Print this page
Saturday, 25 August 2018 13:24

ልዕለ ኃይል

Written by  ከቃል ኪዳን
Rate this item
(15 votes)

 የሆነ ቀን፤ በሆነ ምክንያት ድንገት ከመሰሎቹ ተለይቶ ሽቅብ እንደ ሸንበቆ የተመዘዘ ቤት፡፡ ቤቱን ከላይ የሲሚንቶ ወለል፤ ከታች የአቡጀዲ ኮርኒስ የሸፈናቸዉ ወፋፍራም ወራጅ እንጨቶች፣ ላይና ታች አድርገዉ፣ ሁለት ቦታ ከፍለውታል፡፡ አጠቃላይ የቤቱ እርዝማኔ ከአራት ሜትር ያልፋል። በዚህ ሎጋነቱ ምክንያት የታችኛው ቤት ሜትር ከሰማንያ የሚሆን ተደራራቢ ብፌ፤ ጨቅጫቃ ሠካራም አባት፤ ተራጋሚ እናትና ቅናተኛ  ሴት ልጅን ሲይዝ፣ ተፈጥሮዉ ለፎቅ የሚያደላው ፎቃ ፎቅ ቆጥ ደግሞ ሁለት ሜትር የሚረዝም ቁም ሣጥንና መለስተኛ አልጋ ከጋድሚያ ጎረምሣ ጋር ይዟል፡፡
የተጋደመው ጎረምሳ አልፎ አልፎ ያንኮራፋል። በቀትር ጸሐይ የጋለው ጣርያ በፈጠረው ወበቅ ምክንያት የደረበውን የአልጋ ልብስ  አውልቆ መሬት ጥሎታል፡፡ የአልጋ ልብሱን አውልቆ መሬት የወረወረዉ ስለሞቀው ብቻ ነው ወይስ የአልጋ ልብስ ለአልጋ እንጂ ለሰዉ አይደለም ብሎ አስቦ? ደግነቱ የአልጋ ልብሱ ከአልጋ ላይ ወርዶ ሲሚንቶ ላይ ቢፈጠፈጥም ምንም አልሆነም፡፡ የሆነው ነገር ቢኖር እንኳን ምንም አላለም።
ለሰዓታት ጎኑን እየቀያየረ ተኝቶ የነበረው ጎረምሳ አንዳች ነገር አልጎምጉሞ በጀርባዉ ተንጋለለ፡፡ አንድ እጁን ያበጠ የሞባይል ባትሪ የመሰለ ሆዱ ላይ አድርጎ ሌላኛዉን ተንተራሰና እግሮቹን እንደ ሙት ከንፈር በትግል ገጠማቸው። ጥቁር ዞማ ጸጉሩ፣ የጎፈረው ጺሙ፣ ሰማያዊ ጃፖኒና ቁምጣ እንዲሁም አንድ እግር ካልሲ ከሸፈነው አካሉ ውጪ የቆዳው ቅላት ለፈረንጅ እሩብ ጉዳይ ያደርገዋል፡፡ ከአባቱ የወረሰው ቁንጅና እና ከእናቱ የወረሰው ቁመና አልጋው ላይ ተዝረክርኮ ይታያል፡፡
ቁንጅናው እሱን ለማሞካሸት ከሚውለው በላይ ለእህቱ ማንጓጠጫነት ስለሚያገለግል አንድ ቀን ከእንቅልፉ ሲነቃ መልከ ጥፉ እንደሚሆን ወይ እህቱ ከእሱ የበለጠ ቆንጆ እንደምትሆን ተስፋ በማድረግ፣ ቁንጅናውን ይዞ እንደ ‹ልዕልት አዉሮራ› ይተኛል። በርግጥ ቆንጆ እህቱ ከግጦሽ መሬት በተሻለ ሁለት ተጎራባች ክልሎችን ሊያጣላ የሚችል ውበት አላት። የጉለሌ ሰውም ይህን ሊክድ አይችልም፡፡ ነገር ግን የጎረምሳው የወንድ ቆንጆ መሆን ውበቷን ደበቀባት፡፡ የጉለሌ ሰውም ለእሱ አደላ - ዘሪቱ ብቻ ናት ‹ደግሞ የወንድ ቆንጆ ብላ› በነገር ሸንቆጥ ያደረገችላት፡፡
እህቲቱ ፊት ለፊቷ ስታየው ሆዷን እስኪያማት ስለምትቀናና ንዴቷን መቆጣጠር ስለማትችል፤ ውሃ ወፈረ ብላ ነገር ትፈልገዋለች፡፡ እሱም ይሄ ነገሯ ስለሰለቸዉ ከቆጡ ሳይወርድ ቀኑን ሙሉ ይተኛል። ጎረምሳዉ አብዝቶ ቢተኛም እንደ ጸሎት ሽቅብ ወደ ላይ ወጥቶ አንጀቱን የሚያደብነው የእህቱ አሽሙር፤ ተኝቶም የእህቱን ውበት መጋረዱን እንደቀጠለ አረዳዉ፡፡ የጉለሌ ሰው እህቱን የቆንጆው ልጅ እህት እንጂ ቆንጆ ብሎ ሙሉ እውቅና ለመስጠት አሻፈረኝ እንዳለ ተገነዘበ፡፡ ነገሩ ሲያስመርረው አንድ ቀን እራሱን ሊያጠፋ ወሰነ፡፡ ውሳኔውን ከማጽናቱ በፊት ግን ‹ደግሞስ የጉለሌ ምላስ መች ሙት ያስተኛል?› ሲል አሰበ። ቆንጆዉ ወንድምሽ፤ በሞተው ቆንጆ ወንድምሽ ላለመተካቱ ማረጋገጫ አጣ። በቁንጅናው እንደ ሴት የምትቀናበት እህቱ በኋላ ሞቶም አልተዉሽ አለኝ ብላ ተከትላው ብትሞትስ? ከእሱ ለመቆንጀት ስትል የሚጠላው ቅናቷን ይዛ ብትከተለውስ? የሞት ዓለም አጥንትን የሚያሳይ መስታወት ፊት ለሰዓታት ተገትራ፤ የአጥንት እጀታ ያለዉ ብሩሿን የአፈር ‹ሜካፕ› ዉስጥ እያጠቀሰች፣ አጥንት ፊቷን ስትቦርሽ ብትዉልስ? በዚህ ምድር እሷን ላለማየት ሲል ቆጥ ላይ ተኝቶ እንደሚውለው፣ እዛም ከጉድጓዱ ሳይወጣ ሊውል ነዉ?
