Saturday, 18 August 2018 09:45

የ‹ሀገር መሪዎች› ንግግር

Written by  ፈለቀ አበበ arthabesha@gmail.com
Rate this item
(3 votes)


    “ለራስ የመታመን ልቦና፣ የልዕለ ሰብእ ፀጋ      ነው።”  ኢመርሰን
የ‹ሀገር መሪው› ንግግሮች፤ በዜጎችና በሀገሪቱ መጻዒ እድል ላይ የፈጠረውን ላቅ ያለ ፋይዳ በማስተዋል፤ በሌላ ሀገር የሚኖሩ ምሑራን ንግግሮቹን አደራጅተው ስለመጠረዝ ተወያዩ፡፡ ከንግግሮቹ አንዲትም ቃል ተነቅሳ እንዳትወጣም (አስነጥሶም ቢሆንኳ) ከመወሰን ደረሱ፡፡ ውሳኔው አስገራሚ ይመስላል፡፡ ለምን ቢሉ። የሀገር መሪው ንግግሮች፣ እንደየሀገራቱና የየሰዉ ግንዛቤ ደረጃ በፈጠረው የተለያየ አመለካከት ምክንያት፡፡ በተለይም የመሪው ንግግሮች አርበ ሰፋፊ መሆናቸው፡፡
በአንደበታቸው መስህብነት ለመሪነት መብቃትና ከስልጣን ዘመናቸው በኋላም ከንግግሮቻቸው ተመርጠው በቅርስነት የተጠበቁላቸው፣ ከዚያም ባሻገር የንግግራቸውን ፈለግ ለማስቀጠል የታደሉ አሉ፡፡ ተማሪዎች ከለጋ እድሜያቸው ጀምሮ የንግግር ክህሎታቸውን እንዲያዳብሩ ይረዳቸዋል በሚል በእኛም ሀገር ኢንተርናሽናል ትምህርት ቤቶች ውስጥ ልምምዱ መተግበር የጀመረውን የኦባማ ንግግር (Obama’s Speech) ከዚህ ዘመን መሪዎች መካከል መጥቀስ ይቻላል። ንግግሮቻቸውን ከሕይወት ታሪካቸው፣ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶቻቸው፣ ጉባኤ፣ አዋጅና ደብዳቤዎቻቸው . . .ወዘተ. ጋር ያካተቱ የገዢዎችና የነገሥታቱ ዜና መዋዕሎችም እንዲሁ ከጥንት ጀምሮ በፔሪፒለስ፣ ፓፒረስ፣ ብራና . . . ሲደጎሱ ኖረዋል፡፡
    
ፕሮፓጋንዳ - የመሪ ንግግር
ከቅርቡ ዘመን የዓለም ታሪክ  በተለይ የኮሙኒስቱ ጎራ መሪዎች፣ የፕሮፓጋንዳ ንግግሮቻቸው፣ ከፖሊቲካዊ ፍልስፍናዎቻቸው ጋር በትልልቅ ጥራዝ ተሰግስገው፤ ሶሻሊዝምን በተከተሉ ታዳጊ ሀገራትም ሁሉ በገፍ እየተሰራጩ፣ ሕዝቡን በኮሚዩኒዚም ርእዮተ አለማቸው እያጠመቁ፤ ከቤተ መንግስት እልፍኝ እስከ አብዮታዊ ካድሬ ቢሮዎች አይጠየፌ መደርደሪያዎች፣ የቀበሌ ጽ/ቤቶች፣ የመስሪያ ቤት ቢሮዎችንና የመኖሪያ ቤቶችንም ጠረጴዛዎች ሲያጣብቡ ኖረዋል፡፡ ሶሻሊዝምም በተራው በካፒታሊዝሙ ጎራ አሰላሳዮች ብዕር ተገዝግዞ፣ አፈር ድሜ እስኪግጥና መጻሕፍቱ ለመንደር የችርቻሮ ሱቆች ስኳርና የሻይ ቅጠል መጠቅለያ ፍጆታነት እስኪውሉ ድረስ፡፡
