Saturday, 25 August 2018 13:15

የአሜሪካ ኮንግረስ አባላት ከመንግሥትና ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር ተወያዩ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

 በኢትዮጵያ ጉብኝት ያደረጉት የአሜሪካ ኮንግረስ አባላት በኢትዮጵያ ወቅታዊ የፖለቲካ ማሻሻያዎች ላይ ከጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ፤ ከፖለቲካ ድርጅቶች እና ከአባገዳዎች ጋር ተወያዩ፡፡
ቀደም ሲል መንግሥት በፈፀማቸው የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ጉዳይ HR128 የተሰኘ የውሳኔ ሃሳብ ለአሜሪካ ኮንግረስ በማቅረብ የሚታወቁት አምስቱ የኮንግረሱ አባላት ከፓርቲ መሪዎችና አክቲቪስቲች ጋር ባደረጉት ውይይት፤ አሁን በሀገሪቱ ስላለው የሰብአዊ መብት አያያዝና የፖለቲካ ምህዳር ይዞታ በስፋት መነጋገራቸው ታውቋል፡፡
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ አመራሮችን ጨምሮ ከወልቃይት የማንነት ኮሚቴ፣ ከአማራ ማህበር በሰሜን አሜሪካ እና ከአማራ ክልል ከተውጣጡ አክቲቪስቶች ጋር በሸራተን አዲስ በተደረገው የተናጠል ውይይት ወቅት፤ በዋናነት በሀገሪቱ ስላለው የዲሞክራሲና የሰብአዊ መብት ይዞታ መሻሻል ጉዳይ ውይይት ተደርጓል፡፡
በዚህ ውይይትም የሀገሪቱ የፖለቲካ ምህዳርና የዲሞክራሲ ይዞታ እንዲሁም የሰብአዊ መብት ሁኔታ የበለጠ መሻሻል እንዳለበት፣ ለዚህም የኮንግረስ አባላቱ ያልተቋረጠ ድጋፍ ወሳኝ መሆኑ ተገልጿል፡፡
በተመሳሳይ የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስን ጨምሮ ከኦሮሞ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ አክቲቪስቶችና አባ ገዳዎች ጋር የኮንግረስ አባላቱ በነበራቸው የተናጠል ውይይት፤ የሀገሪቱ የፖለቲካ ምህዳር በሚሰፋበትና ነፃ፣ ፍትሃዊና ተአማኒ ምርጫ መካሄድ በሚችልበት ሁኔታ ላይ ምክክር መደረጉን የኦፌኮ ሊቀ መንበር አቶ በቀለ ገርባ ለአዲስ አድማስ አስረድተዋል፡፡
የሀገሪቱ የምርጫ ስርአት፣ ምርጫ አስፈፃሚው አካል፣ የፍትህ ስርአትና የሠብአዊ መብት ተሟጋች ተቋማት ነፃ ሆነው በሚደራጁበት ሁኔታ ላይ የኮንግረስ አባላቱ ድጋፍ እንዲያደርጉ በውይይቱ ወቅት መጠየቁን አቶ በቀለ ጠቁመዋል፡፡
የኮንግረስ አባላቱ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ጋር በነበራቸው ቆይታም በተመሳሳይ አጀንዳዎች ላይ ውይይት መደረጉን የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቃል አቀባይ አቶ ፍፁም አረጋ አስታውቀዋል፡፡
የHR128 ውሳኔ ሃሳብን ለአሜሪካ ኮንግረስ በማቅረብ የሚታወቁት የኮንግረስ አባላቱ ውሳኔ ሃሳቡ ለሀገሪቱ ላዕላይ ም/ቤት መቅረቡን ከመግለፅ ውጪ ዝርዝር ሃሳብ ከመስጠት መቆጠባቸውን በውይይቱ የተሳተፉት አቶ በቀለ ገርባ ጠቁመዋል፡፡ በዶ/ር ዐቢይ አህመድ አስተዳደር በአጭር ጊዜ የመጣውን ለውጥ ያደነቁት የኮንግረስ አባላቱ፤ “የኢትዮጵያ ህዝብ የላቀ አመራር ማግኘት ይገባው ነበር፤ ያንንም አሁን እያገኘ ነው” ብለዋል፡፡

Read 2240 times