Saturday, 11 August 2018 11:13

“እርስ በርስ የምንናቆርበት ጦርነት ፍፃሜ አግኝቷል”

Written by 
Rate this item
(3 votes)

 · ያለ ዶ/ር ዐቢይ፤ የደቡብ ሱዳን ስምምነት አይታሰብም
   · የውጊያ ቀጠናዎችን የልማት ጣቢያ እናደርጋቸዋለን
   · ሁለቱን አገራት የሚያገናኝ የባቡር ሃዲድ ይዘረጋል

     ሚስተር ጄምስ ፒተር ሞርጋን፣ በኢትዮጵያና በጅቡቲ የደቡብ ሱዳን አምባሳደር ናቸው፡፡ የምስራቅ አፍሪካ በይነ መንግስታት (ኢጋድ) እና የአፍሪካ ህብረት እንዲሁም የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን (UNECA) ተወካይ በመሆንም እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡ በእርስ በርስ ጦርነት ለዓመታት ስትታመስ የቆየችው ደቡብ ሱዳን፤ በመሪዎቿ ስምምነት አለመድረስ የተነሳ ማጣት በመቶ ሺዎች የሚሰሉ ዜጎቿን ለስደትና እንግልት ዳርጋለች፡፡ ባለፈው ሳምንት ግን ታሪክ የተለወጠ ይመስላል፡፡
የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ሳልቫኪርና ተቃዋሚያቸው ዶ/ር ሪክ ማቻር ጦርነት አቁመው፣ በአገራቸው ላይ በሰላም ለመስራት በካርቱም ስምምነት ተፈራርመዋል። ስምምነቱን ተከትሎ በኢትዮጵያ የሚገኙት አምባሳደሩ ትላንት ረፋድ ላይ ለአገር ውስጥና ለውጭ አገር ጋዜጠኞች በደቡብ ሱዳን ኤምባሲ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡ በመግለጫው ላይ የተገኘችው የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ፤ ከዚህ ቀደም የተደረጉት ስምምነቶች ለምን እንዳልተሳኩ፣ የአዲሱ ስምምነት አስተማማኝነት ምን ያህል እንደሆነ፣ በኢትዮጵያና በደቡብ ሱዳን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ዙሪያና ሌሎች ጥያቄዎች አንስታ አነጋግራቸዋለች፡፡


    ኢትዮጵያ ሲመጡ የመጀመሪያዎ ነው ወይስ ከዚሀ በፊት ያውቋታል?
ኢትዮጵያ ስመጣ የመጀመሪያዬ ነው፤ ኢትዮጵያን ሳውቃት ግን የመጀመሪያዬ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያን የማውቃት ባልሳሳት በ1974 ዓ.ም ነበር፡፡ ያን ጊዜ እድሜዬ ምናልባት ከ8-10 ዓመት ባለው ውስጥ ይሆና።፡ ገና የመጀመሪያ ደረጃ ት/ቤት ተማሪ ነበርኩኝ፡፡ ንጉስ ኃይለሥላሴ ጁባን ለመጎብኘት ሲመጡና ሳያቸው የመባረክ ስሜት ነበር የተሰማኝ። ከኤርፖርት እስከ ጁባ ስታዲየም ድረስ ነበር አቀባበል ያደረግንላቸው፡፡ እስካሁን ድረስ ከውስጤ ያልጠፋውና የመሰጠኝ የንጉሠ ነገሥት ኃይለሥላሴ አለባበስ ነው፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ነው ኢትዮጵያን ማወቅ የጀመርኩት፡፡ ይሄ ደግሞ በጣም ረጅም ጊዜ ነው፡፡ ሆኖም ከጃንሆይ እስከ ቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ድረስ የነበሩት የኢትዮጵያ መሪዎች ሲደግፉንና ሲረዱን ነው የቆዩት፡፡ በዚህ ምክንያት ኢትዮጵያን በደንብ እናውቃታለን። እዚህ በመምጣቴ ደስተኛ ነኝ፡፡ ቤቴ እንዳለሁ ይሰማኛል፡፡ የኢትዮጵያ የተለያዩ ብሔረሰቦች ዳንሶች ደስ ይሉኛል፡፡
የዛሬው ጋዜጣዊ መግለጫ ዓላማው ምንድነው?
