Saturday, 12 May 2012 09:22

ሁለት ጭብጨባዎች ለ’ኮሜዲያችን ጉዶች’

Written by  ትዝብት) ፊያሜታ
Rate this item
(0 votes)

ሚያዝያ 29 ቀን 2004 ዓ.ም

አመሻሽ ላይ፡፡የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቲያትር ከአፍ እስከ ገደፍ በታዳሚ ተጨናንቋል፡፡ ከጓዳ እስከ ደጃፍ በቀይቀለም አሸብርቋል፡፡ደራሲና ዳይሬክተር ቅድስት ባየልኝ ከአመታት ልፋትና ድካም በኋላ ከአትላንቲክ ባሻገር የደገሰችውን ሦስተኛ ፅዋዋን ‘ከአትላንቲክ ባሻገር’ን ይዛ ወደ አገሯ ተመልሳለች፡፡የጥበብ ፅዋዋን ለአገሯ ልጆች ልታቃምስ ተዘጋጅታለች፡፡ ከብሔራዊ ቲያትር ደጃፍ ቀይ ምንጣፍ ዘርግታለች፡፡ ጥሪዋን ሰምቶ ከየአቅጣጫው የጐረፈው ታዳሚም ውቅያኖስ ተሻግሮ የመጣለትን በረከት ለመቋደስ ጓጉቶ አዳራሹን ሞልቶ ይጠባበቃል፡፡በሰሜን አሜሪካ የተለያዩ የኢንተርቴይንመንት ፕሮግራሞችን በተሳካ ሁኔታ በማከናወን የሚታወቀውና በቅድስት ባየልኝ ተመስርቶ በራሷ የሚመራው‘ኢትዮውድ ኢንተርቴይንመንት’ ዝግጅቱን ባማረ መልኩ ለማከናወን ተፍ ተፉን ተያይዞታል፡፡

በአገሪቱ የመጀመሪያዋ ሴት የፊልም ደራሲ፣ አዘጋጅና ፕሮዲዩሰር የሆነችው ቅድስት፣ መጀመሪያ ‘ህይወት እንደዋዛ’ን፣ በመቀጠልም ‘ዕፀ-በለስ’ን፣ አሁን ደግሞ በአሜሪካሰርታያጠናቀቀችውን ‘ከአትላንቲክ ባሻገር’ የተሰኘ ሦስተኛ ፊልሟን ‘እነሆ!’ልትልነው፡፡በቅድስትባየልኝተደርሶናተዘጋጅቶበ’ኢትዮውድኢንተርቴይመንት’ ፕሮዲዩስ የተደረገው ‘ከአትላንቲክ ባሻገር’ በ’ቀይ ምንጣፍ’ ስነስርአት በደማቅ ሁኔታ በተመረቀባት በዚያች ምሽት እኔም ከታዳሚው መካከል ነበርኩ፡፡ በምረቃ ስነስርአቱ ላይ ተገኝቶ የ’ኢትዮውድ ኢንተርቴይመንት’ን የጥበብ ድግስ ሲቋደስ ካመሸው ታዳሚ መሃል ሆኜ ሁለቱንም ጭብጨባዎች አይቻለሁ፤ ሰምቻለሁ! ተመልካቹ ሲያጨበጭብ አመሸ - ሁለት ጭብጨባዎች!አንድም ለብስል፣ አንድም ለጥሬ፡፡ተመልካቹ ለብስሉ አጨበጨበለት፣ በጥሬውም አጨበጨበበት፡፡

 

በእለቱ በብሔራዊ ቲየትር መድረክ ለተመልካቹ የቀረበለት የጥበብ ማዕድ ከብዙ ብስል መካከል ጥቂት ጥሬ ስለተገኘበት በደፈናው ሊነወር አይገባውም፡፡‘ከኑግ ጋር የተገኘ ሰሊጥ…’ የሚሉትን አጉል አባባል በክስ ማቅለያነት በማቅረብ ከተጠያቂነት ለማምለጥ በማሰብ ኑጉንም ሰሊጡንም አብሬ አልወቅጥም፡፡

ከኑግ ጋር የተገኘን ሰሊጥ ያለ ዕጣው በጅምላ ማድቀቅ ችኩል ወቃጭ በሚሰነዝረው ዘነዘና የሚፈፀም ስህተት ነው፡፡ ይህን መሰል ስህተት ለመፈፀም አልፈልግም! ስለዚህ … መጀመርያ ኑጉን ከሰሊጡ መለየት ይቅደም፡፡ ሁለቱ በየጐራቸው ተለያይተው ሲታዩ ይሄን ይመስላሉ፡፡

