Saturday, 18 August 2018 09:46

በሀሳብ መንገድ ላይ

Written by  ተመስገን
Rate this item
(3 votes)

“ራስህን ስትሆን አሁንን ትኖራለህ”
              
    በጥንት ዘመን ነው፡፡ አንድ ሰው በአንድ ወንዝ ዳር ሰውነቱን ሲታጠብ፣ በወንዙ ላይ ተንሳፎ የሚያልፍ ብልቃጥ ተመለከተ፡፡ ዘለለና ለቀም አደረገው፡፡ ብልቃጡ ውስጥ የተጠቀለለ ወረቀት ነበር፡፡ አውጥቶ ሲያነበው፤
“ይህን ወረቀትና ካርታ በማግኘትህ ዕድለኛ ነህ፡፡ ፀሐፊው ግን ዕድለ ቢስ ነው፡፡ ብዙ ወርቅና አልማዝ ቢኖረውም ደስተኛ አይደለም፡፡ … በደብዳቤው መጨረሻ ላይ የተሸፈነውን መስመር እንዳትነካ፡፡ እሱን የምታነበው እዚህ የወንዙ መነሻ ላይ ስትደርስ ነው።” ይላል፡፡
ሰውየው ባጋጠመው ነገር ተገረመ። የሚያስፈልገውንም ነገር አዘጋጅቶ፣ ወንዙ የመጣበትን መንገድ እየተከተለ ተጓዘ፡፡ .. ከዓመታት በኋላም ቦታው ደርሶ የደብዳቤውን የመጨረሻ መስመር ገልጦ ተመለከተ፡-
“ብልቃጡን ከፊት ለፊት ከሚታየው ትልቅ ዋርካ ስር አስቀምጥና ሂድ፡፡ … ነገ ጠዋት ተመለስ” የሚል ነበር፡፡
***
መሰረቱ ጥንታዊ ባቢሎን የነበረው አስትሮሎጂካል እምነት ወደ  ሶሪያ፣ ፐርሺያ፣ ግሪክ፣ ሮምና አረብ አገሮች ከመስፋፋቱ በፊት ማረፊያ ያደረገው ግብፅን እንደሆነ ተፅፏል። ጥንታዊ ግብፃውያን ብሩህ ኮከብ ለሆነችው ሳይረስ ትልቅ ክብር፣ ፍቅርና እምነት ነበራቸው። ዓባይን ያመጣችልን እሷ ናት ይላሉ። ህንዳውያንም እንደዚሁ ከሂማሊያ ተራሮች ስር እየፈለቀ ወደ ካልካታና ባንግላዴሽ የሚዘልቀውን፣ የትውልድን ሃጢአት ያነፃል፣ ከህመምና ከችግር ይፈውሰናል ብለው የሚያምኑበትን የጋንጅስ ወንዝ የሰጠቻቸው አምላክ ቪሺኑ መሆኗን በቅዱሳን መጽሐፍቶቻቸው አስፍረዋል፡፡
የወንዝ ነገር ከተነሳ፣ በዘመናዊው ዓለምም እንደነ ቮልጋ (ዶን)፣ ሬይኔ፣ ሚሲሲፒና ቴምስ ለመሳሰሉት ወንዞች - ሚካኤል ሾሎክቭና ማርክ ትዌይንን ጨምሮ ታላላቅ ፀሀፊዎች፣ ገጣሚዎችና ሙዚቀኞች ብዙ ብለውላቸዋል፡፡
የዚህ ማስታወሻ ቁምነገር፤ ወንዝም ሆነ ውቅያኖስ፣ አለትም ሆነ ቋጥኝ፣ ጊዜም ሆነ ወቅት፣ ሰውም ሆነ እንስሳ … ቁጥርም ሆነ ካላንደር፣ አፈጣጠርና አኗኗር፣ የምንኖርባትን ዓለም ሆነ ከሰማያዊ አካላት (Heavenly bodies) እንቅስቃሴ ጋር የተሰናኘ መሆኑን መቀበል አንድ ነገር ሆኖ፣ በእግረ መንገድ እንደ ሆሮስኮፕ የመሳሰሉት እምነቶች ኢ-ሳይንሳዊ በሆነ ስሌት የተቀመሩ በመሆናቸው፣ የ‹ዕጣፈንታችን› ወሳኞች አድርጎ ማሰብ ስህተት መሆኑን መረዳት ነው። ምክንያቱም … በእጃችን የያዝናትን፣ አሁን የምንላትን ይቺን ቅጽበት እንዳንጠቀምባት ከማጃጃላቸውም በላይ ትልልቅ እምነቶች የተገነቡበትን መሰረቶች ስለሚንዱ ነው፡፡
