Saturday, 25 August 2018 13:18

በጀዋር መሃመድ የሚመራ የፖለቲካ ፓርቲዎች ውይይት ነገ ይካሄዳል ውይይቱ በቴሌቪዥን የቀጥታ ሥርጭት ይተላለፋል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(5 votes)

በኢትዮጵያ እየታየ ባለው ፖለቲካዊ ለውጥ ላይ ያተኮረ የፖለቲካ ፓርቲዎች ውይይት በነገው ዕለት በሂልተን ሆቴል የሚካሄድ ሲሆን ውይይቱ በቀጥታ የቴሌቪዥን ሥርጭት ለህዝብ ይተላለፋል ተብሏል፡፡
ይሄን ውይይት የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትወርክ (OMN) ያዘጋጀው ሲሆን አቶ ጀዋር መሃመድ መድረኩን እንደሚመሩት ታውቋል፡፡
በአዲስ አበባ ሂልተን ሆቴል ከጠዋቱ 2፡30 ጀምሮ እስከ ምሽት 12 ሠዓት ቀኑን ሙሉ በሁለት ፈረቃ በኦሮሚኛና በአማርኛ ቋንቋዎች በሚካሄደው በዚህ የፖለቲካ ውይይት ላይ በቅርቡ ወደ ሃገር ቤት የተመለሱ እና በሃገር ውስጥ ያሉ ፓርቲዎች በሙሉ እንዲሳተፉ ጥሪ መተላለፉን የኦ ኤም ኤን የአዲስ አበባ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ቶሌራ ፍቅሩ ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡
“በኢትዮጵያ እየታየ ያለው ለውጥ ቀጣይነትና አስተማማኝ መሠረት እንዲኖረው ከፖለቲካ ድርጅቶችና ከህዝቡ ምን ይጠበቃል?” በሚል ርዕስ በኦሮሚያ ሚዲያ ኔት ዎርክ ዳይሬክተርና አክቲቪስቱ አቶ ጀዋር መሃመድ የመድረክ አጋፋሪነት በሚካሄደው በዚህ ውይይት ላይ ለውጡን ወደፊት የሚያሻግሩና የተሻለ ደረጃ የሚያደርሡ ሃሳቦች ይቀርባሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም አቶ ቶሌራ ተናግረዋል፡፡
በውይይት መድረኩ ላይ ኢህአዴግን ጨምሮ ተቋዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሙሉ ይሣተፋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ የጠቆሙት አቶ ቶሌራ ፕሮግራሙም በሁለት ክፍሎች የተዘጋጀ ነው ብለዋል፡፡
በጠዋቱ ክፍለ ጊዜ ከ2፡30 እስከ 6 ሰዓት በአፋን ኦሮሞ ውይይት የሚደረግ ሲሆን በዚህ ውይይት ላይ የኦሮሞ የፖለቲካ ድርጅቶች ውይይት ያደርጋሉ፡፡
ከሰአት ከ8 ሰዓት እስከ 12 ሰዓት ደግሞ ሌሎች ሃገር አቀፍ ፓርቲዎች ውይይት የሚያደርጉ ይሆናል፡፡ ሁለቱም ውይይቶች ለህዝብ በቀጥታ በኦኤምኤን ቴሌቪዥን ይተላለፋሉ ተብሏል፡፡
የሃገሪቱ ዲሞክራሲያዊ ስርአት እንዲጎለብት አመርቂ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እድገት እንዲሠፍን ህዝቡና የፖለቲካ ድርጅቶች በቀጣይ ምን መስራት እንዳለባቸው የሚመከርበት ተመሳሳይ ውይይት በቀጣይም እንደሚዘጋጅ ለማወቅ ተችሏል፡፡


Read 8140 times