Saturday, 18 August 2018 09:43

መፍልስት!

Written by  አብይ ተስፋዬ አሳልፍ (አተአ)
Rate this item
(6 votes)

 አንድ ቀን አስመራ ስለመሄድ አቅዳለሁ። እቅዴ መንታ ሀሳቦች የያዘ ነው፡፡ እትዬ ዝማምንና ልጆቻቸውን ማግኘት፡፡ እንደ ልማዴ ቀዝቃዛ ፔፕሲዬን እየቀመስኩ ሀሳቤን ማላመጥ እጀምራለሁ፡፡ ድሮ ድሮ የተለመዱ አይነት ሰላማዊ ጦርነቶች ሰፈራችን ነበሩ፡፡
… ጓደኛሞቹ!
ባደግሁበት ሰፈር፣ በልጅነቴ ጎረቤታችን የነበሩ አቶ ላዕከ የሚባሉ ሰው ነበሩ፣ በጣም አራዳ ናቸው ቢባሉም ሁሌም የማያቸው ሲጃራቸውን እያንቦለቦሉ ጠጅ ቤት ሲገቡ ነው (በፊት ወታደር የነበሩ ጡረተኛ ናቸው!)፡፡ በልጅነቴ አራዳ ማለት ጠጅ የሚጠጣ ነው ብዬ ማሰብ የጀመርኩት ያን ጊዜ መሆኑን የተረዳሁት አሁን ሳስበው ነው፡፡ የኔ አባት ደግሞ ከሰፈሩ በጣም ጉልበተኛውና ዘናጩ፣ የሁለት ልጆች አሳዳጊ ላጤ ነው (እናታችን ከሞተች ቆይታ ነበርና!)፡፡ ሁለቱ ጎረቤታሞች ጓደኛሞች ናቸው፡፡ አሁን ስገምት ጓደኝነታቸው ከመፈራራት የመጣ ይመስለኛል፡፡ ጉልበትና ብልጠት ይከባበራሉ ብዬ አስባለሁ፡፡
የጋሽ ላዕከ ሚስት በጣም ውብና ከሁሉም ተግባቢ ስለሆኑ ባለቤታቸው በጣም ነው የሚቀኑባቸው፣ ሲወጡም ሲገቡም ከሚስታቸው አጠገብ አይታጡም። ባለቤትየው ብዙ ጊዜ ከቤታቸው አይጠፉም፡፡ ሰውየው ወጣ ካሉ ደግሞ ሚስትየው አይያዙም፡፡ ንፁህና ሽቶ ሽቶ የምትሸት ወተት የመሰለች ነጠላቸውን ደርበው ላጥ ይላሉ፡፡ ቀይና ቆንጅዬ ናቸው፡፡ በመንገድ ሲያልፉ ከልጆች መሃል ጎተት አድርገው ጉንጮቼን የሳሙኝን እስካሁን አስታውሰዋለሁ፡፡ እናም ቀይ ሴቶች ሁሉ እትዬ ዝማምን እንዳስብ ያደርጉኛል፣ ደግሞ እንደምናውቀው ቀያይ ሴቶች ያምራሉ!
… ባለ ቮልሱ አባቴ!
አንድ የሆነ ብሩህ ቀን፣ አባቴ፣ እኔን ጋቢና አስቀምጦኝ፣ ቮልሱን እያሽከረከረ ከነጋሽ ላዕከ ደጅ ሲደርስ ያቀዘቅዛል፡፡ ወደ አጥሩ ጠጋ ብሎ አካባቢውን ከቃኘ በኋላ አንድ ጊዜ ክላክስ አድርጎ ያቆማታል፡፡ ምን ፈልጎ እንደሆነ ገና ሳይገባኝ በፊት የጋሽ ላዕከ ባለቤት ነጭ ነጠላቸውን ዘቅዝቀው እንደለበሱ ብቅ ቢሉ ገረመኝ፡፡ አባቴን ሲያዩ መቼም በደስታ ይቅለሰለሳሉ (ለምን እንደሆን አላውቅም!)   
