Wednesday, 22 August 2018 00:00

የእምነት ዘረ-መል (GoD Gene)

Written by  ሌሊሣ ግርማ
Rate this item
(4 votes)

  (የፈጣሪ ማንነትና አስፈላጊነት)
                 
    በዚህ ሳምንቱ ፅሑፌም ባለፈው ካነሳሁት ጥያቄና አካባቢው አልወጣም፡፡ ጥያቄው የፈጣሪ ማንነትና አስፈላጊነት ላይ ያጠነጠነ ነው፡፡
ተዋነይ በቅኔው ለጥያቄው የራሱን መልስ ሰጥቷል። “ሙሴ ፈጣሪን ፈጠረ፡፡ ፈጣሪ ደግሞ በመቀጠል ሙሴን ፈጠረ” ብሏል፡፡ እኔ ደግሞ ወደ ጥበብ ስለማደላ … “የሰው ልጅ ያልፈጠረውን ነገር መረዳት አይችልም” ከዚህ ቀደም ያልኩትን አሁንም አፅንኦት ሰጥቼ እደግመዋለሁኝ፡፡ አንድ ነገር በሰው ፈጠራ አማካኝነት እስካልተገለፀ፣ መኖር እና አለመኖሩን ሊረዳ አይችልም። ስለዚህ ሙሴ የፈጣሪን ትዕዛዝ ለህዝቡ መግለፁ ራሱ የፈጠራ ባለቤት ያደርገዋል፡፡ ካልነበረ ነገር ወደ መሆን በገለፃው አመጣው ማለቴ እንዳልሆነ፣ እዚህ ጋ እንዲሰመርበት እፈልጋለሁኝ፡፡ በሰማይ ያለ ፈጣሪን ወደ ምድር አውርዶ ለመግለፅም ሚዲየም ያስፈልጋል፡፡
ፈጣሪ የፈጠረበት ሚዲየም በዚህ ረገድ ሙሴ ሆነ፡፡ ያለ “Motif” እና “Medium” ጥምረት ጥበብም ቢሆን አይከወንም፡፡ ፈጣሪ (GoD) ነባራዊውን ህዋም ሆነ ሰው በመፍጠሩ ነው ስለ ራሱ ምንነት መገለጫዎቹን ማስቀመጥ የቻለው ብዬ አስባለሁኝ፡፡ በፈጠረው ውስጥ ነው የተገለፀው። ሙሴም ደግሞ በተመሳሳይ መንገድ ፈጣሪውን በመግለፅ ብቻ ነው፣ ለራሱም ሆነ ለህዝቦቹ ስለ ፈጣሪው ማስረዳት የሚችለው። ለመረዳት መፍጠር ያስፈልጋል፡፡ ለማሰብ መግለጽ እንደሚያስፈልገው። ለማመን፤ ለአማኙ በሚገባ መንገድ ፈጣሪ በሀሳብና ቋንቋ ተቀናብሮ መገለፅ አለበት፡፡ ስለዚህ ሙሴም ፈጣሪን ፈጥሮታል። ፈጣሪም ሙሴን እንደዚያው። ቅደም ተከተሉ ብዙም የሚያጣላ አይመስለኝም። የተፈጠረ ነገር ሁሉ ለፈጣሪው አስፈላጊ ስለሆነ እውነትም ነው፡፡
አንድ ነገር ማስረገጥ ይቻላል፤ ይኸውም፤ ሀይማኖትና እምነት የሰው ልጆች ምንነት ላይ ወሳኝ ቦታ የሚይዝ ቋሚ ነገር መሆኑን ነው፡፡ ብዙ ሰዎች የሀይማኖትን አስፈላጊነት ለማስረገጥ ሲፈልጉ፤ “ያለ ሀይማኖት አለም በማያባራ ቀውስና ኢ-ፍትሃዊነት ምስቅልቅሏ ይወጣ ነበር” ይላሉ። ነገር ግን ሃይማኖት ሁሌም ከሰው ልጆች ጋር ቢኖርም ቀውስና ምስቅልቅል ግን ተወግዶ አያውቅም፡፡ ሃይማኖት ኖራቸውም አልኖራቸውም አንዳንድ ሰዎች ሞራል ያላቸው፣ ሌሎቹ ደግሞ የሌላቸው መሆናቸው በተደጋጋሚ ተስተውሏል። ማህበረሰብም በጦርነትና ሌላ እኩይ መናጆ ዘወትር የሚታመስበትን ምክኒያት አጥቶ አያውቅም፡፡
