Print this page
Saturday, 25 August 2018 13:30

የኢህዴን መሥራች አቶ ያሬድ ጥበቡ ምን ይላሉ?

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(5 votes)


  • ረጅም የሽግግር ጊዜ ያስፈልገናል፤ የተጣደፈ ምርጫ አያስፈልግም
  • የመንግስት መንግስታዊ መብት በድርጅቶች ሊነጠቅ አይገባም
  • ዲሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ ፈታኝ እንደሚሆንብን እገምታለሁ
  • ለውጡ የጥገናም የአብዮትም ባህሪ ያለው ሂደት ነው


   አንጋፋው የኢህዴን (ኋላ ብአዴን) መሥራችና አመራር የነበሩት አቶ ያሬድ ጥበቡ፤ ከ30 ዓመት በላይ በስደት ከኖሩበት አሜሪካ ሰሞኑን ወደ ሃገር ቤት ተመልሰዋል፡፡ በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ላይ ሳያሰልሱ የሃገሪቱን ፖለቲካዊ ሁኔታ በመተንተን የሚታወቁት አቶ ያሬድ፤ ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ጋር ባደረጉት ቆይታ በፖለቲካ ለውጡ ዙሪያ ተስፋና ስጋታቸውን እንዲሁም መደረግ ስለሚገባቸው ቅድመ ጥንቃቄዎች ሃሳባቸውን ሰንዝረዋል፡፡ “ወጥቼ አልወጣሁም” በሚል ርዕስ በቅርቡ ለንባብ ባበቁት መጽሐፍ ላይ የተነሱ አንዳንድ ሃሳቦችንም አብራርተዋል፡፡ እነሆ፡-


   ከረጅም ጊዜ በኋላ አዲስ አበባ ሲመጡ የጠበቅዎት አቀባበል እንዴት ነበር?
አዲስ አበባ አውሮፕላን ማረፊያ ስደርስ ያልጠበቅሁት አቀባበል ነበር የገጠመኝ፡፡ የሰፈሬ ወጣቶች (ደጃች ውቤ ሰፈር ነው ተወልደው ያደጉት) የኔ ምስል ያለበትን ቲ-ሸርት ለብሰው፣ እንኳን ደህና መጣህ የሚል ባነር ይዘው ደማቅ አቀባበል ነው ያደረጉልኝ፡፡ በዚህ ደስታም ድንጋጤም ነው የተሰማኝ። አንድ የገረመኝ ነገር አዲስ አበባ እኔ ከማውቀው አንፃር፣ አሁን አየሩ በጣም ተለውጧል፡፡ ገና ኤርፖርት ስደርስ አየሩ አፍኖኛል፡፡ ጉሮሮዬ ራሱ ተዘግቷል፡፡ አየሩ እንደተቀየረ በግልፅ ያስታውቃል፡፡ ድሮ የማውቃት አዲስ አበባ አየሯ እንዲህ አልነበረም። ሌላውን ግን ገና  ተዘዋውሬ ስላልተመለከትኩ ብዙ መናገር አልችልም፡፡
ከኢህዴን (በኋላ ብአዴን) መሥራቾች አንዱ እንደነበሩ ይታወቃል፡፡ እንዴት ነው ከትግሉ ወጥተው ወደ አሜሪካ የሄዱት? ከትግሉ የወጡበት ምክንያት ምን ነበር?
ከትግሉ በምን ምክንያት እንደወጣሁ ለኔም ለራሴም እስከ ዛሬ ግልፅ አይደለም፡፡ የተለያዩ ሁኔታዎች ናቸው እንድወጣ ያደረጉኝ፡፡ የራሴ አስተሳሰብ መለወጥ አንዱ ምክንያት ነው። ከህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ ጋር በተለይ አቶ መለስ ወደ አመራርነት ከመጡ በኋላ በኔ ላይ የነበራቸው ትኩረትና እንደ ጠላት የማየት አዝማሚያቸው ሌላው ገፊ ምክንያት ነው። በመሃከላችን የነበረው መተማመንና ፍቅር እየቀነሰ ሲመጣ፣ እነ አቶ ታምራት ላይኔ ከእነ አቶ መለስ ጋር በህቡዕ ተደራጅተው የሚሰሩበት ሁኔታ ተፈጥሮ የድርጅታችን ሚስጥሮች ወደ ህወሓት የሚሄዱበት ሁኔታ መፈጠር የመሳሰሉት ከድርጅቱ ለመውጣቴ የራሳቸውን አስተዋፅኦ አድርገዋል፡፡
የራሴ አስተሳሰብ መለወጥ አንዱ ምክንያት ነው ብለዋል፡፡ እስቲ የአስተሳሰብ ለውጡን ያብራሩት?