የሀገር መሪዎች ዜጎቻቸውን የሚያስተባብሩበትና አላማና እቅዳቸውን የሚያሳውቁበት ግንባር ቀደም መሳሪያ ሆኖ የሚጠቀሰው ይህ የመሪ ንግግር፣ በየዘመኑ የየጊዜውን መልክ ይዞ መከሰቱ እንዳለ ሆኖ፤  የንግግር አዋቂነት በተለይ በዚህ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ላይ ምናልባትም አንድ መሪ ሊያሟላቸው ከሚገባቸው መስፈርቶችና ከመሪነት ጥበብ መመዘኛነት የደረሰ መሆኑ ይስተዋላል፡፡ በርግጥ ያኔ ከብሉይ ዘመን ጀምሮም ቢሆን አስፈላጊነቱ አጠያያቂ እንዳልነበረም መጽሐፍ ይመሰክራል፡፡ ሕዝቡን ከባርነት ለማውጣት በእግዚአብሔር የተመረጠው ነቢዩ ሙሴ፣ የአንደበቱን ኮልታፋነት፣ በወንድሙ አሮን ርቱእ አንደበት እንዲታገዝ ‹‹እርሱ አፍ ይሆንልሀል›› ተብሎ ነበር የታዘዘው፡፡ በፀጋ ስጦታ ጉዳይ - ‹ይታደሏል እንጂ አይታገሉትም› አይደል . . . ካልተሰጠህ አልተሰጠህም። የተሰጣቸው ደግሞ አንድም ለመላው ዜጋ የወል ሰላምና እድገት በመግባቢያ ድልድይነት ባግባቡና በሚያስመሰግናቸው ሁኔታ ጥቅም ላይ ያውሉታል። ያልታደሉቱ ግን ለጥፋት የሚመዝዙትና መልሶ መጥፊያቸው የባለጌ ምላስ ያደርጉታል - ለምሳሌ እንደ ሂትለር፡፡ ጠቢቡ ሰለሞን በምሳሌው ‹‹ሞትና ሕይወት በምላስ እጅ ናቸው›› እንዲል፡፡ አንዳንዶችም ንግግሮቻቸውን በውስጣቸው ለሸሸጉት መሰሪ እቅዳቸው መከለያነት ይገለገሉበታል፡፡ ‹‹አፈ ቅቤ ልበ ጩቤ›› እንዲሉ፡፡
ባንጻሩ ግን ያመኑበትን ፊት ለፊት የሚገልጡቱ፣ ገዢውም ሆኑ ተገዢው፣ ንግግሮቻቸውን በድፍረት የአቋማቸው ማንፀባረቂያ ያደርጉታል። ኮሪዮን፤ ‹‹ንጉሥነት እንጀራዬ ነው›› ሲል፤ አንቲገን በበኩሏ፤ ‹‹እኛ ግን እውነትን ከሚናገሩት ወገን ነን›› ትላለች፡፡ ኢትዮጵያዊው ሊቅ ነጋድራስ ገብረ ሕይወት ባይከዳኝ ደግሞ ‹‹እያንዳንዱ ሰው ሌላውን ሰው ሁሉ አጥቅቶ ለብቻው እንደ ፈቃዱ እንዲኖር ይወዳል፡፡ . . . የመንግሥት ጥረቱ ሕዝቡን ሁሉ አስማምቶ፣ በመካከላቸው ሰላም ማድረግ ነው፡፡›› ይላሉ - መንግሥትና የሕዝብ አስተዳደር  በሚለው መጽሐፋቸው፡፡  
ዲፕሎማሲ - ቀ ኃ ሥ - መንግሥቱ - መለስ - ኃይለማርያም
‹‹ዲፕሎማት የራሱን ሀገር ‹ከፍ ከፍ እንዲያደርግ› የሚሾም ሰው ነው›› የሚለው የተለመደ አባባል ነው፡፡  ዲፕሎማቶችና የአገር መሪዎች ወደ ሌላ ሀገር ሲሄዱም ሆነ የሌሎች ሀገራትን ልዑካን/እንግዶች በሀገራቸው ሲቀበሉ፣ ይህን ያደርጉ ዘንድ ግድ ይላቸዋል፡፡ ፔሪ፤ ንግግር ለተናጋሪውም አጉል ያልተንዛዛ ላድማጩም እጅግም ያላጠረ አድርጎ  በማዘጋጀቱ ጉዳይ ላይ ያለውን አበሳ እንደጠቆመው፤ “Speeches cannot be made long enough for the speakers, nor short enough for the hearers” ንግግሮቻቸው ቅልብጭ ያሉ ማራኪና የግንኙነቱን ሀሳብ የሚያንጸባርቅ ከመሆኑ ጎን ለጎንም፣ አንዱ ሀገር ከሌላው ጋር ያለውን ነባር ታሪካዊ እሴት በግብአትነት በመጠቀም ውበትና ኃይል እንዲፈጥር ሲያደርጉ ይታያሉ፤ መሪዎች፡፡ በዚሁም አንዳንድ ጊዜ ታላቅ መደነቅን ሲቀዳጁ፡፡