የጎረምሳው ዉስጣዊ አካል ቆዳዉ ከሸፈነዉ ዉጫዊ አካሉ የበለጠ እጅግ ያምራል፡፡ ይህንን ማንም አያውቅም፡፡ የጅማቶቹ አደራደር፣ በከበረ ደንጋይ የታነጹት አጥንቶቹ፣ የደሙ ጥራትና አፈሳሰስ፣ ያሬዳዊዉ የልብ ምቱና እውነተኛ የልብ ቅርጽ ያለው ልቡ ድንቅ ናቸዉ፡፡ እንኳን የጉለሌ ሰዎች ይህን አላዩ! እንኳን እህቲት ይህን አላወቀች!።
የተኛው ጎረምሳ ማንኮራፋቱን አቁሞ አንዳች ነገር አልጎመጎመና የጥርሱ ጫፍ እስኪታይ ድረስ ፈገግ አለ፡፡ ከተጨፈነው የዓይኑ ክዳን ጀርባ አንስቶ ጠባብ ግንባሩን እስኪሞላ ድረስ ብርሃን ሆነ፡፡ በዚህ ሰዓት ተመሳሳይነት ያለው ህልም ማየት ከጀመረ ዛሬ ሃያ አንደኛ ቀኑ ነው፡፡ ህልሙ እንደ‹ፕሮጀክተር› ከዓይኑ ክዳን የሚነሳ ጨረርን ተጠቅሞ ግንባሩ ላይ በተወጠረ አቡጀዴ ላይ የማያውቃቸዉ የቅድመ አያቱን ምስል ይፈጥራል።
ቅድመ አያትየዉ ‹ፕሮጀክተሩ› እስኪግልና ምስልን ከድምጽ ማስተላለፍ እስኪጀምር ከቦርሳቸው ትንሽዬ የፊት መስታወት አውጥተዉ ተመልክተው፣ ከንፈራቸውን በምላሳቸው ማራስ ጀመሩ፡፡ ጎረምሳው ቅድመ ወላጅነታቸውን የተቀበለው ከቅናተኛ እህቱ አንድ የሚያደርጋቸዉን ይህን መስታወት የማብዛት ነገራቸውን ካየ በኋላ ነዉ፡፡ የተኛው ጎረምሳ ሰርኑ ጋ የተቀመጠው ‹ፕሮጀክተር› የሚያወጣው ድምጽን (የሚያቃጥል) ሽሽት አንዴ ተገላበጠና ተዘርሮ ተኛ። አያቱ መኳኳላቸውን ማብቃታቸውን ሲያይ ደስ አለው። ዛሬ የመጨረሻዉ ቀን በመሆኑ የኳስ ሜዳን ባለንብረትነት የሚያረጋግጥ ደብተር የት እንዳለ እንዲነግሩት እንደሚያሳምናቸው ለራሱ ቃል ገባ፡፡
‹‹የልጅ ልጄ ዛሬ የመጨረሻውን ሰባት ትውልድ፤ ማለት እስከ አንተ ድረስ ያለውን ትውልድ ኃይልና ኃላፊነት አሳውቅሀለዉ፡፡ እስከዛሬ የነገርኩህ የ‹ሃያ›፤ ሰባት ትውልድ፤ የእኛንም ‹ሃያ አንደኛ›፤ ሰባት ትውልድ ጨምሮ እስከ አባትህ ድረስ የመቶ አርባ ስድስት ትውልዶች ህልም ያለዉ ባንተ እጅ ነው፡፡ የአንተን መወለድ በተስፋ ስንጠብቅ ነበር።››
‹‹ታድያ አባቴ ‹የሬሣ ብዛት! ሬሣ! ዝም ብለህ ተጋደም ብቻ!……ኧ! እናቴ ደግሞ ‹ምነው አንተንስ በደፋህ!› ያቺ መስታወት ፊት…..ይቅርታ ያቺ እህቴ ደግሞ አንድ ቀን ተደብቃ የጊዮርጊስ ምስል ፊት ተንበርክካ ‹ብሩክታዊትን ያዳንክ ምናለ ከዚህ ድራጎን እኔን ብታድነኝ! ፈረስ ጭነህ፣ ጦር ወድረህ መምጣት ባትችል እንኳን ምናለ በስምህ ያለውን ቢራ ሲጠጣ መርዝ አድርገህ ብትገልልኝ› ሲሉ ሰምቻቸኋለሁ፡፡ እኔ እስከማውቀው የኔን ሞት እንጂ መኖር የሚፈልግ የለም፡፡›› ቅድም አያቱ መስታወት ላይ ተተክለው የሚለውን አልሰሙትም፡፡ ድምጽ ሲያጡና ዝምታ እንደሰፈነ ሲገባቸው ደንገጥ ብለው፤
‹‹ዛሬ አንድ ሚስጥር እነግርሀለው፡፡ የአባትህ አለሌ ሠካራምነትና የእናትህ ተሳዳቢነት ምክንያት ከነገዱ የደህንነት ሥራ እረፍት ወስደው አንተን እንዲንከባከቡ በመደረጋቸው ነው፡፡ እህትህ ደግሞ መስታወት ላይ ተገትራ የምትውለው ሥራ ፈት ሆና ሳይሆን በነገዱ የደህንነት ክፍል በተሰጣት ግዴታ መሠረት ነው፡፡ ደግሞ መስታወቱ ተራ የፊት መስታወት ሳይሆን እጅግ የረቀቀ ‹የኮምፒዩተር ቴክኖሎጂ› ነዉ››
‹‹ሂሂሂ-- አባቴና እናቴ ደህንነቶች? የሞባይል ስልክ ላይ ስም በደንብ መመዝገብ የማትችለው እህቴ የረቀቀ የፊት መስታወት ኮምፒዩተር ተጠቃሚ? ደግሞ የምን ነገድ ነዉ የምታወሪው ቅድመ አያቴ? ለምን ዝም ብለሽ ነገድ፣ ነገድ ትይኛለሽ? የማይመስል ነገር አታዉሪ!›› ቅድመ አያት መስታወት ላይ አቀርቅረዋል፡፡ ዝምታው ሲበረታ ደንገጥ ብለው፤
