Tuesday, 14 August 2018 00:00

የኢህአዴግ ምርጫዎች:- እንደ ፖላሮይድ መሆን ወይስ እንደ ማይክሮሶፍት?

Written by  ተመስገን ማርቆስ (ዶ/ር)
Rate this item
(4 votes)

 ፖላሮይድ
የአሁን ጊዜ ልጆች ባትደርሱበትም ድሮ ድሮ ሰው ፎቶ በካሜራ ይነሳና ከዚያም ካሜራው ያለው ፊልም ሲሞላ እናንተ ሚሞሪ እንደምትሉት ማለት ነው ከካሜራው የፊልም ጥቅልሉን አውጥቶ ለአጣቢ ይሰጣል። አጣቢው ደግሞ ጨለማ ቤት ውስጥ የተቀመጠ ትልቅ ማሽን ውስጥ ከትቶ “ያጥባል”። ከዚያም ከሦስት ቀናት ምናምን በኋላ ባለፎቶው ተመልሶ ይመጣና፣ በወረቀት ላይ የታተሙለትን ፎቶዎች ይወስዳል።
እንግዲህ ከዛ መልስ ነው ፎቶው ይመር አይመር የምታዩት። የወላጆቻችሁ የሰርግ አልበም እንግዲህ እንደዚያ ነው የተሞላው። ሙሽራዋ በላብ ኩሉዋ ተበላሽቶ ከነበረ ”ዲሊት አርገው“ የለ፣ እንደገና መነሳት የለ። ድሮ አንድ የሃይስኩል ጓደኛዬ፣ አዋሳ ሃይቅ ዙሪያ ፎቶ አንሱኝ የሚሉ ጥንዶች ካናደዱት፣ እግር ብቻ ወይ ከጎን ያለውን ዛፍ ብቻ አንስቶ ይመልሳል። ያው ከወር በኋላ ፊልሙ ሞልቶ ታጥቦ ሲያዩት ይረግሙታል፡፡ እሱ ከዚያ በፊት ገብርኤል ጃንጥላ አስገብቶ፣ ይሄኔ አምክኗል እርግማኑን (ማንነትህን ታውቃለህ፤ ስምህን አልጠቅስም!)
እንዲህ ባለ ጊዜ ነው ኤድዊን ላንድ የሚባል ሳይንስ በጊዜ የገባው ልጅ፣ ከሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ትምህርቱን አቋርጦ ፖላሮይድ የተባለውን ኩባንያ  ያቋቋመው። የኬሚስትሪና የብርሃን እውቀቱን አገናኝቶ፣ ከፈለሰፋቸው ነገሮች አንዱ፣ ፎቶ አንስቶ ወዲያው አትሞ የሚሰጥ ካሜራ ነበር። ፖላሮይድ፤ ካሜራ በጨለማ ክፍል ያለውን ፕሮሰስ እንዳለ በካሜራ ሆድ ውስጥ እንዲያልቅ ያደርጋል - miniaturization። ሌሎች ብዙ እንዲህ አይነት በኬሚስትሪ ላይ የተመሰረቱ ነገሮች እየፈለሰፈ፣ በአሜሪካ ታላቅ የሆነ እና በአንድ ወቅት 21000 ሰራተኞች የነበሩት ድርጅት ኖረው፤ እሱም የጊዜው ታላቅ ሳይንቲስትና የፈጠራ ሰው ተብሎ ተሞካሸ።
ታዲያ እንዲህ ያለው ድርጅት በ2001 ከስሮ ፈራረሰ። ከዚያ በፊት መስራቹም ተገፍቶ ከሃላፊነት ለቀቀ። ምክንያቱም የዲጅታል ካሜራዎች መስፋፋት ነበር። እንዴት ይህን የመሰለ ፈር ቀዳጅ መሪና ስንት ሳይንቲስቶች የነበሩት ድርጅት፣ የኤሌክትሮኒክስ ቴክኖሎጂን ሳይረዳ ቀረ? አረ ተረድቷል። እንዲያውም የራሳቸው ዲጅታል ካሜራ ሰርተው ነበር። ግን ሰው ሁሌም ፎቶውን በወረቀት ላይ ማየት ይፈልጋል የሚል እምነት ስለነበራቸው፣ ካሜራቸው አሁንም ወዲያው በወረቀት አትሞ የሚሰጥ ነበር። ያ ደግሞ ከሌሎች ዲጅታል ካሜራዎች አንጻር ፖላሮይድ ካሜራን ውድ አደረገው።
ፖላሮይድ እየከሰመ በነበረበት ወቅት አንድ ሃላፊ እንዳለው፤ “It’s amazing, but kids today don’t want hard copy anymore!”
