Print this page
Saturday, 18 August 2018 10:08

ለመጀመሪያ ጊዜ በካፒታል ማርኬት ላይ ስልጠና ተሰጠ

Written by  መንግስቱ አበበ
Rate this item
(0 votes)

 አዲስ አበባ የሚገኘው ዌስተርን ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ከሊንከን ዩኒቨርሲቲ ካሊፎርኒያ ጋር በመተባበር በካፒታል ገበያ ላይ ያተኮረ ትምህርታዊ ስልጠና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በእሸቱ ጮሌ (ዶ/ር) የስብሰባ አዳራሽ ሰሞኑን ተካሄደ፡፡
ለአምስት ቀናት የተሰጠውን ሥልጠና የከፈቱት የዌስተርን ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ፕሬዚዳንት አቶ አቤቱ መላኩ ለመጀመሪያ ጊዜ የተሰጠው በዓይነቱ ልዩ የሆነ ኮርስ ሀገራችን የደረሰችበትን የኢኮኖሚ ዕድገት በማገናዘብ በቀጣይም የኢኮኖሚ ሥርዓቱን ዕድገት ለማሳለጥ ያግዛል ብለዋል፡፡
ከሊንከን ዩኒቨርሲቲ ካሊፎርኒያ የመጡት የካፒታል ማርኬት ከፍተኛ ባለሙያ ዶ/ር ሰርጉይ ኤቲያን በበኩላቸው የካፒታል ማርኬት ባደጉትና በማደግ ላይ በሚገኙት ሀገራት በተግባር በማዋል የሀገሮቻቸውን የኢኮኖሚ ስርዓት በማሳለጥ ጉልህ ሚና የሚጫወት በመሆኑ የስልጠናው ተሳታፊዎች በቆይታቸው በቂ ዕውቀት በማግኘት በቀጣይ በተግባር ለማዋል እንደሚያግዛቸው አስረድተዋል፡፡
ሥልጠናው በዋናነት ያተኮረው በካፒታል ገበያ፣ የንግድ ልውውጥና ምንነት፣ በካፒታል ገበያ ዝውውርና ትንታኔ እንዲሁም ሊኖሩ ስለሚገባቸው ጥብቅ የንግድ ህጎችና ደንቦች በሚሉ አበይት ርዕሶች ላይ ግንዛቤ ማስጨበጡ ታውቋል፡፡
በዚሁ ትምህርታዊ ስልጠና ላይ ከካፒታል ገበያ ጋር የቅርብ ግንኙነት ያላቸው የፋይናንስ ተቋማት፣ ባንኮች፣ ኢንሹራንሶች እንዲሁም ከተለያዩ የግል ድርጅቶች የተወከሉ ባለሙያዎች የተሳተፉ ሲሆን ስልጠናው በካፒታል ገበያና ተዛማጅ ርዕሶች በቂ ዕውቀትና ግንዛቤ እንዳስጨበጣቸው ገልጸዋል፡፡
አዲስ አበባ የሚገኘው የዌስተርን ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ አሜሪካን ሀገር ካሊፎርኒያ ከሚገኘው ሊንከን ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር የሚሰራ ሲሆን ሀገሪቱ ያለባትን የመምህራን፣ የባለሙያ እጥረትና ጥራት ያለው ትምህርት ችግር በማገናዘብ በቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን (BA) በማስተርስ MBA ዲግሪ ፕሮግራም ቁጥራቸው ጥቂት ቢሆንም በጥራት ላይ የተመሰረተ ትምህርት በማስተማር ላይ ሲሆን አሁንም በካፒታል ማርኬት የሰጠው ስልጠና የዚሁ ዓላማ አካል መሆኑንና በቀጣይም ለኢኮኖሚው ዕድገት አሳላጭ የሚያግዙ የተለያዩ ትምህርታዊ ስልጠናዎች ለማዘጋጀት እየሰራ መሆኑን የዩኒቨርሲቲ ኮሌጁ ፕሬዚዳንት አቶ አቤቱ መላኩ ገልፀዋል፡፡

Read 2098 times