አንደኛ ጐራ፡- “ኢትዮውድ”

ሁለተኛው ጐራ፡- “ኢትዮጉድ”

ኢትዮ ውድ፡- ተቀማጭነቱ በአሜሪካ የሆነና በደልም ደራሲና አዘጋጅ ቅድስት ባየልኝ ተመስርቶ፣ በእሷው እየተመራ ስኬታማ ጉዞ ላይ የሚገኝ ድርጅት ነው፡፡ “ኢትዮውድ” ከፍተኛ ወጪና ድካም ልፋት የጠየቀውን “ከአትላንቲክ ባሻገር” የተሰኘውን ፊልም በተሳካ ሁኔታ አጠናቅቆ “መርቆልኝ” ብሎ ወደ አገር ቤት ይዞ ለመምጣቱ ምስጋናና ውዳሴ ይገባዋል፡፡ ተመልካቹ በዕለቱ ከኢትዮ ውድ ማዕድ የተቋደሰውን “ከአትላንቲክ ባሻገር” ቀምሶ፣ ብስል ስለ መሆኑና ስለመጣፈጡ ምስክርነቱን በጭብጨባ ገልጿል፡፡ እርግጥም ኢትዮ ውድ ጭብጨባና ሙገሳ እንደሚገባው አምናለሁ፡፡ ድርጅቱ ጥሩ ፊልም ሰርቶ ወደ አገር ቤት ይዞ ከመምጣቱ ባሻገር እዚያው በአሜሪካ ሌሎች በርካታ አስመስጋኝ ስራዎችን እንደሚሰራ አውቃለሁ፡፡ በውጭ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን አርቲስቶችን በማቀራረብ የተሻለ የጥበብ ስራ መስራት የሚቻልበትን መንገድ በማመቻቸት ሲተጋ ቆይቷል፡፡ አርቲስቶች ችግር ሲገጥማቸው ከጐናቸው በመቆም ድጋፍ እንደሚያደርግ ለመመስከርም ድምፃዊ ደረጀ ዱባለን ከሞት ለመታደግ ያደረገውን ከፍተኛ ጥረትና ለቤተሰቦቹ ያበረከተውን ተጠቃሽ ድጋፍ መጥቀስ ይበቃል፡፡“ኢትዮውድ”ንሊያስመሰግነው የሚገባው ሌላው ነገር ደግሞ፣ በአይነቱ ለየት ያለ ሳምንታዊ የ”ስታንዳፕ ኮሜዲ” ዝግጅት በቤላ ቨርዴ ሆቴል ማስጀመሩ ነው፡፡ ይህም ብቻ አይደለም፡፡ ኮሜዲያኑ በአገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን ወደ ውጭ አገራት ሄደው ዝግጅታቸውን እንዲያቀርቡ መንገድ መክፈቱም “ጐሽ” ያሰኘዋል፡፡ ሰኞ ምሽት በብሔራዊ ቲያትር የጥበብ ገበታ ላይ ቀርቦ ታዳሚው ብስል ስለመሆኑ የመሰከረለትን፣ ቀምሶ ያጣጣመውንና ያጨበጨበለትን ከአትላንቲክ ባሻገርን የደገሰው “ኢትዮ ውድ” ይሄ ነው! …

ይሄን ያህል ካልኩ ኑጉን ከሰሊጡ የመለየቱን ስራ አከናወንኩ ማለት ነው፡፡ “ኢትዮውድ”ን ወደ ጐን አስቀምጬ፣ ወደ “ኢትዮጉድ” ልመለስ፡፡