ዋና አላማው ደቡብ ሱዳን በመሪዎቹና በተቃዋሚዎቹ ምክንያት የእርስ በእርስ ጦርነት ውስጥ ገብተን፣ ሰላም አጥተን ከርመናል፡፡ ይህንን ችግር ለመፍታትና አገራችን ወደ ሰላም እንድትመጣ ደግሞ ኢትዮጵያ ብዙ ደክማና ብዙ ጥረት አድርጋ፣ በመጨረሻም ፕሬዚዳንት ሳልቫኪርና ተቃዋሚው ምክትላቸው ዶ/ር ሪክ ማቻር ስምምነት ላይ ደርሰው፣ ባለፈው ሳምንት ጦርነት ለማቆምና ወደ ሰላማዊ መንገድ ለመምጣት ካርቱም ላይ ስምምነት ተፈራርዋል፡፡ ይህንን ትልቅ ስኬት ለኢትዮጵያና ለሌሎች ዓለም አቀፍ ሚዲዎች ለማብሰርና ኢትዮጵያን ለማመስገን ነው ጋዜጣዊ መግለጫው የተዘጋጀው፡፡ ለዚህ የእርስ በርስ ጦርነት ማብቃት የወቅቱ የኢጋድ ፕሬዚዳንትና የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ከፍተኛ ስራ ሰርተዋል፤ እናመሰግናል። በቀጣይ ይህንን ስምምነት በጁባም በአዲስ አበባም በደማቅ ሥነ ስርዓት እናከብረዋለን፡፡
መቼ ነው የሚከበረው?
በቅርቡ ይሆናል፡፡ አሁን ስምምነቱን ያፈራረመው ቡድን አንዳንድ ሞዳሊቲዎችን በመጨረስና የጊዜ ፍሬሙን በመስራት ላይ ይገኛል፡፡ ያንን ሰርተው ሲጨርሱ በዚህ ወር አጋማሽ ወይም በወሩ መጨረሻ በደማቅ ሁኔታ በማክበር፣ ደስታችንን ለመላው አፍሪካና ለመላው ዓለም ማሳየት እንፈልጋለን፡፡
በአገራችሁ ላይ ሰላም ለማስፈን በተለያዩ ጊዜያት የተለያዩ ስምምነቶች ተፈራርማችሁ ሳይሳካ ቀርቷል፡፡ ለምን ነበር ያልተሳካው? የአሁኑስ ስምምነት ምን ያህል አስተማማኝ ነው ይላሉ?