‹‹ይቅርታ ‹ኢ ሜይል› እያነበብኩ ነበር፡፡ እና እንዳልኩህ የደህንነት ሥራ ‹ፈን› ነዉ፡፡ እኔና ወንድ አያትህ ቶሌራ ብዙ ነገሮችን አሳልፈናል፡፡ ነግሬህ ከሆነ በነገዱ ተመርጬ ለቶሌራ…››
‹‹ነገድ፣ ነገድ አትበይኝ አልኩሽ እኮ! ሳምንቱን ሙሉ ነገድ፣ ነገድ እያልሽ ስትጨቀጭቂኝ ከረምሽ። ቆይ ብሔር ለማለት ፈልገሽ ነዉ?›› በጩኸት አቋረጣቸው
‹‹የጠፋው ነገድ ነዋ! የነገርኩህ ነገድ፡፡ እንደ አየር የማይታየውና የማይዳሰሰው ነገድ፡፡ ግን ኢትዮጵያን ብሎም አፍሪቃን ከጥፋት የታደገውና እየታደገ ያለው ነገድ ነዋ! ባለፈዉ እንዳልኩህ……ኧ! ለምሳሌ አንተ ስትወለድ ህጻናትን እንደ ሄሮድስ እየፈጀ የነበረውን ኮለኔል መንግሥቱን እንድትሸሽ የጉለሌ ሰው እናትህን ‹ሰናድር ግቢ ካለ አህያ አንዱን ተዉሳ እንድታስጭንና አባትህ ደግሞ እራስ መስፍን ስለሺ ግቢ ካለ ዛፍ አንድ እንጨት መርጦ ምርኩዝ አበጅቶ እየመራ በሞያሌ አድርገው ወደ አሜሪካ ይሰደዱ ሲል› ነገዱ ግን እናትህና አባትህ ሳይሆኑ መንግስቱ ፈርጥጦ እንዲጠፋ አደረገው››
‹‹እና ከአሜሪካ አስቀራችሁኝ?››
‹‹አዎ የልዕለ ኃይል ስደትን በፍጹም ልንደራደርበት አንችልም! ከባለ ካባና ባለመብረቅ የተረት ‹ሱፐር ማኖቻቸዉ› አንዱ እንድትሆን በፍጹም ልንተውህ አንችልም!››
‹‹ቆይ ጀግና ከፈለጋችሁ ለምን መንጌን አባረራችሁት፡፡ እኔ አሜሪካዬ ብሄድ ይሻለኝ ነበር።››
‹‹ባናባርረው እኮ ያዘምትህ ነበር?›› ቅድም አያት ጮኹ፡፡ ‹‹ደግሞ ጀግና ቢሆን አይፈረጥጥም ነበር፡፡››
‹‹ፈርጥጦ እኮ አይደለም አያቴ! ስብሰባ ብለዉ ልከዉት ሸወደዉት እኮ ነው ሂሂሂ፡፡››
‹‹ልጄ ስለሱ ጉዳይ ብዙ የማታውቀዉ ነገር ስላለ እንተወዉ፡፡ ዋናው እሱ ከአገር መውጣቱና አንተ አለመዝመትህ ነው››
‹‹ቆይ ጀግና እንድሆን ከፈለጋችሁ እኮ እንደውም መዝመት ነበረበኝ፡፡ የ‹ስፓርታን› ፊልም አላየሽም አያቴ?›› ቅድመ አያቴ ማለት ስላደከመው አያቴ እያለ መጥራት ጀምሯል፡፡ ‹‹……በቃ መዋጋት፣ መደባደብ፣ ስፖርት መሥራት እና ቀኑን ሙሉ መቀጣቀጥ፡፡ እንደውም በቡጢ ወይ በሰደፍ ፊቴን ቢመቱኝ እኮ ፊቴ ተጣሞ ያቺ እህቴ ብቸኛዋ ቆንጆ ትሆንና እኔም ከነገር አርፍ ነበር፡፡›› ቅድመ አያት መስታወት ላይ ተተክለዋል፡፡ ዝምታው ሲሰማቸዉ ደንገጥ ብለው፤
‹‹ኧ ምን መሰለህ የነገዱ መተዳደሪያ ደንብ ላይ ወንድም በወንድም አንገት ሰይፍን አይለማመድም ይላል፡፡ ቂቂቂ ስለ ልምምድ ሲነሳ ምን ትዝ አለኝ መሰለህ! ጠራ እያለሁ አንዲት ሴት ፍቅረኛዬን ቀማችኝ…››
‹‹የት ነው ደግሞ ጠራ? ጠራ የሚባል አገር አለ እንዴ?›› አቋረጣቸው፡፡ ቅድመ አያት ግን እንዳልሰሙት ቀጠሉ፡፡
‹‹ፍቅረኛዬን ቀማችኝና ንድድ ብዬ እረጅም ዱላ ያዝሁና አበቡ የምትባል የአክስቴን ልጅ አስከትዬ እቤቷ ድረስ ሰተት ብዬ ሄድሁ፡፡ ከዛም በሯን በርግጄ ገብቼ ገባሁና በዛ ትልቅ ዱላ ልላት ስል ዱላው እሷን ሳይነካት ግድግዳ እየገጨ ይመለስ ጀመር። ስሰነዝር ግድግዳውን ገጭቶ ይመለሳል፡፡ ንድድ አልሁ! ነገሩ የገባት አበቡ፤ ቤት ውስጥ ያለ ማማስያ አንስታ እንዳትሞት እንዳትድን አድርጋ ቀጠቀጠቻት ቂቂቂቀ……በነጋታው የቆሎ ተማሪዎች ደጀሰላም ደጃፍ ምን ብለው ጽፈው ለጠፉ መሰለህ?
