Saturday, 12 May 2012 09:42

እምነትና አማኞች ሁለት

Written by  ዓለማየሁ ገላጋይ-
Rate this item
(0 votes)

“ATHENS” የምትል የቱሪስት ስዕላዊ ማነቃቂያ በሉት ማጥመጃ ማማለያ አጋጥማኝ፣ ለቱሪስት የተተኮሰው ተባራሪ እኔን ችስታውን አገኘኝ፡፡ የችስታ ቱሪስት የለውም፤ ቢኖርም የክብር ሥሙ የእግዜር እንግዳ ነውና ከአገር ውስጥ የእግር በረራ ውጭ አለማቀፉ ውስጥ የለበትም፡፡ የምናብ በረራ ግን የሚከለክለው የለም (የከሸፈ የእግዜር እንግዳ መሆን ካላሰጋው)

የከሸፋችሁ ቱሪስቶችና የእግዜር እንግዶች ሆይ፣ ለምናብ በረራው ቀበቷችሁን አላሉ - እንዳይጨንቃችሁ፡

“The religion of Beauty” የሚል መጠሪያ ያተረፈው ብቸኛው የግሪኩ አማልክታዊ እምነት እነሆ ከፊታችሁ ተዘረጋ (ሁሉን ቻይ ምናባችን ይክበር - ይመስገን!) በእርግጥም ደግሞ ጥንታዊው የግሪክ እምነት ቤተ-ውበት ሊባል ያንሰዋል፡፡ ከሆሜር ቅኔአዊ የአማልክቶች መወድስ እንነሳ፣ ከክርስቶስ ልደት ከ850 አመታት በፊት ነው እንግዲህ Iliad and odyssey ን የፃፈው፡፡

ስንት የዘመን ወንዝ፣ ስንት የዘመን ጉድባ፣ ስንት የዘመን ሜዳና ተራራ .. አቆራርጦ፣ ወጥቶ ወርዶ እዚህ ቢደርስም፣ የሆሜር ሥራ ተአምራዊ ውበቱ አልረገፈም፡፡ በውበቱ መደመም ለዚያ ሁሉ የትውልድ ትውልዳት አታካች ሰልፍ ተዳርሷል፤ መበርከቱ!

Iliad ቃሉ “የአሊዎስ ወግ” ማለት ነው፡፡ Ilios ደግሞ የትሮይ ቀደምት ስም፤ የሆሜር መፅሐፍ ርዕስ እንደዚያ ይሁን እንጂ የቅኔው ሙሉ ትኩረት የ ACHILLES ቅጥ ቅጥ ያጣ ቁጣ፣ መዘዙ ሲከታተሉ እያየን እኛ አንባብያን እንድንከታተል፣ እስከ ትሮይም ዘልቀን ጀግንነት፣ ውበት፣ ፍቅር እንድንኮመኩም ዕድሉን መፍጠር፡፡ ከዚያ ደግሞ Odysseus ይተካላችሁና ሌሎች ብዙ ተአምራት በሆሜር የመተረክ ጥበብ እየታገዙ፣ የገጠሙዋችሁ እስኪመስሏችሁ እየተሳተፋችሁ ትቀጥላላችሁ፡፡

ሆሜርን የግሪክ ኃይማኖታዊ ውበት ታሪካዊ ተቋዳሽ ወዳደረገው ጉዳይ መዝለቅ፣ መዘላለቅ፣ ጀመርን ውድ ችስታ ቱሪስታውያን ወይም የእግዚአብሔር እንግዳውያን! ሆሜር የአማልክቱን ዘፍጥረት ከቅድመ አለም አንስቶ ይተርክልናል፡፡ “ፀሐዩ ንጉስ” ዚየስ (የፀሐይ ገዢ በመሆኑ) “የባህሩ ዘንዶ” ኔፕትዩን (የውቅያኖስ ገዢ በመሆኑ)፣ “አባ እንጦሮጦስ” ሀዴስ (የምድር ሥር ገዢ በመሆኑ) … የአማልክቱ ተዋረድ፣ የሥራ ድርሻና ባህርይ እንዲሁም እርስ በእርስ ያላቸው ግንኙነት ሳይዛነፍ (ማረጋገጥ ቢከብድም) በውብ ቃላት (ማረጋገጥ ስለማይከብድ) አቅርቧል፡፡ አማልክታዊ ገድሉን እዚህ ድረስ አዝሎ ያመጣው እውነቱ ሳይሆን ውበቱ ይመለሳል፣ አቤት ውበት!