በአንድ ወቅት የማርክስን “ኢኮኖሚክስ ማኑስክሪፕትስ ኦፍ 1884 ሪቮሉሽንስ” ሳነብ፣ አንድ ስልተ ምርት ለእድገት የሚበቃ ቦታ እስካለው ድረስ በአብዮት የመለወጥ ዕድል የለውም የሚል ሃሳብ አገኘሁ። ደርግ ደግሞ በወቅቱ እንጭጭ የሆነ የመንግስታዊ ካፒታሊዝም ስርአት ነው ብለን አምነን ስለነበር፣ ይሄ እንጭጭ የሆነ የመንግስታዊ ካፒታሊዝም ስርአት ለማደግ ሰፊ ነው፤ስለዚህ እኛ በጦር ሃይል አሸንፈን ብንገባ ይሄንኑ መንግስታዊ ካፒታሊዝም ምናልባት በሰፋና በጠነከረ መንገድ እውን እናደርገው ይሆናል እንጂ ከመንግስታዊ ካፒታሊዝም ሞድ ውስጥ የሚወጣ ነገር አይደለም የሚል እምነት አደረብኝ፡፡ የአብዮት ጉዳይ ተጠናቋል፤ የስርአት ለውጥ ማምጣት አይቻልም የሚል ግንዛቤም ነበረኝ፡፡ ከዚህ በኋላ የአርሶ አደሩን ልጆች ወደ መስዋዕት ለመጋበዝና ኑ አብራችሁ ታገሉ ለማለት ሞራሉ አልነበረኝም፡፡ በነገራችን ላይ እኔ ይሄን ውሳኔ በወሰንኩበት ወቅት በአመራር ደረጃ ነበርኩ፡፡ የአመራሩ የመስዋዕትነት ጊዜ ያበቃበት ወቅትም ነበር፡፡ እኔ ከወጣሁ በኋላ በአመራር ደረጃ ሆኖ የተሰዋው አንድ ሰው ብቻ ነው፡፡ እሱም ጌጡ የሚባል የጎንደር ልጅ ነበር፡፡ ለውጡን በወታደራዊ ትግል ልናመጣው እንደምንችል እርግጠኛ ነበርኩ፤ ነገር ግን ስርአታዊ ለውጥ ማምጣት እንደማንችል አስቀድሜ ግንዛቤ ስለያዝኩ በጊዜ ከእንቅስቃሴው ልወጣ ችያለሁ፡፡
በኋላ ለውጡን እርስዎ እንዳመኑበት ሆኖ አገኙት?
ዲሞክራሲያዊ ስርአትን ከዜግነት ጋር አያይዤ ነው የማየው፡፡ እንደ ዜጋ ብቻ ቆሞ ለመቆጠር ፍቃደኛ የሆነ ሰው እስካልፈጠርን ድረስ ዲሞክራሲ ይቻላል ብዬ አላስብም፡፡ መሞከር ይቻል ይሆናል፡፡ በተወሰነ ሰው ተጀምሮ እየሰፋ ሃገራዊ መልክ እንዲያዝ ሊደረግ ይችላል፡፡ በኢትዮጵያ የፖለቲካ መልክአ ምድር በተለይ ምሁሩ አካባቢ ያለው እርስ በእርስ መጠላለፍ፣ገና ሁለት ቃላት ተወራውሮ መዘላለፍ ውስጥ ሲገባ ሲታይ ገና ብዙ እንደሚቀረን ያመላክተኛል፡፡ ብዙ ድክመቶች አሉን፡፡ ዲሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ ከዚህ በኋላም ፈታኝ እንደሚሆንብን እገምታለሁ።
አሁን በአገሪቱ የሚታየውን ፖለቲካዊ ለውጥ እንዴት ይገልጹታል?
እኔ እንደተረዳሁት፣ አሁን ያለው ለውጥ  በሁለት መልኩ የመጣ ነው፡፡ ከታች የህዝባዊ ንቅናቄው አለ። በተለይ በኦሮሚያ የቄሮ፣ በአማራ ክልል ጎንደር፣ ጎጃም አካባቢ የነበረው የወጣቶቹ ንቅናቄ (በኋላ ፋኖ የሚል ስም ተሠጥቶታል) አለ። በሌላ በኩል በኢህአዴግ ውስጥ በዚህ መንገድ መቀጠል አንችልም የሚሉ ሃይሎች ወጥተው ከህዝቡ ፍላጎት ጋር ራሳቸውን በማስማማት የተንቀሣቀሡበት ሁኔታ ነው የተፈጠረው። በዚህ ጉዳይ ላይ  በመፅሐፌ ውስጥ ሰፋ ያለ ትንታኔ ለማቅረብ ሞክሬያለሁ፡፡ በኢህአዴግ በራሱ ውስጥ የለውጥ ሃይሎች ይጠነክሩ ይወጡ ዘንድ፣ የህወሓትን ዘረኛ አስተሣሠብና ጭቆና እምቢ ይሉ ዘንድ ሃሣብ ለማቅረብ ሞክሬ ነበር። ይህ እንደሚሆንም እምነቱ ነበረኝ፡፡ አሁን ያ የሆነ ይመስለኛል፡፡ ይህ ለውጥ ከሁለቱም ወገን የመጣ ለውጥ ስለሆነ በጥንቃቄ መያዝ ያለበት ነው፡፡ የህወሓት የበላይ አመራሮች በዚህ ለውጥ አኩርፈው መቐሌ ከትመዋል፣ በየቦታው የሚነሱ የማንነት ግጭቶች ወይም ተራ ውንብድና እነሱ ናቸው ከመቐሌ ሆነው የሚያዙት የሚል ነገር ሲመጣ ለውጡ ከቁጥጥር  ውጪ እንዳይወጣ የሚል ስጋት ነበር፡፡ በዚህ ምክንያት ባገኘኋቸው መድረኮች ሁኔታው መስመሩን እንዳይስት የተቻለኝን ሃሳብ ሳቀርብ ነበር፡፡ መካረሩ አይጠቅምም፡፡ ለውጡ በአንድ በኩል ልክ እንደ ጥገናዊ ለውጥ ሆኖ ነገር ግን በቀጥታ ወደ ዲሞክራሲያዊ ተስፋ ሊያመራ ስለሚችል፣ ስም ሳጣለት “ጥገናዊ አብዮት” ብዬዋለሁ፡፡ ስለዚህ አሁን እየተደረገ ያለው ጥገናዊ አብዮት ነው ማለት እችላለሁ። የጥገናም የአብዮትም ባህሪ ያለው ሂደት ነው፡፡
እስከ ዛሬ እንደምናውቀው የደም፣ የተወሰኑ ሃይሎችን የማጥቃት፣ የጠላትነት፣ የሴረኝነት ሳይሆን ስርአታዊ ለውጥን በማምጣት የሚጠናቀቅ፣ ሰላማዊ ዲሞክራሲያዊ የሆነ ስርአት ልንፈጥር እንችል ይሆናል የሚል ተስፋ አለኝ፡፡ በራሴ ንባብና ግንዛቤ፣ እንደ ፈረንሣይ አይነት አብዮት ካካሄዱት ይልቅ በሽግግርና በመደራደር የሄዱት እንደ ጀርመንና እንግሊዝ አይነት ሃገሮች መሆን አለበት፡፡ እነዚህ የተሻለ የተረጋጋ ዲሞክራሲያዊ ስርአት መገንባት ችለዋል። በዚህ ለውጥ የግድ ነባር የገዥው ፓርቲ አባላት መዋረድና መደምሰስ፣ ወደ እስር ቤት መላክም የለባቸውም። ተቻችሎ ሁሉን አቀፍ ለውጥ እንዲሆን ማድረግ ይቻላል፡፡ ይሄ ለውጥ ይጎዳናል ብለው የሚፈሩም ሆነ ሂሳብ ማወራረድ እንፈልጋለን የሚሉትም ካሉበት ጥጋት ወጥተው ወደ መሃል ቢመጡ የተሻለ ነው። ለውጡንም የተሻለና ፍሬያማ የምናደርገው በዚህ መንገድ ከተጓዝን ነው፡፡
ህወሓት ውስጥ ባሉ ለውጥ ፈላጊዎችና ለውጡን በማይፈልጉ ሃይሎች መካከል አሁን የሚታያው መካረር እንዴት መርገብ ይችላል?
መካረሩ ተጠናክሮ ከሄደ ትግራይን እስከ መገንጠል ሊሄድ ይችላል፡፡ አብዛኛው በሃገሩ ያለው ወጣት ነው፡፡ የወጣት ሃገር ሆኗል፡፡ ጥናቶችም 70 በመቶ ወጣት መሆኑን ያስቀምጣሉ፡፡ ትግራይ ውስጥ ደግሞ የህወሓት እድሜ ከወጣቶቹ እድሜ ይበልጣል፡፡ የህወሓትን የፖለቲካ አስተምህሮ፣ የህወሓትን የብሄር ጭቆና ትንታኔ እየሠማ ያደገ ወጣት ነው ያለው፡፡ ይሄ ሃይል ሙሉ ለሙሉ ከህወሓት የተለየ ነው የሚል ትንታኔ ሲቀርብ እሰማለሁ፤ ነገር ግን ይሄ ለኔ አጠያያቂ የሆነ ጉዳይ ነው፡፡ በጥንቃቄ መታየት ያለበት ነው፡፡ ህወሓት በአሁኑ ሰዓት ቢያንስ ትግራይን ይወክላል። ይህ ማለት ትግራይ ውስጥ ለውጥ አይመጣም ማለት አይደለም፤ ነገር ግን በፖለቲካው መንበር ላይ ተንሰራፍቶ በትግራይ የተቀመጠው አሁንም ህወሓት ነው፡፡ አሁን ትግራይ ላይ ያለው የብረት መዝጊያ ተከፍቶ አማራጭ ሃሳብ ያላቸው ሰዎች ገብተውበት፣ ለውጡ እስኪመጣ ድረስ የግድ ከእነዚህ ሃይሎች ጋር በሠላማዊ መንገድ ነገሩ መፍትሄ የሚያገኝበትን ሙከራ ማድረግ ያስፈልጋል። በሌላ በኩል ከማኩረፋቸው ጋር በተያያዘ ለውጡን የማሣነስ፣ የማኮላሸት፣ የመበተን አቅም እንዳይኖራቸው ደግሞ አቅማቸውን መቆጣጠር ያስፈልጋል፡፡ በእነዚህ ሁለት መንገዶች ቢኬድ ነው ጥሩ ውጤት ሊመጣ የሚችለው እንጂ ዝም ብሎ ፍቅር…ፍቅር ብቻ በሚል በጎ ነገር መጠበቅ አያስፈልግም፡፡ እነሱንም ቢሆን የለውጡ ጉዳይ ስለነቀላችሁት ጥፍር፣ በብልት ላይ ስላንጠለጠላችሁት የውሃ ኮዳ፣ ስለዘረፋችሁት ገንዘብ አይደለም፤ ሁሉንም ነገር ልንተውላችሁ ፍቃደኛ ነን የሚል ማስተማመኛ ማቅረብ ያስፈልጋል። በዚያው ልክ ጥንቃቄም ያሻል። እንደኔ እምነት ህወሓት ስለመገንጠል ሲያስብ፣ በመጀመሪያ ከሱዳን ጋር ድንበር ፈጥሮ፣ በሱዳን ወደብ በኩል የባህር በር አግኝቶ ነው። ይሄን ማድረግ የሚችለው ደግሞ ከጎንደር ላይ የወሰደውን የወልቃይት መሬት ይዞ ነው፡፡ ስለዚህ ወልቃይትን በተለየ መንገድ ማየት ያስፈልግ ይሆናል። ምናልባት በወልቃይት ያለው የሰብአዊ መብት ጥሰት የፌደራል መንግስት ጣልቃ ገብነትን የሚጠይቅ ሊሆን ይችላል፡፡ ስለዚህ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ የተለየ ትኩረት ሊሰጠው ይገባ ይሆናል።
 እኔ ከትግራይ በላይ ለዚህ ለውጥ አደጋ ሊሆን የሚችል ነገር፣ ከኦሮሚያ አካባቢ ሊመጣ ይችላል የሚል ስጋት አለኝ፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩንም ሆነ የቲም ለማን የኢትዮጵያን አፍቃሪነት ስነ ልቦና፣ የኦሮሞ ብሄርተኞች ከልባቸው ተቀብለውታል ብሎ መደምደም አይቻልም፡፡ በተቻላቸው መጠን ተግዳሮት ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ አሁን እንደምሰማው፣ ወለጋ አካባቢ የኦነግ የበላይነት የነገሠበት ሁኔታ እንዳለ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ትልቁ ተግዳሮት፣ ከዚህ አካባቢም ሊነሳ ይችላል የሚል ስጋት አለኝ፡፡ ኦህዴድ የነበረውን ጥንካሬ ይዞ የለውጡ አንቀሳቃሽ ሆኖ የመቀጠል አቅሙ እንዴት ነው የሚዘልቀው? የኦነግ ሃይሎች ካኮረፉት የህወሓት ሃይሎች ጋር ሊተባበሩ ይችሉ ይሆን? የፕሮግራም የሃሳብ አንድነት ይፈጥሩ ይሆን? ከእነዚህ ጥያቄዎች አንፃር ብዙ መታየት ያለባቸው ጉዳዮች አሉ፡፡ ስለዚህ አደጋውንና ስጋቱን ቀንሶ እንዴት ነው ተስፋውን የበለጠ ማበልፀግ የሚቻለው የሚለው መታየት አለበት፡፡ ህዝቡ አሁንም ተጠባባቂ ነው፡፡ በቀበሌ ደረጃ የበደሉትን አስተዳደር ለማስለወጥ እንቅስቃሴ ሲያደርግ አናይም፡፡ ፓርቲዎች የተሻለ አቅም ለመገንባት ጥረት ሲያደርጉ እያየን አይደለም፡፡ በሌላው አለም አራት የለውጥ ወራት ብዙ የሚሠራበት ነው፡፡ ሚዲያውም ለለውጥ የጎላ እንቅስቃሴ ሲያደርግ አይታይም፡፡ የተገኘውን ዕድል በእጅ የማስገባት አቅማችን ደካማ ነው፡፡ ይሄ መሻሻል አለበት። በመፅሐፌ ውስጥ ደጋግሜ እንደጠቀስኩት፣ ለዜግነታችን ዘብ መቆም አለብን፡፡ ዜጎች በዚህ የተጠባባቂነት መንፈስ ታጥረን የምንቀመጥ ከሆነ የትም አንደርስም፡፡ እዚያው የነበርንበት ድህነት ውስጥ ነው ልንዳክር የምንችለው፡፡
በመጽሐፍዎ ውስጥ ፖለቲካችን ዜግነት ላይ የተመሰረተ መሆን አለበት ሲሉ ይሞግታሉ… አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ በዜግነት ላይ የተመሰረተ ፖለቲካ እንዴት ማምጣት ይቻላል?