‹የማሚቴስ ዱላ ምንም አላለኝ
የአበቡ ነዉ እንጂ እኔን የጎዳኝ› ቂቂቂ››
‹‹አያቴ!›› በጩኸት ቅድመ አያቱን ከሣቃቸው አናጠባቸው፡፡ ‹‹ቆይ በዱላ እንኳን ሰው መምታት የማትችይው ሴትዮ እንዴት ደህንነት ልትሆኚ ትችያለሽ?›› አፈጠጠ፡፡
‹‹ሴትዮ ነዉ ያልከው? ቂቂቂ ‹ሴትዮ› የሚለው ቃል በጣም ያስቃል›› በሣቅ ተንከተከቱ፡፡ ሉል የሚመስለዉ የጎረምሣው ዓይን ተጉረጠረጠ፡፡ ቅድመ አያት ደንገጥ ብለው ሣቃቸውን አቋርጠው…
‹‹የደህንነት ሥራ የድብድብ ሥራ ብቻ አይደለም ልጄ፡፡ ደግሞ ዘመኑ የጉልበት ሣይሆን የጭንቅላት ዘመን ነው፡፡››
‹‹ጭንቅላት ቢኖርሽማ አንድ ጎጆ ቤት ውስጥ ከምሶሶዉ የሚረዝም ዱላ ይዘሽ ገብተሽ ሰዉ ልትደበድቢ አትሞክሪም ነበር፡፡ ደግሞ ከደበደብሽ ልክስክሱ ወንድ አያቴን እንጂ እሷን አልነበረም፡፡›› በጩኸት ተናገራቸው፡፡(ቆይ ግን ጎረምሳው ምንድነው ግን እንደዚህ የሚያስቆጣው?)
‹‹በል ሥነ ሥርዓትን ያዝ! ምንም የተመረጥክ ብትሆን ዕጣ ፈንታህ በእጄ እንደሆነ አትርሳ፡፡ ደግሞ ማወቅ ያለብህ እኔ ላይ የማገጠው ወንድ አያትህ ቶሌራ ሳይሆን የልጅነት ፍቅረኛዬ ነዉ፡፡ ቶሌራማ አሁንም ታማኝ ፍቅረኛዬ ነዉ፡፡ ‹ጠራ ሆዱ አይጠራ!› ይባል ነበር ያኔ፡፡ ከቶሌራ በኋላ ግን ‹ጠራ ሆዱ አይጠራ ያለ ቶሌራ› ተባለ፡፡ ቶሌራ በ‹ቶ› መስቀሉ ሆዴን አጠራው ቂቂቂ፡፡ አይ የቶሌራ ‹ቶ› መስቀል!›› ሴት አያት በረጅሙ ተንፍሰው በሀሳብ እንደነጎዱ ፍዝዝ አሉ። ጎረምሳው ግራ ተጋባ፡፡ አሁንም አብሯት ካለ ታድያ ምን እንዲህ ያደርጋታል? ሲል አሰበ፡፡
‹‹ቅድም አያቴ የኳስ ሜዳ መሬት የናንተ እንደነበር ሰምቻለሁ፡፡ የኳስ መጫወቻ ሜዳው የጤፍ እርሻችሁ እንደነበረ ልጅ እያለሁ አያቴ ስታወራ ሰምቻት ነበር፡፡ ወለጋ በረንዳ የማርና የቅቤ መደብ ነበራችሁ አይደል? ቆይ ምንድን ነበር የሚባለው? ሸኾኔ በረንዳ ነው? ደግሞ ኳስ ሜዳ ጋ ጣልያን ያፈራረሰው ጠጅ ቤት የቱ ጋ ነበረ?››
‹‹እሱን ጊዜ አታስታወሰኝ ልጄ! ያኔ የአባትህ ክርስትና ደርሶ ድግሱን እያጣደፍነው ነበር፡፡ ጣልያኖቹ መሪያቸው ላይ ገነተ ልዑል ውስጥ ቦምብ ተጥሎበት ኖሮ በንዴት ያገኙትን ሲገሉና ቤት ሲያቃጥሉ ነበር። ደግሞ ሤራዉን ‹ተልዕኮ ስሞን አደፍርስ› በሚል ያቀናበረው የጠፋው ነገድ ነበር፡፡ እኔም ጉዳዩን ከቶሌራ ጠጅ ቤት ሆኜ እንደምመራ ሰምተው ነው መሰል መጥተው ጠጅ ቤቱን ሰባብረው፤ ለአባትህ ክርስትና የተጣለዉን ጠጅ እንኳን ሳይቀር ገልብጠው አፍሰውት ሄዱ፡፡ ያን እለት ብዙ ባርያዎቻችን ደንግጠው ጠፉ፡፡ እኔና ቶሌራ ልጆቻችንን ሰብስበን፤ ከአንድ ጎረቤታችን ጋር ጥምቀተ ባህሩ ጋር ካለ የውሃ ጉድጓድ ውስጥ ተደብቀን ነው ህይወታችንን ያተረፍነው፡፡››
‹‹ቆይ የዚህ ሁሉ ንብረት ካርታ የት ነው?›› ጎረምሳው ጠየቀ፡፡ ቅድመ አያት እንዳልሰሙ ቀጠሉ፤
