Saturday, 18 August 2018 14:00

ፈቲያ መሐመድ በዓለም አቀፉ የወ/ሮ ቱሪዝም የቁንጅና ውድድር ትሳተፋለች

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

አግብተው የወለዱና ራሳቸውን የጠበቁ ሞዴሎች ብቻ ይሳተፉበታል

ሞዴል ፈቲያ መሐመድ ማሌዢያ ኩዋላላንፑር በሚካሄደው “ዓለም አቀፉ የወይዘሮ ቱሪዝም ንግሥት የቁንጅና ውድድር” (Mrs Tourism Queen Intenational Pageant) ላይ ኢትዮጵያን ወክላ እንደምትወዳደር ተገለፀ፡፡ ውድድሩ ከዚህ ቀደም አገራቸውን ወክለው በመወዳደር ማዕረግ ያላቸውና አግብተውና ወልደው ራሳቸውን በመጠበቅ፣ በጥሩ ሁኔታ ላይ የሚገኙ ወ/ሮ
ሞዴሎች ብቻ ይሳተፉበታል ተብሏል፡፡
በዓለም አቀፍ የቁንጅናና የፋሽን ውድድሮች እውቅና ያለው ዓለም አቀፉ” የወይዘሮ ቱሪዝም ንግሥት” ድርጅት እንዳስታወቀው፤ በኩዋላላንፑር የሚካሄደው “የወይዘሮ ቱሪዝም ንግስት የቁንጅና ውድድር” በሀገራት መካከል ወዳጅነትን ለማጠንከርናሰ ለባህል ልውውጥ ማደግ ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል፡፡
ተወዳዳሪዋ ሞዴል ፈቲያ መሐመድም በተሳትፎዋ ወቅት የኢትዮጵያን የቱሪዝም ልማትና የአገሯን በጎ ገፅታ ለመላው ዓለም ለማስተዋወቅ እድሉን ታገኛለች ተብሏል፡፡ በውድድሩ አሸናፊ የምትሆነው ወይዘሮ የምትመረጠው ባላት ተፈጥሯዊ ውበት ብቻ ሳይሆን በምታሳየው ልዩ ችሎታና የሀገሯን ባህልና ቱሪዝም በምታስተዋውቅበት ጊዜ ባላት እውቀትና በራስ መተማመን ጭምር እንደሆነም ታውቋል፡፡ 50 የዓለም ሀገራት ወይዘሮዎች በሚሳተፉበት በዚህ ውድድር፤ የኢትዮጵያ፣ አሜሪካ፣ ጃፓን፣ አውስትራሊያ፣ ብራዚል፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ፈረንሳይ፣ ህንድ፣ ካዛኪስታን፣ ኬንያ፣ ኒውዝላንድ፣ ፊሊፒንስ፣ ሩሲያ፣ ስዊድን፣ ታይላንድ፣ ኔዘርላንድ፣ ፖርቹጋል ቬትናምና የሌሎች ሀገራት ወ/ሮ ሞዴሎች ይሳተፉበታል ተብሏል፡፡
በዚህ ትልቅ ውድድር አሸናፊ የምትሆነው ወይዘሮ ንግሥት፤ ከዓለም አቀፉ የቱሪዝም ድርጅትና ከትልልቅ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ጋር በመሆን የአገሯን ባህል ቱሪዝምና አጠቃላይ ተፈጥሮ ለዓለም ለማስተዋወቅ እድል እንደምታገኝ ታውቋል፡፡ ሞዴል ፈቲያ መሐመድ ከዚህ ቀደም እ.ኤ.አ በ2005 ዓ.ም በተካሄደው የቁንጅና ውድድር “የወ/ሪት ቱሪዝም” አሸናፊ ስትሆን
በዚሁ ዓመት የምርጥ አፍሪካ ንግሥት” ሆናለች፡፡ እ.ኤ.አ በ2006 ጃፓን በተካሄደው ውድድር “የወ/ሪት በጎ ፈቃደኛ ንግሥት”
ማዕረግ አሸናፊም ነበረች፡፡

Read 2522 times