Saturday, 18 August 2018 09:53

“የአገር ልጅ ዘው ዘው”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(5 votes)


       “--እናማ፣ ምን መሰላችሁ… እናንተ ዘንድ የፈለገ ሰው ‘የፓርኪንግ ሎት’ ኤክስፐርት እንደሚሆነው፣ እኛ ዘንድም የፈለገ ሰው ‘የፖለቲካ ተንታኝ’ መሆን ይችላል፡፡ እዚህ አገር “የት የሚያውቀውን!” የሚል ሀረግ አይሠራም፡፡ አንዲት እንጨት በመጋዝ ቆርጦ የማያውቀው ሁሉ የህንጻ ግንባታ ባለሙያ መሆን ይችላል፡፡--”
      
    እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ስሙኝማ…ዳያስፖራ ወዳጆቻችን አገሪቷን ሊያጥለቀልቋት አይደል! እንኳን ለአገራችሁ መሬት አበቃችሁ እንላለን፡፡ ቆይታቸው ደስተኛ እንዲሆንና መመለሻ አውሮፕላናቸውን በፈገግታ እንዲሳፈሩ የሚደረገው ዝግጅት አሪፍ ነው፡፡
ያው እንግዲህ ብዙዎቻችን ከስንት ጊዜ በኋላ ልንገናኝ አይደል! ዓይንም ፈጠጥ፣ ግንባርም ከስክስ ማለቱ አይቀርም፡፡ ስለዚህ ‘ኮንፌሽን’ አለን… እስከ ዛሬ እንልክላችሁ የነበሩት ፎቶዎቻችን  “እድሜ ለፎቶሾፕ፣” እያልን ያሳመርናቸው ናቸው። እንዲህ ተናግሮ እርፍ ማለቱ አይሻልም! ልክ ነዋ…ፎቶሾፕ ገላግሌ ጉንጮቻችንን የህጻን ልጅ ኳስ ያስመስላቸው እንጂ እንደ እውነቱ እኮ ቁፋሮው ያለቀለት የውሀ ጉድጓድ ነው የሚመስሉት፡፡ ያው ስትመጡ ታዩት የለ!
እናማ… “አንተ ፎቶ ላይ እንደዛ ልትፈነዳ የደረስክ የምትመስለው ሰውዬ፤ ምንድነው በአንድ ጊዜ እንዲህ ያከሳህ? የእትዬ እንትና እንዝርት መስለሀል እኮ!” እንዳትሉን፡፡ (የ‘እንዝርት’ን ትርጉም ማወቁ ከጉብኝቱ ስኬቶች አንዱ እንደሚሆን ተስፋ እናደርጋለን፡፡) እንደዛ ስትሉን ሆድ ሊብሰን ይችላላ! አሀ…እናንተ በ‘ፋይቭ ናይንቲ ናይን’ ምናምን “ሀምበርገር፣ ቺዝ በርገር፣ ቺክን በርገር” እያላችሁ እንደምታማርጡት እንዳይመስላችሁ። እዚህ አንድ ቺዝ በርገር ከመግዛት ዶሮይቱን ከእነ ነፍሷና ከእነ አስራ ሁለት ቅመሞቿ መግዛቱ ሊረክስ ምንም አልቀረው፡፡ እናንተ “ጀንክ ፉድ” የምትሉት እዚህ “ቪ.አይ.ፒ. ፉድ” ነው፤ ቂ…ቂ…ቂ…! (እግረ መንገድ…“መግቢያ መደበኛ አራት መቶ ብር፣ ቪ.አይ.ፒ አንድ ሺህ ብር” ሲባል እንዳትደናገሩ፡፡ እዚህ ቪ.አይ.ፒ. የሚባለው ሰዉ ሳይሆን ወንበሩ ነው፡፡)
“ፎቶሽ ላይ ፀሀይን ብርሀኗን የቀማሻት የምትመስዪው ልጅት፤ ምንድን ነው በአንድ ጊዜ እንዲህ ያጠቆረሽ? የከሰል ቤት ጆንያ መስለሻል እኮ!” እንዳትሉን፡፡ (የ‘ከሰል ጆንያ’ን ትርጉም ማወቁ ከጉብኝቱ ስኬቶች አንዱ እንደሚሆን ተስፋ እናደርጋለን፡፡) እዚህ እኮ…ለአንዲት ቢልቃጥ ሎሽን የሚወጣው፣ የሆስፒታል ሙሉ ቼክአፕ ወጪን ሊያክል ምንም አይቀረው፡፡
እናማ…“መኮረጅ ልማዳችሁ ነው” አትበሉንና መአት ነገር ከእናንተ ወስደናል፡፡ ልክ ነዋ… እናንተ ታቱ የምትሉት ‘ኒቂሴ’ን ከሆነም እኛ የትና የት ሄደናል፡፡ ልክ ነዋ… ስንቶቻችን ቻይና የሠራው የአበባ ማስቀመጫ የመሰልነው ‘እድሜ ለኒቂሴ።’ የእናንተ ‘ታቱ’ የሥራ ማመልከቻ ደብዳቤ ስታክል፣ የእኛ “ዋሺንግተን ፖስት”ን እያስናቀ ነው፡፡ (--ፊት ለፊት ከሚታየው ውጪ የትኞቹ ቦታዎች ላይ እንደምንነቀስ ጠያይቁና ‘ብታምኑም ባታምኑም’ የሚል መፅሐፍ ማሳተም ትችላላችሁ፡፡)
ስሙኝማ… መዝናናቱ አሪፍ ነው፡፡ ቸስ በሉ። ‘ኦሪጂናል’ እንጀራም እስኪበቃችሁ መመገቡ ‘ለሜሞሪ’ ጥሩ ነው፡፡ የምር…እንደምንሰማው አሁን ተሻሻለ እንጂ በፊት ዲሲ ምናምነኛ ጎዳና፣ሬስቱራንት የሚያገኙት እንጀራ፣ ባላ ላይ ቢያስሩት፣ ለወፍና ለአሞራ አደን ይሆናል ይባል ነበር፡፡
በነገራችን ላይ… እግረ መንገዳችሁን ዘወር፣ ዘወር ብላችሁ ኑሯችንን እዩልንማ፡፡ በዶላርና በዩሮ ባትችሉ እንኳን በሙያችሁ ብዙ እገዛ ማድረግ ትችላላችሁና፡፡ በየመስኩ ጠፍንጎ ያያዘን የሙያ እጥረት አለብን፡፡ የእውቀት እጥረት አለብን። እንኳን ላይ በላይ ልንጨምርበት ጭራሽ ያለንም እየጠፋብን ያለ ነው የሚመስለው፡፡
የትምህርት ባለሙያዎች በጣም ትፈለጋላችሁ። በየትምህርት ተቋሙ ያለውን እውነት፣ ማለትም የመማሪያ ክፍሎችንና የትምህርት መጻህፍትን እጥረት እዩልንማ፡፡ ግድግዳ ላይ ከተሰቀሉ ባለቀለም ሳይንሳዊ ፖስተሮች በቀር ይህ ነው የሚባሉ ዘመን ያፈራቸው መሳሪያዎች እጥረት ያለባቸውን ቤተ ሙከራዎች እዩልንማ፡፡ የአስተማሪዎቻችንን የማስተማር ብቃት አይታችሁ፣ እንዴት ተሻሽሎ የተቀረው ዓለም ደረጃ  እንደሚደረስ፣ በጉዳዩ ላይ የሚሠሩ ምሁራኖችንን በሀሳብ አግዟቸውማ፡፡ የትምህርት ጥራት ለማሻሻል በሚደረገው ጥረት የሙያችሁን አስተዋጽኦ አድርጉልንማ፡፡