የዶ/ር ዐቢይ እና የአቶ ለማ ቡድን፤ ሃገሩን ከዳር ዳር ያነሣሣው፣ የስደተኛውንም እንባና ፍቅር ያዘነበው “ኢትዮጵያ…ኢትዮጵያ” የሚለው መልዕክት ነው፡፡ የእኔ የቅርብ ዘመዴ፤ “ዐቢይና ለማን ስሰማቸው አነባለሁ” ትላለች፡፡ ለምን ስላት፤ “ኢትዮጵያን በመልካም ጎኗ ሲያነሱ የምሰማው መሪዎች ስራብ ነው የኖርኩት እና ከዚህ ረሃቤ የተነሣ ይመስለኛል” ትለኛለች፡፡ ይሄ የበርካታ ዜጎች ስሜት ነው፡፡ በዜግነት አስተሳሰብ የሚያምነው አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ስሜት ነው ይሄ። በሌላ በኩል፤ የቡድን የብሄር ማንነት ጉዳይ ደግሞ በየቦታው አለ፡፡ በተለይ በደቡብ፣ ኦሮሚያ እንዲሁም በሌሎቹም አካባቢዎች ይታያል፤ ይህ አካሄድ፡፡ ካወቅንበት በተለይ አሁን ያለውን ሁለቱን ያቻቻለ የለውጥ አመራር ይዘን ወደፊት መሄድ ይቻለናል፡፡ ነገር ግን የዜግነት አስተሳሰብ በሃገራችን እንዲጎለብት የበለጠ ውይይት፣ ጥናት፣ ምክክር ያስፈልጋል። እስካሁን በዚህ ደረጃ ውይይት አልተጀመረም፡፡ የሚደረጉት ንግግሮች በሙሉ የታሪክ ትርክት ላይ ያተኮሩ ሆነው ነው የምናገኛቸው፡፡ አሸጋጋሪ ሃሳብ ያላቸው ሰዎች ሃሳባቸውን አቅርበው፣ በዚያ ሃሳብ ላይ ውይይትና ክርክር ማድረግ አልጀመርንም፡፡ አሁን ያለፈውን እየተረክን መቆዘም ላይ ነው ያለነው፡፡ ከዚህ ወጥተን ወደፊት የሚያሻግሩን ሃሳቦች ላይ መነጋገር መጀመር አለብን፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እያየለ የመጣውን የአማራ ብሔርተኝነት ጉዳይ እንዴት ይመለከቱታል?
በእርግጥ የአማራ ብሔርተኝነት የመጣው ከተገፊነት ነው፡፡ ህወሓት ስልጣን ይዞ በቆየባቸው ያለፉት 27 ዓመታት አማራን እንደ ጨቋኝ በመቁጠር የተለያዩ ትርክቶች ሲነገሩ ነበር፡፡ በአማራው ላይ በተለያዩ አካባቢዎች ሲፈፀሙ የነበሩ ማፈናቀሎችና ግድያዎችን እንደ ማዕከላዊ መንግስት ያገባናል ብለው በየትም ቦታ ድርጊቱን ለማስቆም ያልሞከሩበት፣ አማራ ክልል ደግሞ በአብዛኛው ቀዳማዊ ማንነቴ ኢትዮጵያዊነት ነው በሚል ያምን የነበረ በመሆኑ ከሚያስተዳድረው ብአዴን ጋር ምንም አይነት የመንፈስም የአስተሳሰብም አንድነት ያልነበረበት እና የህወሓት መሣሪያ ናቸው የሚል እምነት በሰፊው ህዝብ ውስጥ የነበረበት፤ ያ ደግሞ የክልሉ አቅም ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ጫና ያሳረፈበት አሳፋሪ የሆነ ጊዜ ነው ያለፈው፡፡ ከትምህርት መስፋፋት ጋር ተያይዞ የአርሶ አደሩ ልጆች መማራቸውና ሌላውን ሲመለከቱ በውስጣቸው የመገለልና የቁጭት መንፈስ ያሳደረው ብሶት ነው፤ አሁን የአማራ ብሔርተኝነትን የፈጠረው፡፡ በጣም የሚያሳዝነው፤ ይሄ የብሔርተኝነት ስሜት ራሱን ወደማደራጀት ባደገበት ወቅት ላይ በኢህአዴግም ሆነ የለውጡ ሃዋሪያ ሆነው በወጡት የኦህዴድ እና የብአዴን መሪዎች፤ ኢትዮጵያን ቀዳሚ ማድረግ የጀመሩበት ወቅት ላይ መሆኑ ነው። ተስፋ የሚሰጠኝ ይሄ አዲሱ የአማራ ብሔርተኝነት እንቅስቃሴ ከብአዴን የለውጡ ሃይሎች ጋር ተቀናጅቶ ለመስራት የሚያሳየው ፍላጎት አለ፡፡ ብአዴን ራሱ መደራጀታቸውን ተቀብሎ አዳራሾችን በመፍቀድ፣ ፀጥታ በማስከበር እየተባበራቸው መሆኑ፣ በቀጣይ ይህ ትብብርና መተጋገዝ ወደ መግባባትና ከተቻለ ወደ አንድ ድርጅታዊ የጋራ አቅም ሊሰባሰቡ ከቻሉ የክልሉን አስተዳደር ለማሻሻል ሚና ሊኖራቸው ይችላል፡፡ በሌላ በኩል፣ ጠንከር ካለው የኦሮሞ ብሄርተኝነት አንፃር ሲታይ፣ የአማራው መደራጀት ሊጠቅም ይችላል። በዚህ መልኩ ነው የማየው ጉዳዩን፡፡ አሁን ያለው የአማራ ብሔርተኝነት ኢትዮጵያዊነትን መፈታተን ግን የለበትም፡፡ እነሱም ከብሶታቸው ወጥተው ወደ ኢትዮጵያዊነት ይመለሳሉ የሚል ተስፋ ነው ያለኝ፡፡
በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ እንደሚካሄድ የሚጠበቀው አገራዊ ምርጫ መንግስት በገባው ቃል መሰረት ነጻ ተዓማኒና ፍትሃዊ ይሆናል ብለው ያምናሉ?