የሰው የሞራል መነሻ ከሃይማኖቱ የመጣ እንዳልሆነ እኔ ባለፈው ሳምንት ፅሁፌ ላይም ለመጠቆም ሞክሬአለሁኝ። እምነት ከተፈጥሮ ጋር የተያያዘ በፈጣሪ የማመን ፍላጎት አለውም ብዬ ደምድሜአለሁኝ፡፡ ከእኔ ድምዳሜ ጋር የተያያዘ አመለካከት ያላቸው አሳቢዎች፣ ተመሳሳይ መላምት ጠቁመው ታዘብኩና ተደሰትኩኝ፡፡
መላምቱ፤ የሰው ልጅ አምላኩን እንዲያምን ወይም ወደ እምነት እንዲሳብ የሚያደርግ ዘረ-መል በውስጡ ይገኛል … የሚል ነው፡፡ መላምቱ ገና በተጨባጭ የተረጋገጠ አይደለም። ባይረጋገጥም ለእኔ ሀሳቡ ስቦኛል፡፡ በእርግጥም አስተውለን ከተመለከትነው … ሃይማኖትን ፈጥሮ የማምለኩ ስበት ከውጭ በባህል መልክ ተምሮ ከሚወርሰው ይልቅ ከተፈጥሮው ጋር ከተሰራ ስበት ፍላጎቱ የሚመጣ ይመስለኛል።
ፈላስፋው ቮልቴር፤ “እግዚአብሔር በህልውና ባይኖር ኖሮ፣ ልንፈጥረው እንገደድ ነበር” ሲልም … ከተፈጥሮአችን ጋር በጣም የተሳሰረ የእምነት ፍላጎት፣ መኖሩን ነው በድጋሚ የሚያስታውሰኝ፡፡
ፓል ብሉም የሚባል የስነ ልቦና ተመራማሪ ከአስር ዓመት በፊት ገደማ ባሳተመው ጥናት፤ የሰው ልጆች በዝግመተ ለውጥ ሂደት ሁለት ዓይነት ፕሮግራሞች፣ በአንጎሉ የስነ ልቦና መዋቅር ውስጥ እንዳዳበረ ይገልፃል፡፡ በስሜት ህዋሳቶቹ የሚያገኛቸውን መረጃዎች የሚተነትንበት መንገድ የሚወስኑ የስነ ልቦና ፕሮግራሞች ሊባሉ ይችላሉ።
አንደኛው ፕሮግራም፡- በአካል የሚገኝ እቃና ነገሮችን (Physical objects) ለመረዳት ይገለገልበታል።
ሁለተኛው ደግሞ፡- በማህበረሰብ ውስጥ የአንጎሉ ባለቤት ከሌሎች መሰለቹ ጋር የሚያደርገውን መስተጋብር ለመረዳት የሚጠቀመው ነው፡፡
ፓል ብሉም በጥናቱ ከሰጠው ጥቆማ፤ ከእነዚህ ሁለት ፕሮግራሞች ውጭ ሶስተኛ ፕሮግራም በሂደት በሰው ልጅ ስነ ልቦና ውስጥ እንዳጎለበተ ይናገራል። በአካል (objects) ሊገለፅ የማይችል፣ እንደዚሁም በማህበራዊ ግንኙነትና ሰውኛ ማንነት (Personality) የማይገለፅ ስነልቦና፡፡ ተጨባጭነቱ ለአንጎሉ ባለቤት የሆነ “እምነት” የሚባል የስነ ልቦና አይነት አዳብሯል ይለናል፡፡ ወይንም ለማለት ይሞክራል፡፡