የህክምና ባለሙያዎች ወደ ህክምና ተቋሞቻችን ጎራ በሉ፡፡ በዚያ ዘርፍ እጅግ ከፍተኛ የሆነ የሙያ ብቃት ችግር አለብን፡፡ የዘመናዊ ህክምና መሳሪያዎች ድርቅ አለብን፡፡ ሰፋ ሲልም…አለ አይደል… የከፋ  የህክምና ተቋማት እጥረት አለብን፡፡ በአሁኑ ጊዜ የተለመዱት ተላላፊ በሽታዎች ብቻ ሳይሆኑ ከዚህ በፊት እኛ አካባቢ በስፋት የማይታዩ ካንሰርን የመሳሰሉ የጤና ችግሮች በፍጥነት እየተስፋፉ ነው። እናማ… የሙያ እገዛችሁን እንፈልጋለን፡፡ ደግሞም ከፍተኛ የሆነ የመድሀኒት አቅርቦት ችግርም አለብን። አይደለም ከፍ ላሉ የጤና ችግሮች፣ ለመለስተኛ የጤና ችግሮች የሚሆኑ መድሀኒቶች ብቻ ሳይሆን ቀላል ማስታገሻዎች እንኳን ማግኘት ችግር ሆኗል። (እግረ መንገድ…ግዴለም ያ በ‘ቪ’ የሚጀምረው ኪኒን ችግር እንኳ ይሄን ያህል ያለብን አይመስለንም፡፡ ለእናንተ ሁሉ ልንተርፍ እንችላለን፡፡ (ቂ…ቂ…ቂ…) እንደውም የሀኪም ትእዛዝ እንኳ ሳያስፈልግ፣ “ስኳር አለ?” ተብሎ እንደሚሸመተው ሁሉ “ቪ… አለ?” ብሎ በቀላሉ መግዛት ይቻላል አሉ፡፡
የአይቲ ባለሙያዎች በጣም፣ እጅግ በጣም የሙያ ድጋፋችሁን እንፈልጋለን፤ በዚያ ረገድ ያለብን ችግር ከዓለም ወደ ኋላ አስቀርቶናልና! የቴክኖሎጂ ሽግግሩን በአስተማማኝ ልታስፈጽሙት የምትችሉት በግንባር ቀደም እናንተ ናችሁ፡፡ ፌስቡኩን ስላጥለቀለቅነው ቴክኖሎጂውን ‘ቀርጥፈን የበላነው’ ያህል የተዋሃደን እንዳይመስላችሁ፡፡  እናማ…ከፍተኛ የሆነ የቴክኖሎጂ ችግር አለብን፡፡ ብዙ ቦታ አሁንም እኮ ሥራዎች የሚካሄዱት “ከአባቶቻቸን በወረስነው” በሚባል አይነት ነው፡፡  ሥራዎች የዛሬ ግማሽ ምእተ ዓመት በሚሠሩበት መንገድ እየተሠሩ ነው፡፡ እንዲህ ሆነን ነው----መካከለኛ ገቢ፣ ምናምነኛ ገቢ የምንለው!
የመንገድ ስርአታችን እንዴት እንደሆነ እዚያም ሆናችሁ ሳትሰሙ አትቀሩም፡፡ ቱሪስቶች ወደዚህ ብቅ ለማለት ሲያስቡ እኮ… “ኢትዮዽያ ውስጥ መኪና አታሽከርክሩ” የሚባል ምክር ይሰጣቸዋል ነው የሚባለው፡፡ ግን ደግሞ መስማት ሌላ፣ ማየት ሌላ፡፡ በዓይናችሁ ስታዩ ልትደነግጡ ትችላላችሁ። የመንገድ ላይ ስርአታችን አይደለም እናንተ፣ እኛ እዚህ ያለነው ግራ እስኪገባን ድረስ የኖህ ዘመን እየመሰለ ነው፡፡ እናማ… ያላችሁበትን ሀገራት ተሞክሮ አካፍሉንማ!
ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል… ያው መቼስ ለረጅም ጊዜያት ተጠፋፍተን ከርመን የለ…“እከሌ ምን ሆኖ ይሆን?”  “ያቺ እከሊትስ ምን እየሠራች ይሆን?” ማለታችሁ አይቀርም፡፡ “እንትና እኮ የሀይማኖት አገልጋይ እሆናለሁ ብሎ ነበር፣ አሁን የትኛው ቤተ እምነት እያገለገለ ይሆን?” የሚል ጥያቄ ካላችሁ፣ እንዳትነደግጡ እንጂ…መልስ አለ፡፡ ‘የፖለቲካ ተንታኝ’ ሆኖላችኋል። “የት የሚያውቀውን ፖለቲካ!” ምናምን እንዳትሉ። (አንዳንድ የአዲስ አበባ ነዋሪዎችን ያየ፣ እንዲህ አይነት ጥያቄ አያቀርብም፤ አራት ነጥብ፡፡) እናማ፣ ምን መሰላችሁ… እናንተ ዘንድ የፈለገ ሰው ‘የፓርኪንግ ሎት’ ኤክስፐርት እንደሚሆነው፣ እኛ ዘንድም የፈለገ ሰው ‘የፖለቲካ ተንታኝ’ መሆን ይችላል፡፡ እዚህ አገር “የት የሚያውቀውን!” የሚል ሀረግ አይሠራም፡፡ አንዲት እንጨት በመጋዝ ቆርጦ የማያውቀው ሁሉ የህንጻ ግንባታ ባለሙያ መሆን ይችላል፡፡
በነገራችን ላይ፣ እንደው ድንገት እንዳትደነግጡ ብለን ነው… ቅዳሜና እሁድ በመጣ ቁጥር “የእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ግጥሚያዎች የሚደረጉት እዚህ ነው እንዴ?” ብላችሁ ከመጠየቃችሁ በፊት መልሱን እንኩማ…እዚህ አይደለም፡፡ ግን እንዲህ ማለት የእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግን በመዘገብ ሌሎቹን አገራት ተዉአቸውና… ራሳቸው እንግሊዞቹ እንኳን ቢበልጡን ስንዝር በምታክል ርቀት ነው፡፡
ደግሞላችሁ አንዱን… “አንተ፣ አጎትህ ታመው እንደነበር አንድ ዘመዳችሁን ኤል.ኤ. አግኝቺያት ነግራኝ ነበር፡፡ አሁን እንዴት ናቸው?” ብላችሁ ብትጠይቁ፣ በምታገኙት መልስ እንዳትደናገጡ። “እኔ አጎት እንዳለኝም አላውቅም” ሊላችሁ ይችላል። ነገር ግን የሜሲ የቁርጭምጭሚት ጉዳትን በተመለከተ፣ የጤንነት ሁኔታውን የሚከታተለው ዶክተር ሊነግራችሁ ከሚችለው እኩል ይነግራችኋል። (‘ግሎባላይዜሽን’ ብዙ አይነት መገለጫ እንዳለው ሹክ እንበላችሁ ብለን ነው፡፡)
እናላችሁ… ዳያስፖራ ወገኖቻችን፤ ተገርማችሁም፣ ተደስታችሁም፣ ዘና ብላችሁም፣ ዞር፣ ዞር ብላችሁም… በመጨረሻ  ወደየመጣችሁበት ስትመለሱ፣ አንድ ጥያቄ ልባችሁን ይሙላውማ… “እኔ በአቅሜ ይቺን ምስኪን አገር በምን መልኩ ልረዳት እችላለሁ?” በየአዳራሹ ባንዲራዋን እያውለበለባችሁ ስትዘምሩላት፣ ስታነቡላት የነበረችው አገራችሁ፣ ከእናንተ የምትፈልገው ይሄን ነውና፡፡ እስከዛው ግን የጋራ ቤታች ውስጥ እስከሆንን ድረስ… “የአገር ልጅ ዘው ዘው” እንባባልማ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 5194 times