Sunday, 19 August 2018 00:00

“የተሰረቁ” ፓርቲዎች

Written by  አያሌው አስረስ
Rate this item
(1 Vote)

 ርዕሱን በማየት “ፓርቲ ደግሞ ይሰረቃል? እንዴት ነው የሚሰረቀው?” የሚል ጥያቄ ወደ አዕምሮ ሊመጣ እንደሚችል  አምናለሁ፡፡ ልቤን ሰረቀው ስንል፡- ወደድሁት፤ አይኔን ሰረቀው ስንል፡- እየው እየው አለኝ፤ ሀሳቤን ሰረቀኝ ስንል፡- እኔ ያነሳሁትን አጀንዳ የራሱ አድርጎ አቀረበው፤ እምነቱን ሰረቀኝ ስንል፡- ከዳኝ ሸፈጠኝ ማለታችን ነው፡፡ ፓርቲ በእምነት፣ በአስተሳሰብና በአላማ ላይ የተመሰረተ ድርጅት በመሆኑ፣ የሚፈፀመው ስርቆትም የሚተገበረው በዚሁ ላይ ነው፡፡ እኔ የተሰረቀ ፓርቲ ስል፣ በመደበኛ የፖለቲካ ቋንቋ አንጃ ማለቴ መሆኑ ይታወቅልኝ፡፡ አንጃ፣ ወገኛ ቃል ሆኖ ስለሚታየኝ አይጥመኝም፡፡
ከኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ በቅርቡ ያገኘሁት መረጃ፤ ሃያ ሁለት አገር አቀፍና አርባ የክልል፣ በድምሩ ስልሳ ሁለት ፓርቲዎች እንዳሉ ያመለክታል፡፡ ይህ ቁጥር ኢህአዴግን ከእነ አባሎቹና ከእነ አጋር ድርጅቶቹ (የክልል ፓርቲዎች) ይጨምራል፡፡ ከውጭ እየገቡ ያሉትን ግን አያካትትም፡፡
የኢዴፓ መስራቾች እነ አቶ ልደቱ አያሌው፤ የመላ አማራ ሕዝብ ድርጅት (መአሕድ) አባላት ነበሩ፡፡ በፕሬዚዳንቱ በፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ መታሰር ድርጅቱ መዳከሙን ያዩት እነ አቶ ልደቱ፤ ጠቅላላ ጉባኤ ተጠርቶ አመራሩ እንዲሟላ ጠየቁ፡፡ አጀንዳው ተጠልፎ ጉባኤው ሙሉ ለሙሉ የአመራር ለውጥ ቢያደርግ፣ የፕሮፌሰሩና ከእሳቸው ጋር የታሰሩት ሌሎች የድርጅቱ መሪዎች ጉዳይ ተራ እስር ይሆናል ብለው የሰጉት እነ ቀኛዝማች ነቅአጥበብ  በቀለ፣ ጥያቄውን ሳይቀበሉት ቀሩ፡፡ እነ አቶ ልደቱ ከድርጅቱ ተባረሩ፡፡ እራሳቸውን ከመአሕድ የሰረቁት እነ አቶ ልደቱ፣ የኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲን (ኢዴፓ) መሰረቱ፡፡
ኢዴፓ፤ ከኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ህብረት (ኢዲዩ) ጋር በመዋሃድ ራሱን አጠናከረ፡፡ ውህደቱ ያልተስማማቸው የራስ መንገሻ ሰዎች ተነጥለው ቀሩ። የገቡትም “ተዘነጋን” ብለው ጥቂት ቆይተው ወጡ። ኢዲዩ ቀጠለ፡፡ ኢዴፓም ሌባ ተነሳበት። እሱም ተሰረቀና የመላው ኢትዮጵያውያን ዲሞክራሲዊ ፓርቲ (መኢዴፓ) ተመሰረተ፡፡ መአሕድ የልጅ ልጅ ከማየቱ በላይ በአቶ ሽፈራው መኢብን ምሥረታ ቅድመ አያት ሆነ፡፡ ሰሞኑን ደግሞ ኢዴፓ ለሁለት ተከፍሎ፣ የእነ አቶ ልደቱ ወገን፣ ከፖለቲካ እንቅስቃሴ እራሱን ማራቁን እየተናገረ ነው፡፡