እውነት ነው! እንዳልሽው የተለያዩ ስምምቶች ተደርገው አልተሳኩም፡፡ ለምሳሌ በ2015 የተደረገውን ስምምነት እንውሰድ፡፡ ይህ ስምምነት ያልተሳካበትን ምክንያት ልንገርሽ፡- አፍሪካ በአምስት ሪጅን ተከፋፍላለች፡፡ የምስራቅ አፍሪካ የቀንዱ አካባቢ አባል አገራት ድርጅት “ኢጋድ” ነው፡፡ የኢጋድ የወቅቱ መሪ ኢትዮጵያ ናት፡፡ የደቡባዊው የአፍሪካ ክፍል “ሳዲክ” ይሰኛል፡፡ “ኢኮዋስ” ደግሞ የምዕራብ አፍሪካ አገራትን የሚመለከት ጉዳይን የሚመራና የሚከታተል ነው፡፡ የሆነ ሆኖ የምስራቅና የቀንዱ አካባቢ አገራትን ችግር ለመፍታት፣ የምስራቅ አፍሪካ በይነ መንግስታት ድርጅት (ኢጋድ) በቂና ጠንካራ ነው፡፡ ነገር ግን እንደነ ሳዲክና ኢኮዋስ ያሉት ድርጅቶች እንዲሁም እንደነ አውሮፓ ህብረት፣ አሜሪካን፣ ኖርዌይንና ብሪታንያን የመሳሰሉ አገራት ጣልቃ ገብነት ነገሩን ሁሉ አበለሻሸው፡፡ የጉዳዩ ባለቤት ያልሆኑ አካላት ባሳደሩት ጫናና ጣልቃ ገብነት ደቡብ ሱዳንናውያን እርስ በእርሳችን መስማማት አልቻልንም፡፡ በጣም አስቸጋሪ ጉዳይ ሆነ፡፡ ተስፋ ቆርጠን በነበርንበት ጊዜ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ ወደ ስልጣን መጥቶ፣ የእኛን ጉዳይ ለምን እንዳልተሳካ ሲመረምር፣ የጣልቃ ገብነቱ ጉዳይ እንቅፋት እንደሆነ ተረዳ፡፡ ይሄ ጣልቃ ገብነት እስካለ ደረስ ደቡብ ሱዳንና ዜጎቿ በፍፁም ወደ ሰላም አይመጡም በማለት፣ በኢጋድ አደራዳሪነት ብቻ ስምምነቱ ተካሄደ፡፡ ራሳቸውን ትሮይካ (Troika) ብለው የሚጠሩት አውሮፓዊያን፣ አሜሪካውያንና ሌሎች ቡድኖች፣ ደቡብ ሱዳን ሰላም እንድትሆን ሳይሆን ጦርነቱ እንዲቀጥል ነው የሚፈልጉት፡፡
በደቡብ ሱዳን ከሚካሄደው ጦርነት ምን የሚያተርፉት አለ?
የሚያተርፉትን የሚያውቁት እነሱ ናቸው፤ ነገር ግን ጦርነቱ እንዲቀጥል ይፈልጋሉ፡፡ መጀመሪያ ችግሩን ካልተረዳችሁት መፍታት አትችሉም ብለን ብዙ ጊዜ ገልፀንላቸዋል፤ ነገር ግን እኛን ሊያዳምጡን አይፈልጉም፡፡ ዶ/ር ሪክ ማቻር አዲስ አይደለም፤ እሱ በ1991 ዓ.ም ለዶ/ር ጆን የችግር መንስኤ እንደ ነበር ይታወቃል፡፡ በ2013ም ሆነ በ2016ም የችግር መንስኤ ነበር፡፡ ይሄንን ነገር ለእኛው ተዉልንና እኛው እንፍታው ብንልም፣ ሊሰሙን ሊያደምጡን አይፈልጉም፡፡ ደቡብ ሱዳንም በነዚህ አገራት ጣልቃ ገብነት እርስ በርስ ስትባላ፣ ሀብቷን ስታወድም፣ ህዝቧን ለሞትና ለስደት ስትዳርግና በኪሳራ ስትጓዝ ቆይታለች። ትሮይካዎች የአገሪቱ ህዝብ 98 በመቶ የመረጠውን መሪ በማስወገድ፣ የአገዛዝ ለውጥ ለማድረግ ሲጥሩ ነበር፡፡ ያን ጊዜ ህዝቡ በአደባባይ ሰልፍ ተቃውሞ አሰምቷል። የደቡብ ሱዳን ህዝብ ትሮይካዎች የሚሰሩትንም ተንኮል ያውቃሉ፡፡ ፕሬዚዳንታቸውንም ያውቃሉ። በዚህ ምስቅልቅል የደቡብ ሱዳን ህዝብ ለከፍተኛ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ቀውስ ተዳርጓል፡፡ ኑሮው ተቃውሷል፡፡ በብዛት ተሰድዷል፡፡
