Sunday, 19 August 2018 00:00

የተጀመረው ለውጥ አይቀለበስም!

Written by  ከወንድወሰን ተሾመ መኩሪያ (የማህበራዊ ሳይንስና የሥነልቦና ባለ ሙያ) E. mail: wondwossenteshome@yahoo.com
Rate this item
(2 votes)

 (የሚያስፈልገው ጥበብ ብቻ ነው)
              
     አየርላንዳዊው ፈላስፋ ፍራንሲስ ሆቺሰን (Frances Hutcheson) ስለ ጥበብ ሲናገሩ፤ “ጥበብ መልካምን ፍፃሜ በመልካም መንገድ መፈለግ ነው” ይላሉ፡፡ በእኚህ ሰው አስተሳሰብ.፤ ፍፃሜውና አካሄዱ መልካም ካልሆኑ ጥበብ ሊባል አይገባውም፡፡ በአገራችን ተንሰራፍቶ የኖረው “የትም ፍጪው ዱቄቱን አምጪው” (the end justifies the means) አሰራር፣ ከጥበብ ብዙ የጎደለ፣ የማካቪሊያንስ አካሄድ ነበር፡፡ ይህ አካሄድ ራስ ወዳድነትን፤ጭካኔንና ብልሹ አሰራርን ያሰፈነ አካሄድ ነው፡፡ ይህ አካሄድ ከሌሎች ስለ ሰው ልጅ ካሉ አሉታዊ አስተሳሰቦች ጋር ተዳምሮ፣ አገሪቱን አዘቅት ውስጥ ከትቷት ኖሯል፡፡ ከእነዚህ አስተሳሰቦች መካከል የኸርበርት ስፔንሰር የሶሻል ዳርዊኒዝም ፍልስፍና ይገኝበታል፡፡ ይህ ፍልስፍና.፤ ጉልበተኛውን የበለጠ ጉልበተኛ የሚያደርግና ደካማውን ከፊቱ የሚያስወግድ፣ ርህራሄና ፍቅር አልባ ፍልስፍና ነው፡፡ በአገራችን የነበረው አሰራር የሚለየው፣ ጉልበተኛውን በብሔር የወሰነ መሆኑ ነው፡፡ ለጥቂት ባለጠጎች ጥቅም ሲባል ድሆች ተፈናቅለዋል፤ ጎዳና ወጥተዋል… ወዘተ
ጠቢቡ ሰለሞን በስልጣን የቆየው ከክርስቶስ ልደት በፊት ከ970 እስከ 931  ሲሆን እስራኤልን ለ40 ዓመታት መርቷል፡፡ ይህ ሰው ወደ ሥልጣን እንደወጣ ፈጣሪን የጠየቀው አንድ ነገር ነው--- ጥበብ!! ሰለሞንም ጥበበኛ ስለነበር በነገሰበት ዘመን፣ የእስራኤል ብልፅግና የገነነበትና በእስራኤል ሰላም የሰፈነበት ወቅት በመሆኑ በእስራኤል ታሪክ ወርቃማ ዘመን (Golden age) በመባል ይታወቃል፡፡ መሪዎች በጥበብ ሲሰሩ አገር ያድጋል፤ ሰላም ይሰፍናል፡፡ ላለፉት ከ40 ዓመታት በላይ ኢትዮጵያ ጥበበኛ መሪዎችን አላገኘችም፡፡ ይልቁንም ጨካኞች አለያም ተንኮለኞችና ከፋፋይ መሪዎችን አስተናግዳለች፡፡ ከጥቂት ወራት በፊት ወደ ሥልጣን የመጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ፤ በመደመር፤ በፍቅርና በምህረት እሳቤ፣ የጥበብ መንገድን ሀ-ብለው ጀምረውታል። በአጭር ጊዜ ውስጥ የሰሯቸው ስራዎችም ያስደንቃሉ፤ ያስደምማሉ። ከዚህም የተነሳ የበርካታ ዜጎችን ድጋፍ ተቀዳጅተዋል። አዲሱ የመደመር መንገድ እንዲሰፋ በርካታ ጥበበኞች ከጎናቸው ሊሰለፉ ይገባል፡፡
 ጥበብ ምንድነው? ጥበብ ሁለት አበይት ጉዳዮችን ያቀፈ ነው፡፡
1ኛ፡-ጊዜን ማወቅ - ሰው ጊዜን ያውቃል ሲባል ዘመኑ የሚፈልገውንና የማይፈልገውን ይለያል ማለት ነው፡፡ ከዘመኑ ጋር አብሮ የሚሄደውንና የማይሄደውን ይገነዘባል ማለት ነው፤ ከአዲስና ከመልካም አስተሳሳብ ጋር ቶሎ ይላመዳል ማለት ነው፤ ይህም  የስሜትና የድርጊት ለውጥን ያካትታል፡፡
