Saturday, 25 August 2018 13:16

የሶማሌ ክልል አዲስ ፕሬዚዳንት አግኝቷል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(4 votes)

 በግጭት ላጋጠሙ ሞት፣ዘረፋ እና ንብረት መውደም የቀድሞ አመራሮች ተጠያቂ ይሆናሉ

    በሶማሌ ክልል ውስጥ በአቶ አብዲ መሃመድ የሚፈፀሙ አስተዳደራዊ በደሎችንና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በማጋለጥ በማህበራዊ ሚዲያ በስፋት የሚውቁት አቶ ሙስጠፋ ኡመር የክልሉ ፕሬዚዳንት ሆነው የተሾሙ ሲሆን ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ 1000 ከሚደሰርሱ የሶማሌ ህዝብ ተወካዮች ጋር ትናንት ተወያይተዋል፡፡
በጅግጅጋና በተለያዩ የክልሉ ከተሞች የተፈጠሩ ግጭቶችን ተከትሎ፣ በበርካታ የሠብአዊ መብት ጥሠቶች የሚወነጀሉትና ክልሉን ለ8 አመታት ያስተዳደሩት አቶ አብዲ መሃመድ ኡመር በአሁን ወቅት በአዲስ አበባ በቁም እስር ላይ እንደሚገኙ ምንጮች የጠቆሙ ሲሆን እሳቸውን በጊዜያዊነት ተክተው ለሁለት ሳምንት ክልሉን የመሩት አቶ አህመድ አብዲ ከስልጣናቸው ተነስተዋል፡፡
አቶ ሙስጠፋ ከክልሉ ፕሬዚዳንትነታቸው በተጨማሪም የሶህዴፓ ም/ሊቀመንበር ሆነውም ተሾመዋል፡፡
የ45 አመቱ አቶ ሙስጠፋ ኡመር፤ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ውስጥ የምስራቅ አፍሪካ የሰብአዊ ድጋፍ ማስተባበሪያ ፅ/ቤት ሃላፊ በመሆን በሞቃዲሾ፣ ዚምባቡዌ፣ ዩናይትድ አረብ ኤምሬትና ኬንያ ተዟዙረው መስራታቸው ታውቋል፡፡
የመብት ተሟጋቹ አቶ ሙስጠፋ፤ በሠብአዊ መብት ጥሠቶች የሚወነጀሉትን የቀድሞውን የክልሉ ፕሬዚዳንት አብዲ ሙሃመድን በማህበራዊ ሚዲያ መድረኮች በንቃት በመተቸትና በማጋለጥ ይታወቃሉ፡፡
ይህ በዚህ እንዳለ ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ 1 ሺህ ከሚሆኑ የክልሉ ነዋሪዎች ተወካዮች ጋር በአዲስ አበባ ትናንት መወያየታቸውንም ምንጮች ጠቁመዋል።
የክልሉ ገዥ ፓርቲ ሶህዴፖ (የሱማሌ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ) በቅርቡ ባካሄደው አጠቃላይ ግምገማ ባለፉት ጊዜያት በክልሉ ከፍተኛ የሠብአዊ እና ዲሞክራሲያዊ መብት ጥሠቶች እንደነበሩ አስታውቋል። በክልሉ የከፋ የሙስና እና የኪራይ ሠብሣቢነት ችግር እንደነበርም በመግለጫው አትቷል፡፡
በቅርቡ በክልሉ ተከስቶ በነበረው ብጥብጥ እና ግጭት ውስጥም የአመራሩ እጁ እንዳለበት የጠቆመው፤ ፓርቲው ለዚህም ጥፋተኞች ተጠያቂ እንደሚደረጉ አስታውቋል፡፡ በዚህ ሁከት እና ብጥብጥ ለሞቱት ንብረት ለመዘረፉና እንዲሁም ለመውደሙ፣ ለተፈናቀለው ሠላማዊ ህዝብ ይሄው አመራር ተጠያቂ እንደሚሆን በመግለጫው ተጠቁሟል፡፡
አዲሱ አመራርም ያለፉትን ጥፋቶች በማረም እና በክልሉ መልካም አስተዳደር ለማስፈን እንደሚሰራ የፓርቲው መግለጫ አትቷል፡፡

Read 3504 times