እኔ አሁንም የሚያሳስበኝ በሁለት ዓመት ውስጥ ወደ ዲሞክራሲያዊ ምርጫ እንገባለን የሚለው ጉዳይ ነው፡፡ በደንብ ታስቦበታል ወይ የሚል ጥያቄ አለኝ። የሽግግር ዕድል ሲገጥመን ይሄ አራተኛው ነው፡፡ የኢትዮጵያ ትልቁ ችግር ደግሞ የተገኘውን የሽግግር ሂደት፣ በስነ ስርአት ለማስቀጠል አለመቻል ነው። ወይ በወታደራዊ የበላይነት አሊያም በአንድ ቡድን የበላይነት የሚጠናቀቅበት ሁኔታ ነው ሲፈጠር የኖረው። የዚህ ዋነኛ ምክንያት ደግሞ የተገኘውን እድል ለመጠቀም ሁሉንም ያካተተ ረጅምና የሽግግር መድረክ አዘጋጅተን ስለማናውቅ ነው፡፡ ቋሚ የሆኑ የሃገሪቱ ጉዳዮች ተነስተው ተከራክረንባቸው ስለማናውቅ ነው፡፡ ህገ መንግስት(constitution) “ኮንስቲትዩት” ማድረግ ወይም ማካተት ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ያሉት ሃሳቦች ተጋጭተው፣ ተፋጭተው ሁላችንም ያግባባ ሰነድ የመፍጠር ጉዳይ ነው፡፡ ያንን ለማድረግ አሁንም ፍቃደኛነት አላይም፡፡ ከዶ/ር ዐቢይ በኩልም የሰማነው፤ ኢህአዴግ ከ2 አመት በኋላ ምርጫውን ለማሸነፍ እየተዘጋጀ ነው፤ ተቃዋሚዎች ብትዘጋጁ ይሻላችኋል የሚል መልዕክት ነው፡፡ ነገር ግን አሁን ላይ ሌላው ትተን ኦሮሚያ ውስጥ ብቻ ያለውን መራኮት ስንመለከት፣ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ምርጫ ቢካሄድ ማን ነው ሃቀኛ ነው ብሎ የሚቀበለው? እንዴት አድርጎ ተዓማኒ፣ ነፃና ዲሞክራሲያዊ መሆን ይችላል? እነዚህን ስመለከት ለኔ የሚታየኝ፣ ምርጫውን አዘግይተነው፣ ሁሉም የፖለቲካ ሃይሎች የሚሰባሰቡበት አንድ የሽግግር ምክር ቤት ቢቋቋም የሚል ነው፡፡ ዶ/ር ዐቢይና አቶ ለማ፤ ለኢትዮጵያ የተሰጡ እንቁ መሪዎች ናቸው ብዬ ነው የማስበው፡፡ እነሱ የመንግስታዊ አመራሩን ይዘው፣ በስራቸው ግን ይህ ምክር ቤት ተቋቁሞ፣ ነፃ ተቋማትን የማደራጀት፣ የህግ ሰነዶችን የማዘጋጀት ስራ ቢሠራ ጥሩ ነው እላለሁ፡፡ ምናልባት ይህ ሂደት አምስት…ሰባት አመት ሊፈጅ ይችላል፡፡ ግድ የለም ይፍጅ ነገር ግን የሃገሪቱ ፖለቲካ በቋሚነት የሚስተካከልበት ሁኔታ ነው በዚህ ሂደት የሚፈጠረው፡፡ እነ ዶ/ር ዐቢይ አሁን ከሚያሣዩት ሆደ ሰፊነትና ከያዙት ራዕይ አንፃር፣ ጥሩ የሽግግር ጊዜ መሪዎች ናቸው። እነሡ መንግስቱን ይምሩ፣ ፀጥታውን ያስከብሩ፣ ሃገሩን ያረጋጉ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ይህ የሽግግር ም/ቤት ተቋቁሞ በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ክርክሮች ውይይቶች ተደርገው፣ የሚያሰሩን የጋራ ህጎችና ነፃ ተቋማት ይደራጁ። ይሄ ሂደት በጣም አስፈላጊ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ረጅም የሽግግር ጊዜ ያስፈልገናል፤የተጣደፈ ምርጫ አያስፈልግም።
በአሁኑ ወቅት በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎች ወደ ሃገር ቤት እየተመለሱ ነው፡፡ የእነዚህ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሃገር ቤት መሰባሰብ ምን አንደምታ ይኖረዋል?