በሶማሊያም በእኛም ዘንድ ችግር በነበረ ጊዜ የኢጋድ አባል አገራት ችግሩን ለመቆጣጠር የኢኮኖሚ ችግር ስለነበረባቸው አልቻሉም፡፡ ይህንን ክፍተት በመጠቀም ትሮይካዎች ሁሉን ነገር ስፖንሰር እያደረጉ፣ ችግር ሲያባብሱ ነው የኖሩት፡፡ ጉዳዩን ወደ ኢሲኤ የስብሰባ አዳራሽ ይወስዳሉ፤ ቁርስ፣ ምሳና ቡና በማዘጋጀት፣ ለነዚህ ቡድኖች የአየር ትኬት በመግዛት ያስመጧቸውና ሃይ ሃይ ብለው ይሸኟቸዋል። በዚህ ዓይነት አገራቱ ዘላቂ የሰላም መፍትሄ ሊያገኙ አልቻሉም፡፡ አላማውን ጠለፉት (ሀይጃክ አደረጉት)፡፡ ሥለ ህግ የበላይነት፣ ስለ ሰብአዊ መብት ያወራሉ፡፡ በአገራት መካከል የተነሳን ጦርነትና እልቂት ግን አያስቆሙም፡፡ አንድ አገሩ ውስጥ የእርስ በርስ ጦርነት ያለበት መሪ (አገር)፤ ስለ ሰብአዊ መብትና ስለ ህግ የበላይነት ብትነግሪው እንዴት ያዳምጥሻል፡፡ አገሩ ላይ ለተነሳው እሳት አስቸኳይ ማጥፊያ መንገድ ብትነግሪው ግን ሄዶ እሳቱን ያጠፋና፣ ከዚያ ስለ ሰብአዊ መብትና ስለ ህግ የበላይነት ይሰራል። ትሮይካዎች ግን ሲቀልዱና ሰው ሲያባሉ ነው የኖሩት፡፡ የደቡብ ሱዳንም ህዝብ በሰላም መኖር እየቻለ፣ በእነሱ ሲሰቃይ ነው የኖረው። ይሄው ዶ/ር ዐቢይ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትርና የኢጋድ ፕሬዚዳንት ሆነ፡፡ ችግሩን ተረዳ፡፡ ያለማንም ጣልቃ ገብነት የችግሩን ባለቤቶች አደራደረ፡፡ አወያየ፡፡ ጦርነታችን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ቆመ፡፡ ተመልሶ ይመጣል የሚል እምነት የለኝም። ዶ/ር ዐቢይ በጣም ስማርት በሆነ መንገድ ነው፣ እነ ትሮይካ ደቡብ ሱዳንን ሊረዱ እንደማይችሉ ገልፆ፤ ጉዳዩን በካርቱም ጨረሰው፡፡ የትሮይካ አባል አገራት ሰዎች ወደ ካርቱም ዝር እንዳይሉ ተደርጎ፣ የደቡብ ሱዳን ተቀናቃኞች በቂ የሆነ ጊዜ ወስደው፣ እርስ በእርሳቸው በደንብ ተነጋግረው፣ እንዲስማሙ ነው ዶ/ር ዐቢይ ያደረገው፡፡ እጅግ በጣም ብልህና በግጭት አፈታት ለደቡብ ሱዳን ብቻ ሳይሆን ለመላው አፍሪካን እንዲሁም ለአለም ምሳሌ የሚሆነን ነው። ፕሬዚዳንት ሳልቫኪርና ዶ/ር ሪክ ማቻር ስምምነት ላይ ሲደርሱ፣ እኔም ካርቱም ነበርኩኝ፡፡ ህዝቡ በደስታ ሲደንስና ሲስቅ ነበር፡፡ ፕሬዚዳንት ሳልቫኪር ከካርቱም ጁባ ሲገቡ፣ ህዝቡ በደስታና በዳንስ አጅቦ በድምቀት ነው አቀባበል ያደረገላቸው፡፡ በርካታ ህዝብ ነበር ለአቀባበል የወጣው፡፡ በአጠቃላይ ዶ/ር ዐቢይ ወደ ስልጣን ባይመጣ፣ ደቡብ ሱዳን ወደ ስምምነት ልትመጣ ቀርቶ ጭራሽ ሙሉ ለሙሉ ትወድም ነበር፡፡ ስለዚህ በዶ/ር ዐቢይ ደስተኛ ነን፤ እናመሰግናለን፡፡
አሁን በድንበር አካባቢ የፀጥታና የትብብር ጉዳይ ምን ይመስላል?