‹‹ጠጅ ቤቱ ዝም ብሎ ጠጅ ቤት እንዳይመስልህ። ጠጅ ቤቱ በዙርያው ካሉ እና ከሌሎች መሰል ጠጅ ቤቶች ይለይ ነበር፡፡ የጠፋው ነገድ የጦር መምርያ ነበር፡፡ በየጫካው ያሉና ጫካ ለመግባትና ለመታገል ያሰቡ አርበኞችን የሚያበረታቱና የሚቀሰቅሱ ብዙ አዝማሪዎች ነበሩ፡፡ ‹አቢቹ ነጋ ነጋ› የሚለውን ዘፈን ታውቀዋለህ? በኛው አዝማሪዎች የተፈጠረ ነው፡፡ የሀገር ፍቅር ቲያትር ቤት ዘፋኞች እንኳን የእኛ ጠጅ ቤት ነበር ‹ናይት ክለባቸው›፡፡ ገጣሚዎች፣ ሰባኪዎችና ዲስኩረኞች የሠከሩ እየመሰሉ ብዙ አሽሙሮችን እየተናገሩ ጣልያኖቹንና እነሱን የተጠጉትን እርር ድብን ያደርጉ ነበር፡፡ በዚህ አሽሙር ሳቢያ ብዙ የጣልያን ቅምጦች የባሎቻቸውን ምስጢር እያመጡ ለአርበኞች እየተናገሩ ንስሀቸውን ይቀበሉ ነበር፡፡ እንደውም ሴት አያትህ ይህ ብልሀት ሲገባት አባትህን ከጣልያን ወልዳ ትልቁን የማሸነፊያ የጦር ምስጢር ከጣልያን የጦር መሪ ለማግኘት ቻለች፡፡››
‹‹ምን የአባቴ አባቱ ጣልያናዊ ነዉ?›› ጎረምሣው በድንጋጤ ውሃ ሆነ፡፡
‹‹ታድያ አባትህ ‹ባቻራ› እየተባለ የሚጠራው ለምን ይመስልሀል? ቂቂቂ-- የጣልያን ዲቃላ ስለሆነ እኮ ነው፡፡ ቆይ አንተስ እራስህ ይሄንን ቅላት ከየት አባትህ ያመጣኸው መሰለህ? እንደውም አንድ ሚስጥር ልንገርህ…..›› ድምጻቸውን በማንሾካሾክ
‹‹ለአባትህ ክርስትና የተጣለውን የጠጅ በርሜል የሠበረው ጣልያን ሳይሆን እራሱ ቶሌራ ነዉ ቂቂቂ። ቶሌራ ከጣልያን የልጁ ልጅ መወለዱን አልወደደም ነበር፡፡ ኋላ ላይ ግን ባባትህ መወለድ ፈንታ የተገኘውን ወታደራዊ ምስጢር ሲያውቅ ተረጋጋ፡፡ ቢሆንም ለአንድም ቀን ቢሆን አባትህን አቅፎ ስሞ አያውቅም። አባትህም በዚህ ንዴት እኮ ነው ጠጪ ሆኖ የቀረዉ ቂቂቂ-›› ጎረምሳው ግራ በመጋባት ቅድመ አያቱን ማየት ያዘ፡፡ ነጩ ቆዳው አስጠላው፡፡ ጣልያንነቱን በፍጹም አምኖ መቀበል አቃተው፡፡
‹‹እሺህ እሱን ተይውና አሁን የኳስ ሜዳ መሬት ባለቤትነታችሁን የሚያረጋግጠው ማስረጃችሁ የት እንዳለ ንገሪኝ!›› በቁጣ አፈጠጠ፡፡
‹‹መሬት ምን ያደርግልሀል? ከዛ በላይ ሁሉን የራስህ የምታደርግበት ነገር ነው የምሰጥህ፡፡›› ጎረምሳው ግራ ተጋባ፡፡ ‹በዚህ ዘመን ከመሬት የበለጠ ምን ስጦታ ይኖራል?› ሲል አሰበ፡፡ አምላክ እራሱ ለእስራኤሎች ቃል የገባላቸው መሬት ነው፡፡ ወተትና ማር የምታፈልቅ መሬት፡፡ ወተት በማር ደግሞ ለእንቅልፍ ነው የሚጠጣው፡፡ እኔ ደግሞ እንቅልፉ አለኝ፡፡ ስለዚህ መሬት ብቻ ነው የሚያስፈልገኝ ሲል አሰበ፡፡
‹‹እኔ የሜዳውን፣ የቤቱን፣ የጠጅ ቤቱንና ወለጋ በረንዳ ያለውን መደብ ባለመብትነት ማረጋገጫ ነው የምፈልገው!››
‹‹የኳስ ሜዳው እኮ ትምህርት ቤት ተሠርቶበታል። ቆንጅዬዋ እህትህ እራሱ እዛ አይደል የተማረችው?›› ምላሻቸው ቢያናድደውም የእህቱን ቆንጆነት ስላረጋገጡለት ደስ አለውና ተረጋጋ፡፡ ምናለ የጉለሌ ሰው ሁሉ ይህን ቢረዳና የእኔን ቁንጅና ቢረሳልኝ ሲልም ተመኘ፡፡
‹‹አዎ ቅድም አያቴ! ትምህርት ቤቱ በእጄ ይግባ እንጂ ‹አልቤርጎ› ላደርገው አስቤአለሁ፡፡›› አለ ረጋ ባለ ድምጽ፡፡
‹‹ምን አልክ?›› ቅድመ አያት ተቆጡ
‹‹ቅድመ አያቴ ደህንነት ነኝ ስትይ አልነበር እንዴ? ቆይ ተምሮ የጭንቀት እንቅልፍ ከመተኛት፤ ሳይማሩ የሰላም መኝታ መተኛት አይሻልም እንዴ?››
‹‹ለነገሩ እድሜ ልክህን ስለተኛህ ስለዚህ ነገር ካንተ በላይ አላውቅም!›› ቅድመ አያት አመኑ፡፡ ጎረምሳው ለመጀመርያ ጊዜ የመተኛቱ ጥቅም እውቅና ስላገኘለት ፈገግ አለ፡፡
‹‹ግን አንድ ነገር እወቅ፡፡ ዛሬ እኔ የምሰጥህ ከቤት ንብረት በላይ የሆነ ነገር ነው…›› አቋረጣቸው
‹‹አያቴ መሬት ስንት እንደገባ አታውቂም እንዴ? እንደናንተ ጊዜ በሦስት ብር…›› ቅድመ አያት ብድር በምድር ብለው እሱንም አቋረጡት