ወዳጄ፡- የእምነት ጉዳይ ይቆየንና ይቺ ‹አሁን› የምንላት በጃችን ያለች ጊዜን ማስከበር ግን የፍላጎትና የምርጫ ጉዳይ አይደለም፡፡ የመሆን ወይ አለመሆን እንጂ፡፡ … በዚች ቅጽበት የማይሰራ፣ የማይስቅ፣ የማይጫወት፣ የማያወራ የማያለቅስ፣ የማይራመድ፣ የማይቀመጥ፣ የማይተኛ … ባጠቃላይ ‹መሆንን› የሚያደርግ ወይ ‹ማድረግን› የማይሆን ማን አለ?... የሌለ ካልሆነ!!
ወዳጄ፡- ሆሮስኮፕ መሬት የዩኒቨርሳችን ዕምብርት እንደሆነች የሚያስመስልበትን መንገድ ኮፐር ኒከስ፣ ጋሊሊዮና ኬፕለርን ጨምሮ ብዙ ሊቃውንት ያረጀ ተረት ብለውታል፡፡ ሁለተኛው ምክንያት፤ ቴሌስኮፕ ከመፈልሰፍ በፊት ዩራነስ፣ ኔፕቲንና ፕሉቶ የተባሉት ፕላኔቶች እንዳልተገኙ እየታወቀ፣ አስትሮሎጂካል ቻርት ላይ ከሌሎች ጋር እንደ ተፅዕኖ አድራጊ መቅረባቸው ስሌቱን ቀልድ ያደርገዋል፡፡ ሶስተኛ ቴሌስኮፕ ከተሰራ በኋላ ያልተጠበቁ ሳይንሳዊ ግኝቶች ዕውን በመሆናቸው … ዩኒቨርስ የምንለው ሁለንተና በመልቲ ዩኒቨርስስ ሲተካ፣ ሌሎች ፀሃዮችና ጨረቃዎች ተገኝተዋል፡፡ አራተኛ፡- በጄነቲክ ሳይንስ ሰው ‹ሰው› የሚሆነው፣ በእናቱ ሆድ ውስጥ ነው የሚለውን ፍሬ ነገር ይቃረናል፡፡ አምስተኛ፡- ከ2000 ዓመታት በፊት የነበረው የፀሐይ ጉዞ፣ በዚህ ዘመን ሲጠና፣ የአንድ ወር የኋላ ልዩነት እንዳለው ታውቋል፡፡ በዚህ ስሌት ምሳሌ ሲወሰድ፤ ሆሮስኮፒክ ቻርት ላይ ጁን መጨረሻና ጁላይ መጀመሪያ ድረስ ባለው ጊዜ “ካንሰር” ሆኖ የተወለደው፤ በትክክለኛው እንቅስቃሴ ስሌት ‹ጀሚኒ› ይሆናል። ይህ ደግሞ ‹ዝምተኛ፣ ጨዋ፣ ገለልተኛ› የተባለውን ሰው ባህሪ በተቃራኒው ተግባቢ፣ ተጫዋች፣ ቀልደኛ” ስለሚያደርገው፤ ጨዋታውን ያበላሸዋል፡፡
ወዳጄ፡- ፈጣሪም ሆነ አማልክት፣ ፀሐይና ከዋክብት፣ የተቃራኒዎች አንድነትና ልዩነት ህግ … ወይም ማንም ይሁን ምን … የፈጠራት ይቺ ‹አሁን› የምንላት ሰዓት ናት፡፡ ዕድሜ የምትሆነው። … አንድ ነገር ላስታውስህ። … ይህንን ማስታወሻ ስታነብ፣ የምትኖርባት ምድር እየዞረች ነው፡፡ … ከተኛህበት አልጋ፣ ከምትራመድበት መንገድ፣ ከምትነዳው መኪና፣ ከምትዘፍንበት መድረክ፣ ከብሩህ አእምሮህና ከበጎ ተግባርህ፣ ከኋላ ቀር ሃሳቦችህና ዕኩይ ድርጊትህ ጋር አብረሃት ትዞራለህ፡፡ … ልብ በል፡፡ … ዕድሜህ እየቆጠረ ነው፡፡ … ወደ ኋላ ልትጠመዝዘው ወደፊት ልታስሮጠው አትችልም። አንተ የምትሽከረከረው ‹አሁን› ላይ ነው፡፡ አሁን ላይ ሆነህ ትናንትን ልታስብ ትችላለህ፡፡ አንተ ግን የትናንትናው ‹አንተ› አይደለህም፡፡ አሁን ላይ ሆነህ ነገን ማሰብ (መሳል) ማድረግ ትችላለህ፡፡ አንተ ግን የ ‹አሁን አንተ› እንጂ የነገው አንተ አይደለህም። ትላንት ላጠፋኸው ስትፀፀት፣ መወቀስ ያለበት የትናንት አንተነትህ አብሮህ የለም፡፡ እንድታጠፋ ያደረጉህ ምክንያቶችም ከትናንት ጋር ሞተዋል፡፡
ትላንት ላበረከትከው በጎነት የሚመሰገነውም ‹የትናንቱ አንተ› ነው፡፡ በጎና ቀና ያደረጉህ ምክንያቶችም ‹ትናንት› የወለደቻቸው ናቸው። ስህተት እንዳይደገም ወይም በጎነት እንዲፀና ከፈለግህ፣ ዛሬ ለተወለዱት ምክንያቶች ራስህን ሁን፡፡ ልክ የሆኑትን ‹ልክ ናቸው›፣ ልክ ያልሆኑትን ‹ልክ አይደሉም› በላቸው፡፡ ላንተ ልክ የሆኑ ለሌሎች ልክ ላይሆኑ ይችላሉ፡፡ … ወይም ደግሞ የተገላቢጦሽ፡፡ … እዚህ ጋ ነው ማሰብ ያለብህ። … እዚህ ጋ ነው የሃሳብ ብልጫ፣ የሃሳብ ትልቅነት የሚረጋገጠው። … እዚህ ጋ ነው እውነት ሃሳብ የሚሆነው፡፡ … ዕውነትህ ዛሬ፣ ዛሬ እውነትህ እንዲሆን ራስህን ሁን፡፡ … ራስህን ስትሆን አሁንን ትኖራለህ፡፡
“ማንኛውም ነገር ይቀየራል፡፡ እንደነበር የሚቆይ የለም፡፡ በማናቸውም ጉዳይ “ልክ” የምትሆነው ይቺን ቅጽበት ስትረዳና እሷን መሆን ስትችል ነው፡፡ (Everything is ever changing and nothing is permanent. To scucceed in any undertaking, one must be aware of … and act in harmony with all changes of the moment) የሚልህ የጥንታዊት ቻይና የለውጥ ማዕበል “canon of changes” የተሰኘ ፅሑፍ ነው፡፡
***
ወደ ተረታችን ስንመለስ፡- በተፃፈው መሰረት፤ ባለታሪኩ በሚቀጥለው ቀን ጠዋት ከቦታው ተገኘ። ምንም አልነበረም፡፡ ትናንት ያስቀመጠው ብልቃጥ ደግሞ ተቀይሯል፡፡ አንስቶ ሲመለከተው እሱም ውስጥ ወረቀት አለ፡፡ ሲነበብ፤
“ያመንከው የማታውቀውን ነው፡፡ ዋናውን ነገር አልመረመርከውም፡፡ የፃፍኩልህን ብቻ እያየህ ወደ ምኞትህ ገሰገስክ፡፡ ወረቀቱ ነበረበት፣ አብሮህ ለዓመታት የተቀመጠው ብልቃጥ የተሰራው ከአልማዝ ነው” ይላል፡፡ ሰውየው ወንዙን እየተመለከተ፣ ብዙ ሰዓት አሳለፈ። በየቅጽበቱ የሚፈሰው ውሃ አዲስ ነው። … ጎጆ ቀለሰ፣ አገባ ወለደ፡፡ ከብዙ ዓመታት በኋላ የመጡ ትውልዶች፤ የ‹እገሌ ነገድ ነን› እያሉ ስሙን ይጠራሉ፡፡ … “የሰው አገሩ … እግሩ!!” … እንዲሉ፡፡
ወዳጄ፡- ለማንኛውም ያንተ የአልማዝ ብልቃጥ፤ ይቺ በጅህ የጨበጥካት ‹አሁን›ህ ናት። …. አይመስልህም? ሠላም!!

Read 1104 times