“ኢትዮጉድ” ሰኞ ምሽት በብሔራዊ ቲያትር በተዘጋጀው የጥበብ ድግስ ለታዳሚው ከቀረበው ማዕድ “ኢትዮውድ”ን ነጥለን ስናወጣ ማዕዱ ላይ የሚቀረው “ኢትዮጉድ” ነው፡፡ “ኢትዮጉድ” በዕለቱ ለታዳሚው ለቀረበውና የመጀመሪያው የማዕዱ መሰናዶ ለሆነው የኮሜዲ ዝግጅት የተሰጠ ስያሜ ነው፡፡ ቃሉ ሌላ (የእንግሊዝኛ) ትርጉም እስካልተሰጠው ድረስ፣ ከዚህ በኋላ “ኢትዮጉድ” የሚለው ቃል በዕለቱ በ”አፒታይዘርነት” ታስቦ ለታዳሚው የቀረበውን የኮሜዲ ዝግጅት የሚገልፅ ነው፡፡ በተለያዩ አዳዲስና ነባር ኮሜዲያን ለቀረበው ለዚህ ዝግጅት “ኢትዮ ጉድ” የሚል ስያሜ የመስጠቴ ሰበብ፣ አሁንም አብሮ የተገኘን አብሮ በመውቀጥ ስህተት ላለመስራት ከመጠንቀቅ ይመነጫል፡፡ ኮሜዲያኑ ለመግቢያነት በጋራ ባቀረቡት “ሰለሜ ሰለሜ” የተሰኘ ትርኢት በጋራ መደነቅ እንዳለባቸው ሁሉ፣ በተናጠል ባቀረቧቸው ቀልዶችም “ኢትዮ ጉድ” ተብለው አንድም በአድናቆት፣ አንድም በንቀት መጠራት ይኖርባቸዋል፡፡ “ኢትዮጉድ” አንድ፡- በአድናቆት ‘ጉድ’ የሚያሰኝ የቀልድ ችሎታ ያላቸው እነ ልጅ ያሬድ፣ “ኢትዮ ጉድ” ሁለት፡- በኢትዮጵያ ኮሜዲ ላይ “ጉድ” የሚያሰኝ አረም መብቀሉን ያሳዩን እነ አሌክስ፡፡ ያቺ ምሽት ታዳሚው እነዚህን እየቅል የሆኑ ሁለት አይነት ኮሜዲያን እያየና እየሰማ “ጉድ” ሲል ያመሸባት ናት፡፡ የአገራችን ኮሜዲያን ብቃት አነጋጋሪ በሆነበትና አንዳንዶቻችን የኋላ ማርሽ አስገብተን በእነ ተስፋዬ ካሳ ተስፋዬ ትዝታ የሳቅ አምሮታችንን ለማስታገስ በምንሞክርበት በዚህ ጊዜ፣ የአዳዲስ ኮሜዲያንን መምጣት ስንሰማ በጉጉት መጠበቃችን አይቀርም፡፡