በ1984 በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ አለሁ አለሁ ከአሉት ብሔራዊ ዴሞክራሲዊ ህብረት (ብዴህ) አንዱ ነው፡፡ “መገንጠል የመሪዎች እንጂ የህዝብ ጥያቄ አይደለም” የሚለው መግለጫው፣ የሕዝብ ድጋፍ አስገኝቶለት ነበር፡፡ በፓርቲው መሪ በአቶ ፀጋየና በእነ አቶ ሙላቱ ጣሰው መካከል ውዝግብ ተፈጥሮ እያለ፣ አቶ ፀጋዬ በሌላ ጥፋት ከርቸሌ ገቡ፡፡ የድርጅቱን መሪነት እነ አቶ ሙላት ያዙት፡፡ ግር ብሎ የመጣው ደጋፊና አባል ብን ብሎ ጠፋ፡፡ በ1992 ምርጫ ቅስቀሳ ላይ ብዴህ ስም እንጂ ሰው እንዳልነበረው በግልጽ ታየ።
የመላው አማራ ሕዝብ ድርጅት እራሱን ወደ መላው ኢትዮጵያ ህዝብ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ለወጠ፡፡ ለውጡን ያልተቀበሉት ራሳቸውን መአሕድ አድርገው ቀሩ - ሁለተኛው ስርቆት፡፡ መኢአድ ለ1997 ምርጫ ከአንዳንድ ድርጅቶች ጋር ውህደት በማድረግ እነዚያን ከፖለቲካ መድረኩና ከድምፅ አባካኝነቱ መራቅ እንዳለበት በማመን መኢአድ እና ብዴህ ተዋሃዱ። እስከማውቀው ድረስ አንዳንድ የብዴህ ሰዎች የፓርቲ ድንኳን ሰባሪዎች ስለነበሩ ተቃውሞ አልነበረም፡፡
ከቅንጅቱ መስራች አንዱ መኢአድ ሆኖ ምርጫ 97 ተካሄደ፡፡ ሕዝብ ድምጼ ተሰረቀ እያለ በሚጮህበት ሰዓት መኢአድ መታመስ ያዘ፡፡ እነ አቶ ሙላቱ ጣሰው ከመኢአድ መነጠላቸውን አወጁ፡፡ ወደ ብዴህ አልተመለሱም፤ እሱ ድሮ ሞቷል፡፡ ይልቅስ ብርሃን ለፍትህና ለዲሞክራሲ የሚባል ሌላ የተሰረቀ ፓርቲ መሰረቱ፡፡
ሕዝቡ፤ “ተባበሩ ወይ ተሰባበሩ” በማለት በፓርቲዎች ላይ ጫና በማድረጉ፣ አራቱ ፓርቲዎች ማለትም፡- መኢአድ፣ ኢዴፓ፣ ቀስተ ደመና እና ኢዲሊ ቅንጅትን መሰረቱ፡፡
ቅንጅቱ ከፍተኛ የህዝብ ድጋፍ አገኘ፡፡ የውህደት ጥያቄ ተነሳ፡፡ ሞቅ ባለ ስሜት ሁሉም ተቀበሉት። የውህዱ ፓርቲ ዋና ዋና ስልጣኖች ለመኢአድ፣ ለኢዲሊ እና ለቀስተደመና ተሰጡ፡፡ ኢደፓ የኢንጅነር ኃይሉ ሻወልን ሊቀመንበርነት ቢቀበለውም፣ የወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳን ምክትል ሊቀ መንበርነትና የአቶ ኢዩኤል ዮሐንስን ጸሐፊነት