Saturday, 25 August 2018 13:26

“እ…ምን መሰለህ…”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(2 votes)

 እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ስሙኝማ…መቼም እኛን እንዳንሆን የሚያደርጉ ነገሮች እየበዙብን…አለ አይደል…ግራ የሚያጋባ ጊዜ ሆኗል፡፡ በብዙ ነገር ራሳችንን መሆን ሳይሆን…እንደሌላው እንድንሆን የሚፈለግ ይመስላል። አለበለዚያ ለቃለ መጠይቅም፣ ለልዩ የበዓል ፕሮግራምም፣ ለምንም አንመችማ!
መቼም ዘንድሮ ይዞልን ‘ቦተሊካ’ እንደ ልብ ሆኖልን የለ! እና በፊት “መታፈር በከንፈር፣” ወይም “የተከደነ አፍ ዝምብ አይገባባትም፣” ምናምን በሚል ጭጭ ብለን ከርመን፣ አሁን የድምጽ ነርቮቻችን ከአቅማቸው በላይ እየሠሩ ነው፡፡ ይቺንስ ማን አየብን! (“የሀኒሙኑ ጊዜ ያለቀ ጊዜ ግን…” ምናምን ያልከው ወዳጃችን ተውማ…  ከሰርረጂዮ ራሞስ የባስክ ነገር ሊያስመስልብህ ይችላል ብዬ ነው፡፡)
ስሙኝማ… በቅርብ የሆነ ነው፡፡ እናላችሁ አንዱ ሌላውን…
“የሰሞኑን ሁኔታ እንዴት ታየዋለህ?” ሲል ይጠይቀዋል፡፡ ያኛውም…
“የምን የሰሞኑ ሁኔታ?” ይላል፡፡
“ፖለቲካችንን ነዋ!” (እንግዲህ፣ ይህ ሰው ከዚህ በፊት ስለ ፖለቲካ አንስቶለት የማያውቅ ሰው ነው፡፡)
“እሱን ማለትህ ነው! እኔ እባክህ ምንም አይመስለኝም፡፡ እንደውም አልከታተልም፡፡”
“እንዴት አትከታተልም…የአገር ጉዳይ አይደለም እንዴ!” (በትኩስ ድንችና በትኩስ ‘ፖለቲከኛ’ መካከል ስላለው ልዩነት ማብራሪያ ‘ጉግል’ ላይ ይኖራል እንዴ? ሁለቱም ‘ከመፋጀታቸው’ ሌላ ለማለት ያህል ነው!”)
“እኔ እባክህ የራሴ ብዙ ከባድ፣ ከባድ ችግሮች አሉብኝ!”
“ቢሆንስ እንዴት የአገርህን ጉዳይ አትከታተልም!” (የእሱ የቀድሞ ‘ፖለቲካ’ እኮ ድራፍት ላይ ስሙኒም፣ ሽልንግም በተጨመረ ቁጥር፣ “አሁንስ የት አገር እንሰደድ!” አይነት ነገር ነበር፡፡ ለምን ፖለቲካ ፓርቲ ምናምን ነገር አያቋቁምም፡፡ ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…ዝም ብላችሁ ስታስቡት… “ይሄኔ ስንቱ ሰው ‘ፖለቲካ ፓርቲ’ ለማቋቋም እየመከረ ይሆን!” እንደ ‘ዓላማም‘ አንደ ‘ቢዙም’ ለማለት ያህል ነው።)
እናላችሁ…ሁለቱ ሰዎች ሊግባቡ አልቻሉም አሉ፡፡ እንደውም ቃላቱ እየጠነከሩ ቅጽሎች በዛ እያሉ ሲሄዱ ሰዎች ናቸው… “በቃ፣ ወሬ ቀይሩ” ምናምን በሚል ያቆሙት አሉ፡፡
ሰውየው እንደ ጊዜው መሆን ይጠበቅበት ነበር ማለት ነው፡፡ ጠዋት ሲነሳ… በባዶ መሶብ፣ ማታ ልጆቹ ምን እንደሚበሉ መጨነቁ ቀርቶ… “ትናንት ማታ ቴሌቪዥን አያችሁ!” ምናምን አያለ መመሳሰል አለበት ማለት ነው፡፡
እናላችሁ…የግድ እንደ ራሳችን ሳይሆን ‘እንደ ሌላው’ መሆን ስለሚጠበቅብን…ሰውየው “የሰሞኑን ሁኔታ እንዴት ታየዋለህ?” ሲባል…አለ አይደል… “እኔ እንዲህ አይነት ዘመን፣ አይደለም በእኔ እድሜ፣ በልጆቼም እድሜ ይመጣል ብዬ ጠብቄ አላውቅም!” ምናምን ማለት አለበት፡፡
የምር ግን…በተለይም እስቲ ብዙ ቃለ መጠይቆችን ነገሬ ብላችሁ ተመልከቱ፡፡ ተጠያቂው በአንደበቱ የሚናገረው ሌላ፣ አካላዊ እንቅስቃሴው የሚያሳብቅበት ሌላ! አሀ…መምሰል አለበታ! ራሴን እሆናለሁ ቢል… “እሱ ማነውና!” ምናምን የምንል ክፍሎች ልንኖር እንችላለና!