እናም በሩ አጠገቡ እንደቆሙ አባቴ ጮክ ብሎ፤  ‹‹ማቆም ክልክል ነወይ?!›› ይላቸዋል፤ እየሳቀ ‹‹..ሃሃሃ...››
እሳቸውም እየሳቁ (ፈገግታቸውና ጥርሳቸው ያምራል!)፤ ‹‹ደሞ በደጃችን ማን ይከለክልሃል!›› ይሉታል፡፡
‹‹ወዴት ልትሔጂ ነው ልሸኝሽ!››
‹‹እዚህ ስድስት ኪሎ ምን የመሰለች ልጅ ተገደለች። ሬሳዋን ወደ ናዝሬት ልንልክ ነው፡፡ ምፅ!››
‹‹ምን ሆና ሞተች?!››
‹‹እወይ! ናይ ተማሃሪ ነገር!  ….  ምፅ! መሪር ሃዘን ኮይኑ፡፡ አንዱ ጎረምሳ ገደላት፡፡ የዩኒቨርሽቲው ተማሪ ነበረች፡፡ ሹሻን ጊላ ትባላላች፤ አባቷ የአገሬ ሰው ነበር፡፡ ሬሳ ልሸኝ ነው--›› ቀይ ፊታቸው ላይ ሃዘን እንደ ደመና ይከብዳል፡፡ ‹መዓረይ! መዓረይ!› እያሉ ዝናቡን ሳያዘንቡት በፊት አባቴ ወሬውን ይቀጥላል፡፡ (ቢጢቆ ማስታወሻ፡ - በኋላ እንደተረዳሁት ሹሻን ጊላ ኤርትራዊት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ ነበረች። ኬኔዲ ላይብረሪ በር ላይ ሃውልት የተገነባላት እሷ ናት። አፍቅሬሻለሁ የሚል ልጅ (ተማሪ) በስለት ወግቶ የገደላት ልጅ። (ደቦ ስብስብ መፅሃፍ ላይ - ከገፅ 253 ጀምሮ፣ በበላቸው መኩሪያ (ዶ/ር) የተጻፈውን ሙሉ ታሪክ ሊያነቡ ይችላሉ!) እናም አሁን አሁን የኤርትራ ሴቶች በሙሉ የፍቅር ምልክት የሚመስሉኝ ለዚህ ነዋ እላለሁ በልቤ፡፡ የበዓሉን የልብወለድ ገፀባህሪ ፊያሜታ ጊላይና እውነተኛዋን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሰማእት ሹሻን ጊላን ሳስብ፡፡)
‹‹አይይ! ያሳዝናል፡፡ ግቢና ልሸኝሻ! … እኔም ወደአራት ኪሎ እየሄድኩ ነው፡፡››
ቀና ብዬ ሳይ ባለፈው ሳምንት ጋሽ ላዕከ በቁራጭ ቆርቆሮ፣ በተወላገደ ፅሁፍ የለጠፉት ‹‹ማቆም ክልክል ነው!›› የሚል ጽሁፍ ቀለሙ እየለቀቀ ነው፡፡ (በሰፈሩ ካለአባቴ በስተቀር መኪና የለምኮ!) ወይም ተላላፊ ሌላ መኪና እንኳን በሰፈራችን እምብዛም ቆሞ አይቼ አላውቅም። አንዳንድ ቀን እዚህ አካባቢ የሚመጣው አባቴ ብቻ ነው፡፡ (ምናልባት ለሰፈር ጋሪዎች ይሆናል ብዬ አስባለሁ!)
