Saturday, 25 August 2018 13:09

መኪና አስመጪዎች በገቢዎችና ጉምሩክ ላይ ቅሬታ አቀረቡ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

       ያገለገሉ መኪናዎችን ወደ አገር በማስገባት ሥራ ላይ የተሰማሩ የነበሩ አገር ውስጥ የሚኖሩና በውጭ የሚገኙ ከ53 በላይ ነጋዴዎች ወደ አገር ውስጥ ያስገቧቸው ከ1500 በላይ ተሽከርካሪዎች ያለ አግባብ ቀረጥ ተጭኖባቸው ያለ ሥራ ለ6 ወር ያህል መቆማቸውን በመግለፅ፤ በገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ላይ ቅሬታቸውን አቀረቡ፡፡
ነጋዴዎቹ ከትላንት በስቲያ ረፋድ ላይ መስቀል ፍላወር አካባቢ በሚገኘው ናዝራ ሆቴል ውስጥ በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት፤ እስከዛሬ በነበረውና በተለመደው አሰራር አንድ ያገለገለ መኪና ወደ አገር ሲገባ 231 ሺህ ብር ቀረጥ ይጣልበት እንደነበር አስታውሰው፤ የመኪናውን ሲሲ እያሳነሳችሁ ታስገባላችሁ በሚል ሰበብ ቀረጡን ወደ 480 ሺህ (120%) አሳድገው ለችግር ተጋልጠናል፤ ለገቢዎችና ጉምሩክ አቤቱታ እያቀረብን ስንመላለስ 6 ወራት በማለፉ ያለንን ብር በሙሉ በመኪኖቹ ላይ አፍስሰን ለኑሮ ቀውስ ተዳርገናል ሲሉ አማረዋል፡፡
ገቢዎችና ጉምሩክ በበኩሉ፤ የአንድ መኪና ቀረጥ የሚተመነው በሲሲው (በጉልበቱ) እንደሆነ ገልፆ፤ ነጋዴዎቹ ለረጅም ዓመታት 1.5 ሲሲ የነበረውን መኪና ወደ 1.3 ሲሲ ዝቅ በማድረግ ያለ አግባብ ሲያተርፉ ገቢዎችና ጉምሩክም ይህን ሳያውቅ ሲሰራ ቆይቷል፤ ነገር ግን አሰራሩ ህገ ወጥ በመሆኑ መቆም እንዳለበት ስንነግራቸው መቃወም ጀመሩ ሲል አስታውቋል፡፡ ነጋዴዎቹ እንደሚሉት፤ መኪኖቹ ኢንጂናቸው ተቀይሮ ሊሸጡልን ይችላሉ፤ መንግሥትም ማየት ያለበት መኪኖቹ ምን ነበሩ የሚለውን ሳይሆን አሁን ያላቸው ይዘት ምንድን ነው የሚለውን በመሆኑ ጉዳዩን ግምት ውስጥ በማስገባት እልባት ሊሰጠን ይገባል ብለዋል፡፡ “የምናስገባቸው መኪኖች በፈረንጆቹ 2003 የተመረቱና ከ15 ዓመት በላይ ያገለገሉ እንደመሆናቸው፣ ከአንዱ ወዳንዱ ሲተላለፉ የተለያየ ነገራቸው ሊቀየር ይችላል” ብለዋል፡፡ “እኛም መኪኖቹን ስናስገባ ከመንገድና ትራንስፖርት ፈቃድ አውጥተን፣ የመኪኖቹ ይዘት ተፈትሾና ብሔራዊ ባንክ ዶላር ከፍሎባቸው ስለሆነ ገቢዎችና ጉምሩክ ያመጣው ድንገቴ አሰራር ከእኛ በተጨማሪ በአገር ኢኮኖሚ ላይ ኪሳራ እያደረሰ ነው” ይላሉ ነጋዴዎቹ፡፡
ላለፉት 6 ወራት ከታገቱት መኪኖች መንግሥት 361 ሚ. ብር አጥቷል ያሉት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፤ እንደቀድሞው አሰራራቸው ቢሆን በስድስት ወራት ውስጥ አራት ዙር መኪና ሊያስመጡ ይችሉ እንደነበርና መንግሥትም ከ1.4 ቢ. ብር በላይ ማግኘት ሲገባው አጥቷል ብለዋል፡፡
በገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን የኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ኤፍሬም መኮንን በበኩላቸው፤ ነጋዴዎቹ እስከዛሬ ባለስልጣኑ ሳይነቃባቸው የመኪኖቹን ጉልበት እያሳነሱ ሲጠቀሙ መቆየታቸውን ገልፀው፤ አሁን ሲነቃ በመኪኖቹ ጉልበት መቀረጥ አለባችሁ ሲባል ፈቃደኛ አለመሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
በጉዳዩ ላይ መፍትሄ ለማምጣት ከነጋዴዎቹም ሆነ ከባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ኮሚቴ ተዋቅሮ ጉዳዩ ከባለስልጣኑ አቅም በላይ በመሆኑ ለገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር መተላለፉን የገለፁት አቶ ኤፍሬም፤ ሚኒስቴሩ ጉዳዮን ለመጨረስ የሚያስቸግረው ከሆነ እስከ ሚኒስትሮች ምክር ቤት ሊደርስ እንደሚችል ተናግረዋል፡፡  

Read 3382 times