“በምን ሰዓት ነው የምትጽፈው?”
“ብዙ ጊዜ ሌሊት ተነስቼ ነው የምጽፈው”
“በምን አይነት ቦታ ነው ስትጽፍ ደስ የሚልህ?”
“እውነቱን ለመናገር ጸጥ ያለ፣ የወፎች ድምጽ ያለበት ስፍራ ሆኜ ብጽፍ ደስ ይለኛል፡፡”  (ሌሊት!)
አዲስ አበባ ውስጥ ነው እንዴ “ጸጥ ያለ በወፎች ድምጽ የተሞላ…” ምናምን ያለው! የእሱ መኖሪያ  እኮ ‘ወከባ’ ከመብዛቱ የተነሳ እዛ ላይ ያሉት አንዳንድ ምናምን ሳት የሚሏቸው ሳተላይቶች፣ ድምጽና ምስል የማስተላለፍ ችግር ሊገጥሟቸው ዳር፣ ዳር እያላቸው ነው፡፡
የምር ግን… እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ፣ ምን አለ መሰላችሁ…ጊዜው መሆንን ሳይሆን ‘መምሰል’ን እየጠየቅን ስለሆነ ምን ይደረግ! አሪፍ የሚባሉት ዓለም አቀፍ የጥንት ወይም የአሁን ደራስያን የሚሉትን በጥቅስም ሆነ በምን እንሰማና እንደ እነሱ ካልመሰልን ለሚዲያ አይመችማ! (የምን አገር ጸሃፊ ነው እንዲሁ መሀረብ ቢጤ እንኳ ጣል ሳያደርግ፣ መለ መላውን መጻፍ ይወድ ነበር የሚባለው! እስካሁን እሱን ቢያንስ በቃለ መጠይቅ የኮረጀ የለም፡፡ እንደ ዘንድሮ አያያዛችን ግን ከዕለታት አንድ ቀን “በቃ ልብሴን ሙሉ ለሙሉ አወላልቄ፣ ከኮንዶሚኒየም በረንዳ ላይ ህዝቡን እያየሁ መጻፍ…” ምናምን የሚል የማይፈጠርበት ምክንያት የለም፡፡ (ያኔ ደንብ ማስከበር ምን እንደሚያደርግህ እናያለን! ቂ…ቂ…ቂ…)
“ለመሆኑ ተሳክቶልኛል ትላለህ?”
“እ…እንግዲህ…ምን መሰለህ…” (ቆይማ… ችኮላ አያስፈልግም፡፡ እንዲህ እያንዳንዱን ፊደል ያዝ፣ ያዝ ካላደረግንማ ዝም ብሎ ኩልል ያሉ ዓረፍተ ነገሮች መናገር… አለ አይደል…ለምናምነኛ ክፍል የድርሰት ክፍለ ጊዜ እንጂ ‘የወፎች ድምጽ እየሰማ የሚቸከችክ ጸሀፊ የሚናገረው አይደለም፡፡)
“እ…ምን መሰለህ…እንግዲህ ይሄን…ዋናው ህዝቡ ነው የሚፈርደው፡፡”
“የህዝቡን ምላሽ እንዴት አገኘኸው?”