ይህ ወቅት በዶ/ር ዐቢይ አህመድ መሪነት ኢትዮጵያዊነትን የሚያጎላ፤ ይቅርታንና ምህረትን የሚያቀነቅንና አንድነትን የሚያበረታታ ወቅት ነው። ሰላም ወዳዱ የኢትዮጵያ ህዝብ ሃሳቡን የገዛው በመሆኑ ሚሊዮኖችን ወደ አንድነት አምጥቷል፡፡ (ጠቅላይ ሚኒስትራችን አንድነት፣ አንድ አይነትነት እንዳልሆነ የተናገሩትን ልብ ይሏል)፡፡ በዚህ ወቅት “የኔ” ከሚለው ይልቅ “የእኛ” የሚለው ሃሳብ የሚፈለግበት፤ ከልዩነታችን ይልቅ አንድ የሚያደርጉንን ጉዳዮች ትኩረት ሰጥተን የምንሰራበት፤ አቅማችንን ሁሉ ተጠቅመን በጎ ተግባር ላይ በማዋል የተጀመረውን ለውጥ የምናጠናክርበት፤ አገራችን እንዴት ብትዋቀርና ምን አይነት ተቋማት ቢኖሯት ሁላችንንም እስከ ልዩነታችን በአንድነት ልታቅፍና ልታኖረን ትችላለች የሚሉ ሃሳቦች  የሚመነጩበት ወቅት ነው፡፡ ይህ ወቅት ሃገሪቱ ውስጥ ያለው ሃብት “የእገሌ ነው” ተብሎ የሚወድምበት ሳይሆን  ሃብቱ የማንም ግለሰብ ወይም ቡድን ይሁን “የአገራችን ሃብት ነው” ብሎ በማመን ደህንነቱ የሚጠበቅበት ወቅት ነው፡፡ ይህ ወቅት “የሌሎች ሃይማኖት እንደ እኔ ሃይማኖት አስፈላጊ ነው” ብለን መቻቻልንና ተከባብሮ መኖርን የምናሳይበት ወቅት ነው፤ ከራስ ወዳድነት ተላቀን የሌሎችን ሃሳብ የምናዳምጥበት፤ ባህላቸውንና እሴቶቻቸውን አክብረን ታላቂቱን አገር በመደመር እሳቤ የምንገነባበት ወቅት ነው።  ይህ ወቅት ዜጎች በከፍተኛ ደረጃ ከመንግስት ጋር አብረው የሚሰሩበት፣ ነገር ግን የመንግስትን ሚና ሊተኩ የማይገባበት ወቅት ነው፡፡ ሰውን ሰው እንዲቀጣው ሳይሆን ሰውን ህግ እንዲቀጣው፣ ህግን በከፍተኛ ሁኔታ የምናከብርበት ወቅት ነው።
ይህ ወቅት ሊያስተናግዳቸው ጊዜው ያልሆነ ጉዳዮችም አሉት፡፡ በዚህ ወቅት ትናንሽ ካርታዎችን በየቦታው ቁጭ ቁጭ ማድረግና በብሔር ላይ ያተኮሩ ባንዲራዎችን እዚህና እዚያ መስቀል፣ ጊዜውን ያላገናዘበ ድርጊት በመሆኑ ጥበብ የጎደለው አካሄድ ነው ባይ ነኝ፡፡ ወቅቱ የመንግስትን ሚና ተክቶ፣ በዎች ላይ በራስ ተነሳሽነት እርምጃ መውሰድን አያስተናግድም። ዜጎች የተገጣጠመ ስዕል ለማየት በሚሞከሩበት ወቅት የተገነጣጠሉ ስዕሎች ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ መሯሯጥ ተገቢ ተግባር አይደለም፡፡ “ለብሄሬ” የሚለው አክራሪ አስተሳሰብ፣ “ለዜጋዬ” በሚል ሊተካ ይገባል፡፡ ወደን ወይም ሰርተን ላላገኘነው የብሔር ማንነት፣ ቀን ተሌት ልንለፋ አይገባንም፡፡ ሰው በብሄሩ ሊሞገስም ሆነ ሊኮነን አይገባውም፡፡ ከአንድ ብሔር መገኘታችን በእኛ አልተወሰነም (ascribed እንጂ achieved አይደለም)፡፡ ላለፉት 27 ዓመታት ትናንሽ ስዕሎች ላይ ሲሰራ ስለተኖረ በአንድ ጊዜ ትልቁን የኢትዮጵያን ስዕል መመልከት ሊያዳግት እንደሚችልም መገንዘብ ጥሩ ነው፡፡ ጉዳዩ ከፖለቲካ መሪዎችና ከአክቲቪስቶች በኩል፣ የተሻለ እሳቤና ፈጣን የሆነ ተራማጅ ተግባር ያስፈልገዋል፡፡
2ኛ፡- አደራረግን ማወቅ፡- አንድ ጉዳይ በውጤት እንዲጠናቀቅ፤ የተፈለገውን ዓላማ እንዲመታ አደራረግን (How? የሚለውን) ማወቅ ሌላኛው የጥበብ መገለጫ ነው፡፡ የሚከተሉትን ከግምት ውስጥ ማስገባት ከብዙ ጥፋቶች ያድነናል፡፡