‹‹ማቆም ይከለከላል እንዴ ደግሞ? በሰፈራችንም መሄጃ ልታሳጡን ነው፡፡ ይልቅ ግቢ!›› ይላል አባቴ ወደ ፅሁፉ እየጠቆማቸው፡፡
‹‹ቂ ቂ ቂ ቂ….›› ደስ የምትል ሳቃቸውን ይስቁና ‹‹መቼም አንተ ጨዋታውን ታውቅበታለህ። ልቅሶማ ከሴቶች ጋር ነው ምሔድ፡፡ አደይ አስኳሉ ዝብሐላ ትዝክረን! ምስአን እየ ዝከይድ።›› ይሉታል አባቴን፡፡
‹‹እውነቴን እኮ ነው! ደግሞ ጤናውን ከሰጠን ማቆም ጥሩ ነው ብዬ ነው’ንጂ! … ሃሃሃሃ … ጥሩ ነው በውይይት እየተወያያችሁ ሒዱ--›› (ምን ማለቱ ነው እላለሁ በልቤ! ውይይቷ ታክሲዋ መሆኗን አውቂያለሁ።)
‹‹ቂ ቂ ቂ ቂ . . . . . ወይ አንተ ሰው!›› በነጠላቸው ከንፈራቸው እያሻሹ አካባቢውን ይቃኛሉ፡፡
በዚህች ደቂቃ ጋሽ ላዕከ ከእትዬ አዛሉ ጠላ ቤት ዘለው እየወጡ ጮክ ብለው፤ ‹‹ምንድነው ያልሽው?!›› ሲሉ ሚስታቸው ላይ ያፈጡባቸዋል፡፡
‹‹እውይ! ወይእነ ግዲ!›› ይላሉ እትዬ ዝማም፡፡
አባቴም ‹‹እዚህ አካባቢ መኪና ማቆም ክልክል ነው! ትለኛለች›› አላቸው፡፡
በጣም ገረመኝና ወደ ጋሽ ላዕከ ገልመጥ ብዬ ‹‹ኸረ እንደሱ አላሉ. . .›› ብዬ አፌን ስከፍት ከየት የመጣ እንደሆን የማይታወቅ ጥፊ ጧ! ብሎ ጎንጬ ላይ ፈነዳ፡፡ ዘወር ብዬ አባቴን ባየው፣ ፊቱን አዙሮ በመስኮት ከጋሽ ላዕከ ጋር ወሬውን ቀጥሏል። ሆሆይ! ምን አጥፍቼ ነው! ብዬ ትንፋሼን ዋጥ አድርጌ ቁጭ እላለሁ፡፡
‹‹እንደሱ ነው ያለችው እንዴ! ደሞ አንተ ትከለከላለህ ወይ!›› ይላሉ ጋሽ ላዕከ፤ ብልጣ ብልጥ ፊታቸውን እያጣመሙ፡፡
‹‹በል ና ግባ ጠጅ ልጋብዝህ ›› ይላል አባቴ ቮልሷን እያስጮኸ፡፡ ዷ ዷ ዷ ዷ ዷ ዷ …. ‹‹ና ግባ! ፈጥኖ ደራሽ ጠጅ ቤት እንሒድ!…››
እናም እሳቸው ቢገቡም ባይገቡም (ብዙ ጊዜ ወደ ቤታቸው ነው የሚገቡት!) እኛ ቮልሳችንን ዷ ዷ ዷ ዷ ዷ ዷ እያደረግን ከሰፈሩ እንጠፋለን፡፡
ከዚያም አባቴ ምክሩን ይጀምራል፡፡ ‹‹ጌታመሳይ! ይሔ ትልቅ ሰው ሲያወራ ጥልቅ ማለትህን ተው ብያለሁ፣ ያድግብሃል! …. ሁለተኛ ብትደግም ነግሬያለሁ!….›› መአት ምክርና ቁጣ እየተቀበልኩ በፔፕሲ አወራርዳለሁ፡፡ እናም አሁን አሁን ፔፕሲ ስጠጣ ምክሩን አስባለሁ፡፡ በሃሳቤ ቃላቱ ይጮሃሉ ‹‹…ይሔ ትልቅ ሰው ሲያወራ ጥልቅ ማለትህን ተው ብያለሁ፣ ያድግብሃል!…››
… ማጣሪያ!