መጥተው ከፊታችን ሲቆሙ ግን እነ አሌክስ ሆነው አገኘናቸው፡፡ እነ አሌክስ “ማዋረድ” የሚሉት የጨዋታ ስልት ይዘው ነው ወደ ሜዳ የገቡት፡፡ በተሰማሩበት የሙያ መስክ ዕውቅና ያተረፉ ግለሰቦችን ከፍ ብለው ከተቀመጡበት ስፍራ ጐትቶ ማውረድና በእነሱ ከፍታ ላይ መቀመጥ “ማዋረድ”  የሚሉት አዲስ የጨዋታ ስልት ግብ ነው፡፡ አሌክስም በዚህ የጨዋታ ስልት ተጠቅሞ ነጥብ ለመያዝ ደፋ ቀና ሲል ያመሸ አዲሱ “የኮሜዲያችን ጉድ” ነው፡፡ እርግጥ በታዋቂ ግለሰቦች ላይ መቀለድ በእሱ አልተጀመረም፡፡ በውጭ አገራትም ቢሆን በአገር መሪዎች ላይ ሳይቀር ይቀለዳል፡፡ ፖለቲከኛውን ከፖለቲካው፣ ነጋዴውን ከንግዱ፣ ሳይንቲስቱን ከሳይንሱ ግለሰቡን ከሙያው ጋር አያይዘው በመቀለድ የተሳቀላቸው ብዙ ኮሜዲያን አሉ፡፡ እደግመዋለሁ … በታዋቂ ግለሰቦች ላይ መቀለድ በእሱ (በአሌክስ) አልተጀመረም፡፡ በእሱ የተጀመረው የታዋቂ ግለሰቦችን ድምፅ በማስመሰል ህዝብን የሚያስቀይም ፀያፍ ነገር በህዝብ ፊት ማነብነብ ነው፡፡ በህዝቡ ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘትና እውቅናን ለማትረፍ “አቋራጭ” ያለው መንገድ በታዋቂ ግለሰቦች አፍ የሃይማኖት ተቋማትን መወረፍ ይመስላል፡፡ አሌክስ አንድን ታዋቂ የአገራችንየሬዲዮ የእግር ኳስ ኮሜንታተር ወደ እምነት አባትነት ወይም ሰባኪነት ወስዶ፣ ሰባኪውን ደግሞ ወደ ኮሜንታተርነት መልሶ ርካሽ ሳቅ ፍለጋ ሲዘባርቅ አመሸ፡፡ እነ ክበበው ገዳ በወጡበት፤ እነ ተስፋዬ ካሳ በቆሙበት በታላቁ የብሔራዊ ቲያትር መድረክ ላይ ከታላቁ መፅሐፍ አንቀፅና ቁጥር እየጠቀሰ የሚያሽሟጥጥ አዲስ “ኮሜዲያን” ታየ! ይሄን ያየው ተመልካች የአሌክስን “ቀልድ” ለማስጨረስ የሚሆን ትዕግስት አልነበረውም፡፡ ቅዱስ መላዕክት እንደ እግር ኳስ ክለብ ተጫዋች ሲቆጠሩ፣ የሰሩት ገድል በእግር ኳስኛ ሲተረክ፣ ወንጌል በፕሪሚየር ሊግ ቋንቋ ሲነገር፣ ኮሜንታተር ከሰባኪ ሲዘነቅ … ይሄ ሁሉ ሲሆን ዝም ብሎ በማየትና በመስማት አሌክስ የጀመረውን ቅሌት ማስጨረስ አልቻለም … ተመልካቹ! ተመልካቹ በአሌክስ ላይ አጨበጨበበት! እሱ ግን ጭብጨባውን ከሙገሳ ቆጥሮ ቅሌቱን ጨርሶ ወረደ፡፡ ይሄኛው የኮሜዲያኖች ጉድ ሲወርድ ሌላኛው ጉድ ወጣ፡፡ ተመልካቹ የሁለቱንም አይነት ኮሜዲያን ቀልዶች እየሰማና እየተመለከተ ሁለት አይነት ጭብጨባ ሲያሰማ የታየበት፡፡ታዳሚው ለእነ ልጅ ያሬድ ሲያጨበጭብላቸው፣ በእነ አሌክስ ሲያጨበጭብባቸው ያመሸባት ምሽት! እርግጥም በዚያች ምሽት በቀልዶቻቸው ተመልካቹን “እንድ ጉድ ያሳቁ” እነ ልጅ ያሬድን የመሳሰሉ የሚገርም ችሎታ ይዘው የመጡ ተወዳጅ ኮሜዲያን ታይተዋል፡፡

በተቃራኒው ደግሞ በሃይማኖት ላይ ቀልደው፣ ወሲብ ተኮር አይነኬ ተረብ ተናግረው ተመልካቹን ያሳቀቁ፣ “እናንተ ጉዶች በቃችሁ” ተብለው በተቃውሞ የተጨበጨበባቸው የኮሜዲያችን ጉዶችም ታይተዋል፡፡ ልጅ ያሬድ የራሱን አዲስ ስታይል ይዞ የመጣ፣ በብዙዎች ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነትን ያገኘና አድናቆት የተቸረው ወጣት ኮሜዲያን ስለመሆኑ፣ ደምሴ (ዋኖሶች) እና ተመስገንም በርቱ የሚያሰኙ ቀልዶቻቸውን ስለማቅረባቸው ሳይናገሩ፣ በአሳቃቂ ቀልዶች ተመልካቹን ወዳሸማቀቁት ወደ እነ አሌክስ መንደርደር፣ የአድናቆት ንፉግነት አልያም የትችት ሱስ የተጠናወተው ብዕር ባህርይ ነው፡፡ እደግ ልጅ ያሬድ! … በርታ ተመስገን! … ብራቮ ደምሴ! …