ባራክ ኦባማ በኢትዮጵያ ቆይታቸው ሉሲን ተመርኩዘው፤  ‹‹ቅድማያቴ/ታችን››  ብለው እንደጠሯትና በቡናችን የረከቦት ማእድም እንደታደሙት፤ ኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማርያምም በረዣዥም  ንግግሮቻቸው በስፋት የሚታወቁትን  የፊደል ካስትሮን ቶስካኖ ሲጋራ አብረው አቡለቅልቀዋል፡፡ የረዣዥም ንግግሮቻቸውን ልምድ ቀስመውም ‹ለአብዮቱ ጥቅም› አውለውታል። ‹‹ወርቅ ሲያቀርቡለት ፋንድያ የሚፈልግ ሕዝብ! ጄኔራሉን ቂጡን በሳንጃ እየወጋን! ለምሳ ሲያስቡን ለቁርስ አደረግናቸው - እናት ሀገር ወይም ሞት!...›› በሚሉ ወቅታዊና አነጋጋሪ ዘይቤዎች እየለበጡ፡፡
ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ፤ የዓለምን ነባራዊ ሁኔታ አገናዝበው፣ በመንግሥታቱ ድርጅት መድረክ ላይ ያቀረቡት ንግግርና ንግግራቸውን ተከትሎ የተከሰተው ኩነት፣ ከነቢይነት እስኪያስቆጥራቸው የደረሰ ነበር፤ ‹‹እድል ስናገኝ ጊዜ የሚቻለንን ሁሉ እናድርግ፡፡ ደስ የማይል እርምጃ ከመውሰድ እንዳን፡፡ . . . የመጀመሪያውን እሳት የሚለኩሰው ማን እንደሆን ይታወቃልን? የሁላችንም እድል አንድ ነው፤ ወይ መጥፋት ወይ መዳን!...››
የቀድሞው ጠ/ሚኒስትር መለስ ዜናዊን እንደ  መብረቅ የፈነዳ ንግግርም ያስታውሷል፡፡ ቶጎ ሎሜ በተደረገው በአፍሪካ አንድነት የመሪዎች ስብሰባ ላይ የወደፊቱ የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ የት ይሁን ብለው ሲዶልቱ፤ መለስ በእንግሊዝኛ ቋንቋ ባደረጉት ታሪካዊ ንግግር፣ ሁለቱንም የቀድሞ መሪዎች ስም ጭምር እያጣቀሱና .... ‘’...who trained Mandela? Emperor Haileselassie the reactionary trained Mandela the revolutionary. Mandela was trained in Ethiopia. who supported Mugabe in his fight against Rhodesim? Mengistu!” (ኧረ ለመሆኑ ማንዴላን ማነው ያሰለጠናቸው? አፄ ኃይለ ሥላሤ ናቸው፡፡ አብዮታዊው ማንዴላ በአድኃሪው ኃይለስላሤ ነው የሰለጠኑት፡፡ ማንዴላ ስልጠና ያገኙት በኢትዮጵያ ነበር፡፡ ሙጋቤ ከያኒስሚዝ ሮዴዢያ አገዛዝ ነጻ ለመውጣት ሲታገል ማን ነበር ከጎኑ? - መንግሥቱ ነው፡፡ መንግሥቱ በሀገር ውስጥ አምባገነንና ጨፍጫፊ ነበር፡፡ ነገር ግን በአፍሪካ ጉዳይ ላይ እሱም እንደ አጼ ኃይለስላሴ ጠንካራ አቋም ነበረው፡፡ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ጉዳዮች ላይ ያላት ቁርጠኝነት በመንግሥታት ለውጥ ውስጥ ፈጽሞ የሚቀያየር አይደለም፡፡ በአጼ ኃይለስላሴ አመራር ስርም ሆነች በመንግሥቱ አሊያም በሌላ የመንግሥት ስርአት የኢትዮጵያ አቋም ያው ነው) ነበር ያሉት፡፡
ያኔ! መለስ ስለ ኢትዮጵያ የአፍሪቃ የነጻነት አርማነት ሽንጣቸውን ገትረው የተሟገቱበት ላይ፤ በተለይ «...አንድ የማንክደው ሀቅ አለ፤ ኢትዮጵያ በየትኛውም የመንግሥት አስተዳደር ስርአት ውስጥ ትሁን ለአፍሪካ ነፃነት ጠንካራ የሆነ አቋም ነው ያላት...›› ያሉት ድንቅ ነበር! እንኳንስ በታሪክ አጋጣሚ ኢትዮጵያን ወክለን በዓለም መድረክ ቆመን ቀርቶ፣ ኢትዮጵያዊ በመሆናችን ብቻ (ኢትዮጵያዊ የሆንን እና ነን ብለን ያመንን ሁሉ) እናስቀረው ብንል እማይቻለን፤ የኖረ፣ ኗሪና የሚኖር፤ ‹‹በውኑ ኢትዮጵያዊ መልኩን ወይስ ነብር ዝንጕርጕርነትን  ይለውጥ ዘንድ ይችላልን?›› ህያው ቃል የሚያረጋግጥ የኢትዮጵያዊ ማንነታችን እፁብ ድንቅ ፀጋ ነውና። ‹‹በዚያን ጊዜ ክፋትን የለመዳችሁ እናንተ ደግሞ በጎ ለማድረግ ትችላላችሁ።›› ኤር 13-23፡፡
የቀድሞው ጠ/ሚኒስትር  ኃ/ማርያም ደሳለኝ ደግሞ ‹‹የለውጡ አካል ለመሆን ስል ስልጣኔን በገዛ ፈቃዴ ለቅቄያለሁ›› ማለታቸው ያልተለመደ ከመሆኑ አንጻር ወይም ለገዛ ራሳቸው ታማኝ በመሆናቸው  ብቻ በአንድም በሌላም መልኩ ታሪካዊ ንግግራቸው ሆኖ ይቆጠር ይሆን ይሆናል - ውሎ ሲያድር። ‹‹ውሎ ሲያድር በታማኝነት የሚደራረበው ካብ ነው፣ ማሕበረሰብን የሚገነባው:  አንዱ በጽናት ባቆመው መሰረት ላይ ቀጣዩ በራስ በመተማመን በሚያስቀምጠው ጡብ፡፡›› ይላል ሳውዝ - “Society is built upon trust, and trust upon confidence in one another’s integrity.” (አንዱን ጥሎ አንዱን አንጠልጥሎ ሳይሆን፤ ሁሌ ከዜሮ መጀመር ሳይሆን Consistency  ...?) ኢመርሰንም ይኸው- ‹‹ለራስ የመታመን ልቦና የልዕለ ሰብእ ፀጋ ነው›› ይለናል -  «Self-trust is the essence of heroism.» ጊዜያችንን አሻግሮ ያስተዋለ እሚመስለው ‹‹ሁሉንም  ያማከለ / በወል ‹‹የደመረ›› ካልሆነ እና ምሉዕነት ከጎደለው - (የትኛውም ወይም ማንኛውም አይነት) በራስ መተማመን/ልበ ሙሉነት አደገኛ ነው።›› ያለው ደግሞ ቤዩሜንት ነበር - “All confidence which is not absolute and entire, is dangerous.”
