Print this page
Saturday, 12 May 2012 09:28

የህይወት ወግ ዘመን ሲዘከር

Written by  ቃል ኪዳን ይበልጣል
Rate this item
(0 votes)

ከአስተማሪው ጓደኛዬ ጋር ሁለት ጠባብ ክፍሎች ያሏት ቤት ውስጥ ተዳብለን መኖር የጀመርንበት ጊዜ ከሁለታችንም ልቦና በመላመድ ዝንጋኤ ተውጦ ጠፍቷል፡፡ ምናልባት ይሄ የክራሞታችንን ስምረት ይጠቁም ይሆናል፡፡ ጥምረትስ ቢሆን “የተወለደበትን” ቀን አስቆጥሮ የሚያስረግመው መንገራገጭ ሲበዛበት አይደል? መርፌና ክር አድርጐ ያዋሃደን እንግዲህ ከኑሮ መደጋገፍ የሚዘል የጠባይ ትውውቅና እርስበርስ መፈላለግ ነው፡፡ ማለቴ - ወሬ ለእርሱ በጣም አስፈላጊ የህይወት አካል ነው፡፡ በሰርክ ውጣ ውረዱ የሚያጋጥሙትን ኩነቶች፣ በልቡ ከሚያጭሩት የስሜት ቅንጣት እንዲሁም በአዕምሮው ከሚፈጥሩት የአመለካከት ዘንግ ጋር አስተሳስሮ እንዲገልጽ፣ እንዲደመጥም ይወዳል፡፡ ይህ አመሉ ታዲያ ለእኔ በጀኝ፡፡ የዘወትር ወጐቹ የጽሑፍ ስራዬን የሚያበረቱ የሃሳብ ማመንጫ ጄኔሬተሮች አሊያም የግርድፍ አስተያየት ማላሚያ ወፍጮዎች ሆነው ተገኙ፡፡