አሁን ጊዜው የእነዚያኞቹ ነው! የእነ አሌክስ …

እነሱ ግለሰቦችን በማንቋሸሽና በሃይማኖት ላይ በማላገጥ ሳቅ ለመሸመት የሚባዝኑ የኮሜዲያችን ጉዶች ናቸው፡፡

እነሱ የሃይማኖትን ስም ያለ አግባብ በማንሳትና በመሳለቅ፣ ከቅዱስ መፅሃፍ ገፆች በእርኩስ ምላሳቸው እየገለጡ  አንቀፅ ቁጥር ጠቅሰው በማሾፍ፣ የመላዕክትን ስም በከንቱ በማንሳት፣ ገድላቸውን ዋጋ በማሳጣትና በማሳነስ የራሳቸውን ዋጋ ከፍ ለማድረግ ሲውተረተሩ ያየናቸው “ዘላፊዎች” ናቸው፡፡ በጋዜጠኝነትና በስፖርት ዘርፎች ታዋቂነትን ያተረፉና ተወዳጅ የሆኑ ግለሰቦችን በሃይማኖት ላይ ሲሳለቁ፣ በመላዕክት ላይ ሲያላግጡ ነው ያሰማኝ የኮሜዲያችን ጉድ አሌክስ! በተለያዩ የኮሜዲ ስራዎቹ በመጠኑም ቢሆን የሚታወቀው ወንደሰን (ዶክሌ)ም ከዚያው መጠኑ ወርዶ ዝቅ ብሎ ነበር የመጣው፡፡

በእነ ልጅ ያሬድ ከፍታ ቀና ብለን የጠበቅነውን ዶክሌን በሚገርም ማሽቆልቆል ከእነ አሌክስ ዝቅታ በታች ወርዶ “ደርቲ ጆክ” ውስጥ ሲላቁጥ አገኘነው፡፡ እነዚህ የኮሜዲያችን ጉዶች በእነ ልጅ ያሬድ ቀልድ ጥርሱ በሳቅ ሲንከተከት የታየውን ተመልካች

ደሙ በንዴት ሲንተከተክ አሳይተውናል፡፡ “የአቶ በቀለ እንትን …” ብሎ የጀመረው “ዶክሌ” “ደርቲ ጆኩን” እስኪጨርስ የፈጃቸው ረጅም የመሸማቀቅ ጊዜያት ነበሩ፡፡ በእምነቱ ላይ ሲቀለድበት፣ በሚያከብራቸው ቅዱሳን መላዕክት ላይ አጉል ተረብ ሲዘንብበት የሰማው

የዚያች ምሽት የብሔራዊ ቲያትር አዳራሽ ታዳሚ፣ ለእነ ልጅ ያሬድ ‘ብራቮ’ ብሎ በአድናቆት ባጨበጨበባቸው እጆቹ፣ እነ አሌክስም ‘ውረድ’ ብሎ በንዴት አጨብጭቧል፡፡ በቅዱሳን መላዕክት ላይ ማውረድ የጀመሩትን የፌዝ መአት እየሰማ ታግሶ ማለፍ ያልቻለው ታዳሚ በእነ አሌክስ ላይ የተቃውሞ ጭብጨባውን አሰምቷል፡፡ በዕለቱ ተመልካቹ አይቶና ሰምቶ ያጣጣማቸው ብዙ ተወዳጅ የጥበብ መሰናዶዎች በቀረበበት በዚህ ማዕድ ላይ ተቀላቅለው የገቡና ተመልካቹን ያቅለሸለሹት እነዚህ “ነውሮች” ተመልካቹን ብቻ ሳይሆን የ”ኢትዮ ውድ”ን ደጋሾች ጭምር ነበር ያሳቀቁት፡፡ በወቅቱ የ”ዶክሌ”ን “ደርቲ ጆክ” ስትሰማ ፊቷ ላይ ከፍተኛ የሆነ የድንጋጤና የሃፍረት ስሜት የታየባት፣ በሃፍረት ተሸማቃ ስታቀረቅር የተስተዋለችው ቅድስት ባየልኝ ለዚህ ምስክር ትሆናለች፡፡ ይህ የበከተ ቀልድ ድግሱን ለማሳመር ታስቦ ሆን ተብሎ በ”ኢትዮውድ” ጣት ተቆንጥሮ  ማዕዱ ላይ የተጨመረ “ማጣፈጫ” አይመስለኝም፡፡ በአግባቡ ቀልዶ የጠበቀውን ያህል ሳቅ ማትረፍ ያልቻለው “ዶክሌ” ምናልባት ቢያዋጣኝ ብሎ ድንገት የደነጐረው በስውር የገባ “ኮንትሮባንድ ጆክ” መሆኑን ከጣፋጩ የጥበብ ድግስ ባለቤት ከቅድስት ባየልኝ የዚያች ቅፅበት የደነገጠ ፊት ላይ ማንበብ ይቻላል፡፡ ተስፋዬ ካሳ በህዝቡ ኑሮ ላይ ቀልዶ ህዝቡን ባሳቀበት በዚህ ታላቅ መድረክ ላይ “ዶክሌ” በህዝቡ ነውር፣ አሌክስ በታላቁ መፅሐፍ … ሁለቱም በማይቀለድበት ላይ ለመቀለድ ሞክረው ህዝቡን አሳቀቁ፡፡እርግጠኛ ነኝ …