የራስን ፍላጎትና የማህበረሰብ ፍላጎትን ሚዛናዊ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ የራስን ስሜት መሰረት አድርጎ፣ ወደ ድርጊት መግባት፣ ብስለት ማጣትን የሚያሳይ በመሆኑ፣ ዜጎች በስሜት ተገፋፍተው የሚፈጽሙትን ክፉ ድርጊት ማቆም ይጠበቅባቸዋል፡፡ የማደርገው ነገር ሌላው ሰው ላይ ምን ጉዳት ያመጣል? የአገር ገፅታ ላይ ምን ሊፈጥር ይችላል? ድርጊቴ በሌሎች ሰዎች እንዴት ሊታይ ይችላል? የትኩረቴ ምንጭ ምንድነው? የአንድ ብሔር ጉዳይ? ወይስ የሁሉም ዜጎች ጉዳይ ነው? እነዚህን ጥያቄዎች ቆም ብሎ አስቦ መመለስ ያስፈልጋል፡፡ አሁን ወቅቱ የሚፈልገው የጋራ ጉዳዮቻችን ላይ በማተኮር አንድ ሰው ዜጋ በመሆኑ ብቻ እኩል ተጠቃሚና ፍትህ የሚያገኝበትን ስርአት የሚያጎናፅፉ አሰራሮችንና ተቋማትን መገንባት ነው፡፡
በነጭና በጥቁር መካከል ግራጫ መኖሩን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ወይ ጥቁር ወይ ነጭ የሚል ፍረጃ፤ ፅንፈኝነትን የሚያመለክት በመሆኑ ጥበብ የለበትም፡፡ ከሁሉም ብሄር መልካም ሰዎች እንዳሉ ሁሉ ክፉ ሰዎችም አሉ፡፡ አንድ ብሔር ውስጥ ያሉ ሰዎች፣ መሉውን መልካም ወይም ክፉ አይሆኑም፡፡ አንድ ሃይማኖት ውስጥ ያሉ ሰዎች ሀሉም መልካም ወይም ሁሉም ክፉ አይሆኑም፡፡ በእያንዳንዱ ሃይማኖት ውስጥ መልካምም ክፉም ሰዎች አሉ፡፡ በመሆኑም ጎሳ እና ሃይማኖት ተኮር ጥላቻዎችን ማስወገድ አለብን፡፡ አርስቶትል፤ ሚዛናዊነት ጥበብ ያለበት ምርጫ ነው ይላል፡፡ ሚዛናዊ መሆን ያስፈልጋል፡፡
ከጊዜያዊ እርካታ ይልቅ ዘለቄታዊ የዜጎችና የአገር ጥቅም ላይ ማተኮር ወቅቱ የሚጠይቀው ጥበብ ነው። ጥበብ አግላይ አይደለም፤ ጥበብ አያዳላም፤ ጥበብ የሰውን ልጅ ህይወት አያጠፋም፤ ጥበብ ንብረትና ሃብትን አያወድምም፡፡ ትልቁ የኢትዮጵያ ስዕል ላይ የሚያተኩር ሰው፤ በማጥፋት ሳይሆን የራሱን ጥቂት በጎ አስተዋፅኦ በማበርከት የተጀመረውን ለውጥ ወደፊት ያስኬደዋል፡፡ በተለያዩ ቦታዎች የሚፈጸሙ እኩይ ተግባራት፤ የዶክተር ዐቢይን አመራር የሚያሳጣ ሳይሆን የእኩይ ተግባር ፈፃሚዎችን ጭካኔ፣ ራስ ወዳድነትና “እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል” ባይነትን የሚያሳይ ነው፡፡
የለውጥ መሪዎችና ተፅእኖ ፈጣሪዎች ህግን በማስከበር፣ ጎጠኛና ዘረኛ አስተሳሰብ ያላቸውን አመራሮችን በአስቸኳይ በተራማጅ ሃይሎች በመተካት፣ ተቋማትን በመገንባትና ምክክሮችን በማድረግ ሃላፊነታቸውን መወጣት ይጠበቅባቸዋል። አሮጌ አስተሳሰብና አሰራር፣ በአዲስ አሳብና አሰራር መለወጥ ሲጀምር ነውጦች  እንደሚኖሩ ተገንዝቦ፣ በከፍተኛ ትዕግስትና በላቀ ትጋት የተጀመረወን ለውጥ ማፋጠን ያስፈልጋል፡፡  
በርካታ ሚዲያዎች ላይ ምሁራን፣ ጋዜጠኞችና ፖለቲከኞች በንግግራቸው መሃል፤ “…የተጀመረው ለውጥ እንዳይቀለበስ” ሲሉ ይደመጣል፡፡  የኔ መልስ፤ “የተጀመረው  ለውጥ አይቀለበስም”  ነው። የሚያስፈልገው በጥበብ መሥራት ብቻ ነው!! እያንዳንዱ ለውጡን የሚፈልግ ዜጋ፣ የሚጠበቅበትን ለለውጡ በሚመጥን  ልክ በትጋት ይሥራ!!
ቸር እንሰንብት

Read 2250 times