kids today! ቄሮ don’t want hard copy anymore
 ማይክሮሶፍት
ቢል ጌትስም እንደ ኤድዊን ላንድ ከሃርቫርድ ትምህርቱን አቋርጦ ነው ማይክሮሶፍትን የመሰረተው። እሱም በጊዜው ሌሎች ያልታያቸውንና እሱ የተገለጸለትን ችግር የሚፈታ ሶፍትዌር ሰርቶ የዴስክቶፕ ኮምፒዩቲንግ አብዮት አመጣ፤ ለራሱም የአለም አንደኛ ሃብታም ሆነ።
ታዲያ የሞባይል አብዮት ሲመጣ ማይክሮሶፍት የጊዜውን ትውልድ ሳይረዳ ቀረ። ለስልክ የሚሆን ሶፍትዌር ቢሰራም ስልክን እንደ ትንሽ ኮምፒዩተር በማሰብ፣ ትንንሽዬ ኪቦርድ ያለው ስልክና ሶፍትዌሩም ኮምፒዩተር ላይ ያለውን እንደሚመስል አድርጎ ነበረ የወሰደው። አፕልና ስቲቭ ጆብስ ተች ስክሪን ስልክ ሲሰሩ፣ የማይክሮሶፍት ሰዎች “ተዏቸው የትም አይደርሱም” ይሉ ነበር፤ ለራሳቸው የድሮ ጥያቄን በመፍታት ተሸውደው።
የአፕልና የአንድሮይድ ስኬትን ሲያዩ ማይክሮሶፍቶች ኖኪያን ይገዛሉ።
በሁዋላ ላይ ይሄን ገበያ ማሸነፍ እንደማይሆንላቸው ሲረዱ ኖኪያን መግዛታቸው ስህተት መሆኑን አምነው አዲስ አመራር አመጡ። 8 ቢሊዮን ዶላር ያህል ከስረውበት ቢሆንም ”አንዴ ካፈርኩ አይመልሰኝ“ ሳይሉ ከዚያ ገበያ ወጡ።
ከዚያ መልስ መጪው ጊዜ የክላውድ ኮምፒዩቲንግ መሆኑን ተረድተው Microsoft Azure ላይ አተኮሩ። ተመልሰውም በአዲስ አመራር ማደግ ጀመሩ። የመጀመሪያዎች መሪዎች ቢል ጌትስ እና ስቲቭ ባልመር ተከብረው፣ በጎ አድራጊ የአገር ሽማግሌና አማካሪ ሆኑ።
ኢህአዴግ
እንደ ኤድዊን ላንድና እንደ ቢል ጌትስ የኢህአዴግም መስራቾች በወቅቱ የታያቸውን ችግር ለመፍታት የዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን አቋርጠው ሲልከን ቫሊ ሳይሆን በረሃ ገቡ። ላመኑበት ዓላማ ግማሾቹ ህይወታቸውን፣ የተረፉትም ወጣትነታቸውን ሰውተው ዓላማቸውን አሳኩ።
የስልሳዎቹ የተማሪዎች አመጽ ካነሳቸው ጥያቄዎች መሃል የብሄር ጥያቄ አንዱ ነበር። ይህን ችግር ኢህአዴግ ብሄር ተኮር በሆኑ ክልሎችና በአፍ መፍቻ ቋንቋ የመማርና የመስራት መብት በማስፈን ፈትቻለሁ ብሎ ያምናል። ኢህአዴግ የሄደበት አካሄድ ልክ ነው ብዬ ባላምንም በዚህ ጉዳይ መሻሻል እንደተፈጠረ አልክድም። በሌላ በኩል  ደግሞ የራሱን ችግሮችም አምጥቷል። የመሬት ላራሹም ጥያቄ ቢሆን ደርግ የተወሰነ ያህል መልሶት፣ ኢህአዴግ እዛው አካባቢ ቆይቷል።
ለውይይት ያህል ኢህአዴግ በረሃ ያስገቡትን እነዚህንም ሆነ ሌሎች ችግሮችን ፈትቷል ብለን ብናስብ እንኳን፣ አልረዳ ብሎ ያስቸገረን አዲስ ትውልድ የራሱን አዲስ ጥያቄ ይዞ መምጣቱን ነው። ኢህአዴግ የሰው ችግር የፍርድ ቤቱ ዳኛ ኦሮምኛ አለመናገሩ መስሎት ከነበረ፣ አሁን ከቁቤ መልስ የተወለደ ወጣት ደግሞ ጥያቄው ፍርዱን በአፍ መፍቻ ቋንቋው ከመስማት አልፎ ፍርዱ ፍትሃዊ ነው? ወይስ አይደለም? ወደሚለው ተሸጋግሯል።
ኢህአዴግ የሰው ችግር ባህሉን ሳይሸማቀቅ መከተል መስሎት ከነበረ፣ አሁን ያ ችግር ከመሆን አልፎ ወጣቱ “አገው አገው ጭፈራ ስልቱ ወላይትኛ ይመስላል አገውኛ” እያለ የራሱን ከማወቅና መከተል አልፎ፣ የሌላውን አክብሮ እያጠና፣ በምስስሉ መቀራረብ በልዩነቱ መደነቅ ላይ ደርሷል።
