Saturday, 25 August 2018 13:10

( Fungal Infection) በሴቶች ብልት የሚታይ መመረዝ…

Written by 
Rate this item
(0 votes)


   ብዙ ሰዎች Fungal Infection በመባል በሚታወቀው የኢንፌክሽን አይነት ይጠቃሉ። መነሻችን ከብልት ጋር በተያያዘ ያለውን ሁኔታ ለማየት ቢሆንም ሰዎች ይህ ኢንፌክሽን ወይንም የሰውነት መመረዝ የሚደርስባቸው በተለያዩ የሰውነት ክፍሎች ላይ ነው፡፡ ከላይ የምትመለከቱት በፊትና በምላስ ላይ በምን መልክ እንደሚወጣ ነው፡፡ በሺዎች ከሚቆጠሩ የፈንገስ አይነቶችም ጥቂቶቹ ናቸው ሰውን ለሕመም የሚዳርጉት፡፡ ብዙ ሰዎች ደግሞ በተፈጥሮ የበሽታ መቋቋም ኃይላቸው ጠንካራ ስለሚሆን በዚህ በሽታ አይጠቁም፡፡ ለምሳሌም በሕክምና ያልታገዘ የኤችአይቪ ኢንፌክሽን ያለበት ሰው ወይም የካንሰር ሕመም ላለባቸው ሰዎች የሚሰጠው እንደ ኬሞቴራፒ ያለው ሕክምና የበሽታ መቋቋም ኃይልን ሊፈታተን ይችላል፡፡ ለረጅም ጊዜ የሚወሰድ የበሽታ መከላከያ መድሀኒቶች (antibiotics) ለሕመሙ ለመጋለጥ ምቹ ሁኔታን ይፈጥራሉ ተብሎ ይታሰባል፡፡ ባጠቃላይም የፈንገስ ኢንፌክሽን በተለያዩ የሰውነት ክፍሎች ላይ እንደሚወጣ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
በእግር ላይ የሚወጣ ፈንገስ፤ ይህ የፈንገስ አይነት Tinea Pedis በመባል ይታወቃል፡፡
ሌላው ቀይ ወይንም ብርማ መልክ ያለው በሰውት ላይ የተጉረበረበ ምልክት የሚያሳይ ነው፡፡ ባብዛኛውም ክብ ቅርጽ የሚይዝ ነው፡፡
በጭንቅላት ወይንም በራስ ቅል ላይ የሚታየው በሳይንሳዊ አጠራሩም Tinea Capitis  ይባላል፡፡
Onychomycosis የተሰኘው የፈንገስ ኢንፌክሽን የሚታየው በአብዛኛው በእግር አውራ ጣት ላይ ወይንም ሌላው የእግር አካል ላይ እንዲሁም በሌሎች ጣቶች ጥፍሮች ላይ ነው፡፡ ይህ በመራመድ ወይንም በመጫማት ጊዜ ሕመም ሊኖረው ወይንም ምቾት ሊያሳጣ ይችላል፡፡
Tinea Versicolor  የተሰኘው ደግሞ ከሌላው የአካል ክፍል ቀለምን ለየት በማድረግ በትናንሽ ክቦች በተለያዩ የሰውነት አካላት ላይ የሚታይ የፈንገስ ኢንፌክሽን ነው፡፡ ጠቆር ወይንም ደብዘዝ፤ ቀይ ወይንም ፒንክ እንደሚባለው ቀለም ባለ መልክ ከሌላው የቆዳ ክፍል ቀለም ሊለይ ይችላል፡፡
ብዙ ጊዜ ሙቀት ባለው ወይንም እርጥበት በሚሰማው የሰውነት ክፍል ሊፈጠር የሚችለው ደግሞ በሳይንሳዊ አጠራሩ Cutaneous Candidiasis ነው፡፡ ይህ አይነቱ ኢንፌክሽን ከተለያዩ ሕክምናዎች ወይንም ውፍረት ፤የስኩዋር ሕመም፤በመሳሰሉት ሁሉ ሊከሰት የሚችል በየትኛውም የቆዳ ክፍል ሊከሰት የሚችል ነው፡፡
ከላይ የተገለጸው ይህ የኢንፌክሽን ሕመም በቆዳ ላይ ብቻ ሳይሆን በአፍ በጉሮሮ አካባቢ እንዲሁም ሴቶች በብልታቸው እንደሚከሰትባቸው እሙን ነው። ሴቶች በአብዛኛው ማለትም እስከ 75% የሚሆኑት በሕይወት ዘመናቸው በብልት አካባቢ የሚፈጠር ኢንፌክሽን ያጋጥማ ቸዋል፡፡ ጥናቶች እንደሚጠቁሙት ወደ 90% የሚሆኑት ኢንፌክሽኖች የሚፈጠሩት ደግሞ በሳይንሳዊ አጠራሩ Candida albicans በሚባለው ዝርያ አማካኝነት ነው፡፡ በእርግጥ ከ20-50% የሚሆኑት ሴቶች በተፈጥ ሮአቸው ይህ Candida የተሰኘው በተፈጥሮ በብልታቸው የሚገኝ መሆኑም ጥናቶች ያረጋግጣሉ፡፡ጤናማ የሆነ ብልት ባክቴሪያ (Bacteria) እና (Yeast) ይስት እንደሚኖረው እሙን ነው፡፡ ነገር ግን   ለኢንፌክሽን መፈጠር በብልት አካባቢ የሚ ኖረው ባክቴሪያ (Bacteria) እና (Yeast) ይስት በመባል የሚጠሩት መጠናቸው ሲዛባ በተለይም (Yeast) የይስት ህዋስ በእጥፍ ስለሚባዛ ችግሩ ይፈጠራል፡፡ በእርግጥ ይህ የኢንፌክሽን አይነት ምንም እንኩዋን በግብረስጋ ግንኙነት ምክንያት መተላለፍ ቢችልም ነገር ግን በግብረስጋ ግን ኙነት  ምክንያት ከሚተላለፉ በሽታዎች ውስጥ የሚመደብ አይደለም። ይህ የኢንፌክሽን አይ ነት በማንኛዋም ሴት ብልት ሊከሰት የሚችል ነው፡፡
የፈንገስ ኢንፌክሽን ለመከሰቱ የሚታዩ ምልክቶች፤
በወሲብ ግንኙነት ወቅት የህመም ስሜት፤
ሽንት ሲሸና ሕመም ወይንም ማቃጠል፤
ከብልት ውስጥ ወፈር ያለ ወደ ግራጫ የሚወስደው እና መጥፎ ጠረን ያለው ፈሳሽ ካለ የኢንፌክሽን ምልክት ሊሆን ይችላል፡፡
የማሳከክ፤ የመቅላት ወይንም የመጉረብረብ…መልክ ካለ ኢንፌክሽን ተፈጥሮአል ማለት ነው፡፡
ብልት ለኢንፌክሽን ከሚጋለጥባቸው ምክንያቶች የሚከተሉት ይገኙበታል፡፡
በብልት ውስጥ መገኘት የሚገባው የባክቴሪያ መጠን ሲቀንስ፤
እርግዝና፤
የህክምና ክትትል የማይደረግበት የስኩዋር ሕመም፤
የሰውነት የበሽታ መከላከል አቅም መቀነስ ፤
የተሟላ አመጋገብ አለመኖር፤
የሆርሞን መጠን መዛባት፤
ጭንቀት፤
የእንቅልፍ እጦት፤
የመሳሰሉት ለዚህ ኢንፌክሽን መፈጠር ምክንያት ይሆናል፡፡ ሆኖም ግን ይህ ሕመም በቀላሉ ሊታከም እና ሊድን የሚችል ነው፡፡
በሴቶች ብልት የኢንፌክሽን ሕመም ከ4/ሴቶች ሶስቱ ያህል በሕይወት ዘመናቸው የመያዝ አጋጣሚው አላቸው፡፡ አብዛኞቹ ቢያንስ ቢያንስ ለሁለት ያህል ጊዜ ሊታመሙ ይችላል፡፡ ከዚህ በተለየ በአንድ አመት ጊዜ ውስጥ ወደ አራት ጊዜ የታመሙ ሰዎች ካሉ ግን ተከታታይ የሆነ የህክምና እርዳታ እደሚያስፈልጋቸው መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
ኢንፌክሽኑን መከላከል ይቻላል፡፡
የተመጣጠነ ምግብ መመገብ፤
እርጎ በተ ጨማሪም ምግብን የሚረዱ እንደ ቫይታሚን ቢ ኮምፕሌክ ያሉትን መውሰድ፤
ልብስን በተመለከተም ከጥጥ የተሰሩ ወይንም ሐርነት ያላቸውን ልብሶች መልበስ
የውስጥ ሱሪን ሞቅ ባለ ውሀ ማጠብ፤
ከጥቅም ላይ የዋሉ የሴት ልብሶችን በቅርብ ጊዜ ወይንም በፍጥነት መተካትወይንም መለወጥ ያስፈልጋል፡፡
ማስወገድ የሚገቡ ነገሮች፤
እንደታይት የመሳሰሉ ሰውነትን የሚያጠብቁ እና ላስቲክነት ያላቸውን ልብሶች አለመጠቀም፤
እንደ ሽቶ ወይንም ጠረን መለወጫ የመሳሰሉ ኬሚካሎችን በብልት አካባቢ መጠቀምን ማቆም፤
ገላ በመታጠብ ጊዜ  ባጠቃላይ በብልት አካባቢ እርጥብ ልብስን ከውስጥ ለብሶ መቀመጥን ማስወገድ፤
የፈላ ውሀ ውስጥ መቀመጥ ወይንም መዘፍዘፍ ወይንም በተቀራረበ ሁኔታ ሙቀት ባለው መታጠቢያ ከመታጠብ መቆጠብ፤
ከላይ የተጠቀሱትን ድርጊቶች በመፈጸም ኢንፌክሽኑን አስቀድሞውኑ መከላከል ይቻላል፡፡

Read 1014 times