ሆሜር የአማልክቱንና የሰዎችን ግንኙነት የእኩያ ውሎ አድርጐ፣ ብዙም ሳይበላለጡ፣ አንዳንዴ እየተፋቀሩ፣ ሌላ ጊዜ እየተደፋፈሩና እየተፎካከሩ፣ እየታገሉ የእርስ በእርስ ታሪካቸውን፣ የአንድ ሰፈር ልጅ ያህል እየተጋገዙ እንዲቀጥሉ አድርጓቸዋል፡፡

ሆሜር የአማልክቱ ውበት እንዲስማማን፣ ኃያልነታቸው እንዳይጐዳን! ጭቆናቸው እንዳይሰማ በሌላ በኩል ደግሞ እርዳታቸው በዝቶ አሻንጉሊት እንዳንመስል … ወዘተ.. ማድረግ ሲችልበት! በሆሜር ትረካ አማልክቱ የሰዎት ተጐራባች፣ ጣጣችን ግድ የሚሰጣቸው፣ ንቀው የማይተውን ተደርገዋል፡፡ Achilles ከጄነራል Agamemnon ጋር አተካራ ሲገጥምና ጠቡ ሲካረር ቀዳማዊት እመቤት (የዚየስ ሚስት) Hera አሳስቧት Athena ን ትልካለች፡፡ “እስኪ ይሄንን ልጅ ተቆጥተሽ ተው በይው” ብላ Achilles ም ለአማልክቱ መልስ ነውና ግንባሩን አጠፈ፡፡ ሆሜር ተአምር ሰርቶ፣ ከተአምሩ መግነን የተነሣ አንዳንድ ጥርጣሬዎች ከአንዳንድ ቀልባሽ ምሁራን ይሰነዘራል፡፡

ከሆሜር በፊትም Iliad እና Odyssey ላይ የተፃፉ ገድላት ቢኖሩም ጠፍተው ኖሯልና ሆሜር የተሰኘ የግሪክ አለቃ ገብረሃና ፈጥረው፣ በእርሱ ስም ብዙ ገጣሚያን እንደውም በትውልድ የሚቆጠሩ እየፃፉ የሆሜር ፋይል ውስጥ አከማቹ ይሉናል፡፡

ቢሆንም ለውጥ አያመጣም፤ የኦሊያድና ኦዲሴ ውበት እስካለና እስከቀጠለ ድረስ የግሪክ አማልክትን እያመሰገንን መኮምኮም ምርጫችን ብቻ ሳይሆን ግዴታችንም ጭምር በመሆኑ፡፡

The Religion of beauty ክህሌቱ (ምንም እንኳ አሀዱ ማለት ብንዘነጋም)

ንግግርን ትቶ የፊዲያስን፣ የስኮፖስን እና የፕራክሲቴለስን እንዲሁም የዚየስን ምስለ ቅርፅ መመልከትን እንመክራለን (የአስጐብኝነታችንን ሥልጣን መከታ በማድረግ) ውበትን ያህል ወጥመድ አለ? የውበቱ ማየል ከአማልክቱ በላይ ሲሆንብን፣ ከኛም ውበት የመቀበል አቅም በላይ ሲሆንብን፣ እራሱ ውበቱ ከሥነ ውበት ልኬት በላይ ሲሆንብን … እውነትን ትተን ተአምረኛውን ውበት ለመከተል እንገደዳለን፡፡