‹‹የምሰጥህ ነገር ከመሬትም ከምንም በላይ የሆነ ነው አልኩህ እኮ፡፡ ቢያንስ ምን እንደሆነ ለማወቅ እንኳን አትጓጓም?››
‹‹ቅድመ አያቴ ስለመሬት ምንም አታርፊም ማለት ነው? እስኪ የኛን ቤት ተመልከቺ፡፡ ከመሬቱ በላይ የያዝነው አየር ይበዛል፡፡ ያን ሁላ መሬት አሳልፈን ሰጥተን አሁን ቁመቱ ከስፋቱ የሚተልቅ ቤት ዉስጥ እንኖራለን፡፡››
‹‹እሱን እኮ ነው የምልህ›› ቅድመ አያት የልጅ ልጃቸውን እጅ ያዙ፡፡ ‹‹ጃንሆይ ቶሌራን የልጅ እያሱ ደጋፊ ነህ ብለው ብዙ እርስቱን ቀምተውታል፡፡ እራስ እምሩ ስለቶሌራ የሽፋን ሥራ ሊያስረዷቸዉ ቢሞክሩም አሻፈረኝ አሉ፡፡ ደርግም መጥቶ ከተረፈችን ጥቂት መሬት ላይ አብዛኛውን ወሰደብን፡፡ በኢሠፓ ዉስጥ አስርገን ያስገባናቸው የጠፋው ነገድ አባላቶች ስለነበሩን ለእነሱ ተልዕኮ ስኬት ስንል እርምጃውን በዝምታ ተቀበልን፡፡ አባትህ ከዛህ ሁሉ እርስት አንድ ክፍል ቤትና አንድ ሱቅ ተረፈችው፡፡ ይሄ መንግስት የተከራይ አከራይ ብሎ ሱቁን አስወረሰብን፡፡ አባትህ የለየለት ጠጪ ሆነ›› ጎረምሳው አባቱ በሁሉ ምክንያት ጠጪ ሆኖ መቅረቱ ግራ አጋባው፡፡ ግን እሱን ተወና እንዲህ አለ፤
‹‹ግን እኮ አበል ያልተበላበት የተወረሰ ቤት እየተመለሰ ነው፡፡ ስለዚህ ማስረጃዎቹን የት እንዳለ ንገሪኝና ሁሉንም እኔ ላስመልስ፡፡ የማትነግሪኝ ከሆነ ግን የሙት መንፈስ ጠሪ ጋር ሄጄ አስጠርቼሽ በውድሽ ሳይሆን በግድሽ ትነግሪኛለሽ፡፡››
‹‹ምን? እኔ የመሬት ባለቤትነት ማረጋገጫ አልሰጥህም ልጄ፡፡ ይልቅ ያለህን ልዕለ ኃይል የሚያጠነክርና እንድትጠቀም የሚያስችልህን የቶሌራ ‹ቶ› መስቀልን ልስጥህ፡፡›› ቅድመ አያት ከጡታቸው መሀል ብርሃን በሁሉም አቅጣጫ የሚረጭ የ‹ቶ› መስቀል አወጡ›› ጎረምሳው የማያውቀዉ ግን ውስጡ የነበረ አንዳች ኃይል ሲላወስ ተሰማው፡፡ መስቀሉን ከእጃቸዉ ተቀብሎ ፈገግ አለ፡፡ ፈገግታው መስቀሉ ከሚያወጣዉ ጨረር የሚስተካከል ብርሃንን ረጨ፡፡
‹‹ግን ቅድም አያቴ ምንም አልሽ ምን መሬቱን ማስመለሴ አልተውም!›› የሰጡትን የ‹ቶ› መስቀል መልሰው እንዳይቀበሉት የሰጋ ይመስል በፍጥነት ወደ ደረቱ አስጠጋ፡፡
‹‹አውቃለሁ! መሬቱን ብቻ ሳይሆን ሁሉን ነገር እንድታስመልስ እንፈልጋለን፡፡ የኛ የነበረውን ሁሉ መልሰህ የኛ አድርግ፡፡ መቶ አርባ ስድስት ትውልድ እየተዋለደ የአንተን መወለድ በተስፋ ጠብቋል፡፡ መወለድህን የተራ ተራክቦ ውጤት አታድርገው፡፡ ብዙዎች ስላንተ መወለድ ሲሉ የድንግልና ህይወትን መስዋዕት አድርገዋል፡፡››
‹‹ቅድም አያቴ፤ በዚህ ኃይሌ ምን ማድረግ እችላለሁ?››
‹‹የልጅ ልጄ፤ ሁሉንም ትክክል ነገሮች ማድረግ ትችላለህ!››
‹‹ግን ትክክል ነገር ምንድነው?››
‹‹ትክክል ነገር ምንድነው?›› ቅድመ አያት ግራ በመጋባት እራሳቸውን ጠየቁ፡፡
‹‹ይኸውልሽማ ቅድመ አያቴ ከሁሉ በፊት ላደርጋቸው የማስባቸው ነገሮች አሉ፡፡ አዲስ አለቃና አዲስ መጥረጊያ አጽድቶ ይጠርጋል አይደል የሚባለው?......መቼም ይሄ ኃይል አለቃ ያደርገኛል አይደል አያቴ?›› ሣቅ አለ፡፡
‹‹ትክክል ነገር ግን ምንድነው?››ቅድመ አያት ድጋሚ እራሳቸውን ጠየቁ፡፡
‹‹ኧ?›› ጎረምሳው በግርምት ቅድመ አያቱ ላይ አፈጠጠ፡፡
‹‹ትክክል አሻሚ ነው ልጄ፡፡ ብቻ የቶሌራ ቶ መስቀል በሚመራህ ሂድ፡፡ እሱ ነው ትክክል የሚሆነው፡፡››