በመጀመሪያውኑ የህወሓት ባዕድ የሆነ አስተሳሰብ ነው እንዲወጡ ያደረጋቸው እንጂ መሰደድ አልነበረባቸውም፡፡ አሁን መመለሳቸው ትክክል ነው። ግን ሲመለሱ ደግሞ ህግና ስርአት ወዳለበት ሃገር መመለስ መቻል አለባቸው። በአንድ በኩል በህግና በስርአት ለመተዳደር ተስማምተው እንመለሳለን ካሉ በኋላ በሌላ በኩል የአስተዳደር ስራን በእጃቸው ለማስገባት የተለያየ እንቅስቃሴ የሚያደርጉ ከሆነ አደገኛ ነው፤ መፈቀድም የለበትም፡፡ መንግስት አለ። ህግና ስርአት ማስከበር አለበት፡፡ የመንግስት መንግስታዊ መብት በድርጅቶች ሊነጠቅ አይገባም፡፡ መፈቀድም የለበትም፡፡ ቁጥጥር መኖር አለበት፡፡ በሌላ በኩል ነፃ ተቋማት ፈጠራ ላይ ያተኮረ ውይይትና ክርክር ተጀምሮ፣ ድርጅቶች ስራ እንዲሰሩ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
ወደ ሃገር ቤት የምንመለስ ሰዎችና የፖለቲካ ድርጅቶች በመጀመሪያ የሃገራችንን ሁኔታ በደንብ መረዳት ያለብን ይመስለኛል፡፡ ከሃገር ወጥተን በነበርንባቸው 20 እና 40 ዓመታት ውስጥ በሃገሪቱ ያለው ነባራዊ ሁኔታ ምንድን ነው የሚለውን ጊዜ ወስደን መረዳት ይኖርብናል፡፡ እኔ በ1997 ዓ.ም መጥቼ ነበር፡፡ አሁን ከ13 አመት በኋላ ስመጣ፣ አዲስ አበባ ውስጥ ብዙ አይነት የስነ ልቦና ለውጦችን እያየሁ ነው፡፡ ብዙ ነገር ለማጥናትና ሆደ ሰፊ ለመሆን ፍቃደኛ መሆን አለብን፡፡
በመፅሐፍዎ ላይ የወልቃይትን ጉዳይ በተመለከተ ሰፊ ትንታኔ አቅርበዋል፤ በአማራ ክልል ለተቀጣጠለው ህዝባዊ አመፅ መነሻ የሆነው የወልቃይት ጥያቄ እንዴት ነው መፈታት ያለበት ይላሉ?
በ1971 እና 72 ህዝብን በማደራጀት ስራ ወልቃይት አካባቢ ነበርኩ፡፡ አካባቢውን አውቀዋለሁ፡፡ ወልቃይት “ወልቀጣይ” ነው፤ አማርኛም ትግርኛም ይናገራል። በሥነ ልቦናው ጎንደሬ ነው፡፡ ይሄን በግጥሞቹ በፉከራው፣ በሽለላው ይገልጣል፡፡ ህወሓት በ1972 መጨረሻ ላይ ከኤርትራ ግንባሮች ጋር ተጣልቶ ስለነበር ወደ ውጭ መውጫ ስለፈለገ ወልቃይትን ወረረ፣ ቦታውን ተቆጣጠረ፤ ከዚያ በኋላ ብዙ የትግራይ ተወላጆችን እያመጣ ቦታው ላይ አስፍሯል። ስልጣን በያዘ ማግስት ደግሞ የሠራዊት ቅነሣ እንዲያደርግ ሲገደድ፣ ከ30 ሺህ ጦር በላይ ደንሻ የሚባል አካባቢ አስፍሯል፡፡ ህወሓት በእነዚህ እርምጃዎቹ ያንን አካባቢ ትግሬ አድርጎ የመግዛት ፍላጎት እንዳለው አሳይቷል። በሌላ በኩል ደግሞ የወልቃይት የማንነት ጉዳይ ታሪካዊ ሃቁ አለ። አሁን ሪፈረንደም ሊደረግ ይችላል ሲሉም ይደመጣል ነገር ግን ማን ነው በህዝበ ውሳኔው የሚሳተፈው? እነሱ ባለፉት 35 ዓመታት ያሰፈሩት ነው ስለ ወልቃይት የሚወስነው ወይንስ ነባሩ ወልቃይት የሃገሩ ነዋሪ ነው? ለኔ የሚታየኝ በግድ ትግሬ የማድረግ ሰብአዊ ረገጣው አሁን መቆም ስላለበት፣ አካባቢው በጠቅላይ ሚኒስትሩ ቀጥተኛ አስተዳደር ስር ለተወሰነ ጊዜ መደረግ አለበት፡፡ ከዚህ በኋላ ምንድን ነው መካሄድ ያለበት የሚለው ለውይይት ቀርቦ ህዝበ ውሳኔ የሚደረግ ከሆነም ማን ነው በህዝበ ውሣኔው መሳተፍ የሚችለው? በቅርብ ጊዜ መጥቶ የሰፈረው ይሳተፋል? ወይንስ ነባሩ ብቻ ነው የሚሣተፈው? የሚለው መወሰን አለበት፡፡ ወልቃይት በፌደራል ልዩ ቁጥጥር ስር መዋል አለበት፡፡