እንዲሁም ለመስገድ፣ እንዲሁም ለመሰዋት፣ እንዲሁም ለአማልክቱ የማይሰግዱትን ለመሰየፍ … ወዘተረፈ፡፡ የውበት ጣዖት አምላኪነት እንዲህ ውስጣችን ገብታ ልትነዳን ትጀምራለች፡፡

ካስር ማስረዳት አንድ ማሳየት በሚለው የአስጐብኝዎች መርሃ መርህ በመነሳት እነሆ Venus፣ እነሆ Venus እነሆ Pan፣ እነሆ Eros እነሆ ሦስቱ አንድ ላይ፡፡ Venus የፀደይና የአፀድ አምላካችን ናት፡፡ አቤት ማማሯ! አንዳንዶች የጣኦተ አምልኮ መናፍቃን ቬነስን፣ የአፍሮዲት ግብር ወካይ አድርገው፣ የፍቅርና የውበትም አምላክ ያደርጓታል፡፡ ቬነስ እራሷ ፍቅርና ውበት ሆና ሳለ!

Pan ደግሞ የእረኞችና የበግ ጠባቂዎች አምላክ ነው፡፡ ግማሽ ሰው፣ ግማሽ ፍየል በመምሰል ጠባቂውንና ተጠባቂውን አንድ ጋ ጠቅልሎ ይዟል፡፡ ሮማውያን አወቅን መስሏቸው Faunus  ይሉታል፡፡ እኛ ደግሞ “የጣኦት አምላኪ ክፉ፣ በስም ይደግፉ” የሚል የሽሙጥ ጥቅስ እንጠቅስባቸዋለን፣ ተደብቀን፡፡ አሸንፈውናላ፣ ጌቶቻችን ሆነዋላ፡፡

Eros አለላችሁ ደሞ፡፡ የፍቅር አምላክ፡፡ ከአፍ የወደቀ ጥሬ የሚያክል አሽከር [በጐንደር]፣ ሙጭቅላ [በእነንትና]፣ ውሪ፣ ጭሎ፣ …ወዘተረፈ፡፡ ክንፍ አለው፡፡ እንደ ድንቢጥ ወፍ፣ ትር፣ ብን እያለ መጥቶ የፀቡን፣ የመናናቁን፣ ያለ መደራረሱን የመፈራራቱን … የወንድና የሴት ግንኙነት የፍቅር አድርጐት ቁጭ ይላል፡፡ Eros ሲመጣ ላስብበት፣ እንጠናና፣ ትምህርቴን ልጨርስ፣ የያዝኩትን ልጉረስ፣ አባቴ ይቆጣኛል … ወዘተረፈ ምክንያታት ቦታ የላቸውም፡፡ እጭ ወደላይ ለፍቅር!

እነዚያ ጌቶቻችን ያሳመሩ መስሏቸው ኢሮስን Cupid ብለው፣ ተአምረ መንሾካሹኩን በፍቅር ቀስት ለውጠው በመናፍቅ ሥራቸው ገፉበት፡፡ ጊዜ ወደነሱ አዘንብሏልና ላሽ አልናቸው (እሳት በላሰው ትውልድ ቋንቋ)

The Religion of beauty ሰልስቱ

ንግግር ትቶ ቤተ-መቅደሶቹን ማየት፡፡ እነ ICtinus፣ እነ Callicrates፣ እነ Posedim፣ እነ temple of Zeus … አሉላችሁ፡፡ ቢፈርሱም፣ ቢፈራርሱም ግርማ ሞገሳቸው ከትከሻቸው ላይ ያልተገፈፈ፡፡ እነሆ ቅምሻ The temple of Hephaestus ወይም Theseion ካስር ማስረዳት አንድ ማሳየት አላልንም? ታዲያ የምን ወሬ ማብዛት ነው? ኤዲያ! ቀጥታ ወደ ማየቱ! ውድ እና ችስታ ቱሪስታውያን!

 

 

Read 2539 times Last modified on Saturday, 12 May 2012 09:50