ደቡብ ሱዳን ውስጥ ቀውስ በነበረ ጊዜ የተለያዩ ቡድኖች፣ በርካታ ህፃናትን ከኢትዮጵያ ጠልፈው ወስደው ነበር፡፡ ይሄ የሚያሳየው የድንበር አካባቢ የፀጥታ ሁኔታ አስተማማኝ አለመሆኑን ነው፡፡ የደቡብ ሱዳን መንግስት፣ ከተቃዋሚዎች ጋር ጦርነት ላይ ስለነበር ድንበሮችን መቆጣጠር አልቻለም። ኢትዮጵያም በዚያ ድንበር አካባቢ እንዲህ አይነት አስደንጋጭ ችግር ይፈጠራል ብላ አላሰበችም ነበር፤ ግን ተፈጠረ፡፡ ይህን ሁላችንም የምናስታውሰው ነው። አሁን ከረጅም ችግር በኋላ እኛም ወደ ሰላም የመጣን በመሆኑ፣ የድንበር አካባቢ ፀጥታ አስተማማኝ ይሆናል። ለዚህ ደግሞ ኢትዮጵያና ደቡብ ሱዳን ተባብረው በመስራት፣ ሰላምና ጉርብትናቸውን ያጠናክራሉ፤ ምንም የሚያጠራጥር አይደለም፡፡ መንገዶች ይከፈታሉ፤ የድንበር አካባቢ ንግድ ይጀመራል፡፡
ከኢትዮጵያ ጋር ያላችሁን ጉርብትና ይበልጥ ለማጠናከር መንገዶችንና የባቡር መስመሮችን የመዘርጋት እቅድ ይኖራል?
ይህንንም ለመስራት ስምምነት ተፈርሟል፡፡ ለምሳሌ የባቡር መስመርን በተመለከተ፣ ከጅቡቲ አዲስ አበባ፣ ከአዲስ አበባ ጁባ ለመዘርጋት ስምምነት ተፈርሟል፡፡ ፕሮጀክቱም ለአንድ የቻይና ኩባንያ ተሰጥቶ ፊርማ ተካሂዷል፡፡ የመኪና መንገድን በተመለከተ ሁለት ዋና ዋና መንገዶች አሉን። አንዱ መንገድ ከአዲስ አበባ ተነስቶ “ፓሎጅ” የተሰኘውና በብዛት ነዳጅ የሚመረትበት የደቡብ ሱዳን ቦታ ድረስ በቀጥታ የሚገባ ሲሆን ሁለተኛው ከጋምቤላ “ቦማ”ባለፈው ህፃናቱ ከተጠለፉበት ተነስቶ ጁባ የሚገባ ነው፡፡ በነገራችን ላይ የኢትዮጵያና የደቡብ ሱዳን ህዝቦች ወደዚያ ለመምጣትና ለመሄድ የግድ አውሮፕላን መጠቀም የለባቸውም፤ መኪና እየነዱ መግባት ይችላሉ፡፡ የድንበር አካባቢ ንግድና ቢዝነስ መስራት ይችላሉ፡፡ የደቡብ ሱዳን ህዝብ ብዙ ነዳጅ አለው። ኢትዮጵያም ነዳጅ ለመግዛት ሩቅ ሳትጓዝ፣ ከእኛ ማግኘት ትችላለች፡፡ እኛም ታላቁ የህዳሴ ግድብ ሲያልቅ የኤሌክትሪክ ኃይል ከኢትዮጵያ በቅርቡ መግዛትና መጠቀም እንችላለን። ብቻ ብዙ ነገሮች በትብብርና በጋራ ለመስራት እንዲሁም አገሮቻችንን ለማልማት የሚያስችሉን፣ የምንጠብቃቸው እድሎች አሉን፡፡ ይሄ በጣም የሚያስደስትና በተስፋ የሚሞላ ነገር ነው፡፡ የውጊያ ቦታ የነበሩትን ቀጠናዎች፣ የልማት ጣቢያዎች ማድረግ እንችላለን፡፡
አገራችሁ ቀውስ ውስጥ በነበረች ጊዜ በርካታ ዜጎች መሰደዳቸው ይታወቃል፡፡ ለመሆኑ ምን ያህል ይሆናሉ የተሰደዱት? ወደ አገራቸው ለመመለስ ምን ታቅዷል?
