Saturday, 18 August 2018 10:07

ቢሻን ጋሪ የምርቱን ይዘት ማሻሻሉን አስታወቀ

Written by  መንግስቱ አበበ
Rate this item
(0 votes)

 በጀርሞች የተበከለና ድፍርስ ውሃን አጣርቶ፣ ንፁህ አድርጎ በማቅረብ የሚታወቀው ቢሻን ጋሪ፤ የምርት ማጣሪያውን ይዘት ማሻሻሉን አስታወቀ፡፡
ቢሻንጋሪ ፒዩሪፊኬሽን ኢንዱስትሪ ኃ.የተ.የግ.ማ ባለፈው ማክሰኞ በካፒታል ሆቴል ባካሄደው የግማሽ ቀን ወርክሾፕ፤ ምርቱን ከድርጅቱ በብዛት ለሚገዙና አብረውት ለሚሰሩ አካላት አስተዋውቋል፡፡
ድርጅቱ ቀደም ሲል ለነባሩ ምርት ማጣሪያ (ክሎሪን) የሚጠቀምባቸው ኬሚካሎች አሉሚኒየም ሰልፌትና ካልሲየም ሃይፓክስሬት ሲሆን ለአዲሱ የማጣሪያ ምርት የምግብ ይዘት ያለውን ሦስተኛ ኬሚካል ፌሪክ ሰልፌት (የብረት ማዕድን) መጨመሩን ገልጿል፡፡
ቀደም ሲል 20 ሊትር በጀርሞች የተበከለና የደፈረሰ ውሃን ለማጣራት 2.5 ወይም 2.6 ግራም አሉሙኒየም ሰልፌትና ካልሲየም ሃይፖክስሬት (ክሎሪን) ይጠቀሙ እንደነበር የጠቀሱት የንግድና ገበያ ልማት ማናጀር አቶ ቢያዝን ላቀ፤ በአዲሱ ምርት ለ20 ሊትር ከፍተኛ የማከምና የማጣራት አቅም ያለውን ነገር ግን የኬሚካል መጠኑ ያነሰ (2.1 ወይም 2.2 ግራም) ኬሚካል እንደሚጠቀሙ አስረድተዋል፡፡
በተመሳሳይ ሙያ ከተሰማሩ ሌሎች ድርጅቶች ቢሻንጋሪን ለየት የሚያደርገው ለምርቱ የሚጠቀመው ጥሬ ዕቃ ከ50 በመቶ በላይ ከአገር ውስጥ የሚገኝ መሆኑ ነው ያሉት አቶ ቢያዝን፤ ምርቱ ውስጥ የሚጨመረው ኬሚካል በጤና ላይ ጉዳት የሚያስከትል እንደሆነ ገልፀዋል፡፡
“ተጠቃሚው የቢሻን ጋሪ ውሃ ማጣሪያ ኬሚካል ይሸታል፣ ይጎመዝዛል ይላል” በማለት ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ ማናጀሩ ሲመልሱ፣ ችግሩ የሚፈጠረው ከአጠቃቀም ጉድለት እንደሆነ ጠቅሰው፣ የተጣራው ውሃ መጠጣት ያለበት ከ30 ደቂቃ በኋላ ነው፤ ምክንያቱም ውሃው እንዲጎመዝዝ የሚያደርገው ክሎሪን ከ30 ደቂቃ በኋላ ከውሃው ውስጥ ተንኖ ስለሚወጣ፣ የሚጠጣው ውሃ ምንም እክል አይኖረውም ብለዋል፡፡
ከአሥር ዓመት በፊት በ2000 ዓ.ም ከ8-10 ሚሊዮን ብር በሚደርስ ካፒታል የተመሰረተው ቢሻን ጋሪ፤ ባለፈው ሁለት ዓመት ሽያጩ ከ70-100 ሚሊዮን ብር እንደደረሰ የጠቀሱት አቶ ቢያዝን ላቀ፣ ምርታቸውን ወደ ውጭ አገር የመላክ ዕቅድ ቢኖራቸውም በአሁኑ ጊዜ እየላኩ እንዳልሆነና ቀደም ሲል ወደ ሱማሌላንድ ለመላክ የተጀመረው ሙከራ መቋረጡን፣ ነገር ግን አሁን የምርታቸው ናሙና ወደ ደቡብ ሱዳንና ወደ ደቡብ አፍሪካ ተልኮ እየተሞከረ መሆኑን አስረድተዋል፡፡   

Read 2049 times