(. . .የመድረክ  ትዕይንትን ትውስታ ካነሳን፤ ከዓመታት በፊት፡ አራት ኪሎ አደባባይ ቆመው፣ አንዲቷን ንግግር ብቻ እየደጋገሙ የሚጮሁትን እብድ ሰውዬ፤ በ‹‹የኮከቡ ሰው›› ተውኔት ውስጥ ውክልና አግኝተው በመድረክ ላይም አይተናቸው ነበር ...  ‹‹አቡነ ሰላማ፤ ኢትዮጵያን ‹‹አንቺ የሰፊ ጠባብ ነሽ!›› አሏት! ግባ ፖለቲካ! ግባ ፖለቲካ!  ግባ!  ግባ! ግባ!  እኔ  የለሁበትም!››) ... ድንቄም የሉበትም ... እ?! 
ስንቀጥል...
በሰው ዘር ታሪክ፤ በመጀመሪያ ደረጃ የሚጠራው የመናገርና ሀሳብን የመግለጽ ነጻነት (ዛሬም ድረስ ምሉዕነት እንደጎደለው ቢሆንም እንኳ) በየሀገራቱ ዜጎች በልዩ ልዩ ክህሎት ዘርፍ ባበረከቱት ክቡር ሰማዕትነት በህግ ደረጃ እስኪጸድቅና በታደሉት/ባደጉት ሀገራትም በተግባር እውን እስኪሆን ድረስ ብዙ ዘመናት ተቆጥረዋል፡፡ ብዙዎች መስዋእትነት መክፈል ነበራቸው፤ እየከፈሉም ነው፡፡ ከጥንት ጀምሮ - ለምሳሌ ሶቅራጥስ በአቴና አደባባይ ቆሞ ዜጎች የየልቦናቸውን እውነት ይፈትሹና ይጨብጡትም ዘንድ ግራና ቀኝ እያዟዟረ፣ የታቹን ከላይ በስልት እያገላበጠ Socratic irony በማጠየቁ፤ ሰዎችን ለአመጽ በማነሳሳት ወንጀል ተከስሶ በኩባያ መርዝ መሞት ነበረበት፡፡ ፍርዱን በጸጋ ተቀብሎ፣ ያንን መራራ ሄሜሎክ መርዝ ጨልጦ ከመሰናበቱ በፊት ተናገረ ያሉት . . . Athena is like a stubborn horse, God gave me the state of the stinging fly - ‹‹አቴና፤ ከተዘረፈጠበት መነሳት እንዳቃተው ‹ከብት› ነች፤ ፈጣሪ ለኔ ያደለኝ የነዳፊውን ትንኝ ድርሻ ነው፡፡›
በኛ ሀገር በ17ኛው ክ/ዘ  እውነትን በጥልቅ ለመመርመር፣ ‹ከሰው መንጋ ተነጥሎ› በዋሻ የተጠለለውና ይህንኑም፤ ‹‹በዋሻ ውስጥ ብቻዬን በኾንኹ ጊዜም በመንግሥተ ሰማያት የምኖር ይመስለኝ ነበር፡፡ ስፍር ቁጥር የሌለው ክፋታቸውን አውቄ ከሰዎች ጋር መኖርን ጠልቻለሁና›› ነበር ያለው ኢትዮጵያዊው ፈላስፋ ዘርዐ ያዕቆብ፡፡ ዴሞስቴን ደግሞ ኮልታፋ አንደበቱን ለማረቅ ነበር በዋሻ የተጠለለው፡፡ ጠጉሩን ሰው ፊት እንዳያቀርበው አድርጎ መድምዶ፣ መልሶ እስኪያድግለት ራሱን ለመነጠል ማዕቀብ ጣለበትና፤ ጠጠር ምላሱ ላይ እያደረገና ጮክ ብሎ እየለፈለፈ ኮልታፋነቱን ገራው። ጠጉሩ ሲያድግና ምላሱ ሲጠብቅለት አንደበተ ርቱእ ሆኖ ከዋሻው ወደ ከተማ ብቅ አለ፡፡ በአቴና አደባባይ ቆሞም ለሕዝቡ ስለ ሀገር ጉዳይ ወተወተ። ግና ሰሚ አጣ፡፡ እንግዲያውስ እንዲህ ላድርግ አለ ዴሞስቴን ...ተረት ላውራላቸው...ንግግሩን ከመስማት ይልቅ እርስበርሳቸው እየተንሾካሾኩ ፀጥታውን ያወኩትን ሰዎች፤ ‹‹የአቴና ሕዝብ ሆይ፤ ተረት ላውራላችሁን?›› አላቸው፡፡ እህኔ ያ ሁሉ ረብሻ ድንገት በዝምታ ተዋጠ፡፡ ጠቃሚ ንግግሩን ለመስማት የታከታቸው ሰዎች፣ አሁን ግን ፀጥ እረጭ ብለው ተረቱን በአንክሮ ማድመጥ ጀመሩ . . .