‹‹የማደርገውን አሳይሻለሁ ቅድመ አያቴ፡፡ መጀመርያ እነዛ ቀባጣሪ፣ ቅብርጥስያም የኳስ ሜዳ ልጆች - የምላስ አድራጊ ፈጣሪዎች እም…….›› ትክዝ አለና ጭንቅላቱን ነቀነቀ፡፡ ቅድመ አያት በመጨነቅ ተመለከቱት፡፡ ‹‹ቅድም አያቴ በዚህች ቤት እንኳን ስንት ነገር ብለውኛል መሰለሽ፡፡ ቤቱ ወደ ላይ መመዘዙንና ቆጥ መጨመሩን ሲያውቁ የኳስ ሜዳ ሰማይ ጠቀስ ህንጻ - ቡርጃ ኳስ ሜዳ ሲሉት ነበር፡፡ እሱን እንዳልሰማ ሆኜ ዝም ብል በስሜ ጠርተው ‹ለምን ታችኛውን ለባንክ አታከራዩትም?› ሲሉ ተሳለቁብኝ፡፡
ተኝቼ በመዋሌ እራሱ መች ተወኝ? ‹እሱ ሲተኛ ተነሳ፤ ሲነሳ ደግሞ ተኛ ነዉ የሚባለው› ሲሉ በእንቅልፍ የማሳልፈዉ ጊዜ ተነስቼ ከማሳልፈው እንደሚበልጥ ቅኔ ተቀኝተው ብሶት አደባባይ ላይ ዘርፈውታል። ተኝቼም፣ ተነስቼም የነሱ መቀለጃ ከመሆን አልተረፍኩም፡፡ መጀመርያ የነሱን አፍ እዘጋለሁ፡፡ ደግመው እንዳይናገሩ፤ ከት ብለው እንዳይሥቁ አድርጌ እደፍነዋለሁ!…..እንደውም እንደ ሱርማዎች ከብት ጠባቂ አደነዝዛቸዋለሁ፡፡›› ቅድመ አያት የሚሰሙትን ማመን ተስኗቸዉ በመገረም ያዩታል፡፡ ታላቁ ኃይል ለተራ ቂም በቀል መወጣጫ ሲታጭ ደንግጠዋል፡፡
‹‹ከዛ ደግሞ አውቶቢስ ተራ የመንገድ አካፋይ ላይ ተቀምጠው የመኪና መስኮት እየከፈቱ የሚነጥቁ ሌቦች ነጥቀው ሲሮጡ ልባቸዉ ፈንድቶ እስኪሞቱ ድረስ እንዳይቆሙ ነው የማደርጋቸው፡፡ ይታይሻል ይሄ ጠባሳ ቅድመ አያቴ?›› ክንዱን ገልጦ አሳያቸው፡፡
‹‹ይሄ ጠባሳ ታክሲ ውስጥ ስልክ ሳወራ መስኮቱን ከፍቶ አንዱ ስልኬን ቀምቶኝ ሲሮጥ አስጥላለሁ ብዬ የመኪናዉ ብረት የቆረጠኝ ነዉ፡፡ አሁን ምን እንደማደርግ ታዉቂያለሽ? አውቄ የታክሲውን መስኮት ከፍቼ ስልክ ማውራት እጀምራለሁ፤ ከዛ አንዱ ሌባ አገኘሁ ብሎ ስልኩን ቀምቶኝ ሲሮጥ ኃይሌን ተጠቅሜ ስልኩ እጁ ላይ እንዲፈነዳና እጁን አንዲበጣጥሰዉ አደርጋለሁ፡፡ ከዛ ደንግጦ ቀኑን ሙሉ ሲሮጥ ይዉልና ደሙ አልቆ ወይ ልቡ ፈንድቶ ይሞታል!››
‹‹ምንድን ነዉ የምታወራዉ አንተ ልጅ ቆይ? ይሄ ኃይል እኮ የትውልዱን ህልም እዉን ማድረጊያ እንጂ የግል ቂም በቀልን መወጫ አይደለም፡፡››
‹‹ቆይ ቆይ ቅድመ አያቴ እነዚህ መቶ አርባ ስድስት ትውልዶች ምን እንዳደርግ ነው የሚፈልጉት? ምንድነው ሥራዬ?›› ቅድመ አያት መልሰዉ መስታወታቸው ላይ ተመስጠዋል፡፡ ዝምታዉ ሲሰማቸው፤
‹‹ኧ….እንደነገርኩህ መቶ አርባ ስድስት ትውልዶች አንተን የፈጠሩት የጠፋውን ነገድ፤ በህቡዕ ያለውን ነገድ ወደ ጸሐይ እንድታወጣውና ታላቅነቱን እንድትመልስ ነው፡፡ ይህ ነገድ ብዙ የተነጠቀው ግን ያላጣቸዉ ነገሮች አሉ፡፡ በቃ እንደደረቀ ግን እንዳልከሰመ አበባ ተመልከተው፡፡ ትንሽ ውሃ ብቻ እንደሚፈልግ አትክልት እየው፡፡››
‹‹ታድያ ይህን ያህል ኃላፊነት ከሰጣችሁኝና ህልማችሁን በኔ ላይ ከጣላችሁ እንዴት የኔ ጠላቶች የናንተ ሆነዉ አይሰማችሁም? እኔስ ብሆን በጠላቶቼና በጠላዋቸው ሰዎች ተከብቤ እንዴት በትኩረትና በአስተውሎት ሥራዬን ልሠራና ህልማችሁን ላሳካ እችላለሁ?››
‹‹ልጄ አንድ ነገር ሊገባህ ይገባል፡፡ ሁሌም ቢሆን አንድ ደረጃ ከፍ ስትል፤ አንድ ደረጃ ከፍ ያለ ደረጃህን የሚመጥን ጠላት ያስፈልግሀል! አንዴ ከመኝታህ ከተነሳህ በኋላ በመተኛትህ የሚቀልዱብህን ሰዎች ጠላት ማድረግ ማቆም አለብህ፡፡ ከተነሳህ በኋላ ጠላቶች በመነሳትህ የሚያሾፉ ብቻ ናቸዉ፡፡ በመተኛትህ የሚያሾፉ ካሉማ እነሱን ‹ሞኝና ምን የያዘዉን አይለቅም!› ብለህ ልትተዋቸዉ ይገባል፡፡