የአገሪቱን ቀውስ ተከትሎ የተፈናቀሉ በርካታ ቁጥር ያላቸው ዜጎች በጋምቤላ፣ በሀዋሳና እዚያው ጋምቤላ ውስጥ ፑኚዶ በተሰኙ ቦታዎች ይገኛሉ፡፡ እስካሁን ሪፖርቶች የሚያመለክቱት፤ ከ35 ሺህ በላይ ስደተኞች እንዳሉ ነው። የስደተኞቹ ሁኔታ … አገሪቱ ሰላም ስትሆን ወደ አገራቸው ስለሚመለሱ ይቀንሳል፤ እንደገና ቀውስ ሲነሳ ተመልሰው ስለሚሰደዱ ከፍ ይላል፡፡ እነሱን ወደ ቤታቸው በዘላቂነት ለመመለስ አገሪቱ በአስተማማኝ ሁኔታ ሰላም መሆን አለባት። አሁን ያንን ሰላም በእጃችን አስገብተናል፡፡ በአሁን ሰዓት ራሱ ጁባ ውስጥ ሰላም ሰፍኗል፡፡ የጥይት ጩኸት ከቆመና ሙሉ ለሙሉ ሰላም ከሆነ፣ በራሳቸው ጊዜም ወደ ቤታቸው ይመለሳሉ፡፡ እኛም የስደተኞች ማቋቋሚያ ፕሮጀክት አለን፤ ሁሉም ጥሩ ይሆናል፡፡
ደቡብ ሱዳን እንደ አገር እውቅና ካገኘችና የተባበሩት መንግስታት አባል አገር ከሆነች በኋላ ከሌላው ዓለም ጋር ያላት ግንኙነት ምን ይመስላል?
እኛ ከየትኛውም የአለም ህዝብ ጋር ችግር የለብንም። ቅድም ከነገርኩሽ ከሩቅ አገር እየመጡ ጣልቃ እየገቡ ከሚበጠብጡን በስተቀር፣ ሌላው ቀርቶ ከጎረቤቶቻችን ከየትኞቹም ጋር በሰላምና በፍቅር ነው የምንኖረው፡፡ ከሩቅ መጥተው ችግር እንፈታለን በሚል፣ የራሳቸውን ፍላጎት ለማስፈፀም የሚረብሹት ከቆሙልን፤ ከየትኛውም ጎረቤትም ሆነ የሌላ አለም አገራት ጋር ሰላማዊ ግንኙነት ነው ያለን፡፡ እርስ በእርሳችን የምንናቆርበት ጦርነትም ፍፃሜ አግኝቷል። በጣም ጥሩና የተረጋጋ አገርና ህዝብ ይኖረናል፤ እናድጋለን እንለማለን፡፡ አመሰግናለሁ፡፡   

Read 3391 times