ኢህአዴግ የሰው ችግር የሃይማኖት ነጻነት ከመሰለው፣ በኢህአዴግ አስተዋጽኦ አሁን በአንድ በኩል “ለጌታ ራፕ ማድረግ”፣ በሌላ በኩል ”የማሪያም እህት ነኝ“ ”እኔ ራሴ ማሪያም ነኝ“ ማለት ላይ ደርሰናል። ግን ከዚህ አልፎ የሃይማኖቱን መሪዎች ደግሞ በነጻነት መምረጥ ሲፈልግ፣ እኛ ካልመረጥንልህ ብሎ ኢህአዴግ የሰራውን ያበላሻል መልሶ። እዚህ ጋ ለመድረሳችን የኢህአዴግን አስተዋጽኦ መርሳት የለብንም። ዋናውን ይዞ ወጣቱ ለትርፍ ሲንቀሳቀስ “አይ የእኛን ብቻ ራእይ እያየህ ተኛ” ስትሉት ነው ችግር የመጣው። ጠያቂ ትውልድ ፈጥረናል ትሉ የለም? ታዲያ ጥያቄውን ሰብስባችሁ ልትታዘቡ ነው? ወይ ጥያቄውን መልሱ ወይም ለሚመልስ በሰላም አስረክቡ።
አዲስ ትውልድ የበፊቶቹ ከደረሱበት ላይ ተነስቶ እንዲያሻሽል መፈቀድ አለበት። አሮጌው ስርአት ይህን ስላልፈቀደለት አዲሱ ትውልድ ማሸነፉ አይቀርም። አሮጌው ለአዲሱ ማስረከቡ ደግሞ ሽንፈት ሳይሆን የትውልድ ዱላ ቅብብል ነው።
ኒውተን የእነ አርስቶትል ሳይንስ ላይ ማሻሻያ አድርጎ ሲያበቃ “ሩቅ አይቼ ከነበረ በታላላቆች ትከሻ ላይ ቆሜ ስለነበረ ነው” አለ። ከዚያም ደግሞ አይንስታይን የኒውተንን ሃሳብ ሲያሻሻል፣ የትውልድ ሃገሩ ጀርመን ሃሳቡን መጀመሪያ “የይሁዲ ሳይንስ” ብላ ብታጣጥለውም ለውጥ አይቀርምና የአንስታይንም ሃሳብ አሸነፈ፤ መጀመሪያ ልትጠቀምበት የምትችለውና በጊዜው የሳይንስ ሃያል ሃገር የነበረችው ጀርመን እያለች አይንስታይና መሰሎቹ አሜሪካ ተሰደው፣ የስደት ሃገራቸውን የሳይንስ መሪ አደረጉ። እናም ኢህአዴግ ሁሌ ትከሻ ላይ ካልሆንኩ ብሎ አዲሱ ትውልድ አሽቀንጥሮ ከሚጥለው፣ በሰላም ትከሻውን እንኩ ብሎ ወጣቱ ቀጣዩን መንገድ አርቆ እንዲያይ ቢረዳው ይሻለዋል።
ልጆች ትልቅ ሰው የአራዳ ቋንቋ ሲናገር ያስገርማቸዋል። ከዚያም ልጆቹ አድገው አዲስ የአራዳ ቋንቋ ሲያመጡ፣ የድሮው አብሮ መሄድ ከቻለ “ነቄ” ተብሎ የወጣቶቹ ጓደኛ ሆኖ ይቀጥላል። አብሮ መሄድ ያልቻለ ከገባው፣ የአራዳ ንግግር ይተውና እንደ ትልቅ ሰው ይከበራል። ያልገባው “የድሮ አራዳ” ተብሎ የሰፈር ልጆች መሳለቂያ ይሆናል። እስካሁን እንዳየነው ኢህአዴግ “ነቄ” ሽማግሌ ለመሆን አልቻለም። ግን ቢያንስ የሰፈሩን ሜዳ ለአዲሱ ትውልድ አስረክቦ፣ የአገር ሽማግሌ መካሪ የመሆን እድል አሁንም አለው። አይ ካለ ልጆቹ ሜዳውን መረከባቸው ላይቀር “ደርግን አሸንፈን፤ የብሄር ብሄረሰቦችን ጥያቄ መልሰን” እያለ የድሮ ጥያቄዎች ላይ ተቸንክሮ “የድሮ አራዳ“ ሆኖ ይቀራል።
መርዶክዮስ ለአስቴር “በዚህ ጊዜ ቸል ብትይ እረፍትና መዳን ለአይሁድ ከሌላ ስፍራ ይሆንላቸዋል” እንዳለው፣ ኢህአዴግ የመፍትሄው አካል አልሆንም የሚል ከሆነ፣ ኢትዮጵያ ላይ አንድ ቀን ሰላም ፍትህና ነፃነት መስፈኑ አይቀርም። ለራሱ ይቀርበታል እንጂ።
ኢህአዴግ ሆይ፤ አሁንም እንደ ፖላሮይድ የመክሰም ወይም እንደ ማይክሮሶፍት ለአዲስ አስተሳሰብ ሃገሪቱን አስረከቦ የመከበርና አብሮ የማደግ ምርጫ አለህ። እንደገና ዕድልህን አታበላሽ!

Read 3913 times