጅት አማካይነት ማሳየት የተፈለገውና በድርብ ሊሰመርበት የሚገባው ዋና ጉዳይ ደግሞ የፖለቲካ ድርጅቶች ብቁና በቂ የሰው ኃይል ሊኖራቸው እንደሚገባ ነው፡፡
ኢሕአዴግ የያዘውን የመንግሥት ሥልጣን በምርጫ አሸንፎ በመረከብ የኢትዮጵያ ሕዝብን መምራት የሚፈልጉ ከውጭ ወደ ሀገር የገቡትን ሳይጨምር ሃያ አንድ አገር አቀፍ የፖለቲካ ድርጅቶች አሉ፡፡ ሃያዎቹ በምርጫ 2007 ተሳትፈዋል፡፡ ከነዚህ ውስጥ አምስቱ ማለትም የገዳ ሥርዓት አራማጅ ፓርቲ፣ የመላ አማራ ሕዝብ ድርጅት፣ የወለኔ ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ፣ የመላው ኦሮሞ ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲና የኦሮሞ ብሄራዊ ኮንግረስ በብሔረሰብ ማንነት መሠረት ላይ የቆሙ ድርጅቶች ናቸው፡፡ ፡  
ሁሉም ፓርቲዎች አገር አቀፍ ፓርቲ ሆነው ለመመዝገብና ፈቃድ ለማግኘት 1500 መሥራች አባሎች እንዲኖራቸው ሕግ ያስገድዳል፡፡ የፓርቲ ፕሮግራምና የመተዳደሪያ ደንብ ሌላው ፓርቲዎች መሟላት ያለባቸው ጉዳይም ነው፡፡ ይህን ማድረግ አለብህ የሚል በሕግ የተቀመጠ ግዴታ ባይኖርም አገር ለመምራት አስፈላጊ የሚሆኑ ፓርቲዎችም ይዘዋቸው ሊገኙ የሚገቡ በርካታ ጉዳዮች አሉ፡፡ ከእነሱም ዋናው ደግሞ የሰው ኃይል ነው፡፡ የሰው ኃይል ሲባል አንድ ሁለት ተብሎ የሚቆጠር ሰው ሳይሆን በየዘርፉ ሙያ ያለው ሰው ማለትም ነው፡፡
ማንበብና መጻፍ የማይችሉት አቶ ሰይድ ይመር በቅፅል ስማቸው ሰይድ ሚሊሽያ ከሚመሩት የኢትዮጵያ ሰላማዊ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ ጀምሮ እጅግ ብዙዎች የፓርቲያቸውን ፕሮግራም ዘርዝሮ የሚያስረዳ ሰው የላቸውም፡፡ ሰይድ ሚሊሽያ ለፓርቲ ቢሮ የተሰጣቸውን ቤት ሸጠው በፍርድ ቤት እንዲመልሱ የተደረጉና ያልተፈቀደ የጦር መሳሪያ ይዘው ተገኝተው ታስረው የተፈቱ ሰው ናቸው፡፡ እንደሳቸው የሥነ ምግባር ችግር  ያለባቸው የፓርቲ መሪዎች በሽበሽ ናቸው፡፡
ይመር ሚሊሽያ በ1997 አገር አቀፍ ምርጫ ጊዜ በቴሌቪዥን መስኮት ብቅ ብለው “እኛ ፕሮግራም የለንም፤ ምረጡን እንጂ የእነሱ (የድርጅት ስም ጠርተው) ፕሮግራም የእኛ ፕሮግራም ነው” በሚለው ንግግራቸው የሚታወቁም ሰው ናቸው፡፡ እንደሳቸው ሁሉ ለኢትዮጵያ ሕዝብና አገሪቱ ላለችበት ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ደረጃ የማይመጥኑ በርካታ የፓርቲ መሪዎች እንዳሉ ስም ባንጠራም በአደባባይ እየታየ፣ ሕዝብም እየታዘበው ያለ ጉዳይ  ነው፡፡
ተቃዋሚ ፓርቲዎች በ2007 አገር አቀፍ ምርጫ እያንዳንዳቸው ያቀረቧቸውን እጩዎች ብዛት፣ ድርጅቱ ያገኘውን  አጠቃላይ ድምፅና እያንዳንዱ እጩ ያገኘውን አማካይ ድምፅ የሚያሳየውን ሠንጠረዥ  ከዚህ በታች አቅርበናል፡፡  

Read 2458 times