ባለ አህያና አህያ ተከራይ ነበሩ፤ ‹‹ማለዳ ከመንደራቸው ተነስተው  ሩቅ መንገድ ሲሄዱ ውለው እኩለ ቀን ሲሆን ጭው ካለ በረሀ ላይ ደረሱ። አህያ ተከራይ ምሳውን መብላት ፈለገና ከአህያዋ ወርዶ ጥላ ቦታ ቢፈልግ ቢፈልግ አጣ፡፡ ከዚያም በቃ አህያዋ ጥላ ስር ሆኜ ብበላስ ብሎ ሊቀመጥ ሲል፤ ባለ አህያው ቀድሞት አህያዋ ጥላ ስር ቁጭ አለ። ከዚያም በአህያዋ ጥላ የይገባኛል መብት ብርቱ ሙግት ጀመሩ፡፡ መግባባትም ተሳናቸው፡፡ አህያ ተከራይ፣ አህያዋን ከተከራየውህ ጥላዋም የኔው ነው ሲል፤ ባለ አህያው ደግሞ አህያዋን እንጂ ጥላዋን አላከራየውህም አለ፡፡ በዚህም ዱላ ቀረሽ ክርክር ገጠሙ . . . ዴሞስቴን ላፍታ ንግግሩን ገታ አደረገና ወደ ሕዝቡ ትክ ብሎ  እያየ፤ ተረቱን ልቀጥልላችሁን? ሲል ጠየቀ፡፡ የታሪኩን ፍጻሜ ለመስማት የጓጓው ወፈ ሰማይ ሕዝብ ምላሽ አስተጋባ ‹‹አ.....ዎ!!!›› ...
የፊደል ካስትሮ መሀረብ
. . . እናም ‹‹ከፊደል ካስትሮ ንግግሮች ከራሱ ሀገር ባለፈ ለኛም በሌሎች ሀገራት ለምንኖር ሕዝቦችም የምንቀስመው ለእድገትና ስልጣኔ የሚተርፍ ፍሬ ነገር አለው!›› ብለው በተነሱ ምሑራን አማካኝነት ነበር፤ ኩባን ለረዥም ዘመን በመሪነት ያስተዳደሯት የመሪው ንግግሮች ተሰባስበው FIDEL CASTRO SPEAKES በሚል አርእስት በፔሊካንና ፔንጉዪን መጻሕፍት አሳታሚዎች በዩናይትድ ስቴትስና እንግሊዝ ውስጥ ከአስርት አመታት በፊት ለህትመት የበቃውና፣ ከላቲን አሜሪካ እስከ ኒው ዚላንድና አውስትራሊያ ድረስ በስፋት ተሰራጭቶ የነበረው፡፡
በፈረንጆቹ ሚሌኒየም ዋዜማ፣ የዓለም መሪዎች በአንድ አዳራሽ ውስጥ ተሰባስበው፣ አጫጭር ንግግር እንዲያደርጉ በክብር ተጋበዙ፡፡ ካስትሮ ተራ ደርሷቸው ወደ መድረክ ሲወጡ፣ ታዳሚዎቹ ሁሉ በሳቅ አውካኩ፡፡ እንግዲህ ያን የሰአታት ርዝመት የሚወስድ ንግግራቸውን ሊዘበዝቡት ነው  በሚል። መነጋገሪያው ፑልፒት ላይ የተቀመጠችው ሰከንድ ቆጣሪ፣ እያንዳንዱ መሪ ከተሰጠችው የአምስት ደቂቃ ጊዜ እንዳያልፍ ደቂቃው ማብቃቱን የምታመለክትበት መብራት ተገጥሞላት ነበር። ካስትሮ መድረክ ላይ እንደወጡ የመሪዎቹን ሽሙጥ ዙሩን አከረሩት፤ ከኪሳቸው መሀረብ አውጥተው፣ ገና ያልበራችውን አምፖል ሸፈኗት። በአዳራሹ ውስጥ ሌላ የሳቅ ሁካታ አስተጋባ፡፡