“ኦ…በጣም የሚገርም ነው፡፡ በጣም  እኔ ህዝቡ እንዲህ የሚያነብ አይመስለኝም ነበር፡፡ (ቆይ፣ ቆይ…እዚች ቦታ ላይ ፍሬን እንዳይበጠስ! “አንጀቱን ልብላው” የተባለውን ህዝብ ላለማሰቆጣት ረጋ ነው፡፡ እንደውም… አለ አይደል… “የእኛ ህዝብ ጥሩ ሥራ ከቀረበለት ያነባል” ማለት ነው የሚያስፈልገው፡፡፡ እዚህ ላይ ‘በስም ማጥፋት’ የሚከስ የለም!)
እናላችሁ…ሌላውን ለመምሰል የግድ ውሸት መናገር ይጠበቀብናል፡፡ ልዩነቱ ‘ውሸት’ የሚለውን ቃል አለመጠቀማችን ነው፡፡ ሌላኛውም ሰው…የድሮ አራዶች እንደሚሉት ‘እየረገጥን’ መሆኑን ቢያውቅም… “ወራጅ አለ” ምናምን ብሎ አያስቆመንም፡፡ እሱም ተራው ሲደርስ እንደዛው ነዋ! ስለ ውሸት ካነሳን አይቀር ይቺን ስሙኝማ…
ሰውየው ጓደኛውን፤ “ሆስፒታል ውስጥ የሆነ ሰው ውሸት ሲናገር የሚለይ መሳሪያ አየሁ፡፡”
“ምን ይገርማል?”
“እንዴት ምን ይገርማል?”
“አንተ ማሽን ነው ያየኸው፣ እኔ ደግሞ ዋናዋን ከእነ ነፍሷ በሰማንያ አግብቻታለሁ” አለ አሉ፡፡
ታዲያላችሁ… ዘንድሮ ወንዝ የሚያሻግረው ‘መሆን’ ሳይሆን ‘መምሰል’ ስለሆነ ምን ይደረግ! እንኳንም የቴሌቪዥን ጣቢያዎች በዙልን እንጂ ሁላችንም “እ…ምን መሰለህ…” ምናምን እያልን ለመሸለል ወይም ሽለላ ቢጤ ለመሞከር እድሉን እናገኛለና!”
“በአሁኑ ጊዜ ምን እየሠራህ ነው?”
“የተለያዩ ሥራዎች ላይ ነኝ…”
“ለምሳሌ ያህል የምትጠቅስልኝ ይኖራል?”
“ዋናው ትኩረቴ ምን መሰለህ…ስነጽሁፋችንን በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍ ለማድረግ ነው…”
“ለመልካም ገጽታ ግንባታ ማለት ነው…”
“እንደዛ ልትለው ትችላለህ፡፡”
እኔ የምለው…ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ… መልካም ገጽታ ግንባታ የሚለው በ‘ልዩ ውሳኔ’ መዝገበ ቃላት ውስጥ ከእነ ትርጉሙ ይግባልንማ! ግራ ገባንሳ! ይህንንም ያንንም ለመልካም ገጽታ ግንባታ እየተባለ…አለ አይደል… ወይ ገንቢዎቹ ይጠሩልንና ያብራሩልን፡፡
ይቺን ስሙኝማ…
“ጥፋተኛ ነህ አይደለህም?” ሲሉ ዳኛው ተከሳሹን ይጠይቁታል፡፡ ተከሳሽ ምን ቢል ጥሩ ነው…
“ክቡር ዳኛ ጥፋተኛ ነኝ ብዬ ነበር፡፡ ግን ጠበቃዬን ሳማክርው ጥፋተኛ አለመሆኔን አሳመነኝ” አለ አሉ፡፡
እኛም…አለ አይደል…‘ፊክሺን’ ቢጤ ከተናገርን በኋላ በልባችን… “አሁን የተናገርኩት እውነት አይደለም፣” ነገር እንላለን፡፡ ደግሞላችሁ… ራሳችንን እንድንሆን ሳይሆን ሌላውን እንድንመስል የሚፈልግብን ‘አቶ ጊዜው’ ደግሞ የተናገርነው እውነት መሆኑን ያሳምነናል፡፡ ይኸው ነው ጨዋታው፡፡
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 1810 times