መሸከም አልቻለም። ለአቶ ልደቱ የተሰጠው ሁለተኛ ምክትል ሊቀ መንበርነት የሚያበሳጭ ነበር፡፡ “ውህደቱ ከመሰረታዊ የፓርቲ አካላት መጀመር አለበት” የሚል ምክንያት ሰጥቶ ኢዴፓ አፈገፈገ፡፡ የፓርቲው ሊቀ መንበርና ምክትል ሊቀ መንበሩ ዶክተር አድማሱ ገበየሁና ዶክተር ኃይሉ አርአያ (ወትሮም ለስም ነበሩ) ምንም ማድረግ አልቻሉም፡፡ ስምምነቱን ውሃ በላው፡፡ አቶ ልደቱ ሲቀሩ፣ የቅንጅቱን አመራሮች፣ ኢህአዴግ ቃሊቲ ከተታቸው፡፡ የአቶ ልደቱ ንግግርም፣ ከመከሰሻቸው ምክንያቶች አንዱ ሆነ፡፡
በ2000 አዲስ ዓመት መባቻ ላይ የቅንጅቱ መሪዎች ተፈቱ፡፡ የተረፈውን ኃይል የማዋሃድ ጥያቄ አሁንም ተነሳ፡፡ መኢአድ ወደ ነበረበት ተመለሰ፡፡ ውህደቱን የሚፈልጉ ግን ያልተሳካላቸው የአራቱም ፓርቲ አባላት፤ አንድነት ለፍትህና ለዲሞክራሲ የሚል ፓርቲ መሰረቱ። የአቶ አየለ ጫሚሶ ቅንጅትም በዚሁ መንገድ ተፈጠረ፡፡ ዋናው ቅንጅት፣በሁለት በተሰረቁ ፓርቲዎች ተተካ፡፡
አንድነት ለፍትህና ለዲሞክራሲ (አንድነት) ሁለት አመት በሰላም ያሳለፈ አይመስለኝም። “ዝም አንልም” የሚሉ ሃይሎች ከውስጡ ተነሱ። እነሱም እንደ ቀደምቶቹ ሁሉ የራሳቸውን ሰማያዊ ፓርቲ መሰረቱ። ሰማያዊም የመሰረቅ እጣ ደረሰው፡፡ አንድነትም የልጅ ልጅ አየ፡፡ በኢንጅነር ይልቃል መሪነት፣ የኢትዮጵያ አገራዊ ንቅናቄ የሚባል የተሰረቀ ፓርቲ ተመሰረተ። አይባልም እንጂ ቢባል “ሰማያዊን እንኳን ማርያም ማረችህ፣ ማርያም በሽልም ታውጣህ” ማለት እፈልግ ነበር፡፡
ከደቡብ ኅብረት ኢትዮጵያ ራዕይ ፓርቲ፤ ከኢራፓ አዲስ ትውልድ ፓርቲ፣ ከኢዲዩ የኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ አንድነት ንቅናቄ (አዲአን) መስረቃቸውን ስንቱ ያውቃል? ከሰራቂዎች በስተቀር፡፡
ለዚህ ሁሉ መበጣጠስ ገዥውን ፓርቲንና መንግሥትን ተጠያቂ የሚያደርጉ ብዙ ሰዎች አሉ። ሽማግሌ መክሮ የማይመስላቸው  የመሆናቸው ነገር የማን ጥፋት ሊሆን ነው? መደራጀት ህገ መንግሥታዊ መብት ነው፡፡ ሃይማኖትን መሰረት አድርጎ የፖለቲካ ድርጅት ማቋቋምን የከለከለው ግን መንግሥት ነው፡፡ ለዚህች አገር ሁለት ወይም ሦስት ፓርቲ በቂ ነው ብሎ ለምን አይወሰንልንም ታዲያ? ለዛሬ በዚሁ ይበቃኛል። ወደፊት ስለ ፓርቲዎች ድርጅታዊ ብቃት፣ በ2002 ስለነበራቸው ተሳትፎና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች እመለስበታለሁ፡፡    


Read 1564 times