‹‹ተረት ተረት...›› ዴሞስቴን ግን በሀዘን ቁልቁል እንዳቀረቀረ ነበር፡፡ አደባባዩን ሞልተው የአህያዋን ተረት እንዲጨርስላቸው ጓጉተው ዓይኖቻቸውን በሚያቁለጨልጩት ሕዝብ ፊት ቆሞ፣ ካቀረቀረበበት ቀና ብሎ በትዝብት እያያቸው፤ ‹‹እናንት የተወደዳችሁ የሀገሬ ሕዝብ ሆይ!›› አለ ‹‹ስለ አንገብጋቢው የሀገራችን ጉዳይ ንግግር ሳደርግ ትእግስት አጥታችሁ ትንጫጫላችሁ፤ ለእንቶ ፈንቶ ወሬና ተረት ተረት ሲሆን ግን... !!!››
‹‹የመሰረት...›› ለውጥ የተፈጥሮ ህግ መሆኑን ከማመኑ ጎን ለጎን፤ እንዲህ ዛሬ ላይ ሆነን ስናስበውና፣ ወደ ኋላ ተመልሰን እምንዘግነውን ያቻምና የአበውን ስንቅ ስንባጅም፤ ሀገር በጭንቅ በተያዘችበት ጊዜ ሁሉ የወል መፍትኼ በመሆን የሚያግባባንና የዘወትር የማንነታችን ቀለም መሆኑ የራሳችንን ተፈጥሯዊ መልክ ከሚያስረግጥልን ሀቅ መሳ፤ በምዕራባዊያኑ የታሪክ ጸሐፍትም ‹‹ያመዛኙ አዛውንት ኢትዮጵያዊያን አይነተኛ ጠባይ›› typical attitude of many older Ethiopians ተብሎ የሚጠቀስልንን፣ አያት ቅድማያቶቻችን ያቆዩልን - ያወረሱንን እሴታችንን በዘላቂነት ማስቀጠሉ አማራጭ የሌለው መላ አይሆንም ትላላችሁ!?. . . ይኼ መወድስ ከተቸራቸው ክቡር ዜጎች መካከል፤ ባንድ ወቅት፡ ከግማሽ ምእተ አመት በፊት፤ እናት ሀገራችን በሁለት ጽንፍ ስትናጥ፤ በወቅቱ በሚኒስትር ማእረግ ተሹመው የነበሩቱ ኢትዮጵያዊ ‹የሀገር መሪ ወ አማካሪ› (ወላጅ አባታቸው መስኮብ የነበሩ፣ የተመራመሩ፣ በእንስሳ ኮሜዲያ/ፋቡላ ማውራት የዠመሩ) ብላታ ግርማቸው ተ/ሐዋርያት፤ ጨርጨር ላይ ለተሰየመ ጉባዔ፤ ከራስ ይልቅ ያገርን ጉዳይ ማስቀደምን በአጽንዖት ባሳሰቡበት ‹ህያው› እናም ዘላቂ፣ ተስፋ ፈንጣቂ፣ ዘመን አድማቂ . . .ወዘተ.  ንግግር እናሳርግ... ‹‹ ልዩነቶቻችን የየራሳችን ጉዳዮች ናቸው፤ ሀገራችንን በተመለከተ ግን ሁላችንም አንድ/እኩል/የወል ምሉዕ ነን/እንሁን፡፡››

Read 1062 times