ከነፋስ ፈጥነህ መብረር እየቻልክ ሳለ ስለታክሲና የታክሲ መስኮት ከፍተዉ ነጥቀው በባዶ ሆዳቸዉ ስለሚሮጡ ህጻናት የምታወራ ከሆነ ችግር ነዉ። ከነፋስ ፈጥኖ ለመብረር የቻለ ጠላቱ ነፋስ ነው ሊሆን የሚችለዉ፡፡ ረግተህ ማርጋት ከቻልህ ደግሞ ነፋስ ዘመድህ ሊሆን ይችላል! ቂቂቂ--›› ጠቀሱት። አላያቸውም፡፡ በሀሳቡ ጠላቶቹን ማን እንደሆነ ሲያሳያቸዉና ያለርህራሄ ሲበቀላቸዉ እያሰበ ፈገግ አለ።
‹‹ልጄ መቼም ቢሆን እንዳትረሳ! ይህ ልዕለ ኃይል የተሰጠህ የነገዱን ታላቅነት እንድትመልስና ለአገርና ለወገን ጠበቃነታችንን እንድታጸና ነዉ፡፡ ነገሥታት ባንሆንም አንጋሾች ነበርን፡፡ ደግሞ ነገዱ ካንተ በላይ እንደሆነ እና የተሰጠህን ኃይል ያለአግባብ ልትጠቀም እንደማትችል ማወቅ አለብህ፡፡ አንዳንድ ነገሮችን ማድረግ ቢኖርብህ እንኳን በዚህ መንገድ አይደለም። የሰረቀህን እጅ ልትቆርጥና የዘለፈህን አፍ ልትደፍን አትችልም፡፡ ተናጋሪዎቹም አደብ እንዲገዙ፤ ሌባዎቹም ሌባነታቸዉን እንዲተዉ የሚያደርግ ኃይል እንዳለህ አትርሳ፡፡ ነገዱ እራሱን የሁሉም እናትና አባት አድርጎ ነው የሚያስበዉ፡፡ እኛ ሁሉም ሰው ኃላፊነታችን ነዉ ብለን ነዉ የምናስበው፡፡››
‹‹ቅድመ አያቴ፤ ጠላቶቼ ጠላቶቻችሁ ናቸዉ፡፡ ይህንን አምናችሁ መቀበል አለባችሁ፡፡ ምንም አልሽ ምንም መጀመርያ ቤቱን አጽድቼ እጠርጋለሁ፡፡ ከዛ በመቀጠል ደግሞ መሬቶቼን በሙሉ አስመልሳለሁ፡፡ ከዛ በኋላ የፈለጋችሁትን ጠይቁኝ››
‹‹እንደዛ ማድረግ አትችልም፡፡ መጀመርያም ሆነ መጨረሻ ልታደርግ የምትችለው ነገዱ የሚፈልገውን ነገር ብቻ ነዉ፡፡››
‹‹የፈለግሁትን አደርጋለሁ! ማንም ሊያስቆመኝ አይችልም አያቴ›› ከአንገቱ ቀና ብሎ በቁጣ አጓራና የቶሌራን ቶ መስቀል ይዞ ተነሳ፡፡
‹‹ልጄ አንተ ጥይት እንጂ ሽጉጥ አይደለህም፡፡ አንተ ያለነገዱ ምንም ነህ!›› ቅድመ አያትዬው አንዳች ነገር ከደረታቸው አውጥተው ጠቅ ሲያደርጉ፣ ልጅዬዉ የያዘዉ ቶ መስቀል ብርሃን ጭልም አለ፡፡ ጎረምሳው ዉስጡ ያለዉ ኃይል እንደ መስቀሉ ብርሃን ሲጨልም ተሰማዉ፡፡ ድካም ድካም አለው፡፡ ብርሃን የለመደ እንዴት ወደ ጨለማ ይመለሳል? ሲል አሰበ፡፡
‹‹ቅድመ አያቴ ምን ማድረግሽ ነው?›› ሲል አምባረቀ፡፡
‹‹አንተ ቂመኛ ነህ፡፡ ደካማ ስለሆንክ በፍጹም ይህን ነገድ ልትወክል አትችልም፡፡›› ቅድመ አያት በሃያ አንደኛ ቀናቸዉ ለመጀመርያ ጊዜ ተቆጡ፡፡
‹‹አያቴ ኃይሉን መልሺልኝ!›› የቅድመ አያቱ ቁጣ አላስፈራውም፡፡ እንደውም ተንደርድሮ፣ ቅድመ አያቱ ቶ መስቀሉን ኃይል አልባ ያደረጉበትን መሣርያ ሊነጥቅ ተወረወረ፡፡
በጠራራ ጸሐይ በወበቅ በተሞላ ክፍል ውስጥ ተራቁቶ ተጋድሞ የነበረው ጎረምሳ፣ አንዳች ነገር አጉተምትሞ ተወራጨና ከሰዓታት በፊት ከላዩ አሽቀንጥሮ በጣለው የአልጋ ልብስ ላይ ደፍ ብሎ ወደቀ፡፡ ሲወድቅ እንደ አልጋ ልብሱ ህመሙን ውጦ ዝም አላለም፡፡ ይልቅ በስቃይ አጓራና ተዝለፈለፈ፡፡ ከወደቀበት መቼም የሚነሳ አይመስልም፡፡


Read 2662 times Last modified on Saturday, 25 August 2018 13:30