ሌላ ቀን ደግሞ፤ ጋሽ ላዕከ ይጠሩኝና ከኪሳቸው ደስታ ከረሜላ አውጥተው ይሰጡኛል፡፡ ከዚያ በመቀጠል ‹‹እስቲ አባትህ ከቤት ካለ ቀስ ብለህ እይና ንገረኝ! ታዲያ እኔ እንደላክሁህ ለማንም እንዳታወራ! ስትመለስ ደግሞ ሌላ እሰጥሃለሁ፡፡›› ይሉኛል፡፡
‹‹መኪናውን ግን አለች!›› እላለሁ፤ ከጨዋታዬ ላይ ላለመነሳት፡፡
‹‹አይ እርሱን ተወው! … ቶሎ እይና ንገረኝ!››
ከረሜላዬን እየመጠጥኩ ወደ ቤት እሮጣለሁ። እናም ደርሼ እንደተመለስኩ ‹‹የለም›› ካልኳቸው ወደ ጠላ ቤት ወይም ወደ ሌላ ቦታ ፈጠን ብለው ይገባሉ፣ ‹‹አለ!›› ካልኳቸው ደግሞ እያልጎመጎሙ ወደ ቤታቸው ይመለሳሉ፡፡ ከዚያም በደቂቃዎች ልዩነት እየተመለሱ ደግመው፣ ደግመው … ሔዷል! እስክላቸው ድረስ ይልኩኛል፡፡
አንድ ቀን ብይ እየተጫወትኩ እያለ ጋሽ ላዕከ ከባለቤታቸው ጋር በአጠገባችን ሲያልፉ ‹‹ጋሽ ላዕከ!…›› ብዬ ጠራኋቸውና፤ ‹‹… አባዬ ቤት የለም!›› አልኳቸው፤ ከረሜላ ቢሸልሙኝ ብዬ፡፡
ኮስተር ብለው አዩኝና፤ ‹‹…ማን ጠየቀህ ወሬኛ!›› አሉና ክፉኛ ገላመጡኝ፡፡ (ገረመኝ!) ኩስስ ብዬ ጓደኞቼን ሳያቸው፣ ሁሉም ፈገግታ ፊታቸው ላይ ተረጭቷል፡፡ በጣም አፈርኩ! ቆይ ሁለተኛ አልላክላቸውም አልኩ በልቤ፡፡
እትዬ ዝማም በማስተዛዘን ያዩኝና ከባላቸው ላይ እያፈጠጡ፤ ‹‹ኢሂ ደኣ እንታይ ግበር ይብልዎ አለው ነዚ ምንም ዘይፍልጥ ቆልዓ? … ምፅ! … ሆሆይ!››
… ሌላ ማጣሪያ!
ሌላ ቀን ጠሩኝና እያባበሉ እንደተለመደው ላኩኝ! እናም ከረሜላዬን ከእነ ልጣጩ እያሻሸሁ ልክ ቤት እንደገባሁ አባቴ አፈፍ አድርጎ ያዘኝ፡፡ ለካስ ለምን እንደምመላለስ አውቋል፡፡
ቀጥሎም ‹‹ እየው አንተ ዝንጀሮ፤ ቀጥ ብለህ ትሔድና አባዬ የለም! ትለዋለህ፡፡›› አለኝ፡፡ ለካ መጋረጃውን ገለጥ አድርጎ በመስኮት እያጮለቀ ወደ ውጪ ያየኛል! ‹‹… ደግሞ እያየውህ ነው!›› ይዝትብኛል፡፡ ምን አጥፍቼ ይሆን እያልኩ አስባለሁ፡፡
ተመለስኩና እየፈራሁ ለጋሽ ላዕከ ድምፄን ለስለስ አድርጌ፤ ‹‹….የለም!›› አልኳቸው፡፡ ደግሞኮ አባቴ አትዋሽ ይለኛል፣ ራሱ ሲፈልግ ደግሞ ውሸት ተናገር ይለኛል፡፡ ቆይ ማታ እጠይቀዋለሁ እያልኩ አስባለሁ። ጋሽ ላዕከ እየሮጡ ከጠላ ቤት ሲገቡ፣ አባቴ ደግሞ ለጥቆ ከቤት ወጥቶ በኩራት እየተጀነነ ይሄዳል፡፡ ወደ ጎረቤት። ለምን ይሆን? እያልኩ ነገሩን አስባለሁ!
… ዛሬ!
እናም አሁን በዚህች ሰዓት ፔፕሲዬን እየጠጣሁ ብቻዬን እፈግጋለሁ፡፡ እትዬ ዝማም ከዚህ ሃገር ሲሄዱ፣ ጎረምሳ ጎረምሳ ሁለት ሴት ልጆች ነበሯቸው፡፡ አንዲቷ እንዲያውም እንደ አባቴ ብስል ቀይ ነበረች፡፡ አባቴና ጋሽ ላዕከ አሁን በህይወት ስለሌሉ ብቸኛው መንገዴ እትዬ ዝማምን ማግኘት ነውና ወደ አስመራ እጓዛለሁ። እንደ ልጅነት አኗኗራችን ከሆነ ምናልባት ፍለጋዬም ይሳካ ይሆን ይሆናል እያልኩ አስባለሁ። ሌላ እህት ላገኝ እችላለሁ፡፡ (ካልሆነ ሌላ ፊያሜታ ጊላይ፣ ፅብቅቲ ጓል አስመራ!)
(መፍልስት፡- የስርቆሽ በር፣ መlለኪያ፣ ስርጥ ጎዳና፣ ስላች መንገድ…! - ኪዳነወልድ ክፍሌ፣ መፅሐፈ ሰዋሰው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ!)


Read 3061 times