በቀደም ለታ እንደወትሮዋችን AMY COFFEE ተጐልተን፣ በስኒ አራት ብር የሚያስከፍል ጥዑም ቡና እየደጋገምን ያለቅጥ የሚያዘግመውን ቀን ወደ ምሽት መለወጥ እንጠባበቃለን፡፡ Long Day’s Journey into Night የተባለውን ተውኔት የትኛው አሜሪካዊ እንደፃፈው ለማስታወስ በከንቱ ስባዝን ሳለ የጓደኛዬ ጥያቄዎች አባነኑኝ፡፡ “የጀበና ቡና አብዮት አንድምታ ምንድነው?  ቤቱስ እንደ ደብል ፌስ ጃኬት ከውስጥና ከውጭ ለየቅል የሆኑ ሁለት መልኮች የያዘው ስለምን ነው? የቃጫ ጆንያ ተተርትሮ ለግድግዳ ማስዋቢያነት እንዲውል አስቀድሞ ያጨው ማን ይሆን?”ኮስታራ አትኩሮቴን ለገስኩት፡፡ አንዲት ሀቲት ሊያቀብለኝ የመሰናዳቱን መንደርደሪያ አላጣውም፡፡ ቀጠለ፡፡ “ዙሪያ ገባውን ተመልከት፡፡ የተከበብንባቸውን ቁሳቁሶች ልብ በል፡፡ ጊቤን አቋርጦ የመጣ ጉድጓዳ የእንጨት ወንበር፣ ሳጠራና የሸክላ ምጣድ ተጋግዘው የሰሩት ጠረጴዛ፤ የፋኖስ ቀፎ ውስጥ የተንጠለጠለች አምፑል፣ የሰበዝና የአክርማ ሙዳዮች፣ ስፌቶች - አሁን እንደቀድሞው ለአገልግሎት ታስበው አይሰሩም፡፡ ማስታወሻነታቸው ብቻ ቀርቷል፡፡ የቅርብ ወቅት እውነታዎቻችን በሙሉ ወደ ቅርስነት መንደርየሚምዘገዘጉበት ፍጥነት ያስገርማል፡፡ ሰፊው ረከቦት ከነስኒዎቹ መድረክ ከመሰለ ጉብታ ላይ ተኮፍሶ ይታይህ፡፡ ከጀርባው አሳላፊያችን ኤሚ፤ ከነተለጣፊ ፈገግታዋ ትቁለጨለጭልሃለች፡፡ ኤሚ እኔና አንተን ለመሰሉ የዘመኑ ባተሌዎች ልዋጭ እናት ወይንም ሚስት ናት፡፡ ክፉኛ የራቁህ ልጅነትህና የመጪው ጊዜ ተስፋህ አስታዋሽ ናት፡፡ ቡናዋን ቆላልታ፣ ጭሷን አጫጭሳ፣ ፈንድሻዋን አፈካክታ የቀዘቀዘ ሳሎንህን ልታስዘነጋህ ትጥራለች፡፡ ቁርስ፣ ምሳ፣ ራት በቀረበልህ ቁጥር ቡና የሚፈላበት ወርቃማ ጊዜ የተፈፀመ አይመስልህም? አንድም የተሰነግንባቸው እጥረትና ውጥረት ባካናዎች አድርጐናል፡፡ አንድም የጥንቱን ያህል ተሳስረን መኖር አቁመናል፡፡ አማራጮቻችን ኤሚ እና ብጤዎቿ ናቸው፡፡ ምናልባት ደግሞ ከዚህ ቀጥላ በቁንዶ በርበሬ የተቆደሰ አዋዜ እና የጠላ ቂጣ የሚሸጥ ሱቅ ትከፍት ይሆናል፡፡ ማን ያውቃል? ከጭንቅላቷ ከፍ ብሎ ደግሞ ይታይሃል? የግዕዝ ሆሄያትና ቁጥሮች የተቀረፁባቸው ሰሌዳዎች ተደርድረዋል፡፡ ኤሚ ቁጥሮቹን ለይታ አታውቃቸውም፡ እየነካካችው ባለችው ተንቀሳቃሽ ስልኳ የመዘገበቻቸውን የወዳጆቿን ስም ለመፃፍ የምትጠቀመው የላቲን ሆሄያትንነው፡፡ በቡና ቤቷ መግቢያ ያስሰቀለችው ትልቅ የንግድ ስያሜ ማስታወቂያ እንኳ አንዲትም የግዕዝ ፊደል አልያዘም፡፡ ሰሌዳዎቹን ከአናቷ በላይ የማስቀመጧ ፋይዳ እንግዲያውስ ምንድነው? በማስታወቂያው ላይ በጉልህ ያስቀመጠችውን ፎቶግራፍ በተመለከተስ ምን ማለት ይቻላል? እውነትም ሁሉም ሰው የየራሱን የሩብ ሰዓት ዝና የሚያጣጥምበት ጊዜ ላይ የደረስን ይመስላል፡፡ ይሄ 15 minutes of fame የሚሉት ነገር፡፡ ማንም በረብ የለሹ ግብር ሁሉ ራሱን ሊያሳውቅ ይችል ዘንድ ዘመኑ ፈቅዷል፡፡ “እከሌ ጫት ቤት” ትልና ከጫቱ ጐን ፎቶህን ገጭ! ሀቅ አይታበልምና አሳላፊያችን ደማም ጉብል ናት፡፡ የትኛውንም ሰው ልታስደነግጥ ትችላለች፡፡ ሆኖም ጉንጯ ላይ ሚጢጢ ለምጽ አለች፡፡ ጭረት ነገር፡፡ የክፉ የኋላ ታሪክ ማስታወሻ ትሆን? እንጃ፡፡ ምንም ትሁን ኤሚ አልወደደቻትም፡፡ ስለዚህም ከፎቶ ግራፏ አጥፍታታለች፡፡ እድሜ ለቴክኖሎጂ እውነትህን ማስተካከልም መቆጣጠርም ተችሏል፡፡ የገጽታህን እንከኖች፣ ብጉሮችህን፣ መግባት የጀመረ ፀጉርህን ወዘተ ማረም ትችላለህ፡፡ ያጠረውን ታረዝማለህ፡፡ የረዘመውን ትከረክማለህ፡፡ ፎቶ አንሺው እንደ ፕላስቲክ ቀዶ ጠጋኝ ነው፡፡ መምሰል የምትሻውን ያስመስልሃል፡፡ ያንን ምስል ደስ እያለህ ትወስድና ፌስቡክ ላይ ትለጥፈዋለህ፡፡ ከስሩ ስለራስህ በርካታ በጐ በጐ ነገሮችን ትጽፋለህ፡፡ ለጓደኞችህ ሆነህ መታወቅ የምትመኘውን አይነት አማራጭ እውነት ትፈጥርላቸዋለህ፡፡ አስቀድሜም እንዳልኩህ ዘመኑ የልዋጭ ነው፡፡ የአማራጭ እውነቶች መፈብረኪያ፡፡ እውነተኛ ወዳጆች ማፍራት ቢሳንህ Virtual ጓደኛችን ፌስ ቡክ ያገናኝሃል፡፡ ዘፋኝ መሆን ሻትክ እንበል፡፡ ተፈጥሮ ግና ልትጫወትብህ ፈልጋ መረዋ ድምጽን ነሳችህ፡፡ ስለዚህ አንተ ይታደሉታል እንጂ አይታገሉትም ብለህ ፊትህን ታዞራለህ! በኛ ጊዜ አታደርገውም፡፡ ሳትታደልም ሳትታገልም ከጉሮሮህ እየተጥመለመለ የሚወጣውን ሰቅጣጭ እንጉርጉሮ ታርቀዋለህ፡፡ ትሞርደዋለህ፡፡ በልከኛ ምጣኔ ታስተካክለዋለህ፡፡ ማራኪ ቅላፄ ትፈጥርና “የእኔ ነው፡፡ እንካችሁ” ትላለህ፡፡ የሚያጅብህ ኪ - ቦርድ፣ ሳክስፎን የሚመስል ድምጽ ይለቅልሃል፡፡ ከአጠገቡ ከፕላስቲክ የተሰሩ እውነተኛ መሳይ በድን አበቦች ታኖርም ይሆናል፡፡ ማን ያውቃል? ልዋጭ ምሁራንም ሞልተውልሃል፡፡ መቸስ አሁን አሁን ስለሆነ ጉዳይ አብጠርጥሮ ለመተንተን የግድ የጠለቀ እውቀት እንድትይዝ አትገደድም፡፡ ድረ-ገጽ የሚሰኝ የጥራዝ ነጣቂዎች መናኸሪያ ምስጋና ይግባው፡፡ ሬዲዮ ስትሰማ ምን እንደሚያጋጥምህ ልገምትልህ - የዲጄ ፈላስፎች፡፡ ዘፈን እያዘነቡልህ በየመሃሉ ስለኑሮ እና ብልሃቱ ሊያስረዱህ ይሞክራሉ…አመለወርቅ የነበረውን የልጅነት መጠሪያዋን ትታ “ኤሚነት”ን የመረጠችው ቆንጆ የዘመናችን ወካይ ናት ማለት እችላለሁ፡፡ ውብ ስሟን ለምን ቆነፀለችው? ከጊዜው ጋር አይሄድማ አንድ ረዥም ነው፡፡ ለመንዛዛት ቦታ የለም፡፡ ትኩረት የለም፡፡ የስልክየጽሑፍ መልዕክቱም ስሙም ምኑም ቢያጥር ጥሩ ነው - ተብሏል፡፡ በዚያ ላይ “ኤሚ” የውጭ ሀገር ቀለም አለው፡፡ ግራ የገባው ነገር - ወዲህ የፈረንጅ ስም ወዲያ የአቡነ ተክልየ ስዕል፡፡ አለባበሷም ከወቅቱ የተዋደደ ነው፡፡ ጂንስ በሸማ፡፡ አየህ መቀላቀል መደባለቅ፤ መቀያየጥ የወቅቱ ፈሊጥ ነው፡፡ Fusion እንደዚህም ገንኖ አያውቅ፡፡ ያልተፈወዘ ምን አለ? ባቲ እና ብሉዝ፣ ትዝታ እና ሮክ፣ እስክስታ እና ሂፕ ሆፕ፣ ቄጠማ እና የገና ዛፍ፣ ሹርባ እና ፍሪዝ - ፓስታ በእንጀራ ይሉሃል ይሄ ነው….”በከፊል የተራቆቱ ሶስት እንስቶች በቀው ቀጭ አረማመድ ወደ ውስጥ ዘለቁና ከዲስኩሩ ገቱት፡፡ ወዲያውም ከምልከታው የተፈናጠረ ወጉን ለጠቀ፡፡ “ለሺህ ዓመታት ተዘግተን፣ ከምስጢር ምሽግ ጀርባ አድፍጠን ማቀርቀራችን ላይ ለበቀል ዘመትን እንዴ? ድንገት እርቃን የመቅረት ፍቅር ከየት ፈለቀ ታዲያ? አባባሌን ከሴት ገላ እና አለባበስ አንፃር ብቻ አትረዳው፡፡ የጓዳቸውን ጣጣ ለአደባባይ ጥናት የሚያውሉ ደፋሮች አልበዙብህም? የመንፈስ ቁስላቸውን በሬዲዮ የሚናዘዙት? ምናልባት እየተውነው የመጣነው የድጋፍና የምክር መረብ አውታሮች - የነብስ አባቶች፣ ቀሳውስት፣ በእድሜ የተፈተኑ አዛውንቶች - እየቀሩ በስፍራቸው አማካሪ ሐኪሞችና የስነ ልቦና ባለሞያዎች እየተተኩ ይሆናል፡፡ ኑዛዜውና ግሳፄው እንዲሁም ምክሩ ግን የመሸፋፈን ፀጋውን አጥቷል፡፡ የሚከወነው በደጀ ሰላም አፀድ ስር ሳይሆን በሸንጐ ህዝብ እየታደመው ሆኗል፡፡ ሸንጐውም ስቱዲዮ ይባላል፡፡ ዘመንኛ ቤቶቻችን እየተገነቡ ያሉበትን አግባብ ስታጤን ደግሞ በቀዝቃዛ መወናበድ ትቸለሳለህ፡፡ ምንድነው የንብና ኤሌክትሪክ አጥርን ጋጋታ፣ የብረት በርን ሙጥኝታ የወለደው? አንዳንዴ “ከውስጥ ምን ደብቀው ይሆን?” ብለህ ለመገረም ትገደዳለህ፡፡ ግን ድብቅነትን አልመሰለኝም አጥሮቹ የሚጠቁሙት፡፡ ፍርሃትን ነው! ግዘፍ ነስቶ በሀገሩ የናኘው ስሜት እርሱ ነው፡፡ ምንድን ነው የሚፈራው? እግዚሃር ይወቀው!፡፡…”