ስለዚህም፤ ከህይወት በላይ እና ውጭ የሆነ፣ ከሞት ወዲያ የሚሻገር … በአካልና በተጨባጭ እውነታ የማይገለጽ ህይወት እንደሚቀጥል ያምናል፡፡ በተጨባጭ ከሚኖርበት ዓለም ውጭ የተቀረፀ ንድፍና የንድፉ ፈጣሪ እንደሚገኝ … (በተጨባጭ ከሚገኝበት ህልውና የበለጠ) ያምናል፡፡ የህይወቱን ትርጉምም ለተሻጋሪው የእምነት አለም ጥላና እንደ መለማመጃ (Virtual) አድርጎ ይቆጥረዋል፡፡ የመቁጠርን አቅም ይኼ ሦስተኛው የስነ ልቦና አማራጭ ይሰጠዋል .. ባይ ነው- ሳይኮሎጂስቱ፡፡
ግን ይኼ አይነት ዝግመተ ለውጥ በሰው አንጎል ተፈጥሮ ውስጥ (በአካል ደረጃ) ለመከሰት የወሰደው ጊዜ እጅግ አጭር ነው፣ በማለት በሳይኮሎጂስቱ ሀሳብ ሳይንቲስቶቹ አይስማሙም። በእርግጥም የ “GoD Gene” የሚባል ነገር ካልተገኘ በስተቀር በሰው ልጅ የአካል ተፈጥሮ ላይ የእምነትን መፈለጊያ አንቴና ከዋሻ ዘመን ወዲህ አልተቀጠለለትም፡፡
ዛፍና አለት ሲያመልክ የነበረ የሰው ንቃተ ህሊና ድንገት በአካልም ሆነ በምድራዊ ሰውኛ መለኪያ የማይገለፅ መንፈሳዊ አምላክ ለመፍጠርና በመንፈሳዊ አለም ለማመን የበቃው … አካላዊ ዝግመተ ለውጥ ሳይሆን በማህበረሰባዊ ዝግመተ ለውጥ ምክንያት ነው፡፡ አካል ለመለወጥ ብዙ ሚሊዮን ዓመት እንደሚወስድበት አይደለም የባህል ለውጥ፡፡ የማሰቢያው አንጎል ቅርፅና ይዘት ብዙ ሳይለወጥ ሀሳብና የሀሳብ መገለጫ የሆነው ባህል በተለይም ሃይማኖት ይለወጣል፡፡ የእምነት አስተሳሰብ የተለወጠው ወይንም እምነትና ሃይማኖት የጠነከረው ሰው እርስ በራሱ ያለው ግንኙነት በመጠንከሩ ምክኒያት ነው … የሚለውን የዳርዊናዊ መላምት እዚህ ጋ መዘንጋት የለብንም፡፡
ከዚሁ በመነሳት የራስን መላምት ለማድረግ ልድፈር፡፡ ድፍረቴን በጥያቄ መልክ ባቀርብ ትህትናን ይላበሳል፤ ስለዚህ በጥያቄ ልድፈር፡፡
ፈጣሪ (GoD) ብዙ ሃይማኖቶች ውስጥ ቋሚና የማይለወጥ መሰረታዊ ነጥብ ነው፡፡ ግን ሰውንና ሥራ ፈጣሪ የሚያስበውን ስንመለከት፣ ዘወትር በለውጥ ውስጥ ሆኖ ነው የምናገኘው፡፡ ለውጡን “ኡደት” ብለን መነሻና መድረሻው የሚደጋገምበት ነጥብ ብንሰጠው እንኳን ለውጥ መኖሩን አንክድም። የሚለወጥ ሰው፣ የማይለወጥ ፈጣሪን እንዴት ይገነዘበዋል? ምናልባት ብዙ ሃይማኖቶች ስለ ፈጣሪያቸው የሚያስቡት ቢመሳሰልም በመሀላቸው ያለው ልዩነት ግን በስነ ልቦናና የሀሳብ ዝግመተ ለውጥ ባህሎቻቸው ከቀሰሙት ተሞክሮ አንጻር ልክ ሊሆን ይችላል ወይ?