እንዲህ ያለ የኮሜዲ ጉድ እዚህች አገር ላይ በቅሎ አያውቅም፡፡ በታላቁ የብሔራዊ ቲያትር መድረክ ላይ እንዲህ ያለ አይን ያወጣ ብልግና ታይቶ የሚያውቅም አይመስለኝም፡፡ ነውሩም ሆነ በሃይማኖት ላይ የሚሰነዘረው “ማላገጥ” የመንደር ኮሚኮች በተሰባሰቡበት ስፍራ ቢደረግ ኖሮ ብዙም ባልገረመ ነበር፡፡ ይሄ ሁሉ የሆነው በታላቁ የጥበብ ቤት በብሔራዊ ቲያትር መሆኑ ነው ችግሩ፡፡ የአሌክስም ሆነ የዶክሌ የጨዋታ ስልት ‘የምናብ አጠሮች’ ወይም “የምግባር አነሶች” ምርጫ ሆኖ ነው የሚታየኝ፡፡ በብሔረሰቦች ላይ መቀለድ በሰሚ ዘንድ የተሰለቸ፣ በህግ ዘንድ የሚያስጠይቅ ነገር የሆነበት ዘመን ሲመጣ፣ አሁን ደግሞ በብሔረሰቦች ቅላፄ ነውር የማውራት አዲስ የጨዋታ ስልት ብቅ አለ፡፡ አሌክስና ዶክሌ ይሄን ስልት ይዘው ወደ ጨዋታው ሜዳ ገቡ፡፡ ገቡና ለራሳቸው ነጥብ ጥለው፣ ለተመልካቹ ንዴት ጥለው ወጡ፡፡ ለልጅ ያሬድ ያጨበጨበለት ተመልካች በአሌክስ አጨበጨበበት! በዚያች ምሽት ሁለት ጭብጨባዎች ተሰሙ፡፡   ለቱን ጭብጨባዎች ለያይቶ ማድመጥ የ’ኢትዮውድ’ ቀጣይ ስራ ይመስለኛል፡፡ “ኢትዮ ውድ” ኮሜዲውን ለማነቃቃት አስቦ አዳዲስና ነባር ኮሜዲያን በማሰባሰብ እየሰራ ያለው በጐ ተግባር ያስመሰግነዋል፡፡ ኮሜዲያኑ ወደ ውጭ አገር ሄደው ስራዎቻቸውን እንዲያቀርቡ ለማስቻል እያደረገ ያለው በጐ ጅምርም ይበል የሚያሰኝ ነው፡፡ ይሄም ሆኖ ግን “ከአትላንቲክ ባሻገር”ን የመሰለ ትኩስና ጣፋጭ የጥበብ ጣዕም ባቃመሰን የብሔራዊ ቲያትር ማዕድ ላይ ተቀላቅለው የገቡ “እጅ እጅ” የሚሉ መሰል ጣዕም አልባ ነገሮችን ጉዳይ ሊያስብበት ይገባል፡፡ “ኢትዮ ውድ” ከአትላንቲክ ባሻገር ይዞት በመጣው ብስል የጥበብ ፍሬ ያገኘውን ምስጋናና አድናቆት ለመድገም ከፈለገ፣ አትላንቲክን አሻግሮ ይዞት ሊሄድ ያሰበውን የኮሜዲ ስንቅ በወጉ መቋጠር ይጠበቅበታል፡፡ ያቺን ምሽት በብሔራዊ ቲየትር መድረክ ባማረው የጥበብ ማሳ ውስጥ ድንገት በቅሎ ያየነውን የ“ኮሜዲያችን ጉድ” እንዳለ ሰባስቦ በአንድ ስልቻ የመጫን ስህተት እንዳይሰራ ያስብበት፡፡ በብሔራዊ ቲያትር ያየነው “የኮሜዲያችን ጉድ” አትላንቲክን ተሻግሮ ሄዶ ሲታይ “ብሔራዊ ቅሌት”

እንዳይሆን መስጋት አይከፋም፡፡

 

 

Read 3893 times Last modified on Saturday, 12 May 2012 09:36