Print this page
Saturday, 25 August 2018 13:14

በአዲስ አበባ በ100 መኪኖች ከሚገጩ ሰዎች 23ቱ ይሞታሉ

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(0 votes)

 46 በመቶ የሚሆኑት ለከባድ ጉዳት ይዳረጋሉ
              
     በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በሚደርሱ ትራፊክ አደጋዎች የሚሞቱት ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ መጠን እየጨመረ ሲሆን በከተማዋ ተሽከርካሪዎች በእግረኞች ላይ ከሚያደርሱት በአንድ መቶ የግጭት አደጋዎች፣ ሃያ ሶስት ሰዎች ህይወታቸው እንደሚያጡ ተጠቁሟል፡፡
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክስ ኮሚሽን አዳራሽ ውስጥ ከነሐሴ 17 ቀን ጀምሮ ለሁለት ቀናት በተካሄደው ኮንፍረንስ ላይ እንደተገለፀው፤ በከተማዋ ተሸከርካሪዎች እግረኞችን ገጭተው የሚያደርሱት የሞት መጠን በከተማዋ በትራፊክ አደጋ በሚደርሰው የሞት አደጋ 84 በመቶውን ይይዛል፡፡
በኮንፈረንሱ ላይ ጥናታዊ ጹሁፍ ያቀረቡት አቶ ወንድወሰን ታደሰ እንደገለፁት፤ ባለፉት ሶስት ዓመታት በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በትራፊክ የደረሱ የሞት አደጋዎች ከኦሮሚያና ከአማራ ክልሎች በመቀጠል በ3ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡ በእነዚሁ ሶስት ዓመታት በመላው አገሪቱ በትራፊክ አደጋ ምክንያት ከተከሰቱ የሞት አደጋዎች አስር በመቶ የሚሆነው የደረሰው በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ነው።
በተሽከርካሪዎች የግጭት አደጋ ሳቢያ ህይወታቸው ከሚያልፈው 85 በመቶ የሚሆኑት በተሽከርካሪው ግጭት የደረስባቸው ሰዎች ሲሆን አሽከርካሪዎቹ በአደጋው ህይወታቸውን የሚያጡት 15 በመቶ የሚሆኑት እንደሆነም አቶ ወንደሰን ተናግረዋል፡፡ ይህም አገሪቱ በተሽከርካሪ አደጋ ህይወታቸውን የሚያጡ እግረኞች ቁጥር በአፍሪካም ሆነ በአለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ እንደሆነ ይጠቁማል ብለዋል- አቶ ወንደሰን ጨምረው ገልፀዋል፡፡
በአዲስ አበባ የሞት አደጋ የሚያስከትሉ ከፍተኛ የትራፊክ አደጋዎች በአብዛኛው የሚከሰቱት ከምሽቱ አንድ ሰዓት እስከ ሁለት ሰዓት ባለው ጊዜ ውስጥ እንደሆነም እኚሁ ጥናታዊ ፅሁፍ አቅራቢ ተናግረዋል፡፡
የተሽከርካሪዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መሄድ፣ የመንገዶች ብቁ አለመሆን፣ የትራንስ ፓራት ፍላጎት መጨመርና ቁጥጥሩ በበቂ መጠን አለመደረጉ የሚደርሰውን የትራፊክ አደጋ ጉዳት እንዲጨምር ማድረጉን የገለፁት አቶ ወንድወሰን፤ ይህንን ችግር ለመቀረፍ ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ቁርጠኛ እርምጃ መውሰድና በጋራ መስራት ይገባቸዋል ብለዋል፡፡
በሉሲ ኮንሰልታንሲ ኢንጂነሪንግና በጅማ ዩኒቨርሲቲ ትብብር ለሁለት ቀናት በኢሴኤ አደራሽ ውስጥ የተካሄደው አመታዊ ኮንፍረንስ በርካታ ጥናታዊ ፅሁፎች ቀርበውበታል፡፡


Read 2243 times