Print this page
Saturday, 18 August 2018 09:39

ፕሬዚዳንት ኢሣያስ አፈወርቂ አማራ ክልልን ይጎበኛሉ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(8 votes)

 የሀገረ ኤርትራ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በቅርቡ በአማራ ክልል ይፋዊ ጉብኝት እንደሚያደርጉ የታወቀ ሲሆን ግብዣው በአማራ ክልላዊ መንግሥት የቀረበ መሆኑ ተገልጿል፡፡
ሰሞኑን ከተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅት ጋር ለመደራደር አስመራ የተጓዘው በአማራ ክልላዊ መንግሥት የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ አቶ ንጉሡ ጥላሁን የሚመራው ልዑክ ከሀገሪቱ ፕሬዚዳንት አማካሪ ከአቶ የማነ ገ/አብ ጋር ባደረገው ውይይት ላይ ፕሬዚዳንት ኢሣያስ የአማራ ክልልን እንዲጎበኙ ያቀረበው ግብዣ ተቀባይነት ማግኘቱ ታውቋል፡፡
ከፕሬዚዳንቱ ይፋዊ ጉብኝት አስቀድሞም በአማራ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ የሚመራ ልዑክ ኤርትራን እንደሚጎበኝ የክልሉ የመንግሥት ኮሚኒኬሽን ኃላፊ አቶ ንጉሡ ጥላሁን ገልፀዋል፡፡
የአማራ ክልላዊ መንግሥት ልዑካን ቡድን፣ ላለፉት 8 ዓመታት ኤርትራ ተቀምጦ የትጥቅ ትግል ሲያደርግ ከቆየው የአማራ ዲሞክራሲያዊ ኃይሎች ንቅናቄ (ኢዴኃን) ጋር በበርካታ ጉዳዮች ላይ ውጤት የተገኘበት ድርድር ማካሄዱን አቶ ንጉሡ ጥላሁን አስታውቀዋል፡፡ በድርድሩ መግባባት ላይ ባልተደረሰባቸው ነጥቦች ላይ በቀጣይ ተጨማሪ ድርድር እንደሚካሄድም ተገልጿል፡፡
ባለፈው ሐሙስ የኤርትራ የውጭ ጉዳይ ም/ኃላፊ በተገኙበት በተካሄደው የሙሉ ቀን ድርድር፤ “ኢዴሃን” የትጥቅ ትግሉን በመተው ወደ ሃገር ውስጥ ገብቶ በሰላማዊ መንገድ ለመንቀሳቀስ ከውሳኔ ላይ መድረሱ ታውቋል፡፡
የንቅናቄው ሊቀ መንበር አቶ ተፈሪ ካሳሁን ከድርድሩ በኋላ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፤ “ኢዴኃን ወደ ሃገር ውስጥ ገባ ማለት የአማራ ህዝብ ጥያቄ ተመልሷል ማለት አይደለም፤ አሁን ሰላማዊ ትግል ማድረግ የሚያስችል ሁኔታ በመፈጠሩ ነው ወደ ሃገር ቤት ገብተን የምንታገለው” ብለዋል፡፡
የኤርትራ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በአማራ ክልል በሚኖራቸው ቆይታ በበርካታ ኤርትራውያን የሚኖሩባቸውን ባህርዳር እና ጎንደር በዋናነት ይጎበኛሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
የኤርትራው ፕሬዚዳንት በጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ግብዣ መሰረት፤ ከ20 ዓመት በኋላ በቅርቡ ኢትዮጵያን መጎብኘታቸው የሚታወቅ ሲሆን ይህም የፍጥጫው ግድግዳ ፈርሶ እርቅ በመውረዱ ለአገራቱና ለመሪዎቹ ዓለም አቀፍ ዕውቅናና አድናቆትን እንዳስገኘላቸው ይታወቃል።


Read 9968 times