የባህሉ ዓይነትና የአስተሳሰብ ዝግመተ ለውጡ ይለያይ እንደሆነ እንጂ የፈጣሪ (GoD) ሀሳብ ያልገዘፈበት የሰው ልጅ የሀሳብ ዘመን የለም። አርስጣጣሊስ እንኳን ወደ ምድርና ተጨባጩ እውነታ አድልቶ የሰውን ምንነት ለመግለፅ ሲሞክር “ዘር ከልጓም ይስባል” እንዲሉ ያቺ በሳይንቲስቶች ተፈልጋ፣ በተጨባጭ ያልገተኘች የ “GoD Gene” እሱንም ታዳልጠዋለች፡፡
አሪስጣጣሊስ በሞራል (ሀሊዮው ውስጥ (Nicomachean ethics) የሰው ልጆች ሙሉ የሆነ የእርካታ ህይወት እንዲኖሩ ሦስት አማራጮችን ይጠቁማል፡፡
አንደኛው፡- የስጋ እርካታን በመፈለግ የሚኖር ህይወት ነው ይለናል፡፡
ሁለተኛው፡- የፖለቲካ ህይወትና እንቅስቃሴ ላይ መሰማራት ነው ይላል፡፡
ሦስተኛው፡- ግን ከሁለቱ የተሻለ ነው ይለናል። … ሦስተኛው በማሰብና ማሰላሰል (Life of contemplation) ህይወትን ማሳለፍ በሁሉም ይሻላል። የሚሻለው ደግሞ የአማልክቶቹን ህይወት ወደ መምሰል ስለሚቀርብ ነው … ይላል፡፡ እሱም ምድር ሆኖ ፈጣሪን ለመፍጠር እየጣረ ነው። የሚፈጥረው ደግሞ በግሪክ ባህልና አስተሳሰብ ቅርፅ ነው፡፡ ይዘቱ ለሁሉም የሰው ልጆች ተመሳሳይ ነው፡፡ ይዘቱ ፈጣሪ በሰው ልጆች የምንነት ግንዛቤ ላይ ትልቅ ቦታ የያዘ ሀሳብ መሆኑ ነው፡፡
ሀሳቡ ደግሞ በተፈጥሮ ደረጃ ውስጣቸው የተቀበረና ከማህፀን ሲወጡ በተወለዱበት ማህበረሰብ ውስጥ በይዘት ደረጃ የማይሰበኩት የተፈጥሮ ሀሳብ ነው። ከተወለዱ በኋላ ከተወለዱበት ማህበረሰብ ውስጥ በተፈጥሯቸው ላለው ስበት ቅርፅ ይፈልጉለታል። ቅርፁ በአንዱ የሃይማኖት ቅርፅ እንዲሰባሰቡ ያደርጋቸዋል፡፡
በሳይንስ ባይደገፍ እንኳን የማመን ተፈጥሮን “GoD Gene” ብዬ ለመጥራት የምደፍረው በዚህ ምክንያት ነው። “ኢቴይስት ነን” የሚሉት ራሳቸው ስለ ፈጣሪ አለመኖር በመነታረክና ፈጣሪን በራሳቸው ባህል አንፃር የገለፁትን ሁሉ በማጣጣል ቢያጠፉም … ከይዘቱ (GoD) መራቅ ምን ያህል እንደማይችሉ ጠቋሚ ነው፡፡ እነሱም ጂኑ በውስጣቸው አለ፡፡ እንዳይሰራ ቢፈልጉም ይሰራል፡፡ የሚሰራው ግን ከመደበኛው በተቀለበሰ አኳኋን ነው፡፡ “የለም” በማለት ነው፣ የሀሳቡን መኖር አፅንኦት ለመስጠት የሚሞክሩት፡፡ እንደዚያ ይመስለኛል፡፡ ከመሰለኝ ደግሞ …!

Read 2978 times