በመፅሐፍዎ ውስጥ የቀድሞውን ጠ/ሚ አቶ መለስ ዜናዊን እንደሚያውቋቸው ገልጸዋል…
አዎ! በእርግጥ አቶ መለስን አውቀዋለሁ፡፡ አንድ ት/ቤት ነው የተማርነው፡፡ እኔ ሚያዚያ 1 ስወለድ፣ እሱ ግንቦት 1 ነው የተወለደው፡፡ በዕድሜም እኩያ ነን፡፡ አብዮቱ ሲመጣ ሁለታችንም የአፄ ኃይለስላሴ ዩኒቨርስቲ የሁለተኛ አመት ተማሪዎች ነበርን፤ ያኔ ብዙም ትውውቅ የለንም፡፡ እሱ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ህብረት ተመራጭ ስለነበር አውቀዋለሁ፡፡ እልኸኛ ሰው እንደነበር አውቃለሁ። ለምሳሌ ከዊንጌት መጥተው አሮጊቷ ቤት የምንለው አለ፤ እዚያ ቴኒስ ወይም “ቤሊየርድ” ሲጫወቱ ካላሸነፈ ወደ ማደሪያው አይሄድም ነበር፡፡ አስታውሳለሁ፤ በዚህ እልህ 19 ቁጥር አውቶቡስ አምልጧቸው በእግራቸው ይሄዱ ነበር፡፡ በኋላም ከእነ አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ ጋር ካርታ ቁማር ይጫወቱ ነበር፡፡ እዚያም ላይ ካላሸነፈ አያቆምም። የማይበገር ሰብዕና አለው፡፡ በሌላ በኩል፤ የትግል አጋሮቹ ጦርነት ላይ ፈሪ ነበር ይላሉ፡፡ ምናልባት ራሱን ኋላ ላገኘው አመራር እያዘጋጀ ነው ወይ የኖረው የሚል ጥያቄ ያስነሣል፡፡
አቶ መለስ በርካታ መፅሐፍትን አንብቧል። በእንግሊዝኛ እውቀቱም የሚታማ ባለመሆኑ በርካታ መፅሐፍትን አንብቧል፡፡ ብሩህ አዕምሮ አለው፡፡ በእርግጥ ይህን ብሩህ አዕምሮ ለምን ዓላማ ተጠቀመበት የሚለው ብዙዎችን የሚያከራክር ነው። አንድ ከ7 መቶ ኪ.ሜ ርቀት የብሔርተኛ ድርጅት እየመራ የመጣ ሰው፣ መሃል ሃገር ገብቶ የ60 ሚሊዮን ህዝብ ስልጣን ተረክቦ፣ ጠብቆ ለማቆየት ማለፍ የነበረባቸው ሂደቶች ያሉ ይመስለኛል፡፡ በዚያ ሂደት ውስጥ ኦነጎችን በአስከፊ ሁኔታ እንዲባረሩ አድርጓል። በዚህም ለብዙዎች ሞት ምክንያት ሆኗል፡፡ ታምራት ላይኔ ሌሎች ኢትዮጵያውያን ዘንድ የሚነሱ ጥያቄዎችን ማንሳት ጀምሯል ብሎ ባሰበ ጊዜ፣ ጓደኝነታቸውን ወደ ጎን ትቶ ወደ እስር ቤት ልኳል፡፡ 6 በመቶ ያህል የሃገሪቱ ህዝብ ድርሻ ያለው ሃይልን የሚመራ፣ እኩል ስልጣኑን ለማስጠበቅ ማድረግ ያለበትን ያደረገ ሰው ነው፡፡ እነዚህ ሁኔታዎች ሰውየው ችሎታም ቢኖረው ከመጣበት ድርጅት ባህሪ የተነሣ የበላይነትን አስጠብቆ ለማቆየት ባደረገው ጥረት፣ የነበረውን አቅም ለገንቢ ዓላማ ማዋል ያልቻለ ሰው ነው፡፡
ከዚህ በኋላ እርስዎ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ በምን መልኩ ለመሳተፍ አስበዋል?
በግልፅ የማውቀው በፓርቲ ፖለቲካ ውስጥ እንደማልገባ ነው፡፡ ለዶ/ር ዐቢይ ባለኝ ድጋፍ የማማከር አስተዋጽኦ ሊኖረኝ ብችል ደስ ይለኛል። ምክንያቱም የፖለቲካ መልክአ ምድሩን፣ ተዋናዮቹን፣ አካባቢዎቹን አውቃቸዋለሁ የሚል እምነት አለኝ፡፡ ከዚህ አንፃር በማማከር ለሃገሬ አስተዋፅኦ ማድረግ ብችል ደስ ይለኛል፡፡ ይሄ እንግዲህ የኔ ስሜትና ፍላጎት ነው፡፡


Read 6314 times