Saturday, 25 August 2018 13:17

በቄሮ ስም “ህገ ወጥ እንቅስቃሴ” ላይ የተሠማሩ እየታሠሩ ነው

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(10 votes)

 ከ580 በላይ ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር ውለዋል

    በኦሮሚያ የተለያዩ አካባቢዎች በቄሮ ስም እየተንቀሳቀሱ የተለያዩ ወንጀሎችን ሲፈፅሙ ነበር ተብለው የተጠረጠሩ ከ580 በላይ ግለሰቦች መታሰራቸው ታወቀ
ከታሠሩት ውስጥ 300 ያህሉ ምርመራ ተጣርቶባቸው፣ ፍ/ቤት መቅረባቸው የታወቀ ሲሆን ግለሠቦቹ በዘረፋ፣ ሰውን በማፈናቀልና በተለያዩ ድርጊቶች የተጠረጠሩ ናቸው ተብሏል፡፡
መንግስት በሀገሪቱ እየተፈጠረ ያለውን ስርአት አልበኝነት ለመግታት እየወሠደ ያለው እርምጃ አካል ነው በተባለው በዚህ የህግ ማስከበር ሂደት በሱሉልታ፣ በሻሸመኔ፣ በቡራዩ፣ በለገጣፎ፣ በጅማ፣ በአዳማ፣ በሞጆ፣ በሠበታና በሌሎች አካባቢዎች በተለያዩ ህገ ወጥ እንቅስቃሴዎች ውስጥ ተሳትፈዋል የተባሉ ግለሠቦች ታስረዋል፡፡
በሞጆ ከተማ በመሳሪያ በመታገዝ ፋብሪካ ለመዝረፍ ሲንቀሣቀሱ የነበሩ 2 ወጣቶች፣ በሠበታ በህገ ወጥ ግንባታ የተሠማሩና ምግብ ቤት ገብተው ከተመገቡ በኋላ ሂሳብ ሳይከፍሉ የሚወጡ የተደራጁ 14 የቡድን አባላት፣ በጅማ ህገ ወጥ ግንባታ ሲያካሂዱ የነበሩ 42 ተጠርጣሪዎች፣ በአዳማ የብሄር ግጭት ሲያነሣሡ የነበሩ 8 ተጠርጣሪዎች፣ በለገጣፎ የቄሮ አደረጃጀት ከቀበሌ ጀምሮ በመንግስት መዋቅር ውስጥ መሳተፍ አለበት በማለት ወጣቶችን ሲያደራጁ የነበሩ ተጠርጣሪዎች ናቸው በቁጥጥር ሥር የዋሉት፡፡
በሱሉልታ ከተማ ደግሞ በቄሮ ስም በመንቀሳቀስ የግለሰቦችን ቤት በማፍረስ ቆርቆሮ በመውሰድ ላይ የተሰማሩ 4 ተጠርጣሪዎች እንዲሁም በቡራዩ የቄሮ አመራር ነኝ በማለት መታወቂያ አዘጋጅቶ፣ የተለያዩ ተቋማትን ስፖንሰር ሲጠይቅ የነበረ ወጣት መታሰሩም ታውቋል፡፡
የኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ ፅ/ቤት የገጠር ፖለቲካ አደረጃጀት ዘርፍ ሃላፊ አቶ አዲሱ አረጋ በፌስ ቡክ ገፃቸው እንዳስታወቁት፤ በባሌ ዞን የእርሻ ኢንቨስትመንት ለማደናቀፍ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ፣ በቡኖ በደሌ ዞን ጮራ ወረዳ አካባቢ፣ የሌላ ብሄር ተወላጆችን የእርሻ መሬት የመነጠሩ ግለሰቦች ታስረዋል፡፡
የክልሉ ፖሊስ ከህብረተሰቡ ጋር በመተባበር በስርአት አልበኝነትና በህገወጥ ተግባር ላይ ተሠማርተው የሚገኙ አካላትን በቁጥጥር ስር ማዋሉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተገልጿል፡፡
በተመሣሣይ በደቡብ ክልል በሁከት እና ብጥብጥ ተሣትፈዋል የተባሉ 300 ያህል ተጠርጣሪዎች መታሠራቸውም ታውቋል፡፡
በክልሉ የህግ የበላይነት የማስከበር ጉዳይ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል የደቡብ ክልል ፖሊስ ኮሚሽነር ቴዎድሮስ ወ/ሚካኤል፡፡

Read 7766 times