በኋላ የዘመን ተቃርኖዎችን አስታርቄ አንዳች መላቅጥ የያዘ እውነታ ላይ ለመድረስ እየታገልኩ፤ ከስራ ጠረጴዛዬ ፊት ተሰየምኩ፡፡ የጨለማው ንግስና ሲጠናከር፣ አህዛብ ሁሉ በየስርቻው ተወትፎ ለእንቅልፍ ነብስያውን ሲሰጥ፣ የአስተማሪው ጓደኛዬ አንደበት እንኳ እረፍት ሸቆ ሲሸነፍ፣ ምድር ፀጥ ስትል ብዕሬን አሾልኩ፡፡ በዚህ በኩል የእድገት አዋጅ ነጋሪት፣ በዚያኛው ድህነት አላምጦ፣ ወዛቸውን መጦ በየጐዳናው የተፋቸው ነዳያን የጣር ድምጽ፤ የ“ማን እንደሀገር” ዘፈኖች ዶፍ እና በየኤምባሲው ደጅ የሚረዝሙ ሰልፎች፣ ወደ የድንበሩ የሚከንፉ እግሮች እንደምን ይጣጣሙ? እንዴት ይስማሙ? ግራይገባል ጃል፡፡ ምናልባት ገዥው መንፈስ ይህ ይሆን እንዴ? ግራመጋባት፡፡ ጥያቄ ማብዛት እርግጠኝነት

ማጣት …በቆየውና በሚመጣው መሃል መዋለል…

 

 

 

Read 3026 times Last modified on Saturday, 12 May 2012 09:42